Sunday, 22 November 2020 00:00

ሀኒባል (የካዛንቺስ ሌሊቶች)

Written by 
Rate this item
(15 votes)


             ሕይወት ደስ አይልም፣ ግና መኖር እዳ ነውና መቋጫውን በውል የማላውቀውን የሕላዌ ጐዳና ተከትዬ በማዝገም ላይ እገኛለሁ፡፡ የኑሮ ግብስብስ ሸክም አጉብጦኛል፡፡ ዛሬም ልክ እንደ ሁልጊዜው ማልጄ ነው ሥራ ቦታ የደረስኩት፡፡ ከካዛንቺስ ለገሀር ለመምጣት ግማሽ ሰአት ብቻ ነው የፈጀብኝ፡፡ የግንበኛው ወዳጄ መሳፍንት ረዳት ሆኜ እዚህ ቦታ መሥራት ከጀመርኩ ሁለት ሳምንት ሆኖኛል፡፡ ከእሱ ጋር የጀመርነው የግንባታ ሥራ ዛሬ ፍጻሜውን ያገኛል፡፡ መሳፍንት የሚከፍለኝ ገንዘብ የአንድ ወር የምግብ ቀለቤን መሸፈን ይችላል፤ቀሪው ገንዘብ ጥቂት አሮጌ መጽሐፎች መግዛት ያስችለኛል፡፡ ከዛ በኋላ ምን እንደሚፈጠር መገመት አልችልም። ወትሮም ረዥም የኑሮ ትልም ኖሮኝ አያውቅም፡፡ የሕይወት ጐዳና ረዥም፣ ጉዞውም ፈጽሞ የማይተነበይ ነው፡፡ ያለፍኩበት የሕይወት መንገድ ይህን እውነት እንድቀበል ተፅእኖ አድርጓል፡፡
የእኔ እና የመሳፍንት ትውውቅ የቆየ ነው። ረዥም ጊዜያትን አብረን ጐዳና ኖረናል፣ አመዳዩንና የቀን ሐሩሩን ችለን፡፡ የጠንካራ ወዳጅነታችን መሠረቱ አብረን ያሳለፍነው የኑሮ ውጣ ውረድ ነው፡፡
“እኔ እምልህ ሀኒባል፣ ባለፈው ስለ አወጋውህ ጉዳይ ምን ወሰንክ?” አለ መሳፍንት የያዘውን የመለሰኛ መፋስ መሬቱ ላይ አኑሮ፣ ጥርብ ድንጋይ ላይ እየተቀመጠ።
“ስለ የቱ ጉዳይ?”
“ከአገር የመውጣቱን ጉዳይ”
“አሁንም በወትሮ አቋሜ እንደረጋሁ ነኝ፣ አገር ለቆ የመሰደድ ሕልም የለኝም፡፡”
“አሁን እየገፋኸው ያለው ኑሮ ተመችቶሀል ማለት ነው?
“ባይመችም ስደትን ግን አልመርጥም። ደግሞም ዳግመኛ ስህተት መሥራት አልፈልግም፡፡” ፊት ለፊቱ ተቀምጬ ሲጋራ ለኮስኩ፡፡
“እኔ ግን በአቋሜ እንደጸናሁ ነኝ፤ ኑሮዬን ለመለወጥ ብቸኛው አማራጭ ሆኖ ያገኘሁት ስደት ብቻ ነው፡፡”
“ብዙዎች የስደትን መጥፎ ገጽታ አይገነዘቡትም፡፡”
“እውነት ነው፣ በስደት ወቅት ብዙ ውጣ ውረድ ያጋጥማል፡፡ ሰው ተስፋው ከተሟጠጠ ግን
ከመሰደድ የተሻለ አማራጭ የለውም።” ከደረት ኪሱ ውስጥ ሲጋራ አውጥቶ አቀጣጠለ፡፡
“በሁሉም ነገር ተስፋ ቆርጠሃል ማለት ነው?”
“አዎ! ከምነግርህ በላይ፡፡ እዚህ አገር እንደምታየው ተስፋን የሚሰጥ አንዳችም ነገር የለም፡፡” አለ ገጹን አጨፍግጎ፡፡ ቀይ ፊቱ ላይ የጐፈረው ሪዙ የተለየ ግርማ ሞገስ ሰጥቶታል፡፡
“አንድ ያቀድኩት ጉዳይ አለ፣ እሱ ከሰመረ በቅርቡ ከአገር እወጣለሁ፡፡”
“አሁንም ወንጀል ለመፈጸም ታቅዳለህ? ለምንድነው ካለፈው ስህተትህ የማትማረው?” አልኩ በቁጣ አፍጥጬበት፡፡
“ይሄ እቅድ ቀሪ ኑሮዬን የሚወስን ነው፡፡ መሞከር ግድ ይለኛል፡፡”
“ብትያዝስ? እስር አይሰለችህም?”
