Wednesday, 02 December 2020 00:00

ኤለን መስክ የአለማችን 2ኛው ባለጸጋነትን ከቢል ጌትስ ተረከበ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

እስካለፈው ሳምንት በአለማችን ቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ በ3ኛ ደረጃ ላይ የነበረው የቴስላ ኩባንያው መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ኤለን መስክ፣ ባለፈው ሰኞ ተጨማሪ 7.2 ቢሊዮን ዶላር ሃብት ማፍራቱንና አጠቃላይ ሃብቱ ወደ 128 ቢሊዮን ዶላር ማደጉን ተከትሎ፣ በማይክሮሶፍቱ መስራች ቢል ጌትስ ተይዞ የነበረውን የአለማችን 2ኛው ባለጸጋነት ስፍራ መረከቡን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የ49 አመቱ አሜሪካዊ ቢሊየነር መስክ የ20 በመቶ ድርሻ የያዘበትና የኤሌክትሪክ መኪኖች አምራች የሆነው ኩባንያው ቴስላ የአክሲዮን ዋጋ ሰኞ ዕለት የ6.5 በመቶ ጭማሬ ማሳየቱን ተከትሎ፣ 7.2 ቢሊዮን ዶላር ያህል ተጨማሪ ሃብት ማፍራቱን የጠቆመው ዘገባው፤ የኩባንያው ሃብትም 521 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን አመልክቷል፡፡ ኤለን መስክ በ2020 የፈረንጆች አመት ብቻ የተጣራ ሃብቱ በ100.3 ቢሊዮን ዶላር ጭማሪ ማሳየቱን ያስታወሰው ዘገባው፣ ይህ የሃብት ጭማሪ በአለማችን ከፍተኛው መሆኑንና ቢሊየነሩ በአለማችን ባለጸጎች ዝርዝር ውስጥ በአመቱ መጀመሪያ 35ኛ ደረጃ ላይ እንደነበርም አክሎ ገልጧል፡፡
የአማዞኑ መስራች ጄፍ ቤዞስ በ182 ቢሊዮን ዶላር አሁንም የአለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፣ ቢል ጌትስ በ129 ቢሊዮን ዶላር ሶስተኛ፣ የፌስቡኩ መስራች ማርክ ዘከርበርግ በ105 ቢሊዮን ዶላር አራተኛ፣ በርናንድ አርኖልት በ104 ቢሊዮን ዶላር አምስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙም  ጨምሮ ገልጧል፡፡

Read 7268 times