Monday, 02 November 2020 00:00

የዘፈቀደ ስድብ ሳይሆን፣ ጠንካራ አቋምና ብልሃት ያዋጣል፡፡

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

 - ዶናልድ ትራምፕ በሰሞኑ ምርጫ ቢሸነፉ፣ ለኢትዮጵያ ጊዜያዊ ፋታ ይሆናል፡፡ ነገር ግን፣ ቢያሸንፉም፣ ጫናዎችን የሚያቃልሉ ዘዴዎች ላይ
     መትጋት ይቻላል፡፡
  - የአንድ የሁለት ሴናተሮችን ድጋፍ ማግኘት፣ ለውጥ ያመጣል፡፡ የአንዱን ሚኒስቴር ጫና ለማለዘብ፣ የሌላውን ሚኒስቴር ድጋፍ መጠቀምም ውጤት         አለው - የጆን ቦርተን መጽሐፍ ይህን ይመሰክራል፡፡
  - የግብጽን ዛቻ ለመግታትና ለመከላከልስ? ዲፕሎማሲና ድርድር ተገቢ ነው፡፡ አፀፋ የመመለስ ወታደራዊ አቅምን ማሳየትም የግድ ነው፡፡
           
           የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ንግግርን ማውገዝ፣ እርዳታ በከፊል ማገዳቸውንም መቃወም፣ የመጀመሪያው ተገቢ ተግባር ነው፡፡ ከአጽንኣት ጋር፣ በተገኘው አጋጣሚ፣  የኢትዮጵያን አቋም ደጋግሞ ማሳወቅ ያስፈልጋል፡፡ “ፎርማል” የዲፕሎማሲ ደብዳቤ አንድ ነገር ነው፡፡ በአጭር አረፍተ ነገር፣ አሳማኝ አቋም ማቅረብ ሌላው ቁምነገር እንደሆነ ግን፣ ገና ልብ አልተባለም። ልብ ብንል ይሻላል፡፡
ታዲያ፣ ስህተትን መቃወም፣ አቋምን ማሳወቅ ማለት፣ ስድብ ማለት አይደለም፡፡ አዳዲስ ቅራኔዎችን ወደሚፈለፍል፣ ሌሎች እርዳታዎችን ወደሚያሳጣ፣ ቀሽም የፀብ መንገድ እየተደናበርን መግባት የለብንም፡፡
በአሜሪካ የፓርቲዎችና የፖለቲከኞች ፉክክር ውስጥ፣ ዘው ብሎ በከንቱ መንቦራጨቅም፣ ጥቅም አልባ ከመሆን አልፎ፣ ጉዳት ያስከትላል፡፡
የኢትዮጵያ ወዳጅነት፣ ከዚህኛው ፓርቲ ወይም ከዚያ ፓርቲ ጋር ተቆራኝቶ፣  ከሌላኛው ፓርቲ ጥላቻን የሚያተርፍ መሆን የለበትም፡፡
ሞቅ ቀዝቀዝ፣ ጠበቅ ላላ ቢልም እንኳ፣ የትኛውም ፖለቲከኛና ፓርቲ ስልጣን ላይ ቢወጣ፣ የኢትዮጵያና የአሜሪካ ወዳጅነት፣ መቼም ሳይቋረጥ፣ ዘመንን የሚሻገር መሆን አለበት፡፡
አዎ፤ ኢትዮጵያን ሊጐዱ የሚችሉ የትራምፕ ንግግሮችና ውሳኔዎችን በአጽንኦት መቃወም ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር፣ በዘፈቀደ ማንቋሸሽ፣ መስደብና መወንጀል ግን፣  ኢትዮጵያን የሚወዱ በርካታ የአሜሪካ ፖለቲከኞች እንዲርቁን እንደመግፋት ይሆናል፡፡
ይልቅስ፣ ብዙ ድጋፍ ለማግኘት መጣር ነው - ብልህነት፡፡ ተቃራኒ አስተሳሰብ የያዙትን ለማለዘብ፣ የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆኑት ደግሞ፣ አቋማቸው ይበልጥ እንዲጠነክር መትጋት ነው - ቁምነገር፡፡ እንዴት?
የአገሪቱ ምክር ቤቶችን ተመልከቱ። የኮንግረስ በተለይም የሰኔት አባላት፣ በአሜሪካ መንግስት ውሳኔዎች ላይ፣ ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡
ለአንድ ለሁለት ሴናተሮች፣ የኢትዮጵያን አቋም ማስረዳት፣ እጅግ አስደናቂ ውጤት ሊኖረው ይችላል፡፡ ለምን? የአሜሪካ ፕሬዚዳንት፣ የአንድ የሁለት ሴናተሮችን ድጋፍ ማጣት አይፈልግም፡፡ የሴናተሮች ተሰሚነት ቀላል አይደለም፡፡ ከአሜሪካ ፖለቲካ ልዩ ባህሪያት መካከል አንዱ፣ ይሄ ነው፡፡ ይህንን በቅጡ ተገንዝበው፣ ለኢትዮጵያ ውጤታማ ጥረት ያደረጉልን ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ ጥሩ አርአያ ናቸው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡
የፕሬዚዳንት ትራምፕ አማካሪዎች እና ሚኒስትሮች ሁሉ፣ አንድ አይነት አቋም ይኖራቸዋል ማለትም አይደለም፡፡ የገንዘብ ሚኒስትር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የምክትሎች፣ የአማካሪዎች አስተሳሰብ፣ ምን ያህል ሊለያይ እንደሚችል፣ በዝርዝር ለማወቅ ከፈለጋችሁ፣ የጆን ቦልተንን መጽሐፍ አንብቡ፡፡ መጽሐፉ፣ እለት በእለት በሰፊው የተዘረዘረ አስገራሚ ትረካ ነው፡፡ ጆን ቦልተን፣ ብዙ ቢዘረዝሩ አይገርምም። የትራምፕ የፀጥታ ዋና አማካሪ የነበሩ ናቸውና፡፡