“የሚከውነውን ጉዳይ በወጉ ሳያጤን የሚነሳ እንዝላል እንዳልሆንኩ ታውቃለህ።” አለ ድፍርስ ዐይኖቹን እላዬ ላይ ተክሎ፡፡
“ግን እኮ በተደጋጋሚ ተይዘህ ታስረሀል።”
“እሱ የሆነው በተባባሪዎቼ ሸፍጥ ምክንያት ነው፡፡”
“ለምን ታማኝ የሆኑ ሰዎች ቀድመህ አልመረጥክም?”
“የሰዎችን ልብ ማወቅ አይቻልም፡፡”
“እንዴት?”
“የቅርብ ወዳጄ ያልካቸው ሰዎች ተለውጠው መቃብርህን ሲምሱ ታገኛቸዋለህ፡፡ ወዳጅና ጠላትን ለይቶ ማወቅ ከባድ ጉዳይ ነው፡፡” ቂጡ የደረሰ ሲጋራውን ስቦ ቡሹን መሬት ላይ ጥሎ በእግሩ ረገጠና ከተቀመጠበት ተነሳ፡፡ ንግግሩ የማይታበል ሐቅ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ግን አልተቀበልኩትም፡፡
“ጊዜው እንዴት ነጉዷል እባክህ!” አለ የእጅ ሰአቱን አይቶ፡፡
“ምሳ ሰአት አልፏል፣ እንውጣ፡፡ በዚያውም የማጫውትህ ጉዳይ አለኝ፡፡” ተያይዘን በአቅራቢያችን ወዳለ ምግብ ቤት አመራን፡፡
ምሳ እየበላን ሳለ መሳፍንት ሊፈጽም የወጠነውን ጉዳይ በዝርዝር አወጋኝ፡፡ የአቀደውን የንብረት ዝርፊያ ለመፈጸም ግብረ አበሮቹን በህቡዕ አደራጅቷል፡፡ በምላሹ እቅዱን አውግዤ ጠንካራ ትችት ሰነዘርኩ፡፡
***
ሮማን በተባለች እርጉም (ጓለሞታ ምሁር) ሸፍጥ ከሥራ ገበታዬ ከተሰናበትኩ በኋላ ወደ ካዛንቺስ አቅንቼ መኖር እንደጀመርኩ ሰሞን ነበር ከአስቴር ጋር የተዋወቅኩት፡፡ ከእሷ ጋር የተገናኘነው እዛው ካዛንቺስ አካባቢ የሚገኝ ቬነስ የተባለ ዝነኛ ሆቴል ውስጥ ነው፡፡ በእዛ እለት ወደ ሆቴሉ ያመራሁት አመሻሽ ላይ ነበር፣ ከስራ እንደወጣሁ፡፡ ጥቂት ተስተናጋጅ ነበር ሆቴሉ ውስጥ የነበረው፡፡ በወቅቱ በስፋት ተደማጭ የነበረ የባሕር ማዶ ሙዚቃ ግድግዳው ላይ በተሰቀሉት ድምጽ ማጉያዎች በኩል ጐላ ብሎ ይንቆረቆራል። አስቴር፣ ፊት ለፊቴ ከሚገኘው ቦታ ላይ ተቀምጣ ቢራ እየጠጣች ነበር፡፡ ዐይኖቼ እሷ ላይ ባረፉበት ቅጽበት ነበር በመግነጢሳዊ ውበቷ የተሳብኩት፡፡ ሙሉ ትኩረቷን ዳንስ ወለሉ ላይ ወጥቶ የሚደንሰው አጭር ራሰ በራ ጎልማሳ ላይ አድርጋ እንቅስቃሴውን ትታዘባለች፡፡ ሐምራዊ ጉርድ ቀሚስ ለብሳለች፡፡ በደብዛዛው ብርሃን ውስጥ ስትታይ የተጋነነ ውበት ያላት ትመስላለች፡፡ ከፊል ፊቷን የሸፈነው ረዥም ፀጉሯ ጀርባዋ ላይ ተኝቷል፣ ሰልካካ አፍንጫዋ ላይ የወርቅ ዝማም አድርጋለች፡፡ ዐይኖቿን ከደናሹ ሰውዬ ላይ ነቅላ እኔ ወደ ተቀመጠኩበት አቅጣጫ ስትዞር ዐይን ለዐይን ተጋጨን፡፡ ቀድማ ዐይኖቿን ሰበረችና እግሯን አነባብራ ሲጋራ አቀጣጠለች፡፡ ሆቴሉ ውስጥ ከገባሁበት ጊዜ ጀምሮ በዐይኖቻቸው ሲያባብሉኝና ሲጠቅሱኝ የነበሩት ሁለቱ ሴቶች ከባልኮኒው ተነስተው ወደ ዳንስ ወለሉ አመሩና ራሰ በራውን ጎልማሳ አጅበው መደነስ ጀመሩ፡፡ ውዝዋዜያቸው የሰመረ ውበት አልነበረውም፤ ግዙፍ ዳሌአቸውን (እንጀራቸውን እሚሸምቱበትን) ለማስተዋወቅ ብቻ ወደ ዳንስ ወለሉ የወጡ ይመስላል፡፡ በተለይ የአንደኛዋ ሴት (ወፍራሟ) ተመሳሳይና አሰልቺ እንቅስቃሴ የዳንስ ልምድ እንደሌላት ያሳብቃል፡፡
የሴቶቹን ትእይንት ቸል ብዬ አፍንጫዋን በወርቅ ዝማም ወዳስጌጠችዉ ሴት ሳማትር ዳግም ዐይኖቻችን ተጋጩ፣ በአጸፋው ፈገግታ ለገሰችኝ፡፡ ራሰ በራውን ጎልማሳ አጅበው ሲደንሱ ከነበሩ ሴቶች አንዷ (ወፍሯሟ) ዳንሷን አቋርጣ፣ የፊቷን ላብ በአይበሉባዋ እየጠረገች ወደ መቀመጫዋ ተመለሰች፡፡
ከውጭ የገቡ ሁለት ጐልማሶች ጐኔ ካለው ቦታ መጥተው እንደተቀመጡ ተነሰቼ ወደ አስቴር አመራሁ፡፡
“መቀመጥ እችላለሁ?” አልኩ፤ ፊቷ ቆሜ በትኩረት እያስተዋልኳት፡፡
“ይቻላል” አለች፤ ፈገግ ብላ ፊቷ ወዳለው ሶፋ እየጠቆመች፡፡ እንደ ኮከብ የሚያበሩ ትላልቅ ዐይኖች አሏት፡፡ በቁሜ ቀሚሷ ያልሸፈናቸውን ጭኖቿን በጨረፍታ ገረመምኩና ሶፋው ላይ ተቀመጥኩ፡፡
“ብቻዬን መቀመጡ ደብሮኝ ነው አንቺ ጋ የመጣሁት፡፡”
“ጥሩ አደረክ፣ ከሰው ጋር መጫወት መልካም ነው፡፡” አለች በፈገግታ ተሞልታ፣ ጥርሶቿ በረዶ የመሰሉ ናቸው፡፡
“ሀኒባል እባላለሁ”
“አስቴር” እጅ ለእጅ ተጨባበጥን፡፡
“ታዲያስ? ሥራ እንዴት ነው? ኑሮ…?” አንገቷን ሰብቃ ከፊል ፊቷን አልብሶ የነበረውን ረዥም ፀጉሯን ወደ ጆሮዋ ኋላ መለሰች፡፡
“ሁሉም መልካም ነው” ብርጭቆዬን አንስቼ ተጎነጨሁ፡፡
“በአንቺስ በኩል?”
