Saturday, 21 November 2020 10:35

“ዳሩ ሲነካ መካከሉ ዳር ይሆናል”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የአንበርብር ጎሹ ሞት
እስኪ ላነሳሳው
አንበርብር ጎሹን
በደራ አደባባይ የወደቀውን
እሱስ ሆኖ አይደለም
ታሪከ ቅዱስ
መጽደቋንም እንጃ
ያቺ ያንበርብር ነፍስ
የሚያዘወትራት የአምበርብር ወዳጅ
ነበረችው አንዲት ጠይም ቆንጆ ልጅ
ሴተኛ አዳሪ ናት እሱም አላገባ
ተሳሚው ቢበዛም ይህቺው አበባ
አያ ማር ወለላ አያ ማር እሸት
እሱ ብቻ ነበር የእሳቲቱ እራት
አንድ ቀን ማምሻውን ደጃፉ ቢመጣ
ውይ የሚለው አጣ ገጠመው ዝምታ
ሌላ ሰው ወርሶታል የሱን ቦታውን
ግራ እንደገባው ነው እንዲህ እንዲሆን
“ወግድ ከዚህ እራቅ ማሚም ላኦቼም
አንተን ያዩ እንደሆን ወደ እኔ አይመጡም”
ተቆጣ ነደደው ተሰማው ንዴት
ለንጉሱ ተመኘ ለዚያ ቀን ሌሊት
ይኸውም ሆነና ዋነኛ ጥፋቱ
አርባ ጅራፍ ሆነ ሃቀኛ ቅጣቱ
ሞራ ሲጠጣ ነው የዋለው ጅራፉ
ግን አላርፍም አለ የገራፊው አፉ
“አይንህን ተጠንቀቅ ወንድ አደራህን
እንዳላጎድልብህ በከንቱ አካልህን”
እያለ ገረፈው
ግርፉ ሲበዛበት
እዚያው ግጥም አለ
ጅራፉም ዕድሜውም 30ን ሳይሞላ
*   *   *
ኸረ ስንቱ ስንቱ ናቸው የሞቱቱ
ለንጉሳቸው ክብር ለባንዲራይቱ
*   *   *
ያለ ዕድሜያቸው የተቀጨ አያሌ ወጣት አለ። በተለይ በአሁኑ ወቅት የኮሮና ክፋት በተባባሰበት ሰዓት ለህልፈተ ሞት የተጋለጠ ወጣት እጅግ በርካታ ነው። ሙዚቃዎችን በግጥሙ መመርመርና ጥንቃቄን ማስቀደም የወቅቱ ዋነኛ አጀንዳ ነው።
ከቤት አትውጡ ሲባል ለዋዛ ፈዛዛ ኤደለም። ሰው በተሰበሰበበት ስፍራ አትገኙ ሲባልም የዋዛ ፈዛዛ ኤደለም።
“ጽናትና ጽናት የሚስፈልግበት ጊዜ መጥቷል” በተለይ ወጣቱ ትውልድ፣ በእንዝላልነትም ሆነ በድፍረት የሚፈጸሙ ድርጊቶች ከአደጋ ሁሉ የበረታ አደጋ፣ ከመከራም ሁሉ የጠለቀ መከራ ውስጥ የሚዳርጉት ከባድ የወቅት እኩያ ሳንካ ተጋርጦበት ይገኛል።
ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፤ ሞት ሳይሞቱት ነው የሚለመድ ካለን እጅግ ረዥም ጊዜ አልፏል። ብዙ አዳማጭ በጠፋበት ጊዜ ቃልን ደግሞ ደጋግሞ መናገር ግድ ይሆናል።
"በማዕበል በፊት የባህር እርጋታ “
ከንግግር በፊት የአርመሞ ጠቅታ
አሁንም ሕዝባችን የአንድ አፍታ ዝምታ
ነገ ግን ሊወገድ መታገዱ አይቀርም
ታግሎም ድል ያደርጋል አንጠራጠርም።
ድንቁርናን እንዋጋ
በሽታን እንፋለም
መዘናጋትን በንቃት እንታገል
ለሀገራችንና ለህዝባችን ማናቸውንም ፈተና እንጋፈጥ
ያለጥርጥር የተሻለች ኢትዮጵያ ትኖረናለች!
ሁሉም መንገድ ሊሾና አስፋልት አይሆንምና ኮሮኮንቹንም ለመራመድ ጥረት እናድርግ። ሁሉም አልጋ ከእርግብ ላባ የተሰራ አይደለምና ተጠንቅቀን እንተኛ፣ ተጠንቅቀን እንነሳ።
ስለሆነም በአሁኑ ሰዓት ቀበቶን ጠበቅ ማድረግ ከሁላችንም የሚጠበቅ ግዴታ ነው። ዙሪያ ገባውን ሀገር በተከፈቱ አይኖች እንይ። ምነው ቢሉ……. ዳሩ ሲነካ መካከሉ ዳር ይሆናል ይሏልና!

Read 15226 times