Tuesday, 24 November 2020 00:00

ፑቲን እና ቤተሰባቸው መቼም እንዳይከሰሱ ዋስትና ሊሰጣቸው ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  የሩስያውን ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ከተጠያቂነት ለማዳን ተብሎ የታሰበ ነው የተባለውንና የአገሪቱ ፕሬዚዳንቶች መንበረ ስልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ ከእነ ቤተሰባቸው በወንጀል እንዳይከሰሱ ዋስትና የሚሰጠው አወዛጋቢ ረቂቅ ህግ ባለፈው ማክሰኞ በሩስያ ፓርላማ አባላት ሙሉ ድጋፍ ማግኘቱን ዘ ሰን ዘግቧል፡፡
የ68 አመቱን ፕሬዚዳንት ፑቲን ብቻ ሳይሆን መላ ቤተሰባቸውን ከህግ ተጠያቂነት ነጻ የሚያወጣው ይህ ረቂቅ ህግ፣ ቤተሰቡ የወንጀልም ሆነ የአስተዳደር ጥፋት ቢፈጽሙ እንዳይጠየቁ፤ እንዳይታሰሩ፣ ምርመራ እንዳይደረግባቸውና ቤት ንብረታቸው እንዳይፈተሽ ዋስትና የሚሰጥ እንደሆነ ዘገባው አመልክቷል፡፡
በፓርላማው አባላት ድጋፍ ያገኘው ረቂቅ ህጉ በቀጣይም ወደ ላይኛው ምክር ቤት ተልኮ ድምጽ እንደሚሰጥበት የጠቆመው ዘገባው፣ ከምክር ቤቱ አባላት አብዛኞቹ የፕሬዚዳንት ፑቲን ደጋፊዎች በመሆናቸው ህጉ የመጽደቅ ዕድሉ እጅግ ሰፊ ነው መባሉንም ገልጧል፡፡
ረቂቅ ህጉ ባለፈው ሃምሌ ወር የተደረገው ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ አካል እንደሆነ ያስታወሰው ዘገባው፤ ማሻሻያው አራተኛ የስልጣን ዘመናቸው በ2024 የሚያበቃው ፕሬዚዳንት ፑቲን ለተጨማሪ ሁለት የስልጣን ዘመናት ወይም 12 አመታት በስልጣን ላይ እንዲቆዩ የሚፈቅድ በመሆኑ በብዙዎች ሲተች መቆየቱንም አክሎ ገልጧል፡፡

Read 2796 times