Print this page
Saturday, 28 November 2020 00:00

የማይካድራው የጅምላ ጭፍጨፋ አስከፊነት ወደር የለሽ ነው ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 “የሟቾች ቁጥር በእጥፍ ሊጨምር ይችላል”

              የህወሃት ቡድን በማይካድራ በንፁሃን ዜጎች ላይ የፈፀሙት የጅምላ ጭፍጨፋ በድርጊት አፈጻጸምም ሆነ በተጎዱ ሰዎች ብዛት፣ እስካሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ከተፈፀሙ አሰቃቂ      ኢ-ሰብአዊ  ድርጊቶች ሁሉ በእጅጉ የከፋ መሆኑን የሰብአዊ መብት ተቋማት ገለፁ።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ድርጅቶች ህብረት አመራርና፤ የህግ ባለሙያው አቶ ያሬድ ሃይለማርያም በማይካድራ የተፈጸመው ጥቃት በአፈጻጸሙም  ሆነ በስፋቱ እስከ ዛሬ በሃገሪቱ ከተፈፀሙት መሰል ወንጀሎች እጅግ የከፋ መሆኑን ተናግረዋል።
“ክስተቱ እጅግ አስደንጋጭ፣ ይሆናል ተብሎ የማይገመትና በሰው ዘር ላይ የተፈጸመ አረመኔያዊ ድርጊት ነው” ሲሉ ገልፀውታል የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ።
“ጭፍጨፋው ዘርንና ማንነትን መሰረት ያደረገ፣ አማራዎች ብቻ በማንነታቸው ተለይተው በጅምላ በአንድ ጀንበር፣ በአሰቃቂ  ሁኔታ የተጨፈጨፉበት ነው ያሉት አቶ ያሬድ እስከዛሬ  በኢትዮጵያ የተፈጸመ እጅግ ዘግናኝ ወንጀል ሆኖ የሚመዘገብ ነው” ብለዋል።
የድርጊቱ አፈጻጸም በራሱ እጅግ ዘግናኝ ነው ያሉት አቶ ያሬድ፤ በገመድ በማነቅ፣በስለት በመውጋትና በሌሎች መሰል አሰቃቂ መንገዶች ግድያው መከናወኑ እንዲሁም በጥላቻ በተሞሉ “ሳምሪ” የሚል ስያሜ በተሰጠው የወጣቶች ቡድን መሆኑ ባለፉት 27 አመታት ሃገሪቱ የተገነባችበትን የጥላቻ ፖለቲካ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
ወጣቶች እየተደራጁ በሰው ልጅ ላይ አሰቃቂ ድርጊት የመፈጸማቸው ነገር፣ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ሲከሰት ቆይቷል፤ ይህም ወጣቶቹ በምን ስነ-ልቦና ውስጥ  እንዳሉ የሚያሳይና የወደፊቱን ጊዜ አስፈሪ የሚያደርጉው ነው የሚሉት አቶ ያሬድ፤ አሁን ከደረሰው አደጋ የበለጠ ነገስ ምን ይመጣል??? የሚለው እጅግ ያስጨነቀኛል” ብለዋል።
በማህበረሰቡ በጣም “አስፈሪ የሆነ የወጣቶች ስነ-ልቦና መፈጠሩ የአገሪቱ መፃኢ ጊዜ አስፈሪ ያደርገዋል፤ እንደ ማህበረሰብ በዚህ ጉዳይ ላይ ቆም በለን ማሰብ ይጠበቅብናል፤ የሃይማኖት ተቋማትና  ማህበረሰቡን በማነጽ ድርሻ ያላቸው ሌሎች  አካላት ጉዳዩ ሊያሳስባቸው ይገባል” ብለዋል አቶ ያሬድ።
በማይካድራ የተፈጸመው ጭፍጨፋ ተራ ወንጀል አይደለም፤ ለዘር ማጥፋት የቀረበ የሰው ዘር ላይ የሚፈጸም ከባድ ወንጀል ነው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ድርጊቱ በድንገት የተፈጸመ አለመሆኑን ሰዎች ለግድያው በዘራቸው ተለይተው አስቀድሞ መታወቃቸው፣ ድርጊቱም ሲፈጸም በስም እየተለዩ ቤት ለቤት እየተዞረ መሆኑ ዘር ተኮር ጭፍጨፋ እንደነበር አስረጅ ነው ይላሉ አቶ ያሬድ።
አምነስቲ ኢንተርናሽናልም የአካባቢውን የአይን አማኞችና ከአደጋው የተረፉትን አነጋግሮ ከሰሞኑ በድጋሚ ባወጣው ሪፖርቱ፤ ድርጊቱ ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ነው ብሎታል።