“የእኛ ሥራ እንደምታየው ነው…” ቢራዋን ተጎንጭታ ትኩረቷን ወደ ዳንስ ወለሉ ትእይንት መለሰች፡፡ በመሐል ጥቁር ጉርድ ቀሚስ የለበሰች ቀይ አጭር ሴት እኛ ወደተቀመጥንበት መጥታ ለአስቴር የሆነ ጉዳይ በጆሮዋ ሹክ ብላት ተመልሳ ሄደች። አጭሯ ሴት ተመልሳ እንደሄደች፣ አስቴር ከመቀመጫዋ ተነስታ እንደምትመለስ ነግራኝ ይቅርታ ጠይቃ ወጥታ ሄደች፡፡
ስገባ ባዶ የነበረው ሆቴል በሰው ተጨናንቋል፡፡ እዛ ሆቴል ከአስቴር ጋር እስከ ሌሊት ድረስ አብረን አመሸን፤ በየመሐሉም እያስነሳኋት አብረን ደነስን፡፡
አስቴርን ተሰናብቼ ሌሊት ላይ ከሆቴሉ ስወጣ ካዛንቺስ ያለ ወትሮዋ አንቀላፍታ ነበር፡፡ ከዛ፣ በድንግዝግዝ ብርሃን በመታገዝ ረዥም መንገድ ከተጓዝኩ በኋላ በአሳር እቤቴ ገባሁ፡፡
በሂደት፣ ከሥራ መልስ አስቴር ወደምትገኝበት ሆቴል ጐራ ማለት አዘወተርኩ፡፡ በዚህም ሰበብ ይበልጥ መቀራረብ ቻልን፡፡ እሷ በማትኖርባቸው ቀናት ቬነስ ሆቴል ውስጥ ማምሸቱን ስለማልወድ በግዴ ወደ ሌሎች ቡና ቤቶች እሰደዳለሁ፡፡
አንድ ቀን የተፈጠረ ክስተት የእኔ እና የአስቴር ግንኙነት ሌላ መልክ እንዲኖረው አደረገ፡፡ በዛ እለት፣ ሥራ አምሽቼ (የግል ጋራጅ ውስጥ ነበር የምሠራው) እኩለ ሌሊት ላይ ወደ ቤቴ የሚወስደውን አውራ መንገድ ይዤ እየገሰገስኩ ነበር፡፡ ከእኔ በተቃራኒ አቅጣጫ አንዲት ሴት ከጥቁር መርሴዲስ መኪና ወርዳ ወደ እኔ መምጣት ጀመረች። እየቀረበችኝ ስትመጣ አስቴር መሆኗን ለየሁ። ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ቤቷ ድረስ እንድሸኛት ጠይቃኝ፣ በጨለማ በተዋጠ ጠባብ የኮረኮንች መንገድ ጉዞ ጀመርን፡፡
“የት አምሽተህ ነው?” ያቀፈችውን ቀኝ ክንዴን ይበልጥ አጥብቃ ያዘች፡፡
“ሥራ”
“ሥራ ነው እንዲህ ያጠፋህ?”
“አዎ ሥራ ይበዛል፡፡” አልኩ በደፈናው። መልካም ጠረኗ ከቀዝቃዛው አየር ጋር ተቀላቅሎ በአፍንጫዬ ይሰርጋል፡፡
“ሁሌም አምሽተህ ነው የምትገባው?” ለስላሳ ነው ድምጿ፣ ልክ እንደ አርጋኖን በጆሮ ውስጥ የሚፈስ፡፡
“አይ አልፎ አልፎ ነው”  ክንዴን ለቃ ወገቤን አቀፈች፣ ትከሻዋን አቀፍኳት፡፡ ከዛ፣ አምሽቶ መግባት የሚያስከትለውን ዳፋ እያወጋች፣ ጠባቡን የኮረኮንች መንገድ ጨርሰን ቤቷ ደጅ ደረስን፡፡   
“ግባ?” አለች ወገቤን ለቃ ከቦርሳዋ ውስጥ የግቢ በር ቁልፍ እያወጣች፡፡ አልተግደረደርኩም፣ አብሬአት ወደ ውስጥ ዘለቅኩ፡፡
ከአከራዮቿ ትልቅ ቪላ ቤት ጀርባ የሚገኘው ቤቷ በቁስ የተሞላ ነው፡፡ ከትልቅ አልጋዋ ፊት ለፊት ከሚገኘው ወንበር ላይ እንድቀመጥ ጋበዘችኝና ባለ ትልቅ ታኮ ጫማዋን ቀይራ ወደ ውስጠኛው ክፍል ዘለቀች፡፡ ጥቁር ሹራቧ የደጋን ቅርፅ ያለው ወገቧ ላይ የተስማማ ነው፡፡ የውስጠኛው ክፍል የሚገኘው እኔ ከተቀመጥኩበት ትይዩ ነው፡፡ በመሆኑም፣ እራት ለማቅረብ ስትንጐዳጐድ ትታያለች፡፡ ዱካ ላይ ፊቷን አዙራ ስለ ነበር የተቀመጠችው ለእይታዬ ግልጽ የነበረው አካሏ ጀርባዋ ብቻ ነበር፡፡ ታላቅ ዳሌዋ ዱካውን ሞልቶታል፡፡
ለግማሽ ሰአት ያህል የተንጐዳጐደችበትን ምግብ አቅርባ ከቀማመስን በኋላ ቀድሜ አልጋው ላይ ሰፈርኩ፡፡ ልብሷን ለውጣ መጥታ ጐኔ ተጋደመች፣ ጀርባዋን ሰጥታ፡፡
“ይኸውልህ ኑሮዬ ይህን ይመስላል እንግዲህ”
“ጥሩ ቤት ይዘሻል፣ ኪራዩ ካልተወደደ በቀር” አልኩ ከገባሁበት የሐሳብ ባሕር ወጥቼ ቤቱን እየቃኘሁ፡፡
“ምን ዋጋ አለው፣ ምን ቢያምር የሰው ቤት የሰው ነው፡፡ ድንኳንም እንኳ ቢሆን የራስ ጐጆ ከሆነ ግን ይሞቃል” የራስጌውን መብራት ካበራች በኋላ ተቀናቃኙን ደማቅ ብርሃን ደረገመችው፡፡
“ሀኒባልዬ፤ ጓደኛህ የት ጠፋ?”
