Sunday, 08 November 2020 00:00

“ቤቢ ሻርክ” በዩቲዩብ 7.04 ቢሊዮን ጊዜ በመታየት ክብረ ወሰን ያዘ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 “ቤቢ ሻርክ” የተሰኘውና በ10 አመቱ ኮርያ አሜሪካዊ ታዳጊ ሆፕ ሴጎይን የተቀነቀነው ተወዳጅ የህጻናት መዝሙር በዩቲዩብ 7.04 ቢሊዮን ጊዜ ያህል መታየቱንና በድረገጹ ታሪክ በብዛት የታየ የመጀመሪያው ቪዲዮ በመሆን አዲስ ክብረ ወሰን መያዙን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በደቡብ ኮርያዊው ኩባንያ ፒንክፎንግ የተቀረጸው “ቤቢ ሻርክ” በዩቲዩብ ላይ ከተጫነበት 2015 አንስቶ የታየበት አጠቃላይ ጊዜ ቢደመር 30 ሺህ 187 አመታት ያህል እርዝማኔ እንደሚኖረው የጠቆመው ዘገባው፣ ኩባንያው በዚህ መዝሙር አማካይነት ከዩቲዩብ ብቻ 5.2 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገቢ ማግኘቱንም አክሎ ገልጧል፡፡
ከዚህ ቀደም በዩቲዮብ በብዛት በመታየት ክብረወሰኑን ይዞ የነበረው “ዲስፓሲቶ” የተሰኘው የድምጻዊ ሉዊስ ፎንሲ የሙዚቃ ቪዲዮ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ቪዲዮው 7.038 ቢሊዮን ጊዜ ያህል መታየቱንም አክሎ ገልጧል፡፡
የኤድ ሼራን “ሼፕ ኦፍ ዩ” በ5.05 ቢሊዮን፣ የዊዝ ካሊፋ “ሲዩ አጌን” በ4.79 ቢሊዮን፣ የጌት ሙቪስ “ማሻ ኤንድ ዘ ቢር” በ4.36 ቢሊዮን፣ የሎሎ ኪድስ “ጆኒ ጆኒ የስ ፓፓ” በ4.14 ቢሊዮን፣ የማርክ ሮንሰን “አፕ ታውን ፋንክ” በ3.99 ቢሊዮን፣ የፒኤስዋይ “ጋንጋም ስታይል” በ3.84 ቢሊዮን፣ የሚሮሻካ ቲቪው “ለርኒንግ ከለርስ” በ3.65 ቢሊዮን እንዲሁም የጀስቲን ቢበር “ሶሪ” በ3.36 ቢሊዮን እይታዎች እንደ ቅደም ተከተላቸው ከ3ኛ እስከ 10ኛ ደረጃ የያዙ፣ በዩቲዩብ በብዛት የታዩ ቪዲዮዎች መሆናቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

Read 2798 times