Saturday, 07 November 2020 12:55

በትግራይ ለ6 ወራት ተፈፃሚ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢፌዴሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣውንና በትግራይ ክልል ለመጪዎቹ 6 ወራት ተፈፃሚ የሚሆነውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  አፀደቀ። ምክር ቤቱ አዋጁን የሚያስፈጽምና በጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም የሚመራ ግብረ ሃይል አቋቁሟል።
ምክር ቤቱ ከትናንት በስቲያ ባካሄደው የ6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ስብሰባው፤ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣውንና በትግራይ ክልል ተፈጻሚ የሚሆነውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያጸደቀ ሲሆን ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነ፣ አዋጁን የሚያስፈጽም ግብረ ሃይል አቋቁሟል፡፡ #የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረሃይል; ተብሎ እንደሚጠራም ታውቋል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መደንገግ ያስፈለገበትን ምክንያት ምክር ቤቱ ሲገልፅ፤ የሀገር ሰላምና ህልውና እንዲሁም የህዝብና የዜጎች ደህንነትን ለማረጋገጥ፤ ሀገሪቱን ወደ ሁከትና ብጥብጥ የሚወስዱ ድርጊቶችንም ለማስቆም ታስቦ እንደሆነ አመልክቷል።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ እየተፈጸመ ያለውን ህገወጥ ተግባር በመደበኛው የህግ ማስከበር ስርዓት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ያለው ምክር ቤቱ፤ በዚህ ሳቢያም በህገ መንግስቱ በተደነገገው መሰረት ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመጠበቅ ልዩ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገግና ተግባራዊ በማድረግ ሁኔታውን መቆጣጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ አዋጁ እንዲፀድቅ መደረጉን አመልክቷል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመላው የትግራይ ክልል ለመጪዎቹ 6 ወራት  ተፈፃሚ ይሆናል ተብሏል።   


Read 697 times