Saturday, 07 November 2020 14:01

በመላው አዲስ አበባ 10 ኩዊንስ ሱፐር ማርኬቶች ይከፈታሉ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 በ350 ሚሊዮን ብር የማስፋፋት ስራ እየተከናወነ ነው ተብሏል
                     
           ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ፤ በየጊዜው በፍጆታ  ሸቀጦች ላይ እየታየ ያለውን የዋጋ ንረት ለመቀነስና ገበያውን ለማረጋጋት አቅርቦቱን በከፍተኛ መጠን መጨመሩን የገለፁት አንድ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር፤ ኩዊንስ ሱፐር ማርኬቶችን በ350 ሚሊዮን ብር ለማስፋፋት ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል። በዚህ ዓመት ብቻ ሶስት ትልልቅ  ኩዊንስ ሱፐር ማርኬቶች በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች የሚከፈቱ ሲሆን ይህም የሱፐር ማርኬቶቹን ቁጥር ወደ 7 ከፍ እንደሚያደርጋቸው የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አንድ ከፍተኛ አመራር ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል።
እስካሁን  በቀራኒዮ፣ ሳር ቤት፣ ጉርድ ሾላና ካዛንቺስ በተከፈቱት ኩዊንስ  ሱፐር ማርኬቶች፣ የተለያዩ የፍጆታ ሸቀጣ ሸቀጦችን በማይታመን ዋጋ በማቅረብ ህብረተሰቡን ከተጋነነ  የፍጆታ ዋጋ እፎይ ማሰኘቱን የተናገሩት  እኚሁ ከፍተኛ አመራር፤ የገበያ ማረጋጋቱን ስራ ይበልጥ አጠናክሮ ለመቀጠልም ዘንድሮ በአቃቂ ቃሊቲ፣ በስታዲየምና በሰፈረ ሰላም ሶስት ትልልቅ ሱፐር ማርኬቶችን ለመክፈት ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልፀዋል።
ባለፈው ነሃሴ ወር የአዲስ ዓመት በዓልን ምክንያት በማድረግ፣ ዘይት ከውጭ በማስመጣት 5 ሊትሩ በ330 ብር ለገበያ ማቅረቡን የሚያስታውሱት ከፍተኛ አመራሩ፤ አሁን በአጠቃላይ ይህን ተከትሎም በገበያው ላይ 5 ሊትር ዘይት ከ300 ብር በታች መሸጥ መጀመሩን ተናግረዋል። ሚድሮክ ከላይኛው አዋሽ የሚያመርተው ጣፋጭ ብርቱካን በኪሎ 25 ብር ለተጠቃሚዎች ማቅረብ ከጀመረ ወዲህም፣ ከ50 እስከ 70 ብር የነበረው የብርቱካን ዋጋ 40 ብር መግባቱን ያስረዳሉ፡፡ 7 ብር ይሸጥ የነበረውን እንቁላል በ4 ብር፣ 500 ብር የገባውን የእስላም ሀላል ስጋ በ250 ብር  እስከ 450 ብር  የሚሸጠውን ማር ራሱ ሜድሮክ በኢሊባቡር የሚያመርተውን ጥራቱን በጠበቀ ደረጃ አሽጎ  በ350 ብር እያቀረበም ነው ብለዋል፣ በሌላ በኩል ሽንኩርት፣ቲማቲም፣ቃሪያ፣ሰላጣ፣ቆስጣ ጎመንና ድንች አትክልት ተራ ከሚሸጥበት ተመጣጣኝ  በሆነ ዋጋ ለተጠቃሚዎች ከማቅረቡም በላይ ባለፉት 3 ወራት እነዚህን ምርቶች ለውጭ ገበያ በማቅረብ 13 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማስገኘቱን የሚድሮክ ከፍተኛ አመራር አስታውቀዋል፡፡
በኩዊንስ ሱፐር ማርኬቶች  ለተጠቃሚዎች በምናቀርባቸው ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶችና  ምክንያታዊ ዋጋ ተጠቃሚው  ደስተኛ ሆኖ ተሰልፎ እየገዛ ነው ያሉት እኚሁ ሃላፊ፤ የማህበረሰቡን ፍላጎት ግምት ውስጥ በማስገባት በየአቅራቢያው አገልግሎቱን እንዲያገኝ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት በሁሉም ክፍለ ከተሞች የኩዊንስ ሱፐር ማርኬቶች ይከፈታሉ ብለዋል።
ሚድሮክ ኢንቨስትመት ግሩፕ በተለይም ባለፈው ዓመት የአመራር ለውጥ ካደረገ በኅላ በ34ቱም ኩባንያዎች ከፍተኛ መነቃቃት መፈጠሩን ነው አመራሩ ለአዲስ አድማስ ያስረዱት። ኩባንያው ማይኒንግ፣ ኮሜርስ፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ እንዲሁም አግሪካልቸርና አግሮ ፕሮሰሲንግ በሚል አራት ዘርፎች አደራጅቶና ለአራቱም ዘርፎች አራት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚዎች መድቦ እስከ ዛሬ ተፋዝዞ የነበረው የንግድ እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ መደረጉን ጠቁመዋል - ኃላፊው።
አዲሱ አመራር ስራው በተቀላጠፈና በተናበበ መልኩ እንዲቀጥል  የሰለጠነ የአመራር ዘዴን ተከትሎ እየሰራ መሆኑን ያስረዱት ከፍተኛ አመራሩ በተለያዩ የሚድሮክ ዲፓርትመንቶች ከፍተኛ የለውጥና የመነቃቃት እንቅስቃሴ መፈጠሩን ገልፀዋል።          

Read 2691 times