“የቱ?”
“ያ ቀልደኛው”
“ሲራክ ነው?”
“ሲራክ ነው ሥሙ? በጣም ተጫዋች ነው። ባለፈው የመጣችሁ እለት እኮ ወጉ አስቆ ሊገለኝ ነበር” መኝታው እንዳልተመቻት አይነት ተነቃንቃ ተጠጋችኝ፡፡
“አዎ፣ በጣም ቀልደኛ ነው” የሚሸተኝ ጠረኗ የቀድሞ አይነት አይደለም፤ ይኸኛው የጽጌረዳ መአዛ አለው፡፡ በመሐላችን ታላቅ ዝምታ ነገሰ፡፡ ከውጪ አስቀያሚ የውሻ ማላዘን ድምፅ ይሰማል፡፡  ለጥቂት ጊዜ ሳመነታ ቆይቼ ወገቧን አቀፍኩ፡፡ ድጋሚ ተነቃንቃ ይበልጥ ተጠጋችኝ፡፡ እጄን ከወገቧ ላይ አሽሽቼ ወደ ጡቶቿ ሰደድኩ። አተኛኘቷን ለውጣ በጀርባዋ ተንጋለለች። ጡቶቿ እንደ እቶን ይፋጃሉ፡፡ በጋራ ለብሰነው የነበረውን አንሶላ ገፋ ወደ እኔ ተስባ መጣችና ጽጌረዳ ከንፈሮቿን ከንፈሮቼ ላይ አኖረች፡፡ ጡቶቿን ጋርዶ የነበረው ቀይ ጡት መሸፈኛ በቦታው አልነበረም፡፡ ወርቃማው ብርሃን የደረንቷና ፊቷን ቅላት አጋኖታል፡፡ የጋመ ገላዋን አቅፌ በውብ ጡቶቿ መሐል ሟሟሁ፣ አልጋው ላይ ድርና ማግ ሆንን፡፡
ሌሊቱ ተሸኝቶ የብርሃን ጐህ ሲቀድ ከእንቅልፌ ነቃሁ፡፡ ወዲያው፣ ድንገት የተወለደ መንፈሴን ክፉኛ ያናወጠ የጥፋተኝነት ስሜት ከበበኝ፡፡
እንዲህ አይነቱ ባሕርይ አብሮኝ የዘለቀ ነው፡፡ አስቴር፣ ጐኔ ተጋድማ እንቅልፏን ትለጥጣለች፡፡ እንዳሻው የተበታተነው ረዥም ፀጉሯ ከፊል የፊቷን ገፅ አልብሷል፣ ከብርድ ልብሱ ሾልኮ የወጣው ቀኝ እግሯን እላዬ ላይ ሰቅላለች፡፡ ተረከዟ ሎሚ የመሰለ ነው፡፡
አድራጐቴ የወለደው ይሉኝታ ሸብቦኝ ከተጋደምኩበት ተነሳሁና ፊቷን ሽሽት በጥድፊያ ልብሴን መለባበስ ጀመርኩ፡፡ ብዙ ጊዜ የሌሎችን በጐነት ለስውር ግላዊ አላማችን እንጠቀምበታለን። እኔም ይችን ገላዋን ሽጣ የምታድር የዋህ ሴት መተኛቴ ትልቅ ፀፀት አሳድሮብኛል፡፡ ለደንቡ ያህል ብጫቂ ወረቀት ላይ አጭር መልዕክት አስፍሬ በችኰላ የአስቴርን ቤት ለቅቄ ወጣሁ፡፡


Read 2641 times