አንዱ ሚኒስትር ወይም አማካሪ፣ ኢትዮጵያን የሚጐዳ ሃሳብ ቢያመጣ፣ ምክትሉ ወይም ሌላ ሚኒስትር፣ ለኢትዮጵያ የሚበጅ አማራጭ ሃሳብ ማምጣቱ፣ የዘወትር አሰራር ነው፡፡ ኢትዮጵያን የሚጠቅሙ ትክክለኛ ሃሳቦች እንዲበረክቱ መጣር፣ ውጤታማ የመሆን እድል የሚያገኘውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡
ይሄ፣ ጥበብንና ትጋትን የሚጠይቅ እንጂ፣ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት፣ አንዳንዴ፣ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከኤምባሲ ጋር ይኮራረፋል፡፡ ያኔ ምን ያደርጋል? ከUSAID ጋር አዲስ ፍቅር ይጀምራል፡፡ ከዚህኛው ጋር ከተቀያየመ ደግሞ፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ሽርክ ይሆናል፡፡ ይሄ ብልሃት፣ ወደ ቀሽም ብልጣብልጥነት እስካልዘቀጠ ድረስ፣ ትክክለኛና ጠቃሚ ዘዴ ነው፡፡
እንዲያውም፣ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥም፣ ከአንድ ኃላፊ ጋር ተኳርፎ፣ ሌላውን ኃላፊ በፈገግታ ማስተናገድ፣ ውጤታማ የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡ እንደ ጉዳዮቹ ክብደትና ባሕርይ ነው፡፡
በአጠቃላይ፣ ከላይ የተጠቀሱት ቁምነገሮች፣ ኢትዮጵያን ዋና አቋም፣ የአሜሪካን የፖለቲካ ባሕርይ እና የዶናልድ ትራምፕን ልዩ አሰራር በማገናዘብ፣ በጥበብና በብልሃት መትጋት እንደሚቻል፣ እንደሚገባም ያረጋግጣሉ፡፡ ይሄ፣ ለዘለቄታውም ይሰራል፡፡ ለምን?
በዚህ ዙሪያ፣ ትራምፕ በሰሞኑ ምርጫ ቢሸነፉም ሆነ ቢያሸንፉ፣ ብዙም ለውጥ አይመጣም፡፡ የጊዜያዊ ፋታ ጉዳይ ነው። ከዚያ ውጭ፣ በኢትዮጵያ ዋና አቋም፣ በአሜሪካ የፖለቲካ ባሕርይ፣ እንዲሁም በግብጽ መንግስት ፍላጐት ላይ፣ ብዙም ለውጥ አይመጣም፡፡ እሺ፡፡ የአሜካን አየን። የግብፅስ?     
አዎ፣ የግብጽ መንግስት ዛቻዎችን ለመግታት፣ መደበኛውንና የተለመደውን የዲፕሎማሲ ወግና ስርዓትን ማሟላት ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት፣ በፍጥነት፣ እግር በእግር የተከታተለ፣ ተቃውሞውን መግለጽ፣ አቋሙን ማሳወቅ፣ …ለአህጉርና ለአለማቀፍ ተቋማት፣ ለሃያልና ለወዳጅ አገራት፣…”እዩልኝ”፣ “ስሙልኝ” ማለት አለበት፡፡ ደብዳቤዎችን በወጉ አሳምሮ ማዘጋጀትና መላክ፣ ለአፍታም መስተጓጐል የለበትም፡፡
ግን፤ የምር የውጭ ጥቃትን ለመግታት፣ ሁነኛው መተማመኛ የኢትዮጵያ ተጨባጭ አቅም ብቻ ነው፡፡
በአንድ በኩል፣ የአገርን የኢኮኖሚ ደረጃና የፖለቲካ ሰላም እያደላደሉ፣ በተቻለ መጠን ወታደራዊ አቅምን መገንባት ያስፈልጋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ለመከባበር በሚጠቅም መንገድ፣ ወታደራዊ አቅምን ማሳየት፣ ጥቃትን ከመነሻው ለማስቀረት ይረዳል፡፡ እዚህ ላይ፣ ለጦርነት ቅንጣት ሰበብ መስጠት የለብንም፡፡ ግን ደግሞ፣ የራስን ብቃት ማሳየት፣ የአፀፋ እርምጃ የመመለስ ጠንካራ አቋምን ከወዲሁ አሳውቆ ማስጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡
ከቀን ወደ ቀንም፣ ዘላቂ አቅም ለማሳደግ መጣር ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ፣ ወታደራዊ አቅምን ማደርጀት፣ ለድሃ አገር ቀላል አይደለም፡፡
ነገር ግን፣ ወጪን የሚቆጥቡ መንገዶችን ማፈላለግ፣ ዘዴዎችን መፍጠር፣ አይከብድም፡፡ ጥቃትን የሚገቱ ጥቂት ወታደራዊ የአፀፋ አቅሞችን መምረጥ ይቻላል፡፡ ጥቃትን ለማክሸፍ የሚያግዙ አቅሞችን እያማረጡ በፍጥነት የማጠናከር ጉዞም መቀጠል አለበት፡፡


Read 611 times