ሰዎች በግልጽ በማንነታቸው ተለይተው ባልጠበቁት ሁኔታ በስለት ከመወጋት እስከ በገመድ መታነቅ የሚያደርስ አሰቃቂ ሁኔታ  መገደላቸውን ነው የአምነስቲ ሪፖርት የሚያስረዳው።
የሰብአዊ መብት ተሟጋች  አቶ ያሬድም ሆኑ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ድርጊቱ በአለማቀፍ ህግ የሚያስጠይቅ፣ በሰው ዘር ላይ የተፈጸመ ከባድ ወንጀል መሆኑን ጠቁመዋል። በማይካድራ የተፈጸመው ድርጊት ብቻውን በህወሃት አመራሮችና በድርጊቱ ተሳታፊዎች ላይ የተፈጸመውን የወንጀል ቅጣት የሚያስከትል መሆኑንም የህግ ባለሙያና የሰብአዊ መብት ተመሟጋቹ አቶ ያሬድ አስረድተዋል።
በማይካድራ አማራዎችን ለይቶ የተፈጸመው ጭፍጨፋ ሲሰማ 560 ሰዎች መገደላቸው በወቅቱ የተነገረ ቢሆንም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከህዳር 5 እስከ ህዳር 9 በቦታው ተገኝቶ ባከናወነው ምርመራ ከ6 መቶ በላይ ሰዎች መገደላቸውን አረጋግጧል።
የኮሚሽኑ የምርመራ ቡድን የጥቃቱ ሰለባዎችና ከጥቃቱ ያመለጡትን፣ የአይን ምስክሮችን፣ የመጀመሪያ እርዳታ ሰጪዎችን፣ የሃገር መከላከያ ሰራዊት አባላትን፣ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችን ጨምሮ ከልዩ ልዩ ምንጮች መረጃዎችን ማጣራቱን አስታውቋል።
ማይካድራ ከተማ ከ45 ሺህ እስከ 50 ሺህ  ገደማ ህዝብ  የሚኖርባት አነስተኛ ከተማ ስትሆን ሰዎች ወደ የመኖሪያ ቤታቸው እንዲገቡ ከተደረገ በኋላ ነው  በየቤታቸው እየተሄደ ጥቃቱ የተፈፀመባቸው ተብሏል።
ጥቅምት 30 ቀን ከቀኑ 9 ሰዓት ገደማ የጀመረው  ጥቃቱ ሌሊቱን ሙሉ ቀጥሎ በማግስቱ ህዳር 1 ቀን ጥቃት ፈጻሚዎቹ ከተማዋን ለቀው ሊወጡ ችለዋል ይላል የኢሰመኮ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት። በጥቃቱም የትግራይ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ “ሳምሪ” ከተባለው የወጣቶች ቡድን እንዲሁም የተማዋ አስተዳደር መሳተፋቸው በሪፖርቱ የተመለከተ ሲሆን። ጥቃቱም በአብዛኛው በወንዶች  ላይ ያነጣጠረ ነበር ተብሏል፡፡
ኢሰመኮ ይህን ሪፖርት ካወጣ በኋላ በማይካድራ ከተማ ተጨማሪ የ74 ሰዎች አስክሬን በጅምላ በስውር ስፍራ ላይ ተጥሎ መገኘቱ የተገለጸ ሲሆን የኢሰማኮ ምርመራ ቡድን በበኩሉ፤ አሁንም ተጨማሪ ማጣራት እያደረገ መሆኑንና የሟቾች ቁጥር ምናልባትም ወደ 1 ሺህ ሊጠጋ እንደሚችል ግምቱን አስቀምጧል።
ይህን በህወሃት  ሃይል የተፈፀመውን አሰቃቂ ድጊርት በእጅጉ ያወገዘው ኢዜማ በበኩሉ፤ በህወሃት  መሪነት አመራርነት የተተገበረው የዘር ፖለቲካ መጨረሻው መልክ እየተለየ፣ ቋንቋ እየተሰማ፣ ስም እየተጠየቀና መታወቂያ እየታየ መተራረድ እንደሚሆን ቀድሞም የታወቀ ነበር ብሏል።
ሃገሪቱ ከገባችበት አዙሪት መውጫው መንገድም የችግሩ ምንጭ የሆነውን የዘር  ጭፍጨፋ ፖለቲካ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ መሆኑን የጠቀሰው ኢዜማ፤ በዚህ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ  የሆኑ ወንጀለኞች ሁሉ ከሃገር ውስጥም ይሁን ከውጭ ከየተደበቁበት ተይዘው ለፍርድ እንዲቀርቡ አሳስቧል።


Read 545 times Last modified on Sunday, 29 November 2020 14:50