Monday, 02 November 2020 08:39

የአዲስ አበባ ባቡርን ማን እንደሚያስተዳድረው ይወሰናል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

 የቀን ገቢው ከግማሽ ሚሊየን ብር ወደ ሩብ ሚሊዮን ዝቅ ብሏል
          በአሁኑ ወቅት በየቀኑ 64ሺህ ሰው እያጓጓዘ ነው
          በየፌርማታው በየ6 ደቂቃው ለመድረስ ተጨማሪ 20 ባቡሮች ያስፈልጋሉ
         የኮሮና ወረርሽኝ የቀን ገቢውን 75 በመቶ ቀንሶበታል


          የአዲስ አበባ ቀላል ባቡርን ማን ያስተዳድር በሚለው ጉዳይ ጥናትን መነሻ ያደረገው የውሣኔ ሃሳብ ጠ/ሚኒስትሩ ለሚመሩት የማክሮ ኢኮኖሚ ጥናት ኮሚቴ ቀርቦ ውሣኔ እየተጠበቀ ሲሆን ባለፉት ዓመታት የባቡር ትራንስፖርቱ ያለማቸውን አገልግሎቶች ሙሉ ማድረግ አልተቻለም ተብሏል፡፡
ጥር 24 ቀን 2007 ዓ.ም ተመርቆ የሙከራ አገልግሎት በመስጠት አገልግሎቱን የጀመረው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት፤ያለማቸውን ግቦች እንዳያሳካ በርካታ ተግዳሮቶች እንደገጠሙት ተጠቁሟል።
የውጭ ምንዛሬ እጥረት የባቡር አገልግሎቱን አቅም ለመጨመር ዋነኛው ተግዳሮት እንደነበር ለአዲስ አድማስ የገለፁት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉቀን አሰፋ፤ የኮቪድ 19 ወረርሽኝም ዕለታዊ የማጓጓዝ አቅሙን እስከ 25 በመቶ እንዲቀንስ እንዳስገደደው ተናግረዋል፡፡
ህብረተሰቡ በኮቪድ-19 ላይ ያለው ግንዛቤ እየተሻሻለ መምጣቱን ተከትሎ፣ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ፣ የቀን የመጫን አቅሙን ወደ 75 በመቶ ለማሳደግ መቻሉን ያመለከቱት ኃላፊው፤ አሁን በቀን በአማካይ 64ሺህ ሰዎችን እያጓጓዘ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ቀደም ሲል በኮቪድ 19 ስጋት ምክንያት የማጓጓዝ አቅሙን  25 በመቶ ድረስ ቀንሶ የነበረው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት፤ 19 የሚደርሱ ፌርማታዎችንም ዘግቶ መቆየቱን ነው ሃላፊው የተናገሩት፡፡ ከጥቅምት 18 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ግን ሁሉንም ጣቢያዎች ከፍቶ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከኮሮና በፊት ባቡሩ በቀን በአማካይ 115ሺህ ተገልጋዮችን እያስተናገደ ሁሉንም  በእኩል ታሪፍ - ለማንኛውም ርቀት 4 ብር እያስከፈለ፣ በቀን እስከ 460ሺህ ብር ገቢ ያስገባ እንደነበር የገለፁት አቶ ሙሉቀን፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በቀን 64ሺህ ያህል ሰዎችን እያጓጓዘ፣ 256ሺ ብር ገቢ እያገኘ መሆኑን አመልክተዋል።
የዛሬ ከአምስት ዓመት የባቡር አገልግሎቱ ሲጀመር ለአጭር ርቀት ተጓዦች 2 ብር፣ ለመካከለኛ 4 ብር እንዲሁም ለረጅም ርቀት ተጓዦች 6 ብር እያስከፈለ፤ በቀን በአማካይ ከ350 ሺህ እስከ 400 ሺህ ብር ገደማ ገቢ ያገኝ ነበር ብለዋል - ኃላፊው። በየጊዜውም ገቢውም እያደገ መሄዱን ጠቁመው፤ የኮሮና ወረርሽኝን  ተከትሎ ግን ገቢው በ75 በመቶ መቀነሱን ይናገራሉ፡፡
