Saturday, 31 October 2020 11:02

አዲስ አበባን ከሞያሌ የሚያገናኘው ጥንታዊ መንገድ በመበላሸቱ ነዋሪዎች መቸገራቸውን ገለፁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

    “ቡና ለዓለም ገበያ ማቅረብ እየቻልን ለድህነት መጋለጥ የለብንም”

            በ1930ዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ ወደ ሞያሌ የተዘረጋው መንገድ በመበላሸቱ  የተፈሪ ኬላ፣ ዲላና አለታ ወንዶ  ነዋሪዎች መቸገራቸውን ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡
ከአለታ ወንዶ እስከ ዲላ የሚደርሰው 34 ኪሎ.ሜትር አስፓልት መንገድ ላለፉት 40 አመታት ገደማ በቂ ጥገና ያልተደረገለት መሆኑን ተከትሎ፣ ተቆፋፍሮ   ለተሽከርካሪዎች አገልግሎት መስጠት አለመቻሉን የሚናገሩት ነዋሪዎች፤ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ለመገበያየትና ጉዳይ ለመፈፀም መቸገራቸውንም ነው ለአዲስ አድማስ ያስረዱት፡፡
የአስፓልት መንገዱ ከጥቅም ውጪ ሆኖ ጉድጓዶች በመፈጠራቸው ሳቢያ አገር አቋራጭ አውቶብሶች ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት መስጠት ያቆሙ ሲሆን ህብረተሰቡም ከፍተኛ ወጪ እያወጣ ባለሁለት እግር ሞተር ሳይክሎችን ለመጠቀም መገደዱን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
መንገዱ እንዲጠገንላቸው የቀድሞ ጠ/ሚኒስቴር  ኃይለማርያም ደሳለኝ በስልጣን ላይ ከነበሩበት ጊዜ አንስቶ በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ በየጊዜው ዘንድሮ በጀት ተይዟል እየተባለ መንገዱ ሳይሰራ ዓመታት  ተቆጥረዋል  ብለዋል - ነዋሪዎቹ፡፡
በዚህም የአካባቢው ቡና አምራች ገበሬዎች ምርታቸውን ለገበያ የሚያቀርቡበት መንገድ በማጣት ምርት ለማቆም መገደዳቸውንና ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ችግር መጋለጣቸውንም  ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡  መንገዱን በባለቤትነት ለሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን  በተደጋጋሚ አቤቱታቸውን እንዳቀረቡ የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፤ እስካሁን ምላሽ የሚሰጣቸው እንዳላገኙ ይገልፃሉ፡፡
የአካባቢው ከተሞች ጥንታዊ መሆናቸውን፣ መንገዱም በ1909 የተቆረቆረችውን ተፈሪ ኬላን ጨምሮ፣ አለታ ወንዶ፣ ቀባይና የጌዲኦ ዞኗን ዲላ ከተማን የሚያገናኝ ወሳኝ መንገድ እንደነበረም ነው ነዋሪዎቹ ያስረዱት፡፡
“ቡና ለአለም ገበያ እያቀረብን ያለን ገበሬዎች፤ በመንገዱ መበላሸት የተነሳ ብቻ ለድህነት እንድንጋለጥ ሊፈረድብን አይገባም፤ መንግስት አፋጣኝ እልባት ይሰጠን” ብለዋል -ነዋሪዎቹ፡፡  

Read 3855 times