Sunday, 29 November 2020 14:49

"የህወሓት አመራሮች በዓለም አቀፍ የጦር ፍርድ ቤት ሊጠየቁ ይገባል"

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

 “ጁንታው ቡድን፤ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ኮትኩተው ያሳደጉት ክፉ ውልድ ነው” - ( ሌ/ጄ ታደሰ ታምራት)
                     
                በትግራይ ክልል በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ በህወሃት ልዩ ሃይል የተፈጸመው ድንገተኛና  አሰቃቂ ግድያ ከኢትዮጵያውያን የማይጠበቅ አረመኔያዊ ወንጀል ነው ያሉት የቀድሞ የጦር መኮንኖች፤ እኒዚህ ቡድኖች (ያዘዙትም ሆነ የፈጸሙት) በዓለም አቀፍ የጦር ፍርድ ቤት ሊጠየቁ ይገባል ብለዋል፡፡
"ይህ የሽፍቶች ስብስብ በአገርና በህዝብ ላይ ለ27 ዓመታት ሲጫወት ኖሯል፡፡ አገር እንድትበተን፣ ታሪክ እንዲጠፋና ትውልድ እንዲመክን ተግቶ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ቡድኑ የአገር ፍቅር ክብር የሚያውቅ አይደለም።" ብለዋል፤ ሌተናል ጄነራል ታደሰ ታምራት በቁጭት፡፡
"የጁንታው ቡድን የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ኮትኩተው ያሳደጉት ክፉ ውልድ ነው" ያሉት ሌተናል ጄነራሉ፤ ቡድኑ በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊትም ሆነ በማይካድራ በፈፀመው የጅምላ ጭፈጨፋ በአለም አቀፍ የጦር ፍርድ ቤት ሊጠየቅ ይገባል ብለዋል፡፡
"በእነዚህ የሽፍታ ቡድኖች የተፈፀመው ወንጀል፣ በናዚ ወታደሮች ከተፈጸመው በምንም አያንስም" ይላሉ፤ ጀኔራሉ፡፡
ለ32 ዓመታት በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ሀገሬንና ህዝቤን አገልግያለሁ የሚሉት የቀድሞ ሰራዊት አባሉ፤ "እንዲህ አይነት አሳፋሪና አሳዛኝ ወንጀል በገዛ ወንድም ላይ ሲፈጸም እንኳን በአገሬ የትም አልሰማሁም፤ አላየሁም" ሲሉ የድርጊቱን አሰቃቂነት በቁጭት ተናግረዋል፡፡
"እነዚህ ከሰውነት ጎራ የወጡ ሳጥናኤሎች ናቸው" ሲሉ የገለጧቸው ከፍተና መኮንኑ፤ "እኛ በሱማሊያ ጦርነት ወቅት እንኳን የማረክናቸውን አልብሰን፣ አብልተን አጠጥተን፣ የቆሰለውን አሳክመን ነው----የምንይዘው፡፡ ወታደራዊ ህጉም የሚለው ይህንን ነው፡፡ ለነገሩ ተራ የመንደር ሽፍታ ወታደራዊ ዲስፒሊን ከየት ያመጣል?; ሲሉ በብስጭት የነቀፉት ጄነራሉ፤ በ11ኛው ሰዓት የህወሃት አመራሮች በመቀሌ የሲቪል ተቋማት ውስጥ መመሸጋቸውን አውግዘዋል። "በወታደራዊ ህግ በቤተ እምነቶች፣ በገበያ ስፍራዎችና ሰው በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ላይ መሽጎ መታኮስ የጦር ወንጀል ነው፡፡ ህዝቡን ነው ከለላ ያደረጉት፤ ይህ የወንበዴና ሽፍታ ስራ ነው፡፡ ለዚህም ስራቸው ተገቢውን ቅጣት ሊያገኙ ይገባል" ብለዋል፤ ሌተናል ጄነራል ታደሰ፡፡
የፌደራል መንግስት የመጨረሻውን ህግ የማስከበር ዘመቻ በመቀሌ ከመጀመሩ በፊት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ዐቢይ አህመድ፣ ባለፈው እሁድ፣ ለህወሃት አመራሮች የ72 ሰዓታት ጊዜ ሰጥተዋቸው ነበር - ለሠራዊቱ በሰላም እጅ እንዲሰጡ፡፡ ሆኖም አመራሩ እጁን እንደማይሰጥና እንደሚዋጋ ከመግለጹም ባሻገር የጊዜ ገደቡን ተሳልቆበታል፡፡ በሌላ በኩል፤ በእነዚህ ሦስት ቀናት በሺዎች የሚቆጠሩ የልዩ ሃይልና ሚሊሻ አባላት ዕድሉን በመጠቀም ለሰራዊቱ በሰላም እጅ መስጠታቸውን ጠ/ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ ባለፈው ሐሙስም የ72 ሰዓቱ ገደብ መጠናቀቁን ተከትሎ፣ የመከላከያ ሰራዊቱ የመጨረሻውን ህግ የማስከበር ዘመቻ ምዕራፍ እንዲፈጽም ትዕዛዝ እንደተሰጠው ጠ/ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡
መንግስት የጀመረውን ህግ የማስከበር ዘመቻ በድል እንደሚወጣውና አገሬ ለ30 ዓመት በጀርባዋ ላይ ወጥቶ ከሚያሰቃየት እባጭ እንደምትፈወስ አምናለሁ ያሉት የቀድሞ ሰራዊት አባል፤ ዘመቻው በቅርቡ እንደሚጠናቀቅም አልጠራጠርም ብለዋል፡፡
"መከላከያ ሰራዊታችንም ሆነ አየር ሀይላችን በዘመናዊ መልክ የተደራጀ፣ ብቃት ባላቸውና አገራቸውን በሚወዱ ወጣት አመራሮች የተዋቀረ በመሆኑ፣ እንኳንስ ለእነዚህ የመንደር ሽፍቶች ለውጪ ጠላትም የማይመለሱ መሆኑን አምናለሁ፡፡ ድል ከኢትዮጵያ ሰራዊት ጋር እንደሚሆንም አልጠራጠርም" ሲሉ በሠራዊቱ ላይ ያላቸውን መተማመን ገልጸዋል፡፡ ሌተናል ጀነራል ታደሰ በመጨረሻም፤ "ወቅቱ የሚጠይቀውን መስዋእትነት ሁሉ በመክፍል አገሬንና ህዝቦቿን ከወድቀት ለማዳን ዛሬም ዝግጁ ነኝ" ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የቀድሞ ሰራዊት ማህበር ሊቀ መንበር ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ በበኩላቸው፤ "ይህ ህግን የማስከበር ዘመቻ አገሪቱ እፎይታን የምታገኝበት የመጀመሪያ ምዕራፍ ነው፡፡ ይህ ወንበዴ ቡድን የሚያራምደው ርዕዮተ ዓለም ራሱ በህግ መከልከል ይኖርበታል" ብለዋል፡፡
ቡድኑ በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊታችን ላይ የፈፀመው ወንጀል እጅግ አሳፋሪ ነው፤ ከ20 ዓመት በላይ አብሮ ኖሮ፣ ህመሙን ታሞ፣ ረሃቡን ተርቦ፣ በገዛ ገንዘቡ ት/ቤትና መንገድ እየሰራ የኖረውን የአገር መከላከያ ሰራዊት አምኖት ራቁቱን ተኝቶ ሳለ፣ አድብቶ ማረድ፣ በዓለም ተፈፅሞ ያልታየ እጅግ ዘግናኝ ወንጀል ነው፡፡ ይህ በየትኛውም አለም ቢሆን በጦር ወንጀለኝነት ሊያስጠይቅ የሚችል ጉዳይ  ነው፡፡ ብለዋል  ሃምሳ አለቃው፡፡
በማይካድራው ስለተፈፀመው ወንጀል ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ ሲናገሩ፤ "በማይካድራው የተፈፀመው ወንጀል እነዚህ ሽፍቶች ከፈፀሙት ጥቂቱ ነው፡፡ ገና ብዙ ማይካድራዎችን መስማታችን አይቀርም፡፡ ገና ብዙ ታሪኮች፣ ገና ብዙ ወንጀሎች፣ ገና ብዙ አስክሬኖች እናያለን፤ እነሱ የተሰሩት ለዚህ ዓላማ ስለሆነ መግደል ልማዳቸው ነው፤ 27 ዓመት ቤተ መንግስት የኖሩት ሲገድሉ፣ ሲዘርፉ፣ ሲያኮላሹ ጥፍር ሲነቅሉ ነው፤ እናም ብዙ ታሪኮችን መስማታችን አይቀርም" ብለዋል፤ ወደፊት ያልተሰሙ አሳዛኝ ድርጊቶች እንደሚሰሙ በመገመት፡፡
"ቡድኑ የእምነት ተቋማት ውስጥ መሳሪያ እያከማቸ፣ ምሽግ እያሰራ ነው እዚህ የደረሰው፤ ሰው ራሱን በሳጥናኤል ደረጃ ካወረደ በኋላ ቤተ እግዚአብሔር ለእሱ ምኑ ነው?! ነገር ግን እነዚህን ቤተ እምነቶች ለእንዲህ አይነት የሽፍታ መመሸጊያ የፈቀዱ የሃይማኖት ሰዎች በህግ ሊጠየቁ ይገባል፡፡" ሲሉ ወንጅለዋል የቀድሞ ሰራዊትአባል፡፡
"በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊታችን ላይ የተፈፀመው ወንጀል ያማል፤ በጣም ያማል፤ ይህ በተለይ ለእኛ ለቀድሞ ሰራዊት አባላት ህመሙ ጥልቅ ነው፡፡ አገሬን ባለ ወገኔን ህዝቤን ባለ፣ በገዛ ወንድሞቹ በሳንጃ ታርዶ ሲገደል ከማየት በላይ ምን የከፋ ነገር አለ!?" የሚሉት የቀድሞ ሰራዊት የድጋፍ የልማት ማህበር ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ታመነ አባተ፤ "ከአገሬ ሰራዊት ጋር እዛው ስፍራው ላይ ሄጄ ለእነዚህ የአገር ነቀርሳ ጠላቶች፣ ተገቢውን ቅጣት መስጠት እፈልጋለሁ" ብለዋል፤ በቁጣ ተሞልተው፡፡
በመጨረሻም ሻለቃ ታመነ፤ "እነዚህ ኢትዮጵያውያን አይደሉም፤ ተልዕኮአቸውም ሆነ አላማቸው ሁሉ ሌላ ነው፡፡ የራሳቸውን ልጆች በውጭ አገር በድሎት እያኖሩ፣ የድሃውን ልጅ ለጦር ይማግዳሉ፤ ክፉዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ታሪክ ብቻ አይደለም የሚፋረዳቸው፤ ህዝቡም ይፋረዳቸዋል፡፡ እኔ ከፍተኛ መኮንን ነኝ፤ መምራት፣ መዋጋት፣ ማዋጋት እችላለሁ፡፡ ሁልጊዜ ከአገሬ ከወገኔ፣ ከሰንደቄ ጎን ነኝ። አገሬ ክብሯ ከፍ ብሎ ማየት እመኛለሁ" ሲሉ አስተያየታቸውን ቋጭተዋል፡፡   

Read 10079 times