ከት/ቤቶች መከፈት ጋር ተያይዞ አስፈላጊውን የጤና መመሪያዎች በመከተል አሁን ከሚያጓጉዘው በቀን 64ሺህ ሰዎች ወደ 80ሺህ ሰዎች ለማሳደግ መታቀዱንም አስታውቀዋል፡፡
ቀድሞ ከነበሩት 41 ባቡሮች ውስጥ አሁን በእለት ተእለት በስራ ላይ የሚገኙት 35 ባቡሮች ሲሆኑ በየተራ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑ ለማወቅ ተችሏል።
 የከተማዋን የባቡር አገልግሎት የበለጠ ለማዘመንና ለማሳደግ የሚያስችል ጥናት  በጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚመራው የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ጥናት ኮሚቴ መቅረቡንና ውሣኔም እየተጠበቀ መሆኑን አቶ ሙሉቀን ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት በማንና እንዴት ይተዳደር በሚለው ጉዳይ ላይም በጥናቱ  አማራጮች መቀመጣቸውን ስራ አስኪያጁ  ይገልጻሉ፡፡
ከአማራጮቹ አንዱም፡- የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱን የአዲስ አበባ አስተዳደር ከባቡር ኮርፖሬሽን ተረክቦ እንዲያስተዳድር የሚለው ነው፡፡
የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱ ሲጀመር በየፌርማታው ከ6 እስከ 8 ደቂቃ ባለው የጊዜ ልዩነት እንዲደርስ በሚል የተቀመጠውን ግብ ለማሳካትም ሆነ አገልግሎቱን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ ከተፈለገ ተጨማሪ 20 ባቡሮች እንደሚያስፈልጉ ነው   በጥናቱ የተጠቆመው፡፡
አጠቃላይ የባቡር ቁጥሩን ወደ 61 ማሳደግና የባቡር ሃዲዱን የሚያቋርጡ የእግረኛና የተሽከርካሪ ማቋረጫዎችን  በሌላ አማራጭ መተካት፤ የባቡሩ አገልግሎቱን በእጅጉ ለማቀላጠፍ ያስችላል የሚል ሃሳብም በጥናቱ ውስጥ መቅረቡንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በባቡር መስመሩ ላይ የመሰረተ ልማት ለውጥ ለማድረግና አጠቃላይ አቅሙን ለማሳደግ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስፈልግ የገለፁት ስራ አስኪያጁ፤ ሆኖም የባቡር ኮርፖሬሽኑ አሁን ካለበት እዳ አንፃር ይሄ በቀላሉ የሚሳካ አይደለም ይላሉ - የበፊቱም እዳ ተከፍሎ አለመጠናቀቁን በመጠቆም፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ለፕሮጀክቱ ድጋፍ እንዲያደርግ ወይም በራሱ እያስተዳደረ እንዲቀጥል የውሣኔ ሃሳብ የቀረበውም በዚህ መነሻ  ነው  ተብሏል፡፡ ሌሎች የባቡር ማስፋፊያ ፕሮጀክቶችም በከተማ አስተዳደሩ እንዲከናወኑ በውሣኔ ሃሳቡ መቅረቡም ታውቋል፡፡
ከአንድ አመት ተኩል በፊት በቻይናውያን የበላይነት ሲመራ የነበረውን አገልግሎት አሁን ሙሉ ለሙሉ ኢትዮጵያውያን መረከባቸውንና የእውቀት ሽግግሩ በተሳካ መልኩ መከናወኑን የተናገሩት አቶ ሙሉቀን፤ የባቡር ዘዋሪዎች፣ ቴክኒሻኖች፣ እንዲሁም የኩባንያው አስተዳደሮች በሙሉ ኢትዮጵያውያን ሆነዋል ብለዋል፡፡
የባቡር ፕሮጀክት እንዴት ይተዳደር፤ ማንስ ያስተዳድረው የሚለውን ጉዳይ ለመመለስ ያስችላል የተባለው መጠነ ሰፊ ጥናት ውሣኔ ካገኘ በኋላ፣ አገልግሎቱን ለማሳደግም  ሆነ ለማዘመን የሚቻልበት ዕድል ይፈጠራል ብለዋል - ሥራ አስኪያጁ።

Read 8950 times