Sunday, 25 October 2020 18:46

"የትግራይ ክልል አስተዳደር ችግር ከእንግዲህ የሚፈታው በህግ ብቻ ይሆናል”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  "የትግራይ ክልል አስተዳደር ለድርድር ፍላጐት የለውም” – ክራይሲስ ግሩፕ

           የትግራይ ክልል መንግስት ከፌደራል መንግስት ጋር ያለውን የፖለቲካ ችግር በድርድር ለመፍታት ፍላጐት አለማሳየቱን የክራይሲስ ግሩፕ ከፍተኛ የጥናት ባለሙያ የገለፁ ሲሆን ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው፤ ከዚህ በኋላ የክልል አስተዳደሩ ችግር የሚፈታው በህግ ብቻ ይሆናል ብለዋል፡፡
የአለማቀፉ ክራይሲስ ግሩፕ ከፍተኛ የጥናት ኤክስፐርት ዊሊያም ዴቪሰን ከሰሞኑ ወደ ትግራይ አምርተው ከክልሉ የመንግስት ሹማምንትና ተቃዋሚዎች አመራር ጋር መወያየታቸውን ጠቁመው፤ በዚህ ወቅትም የክልሉ መንግስት ከፌደራሉ መንግስት ጋር የገባበትን ፍጥጫ በውይይትና ድርድር ለመፍታት እምብዛም ፍላጐት እንደሌለው መገንዘባቸውን ነው ያስታወቁት፡፡
ከፍተኛ የጥናት ኤክስፐርቱ ወደ ትግራይ ያቀኑት፣ከሁለት ወር በፊት የፌደራሉና የትግራይ ክልል ችግራቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ቡድኑ ያቀረበው ምክረ ሃሳብ አለመተግበሩን አስመልከቶ፤ ክፍተቱ ማን ጋ እንዳለ ለማጥራት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በነሌላ በኩል፤ በሣምንቱ መጀመሪያ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተገኝተው ለጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ ;ከትግራይ አስተዳደር ጋር ያለው ችግር ከእንግዲህ ወዲህ ህግና ሥርዓትን ብቻ መሠረት አድርጐ የሚፈታ ይሆናል; ብለዋል፡፡ በቀጣይም የህዝብ ተወካዮች ም/ቤትና ፌደሬሽን ም/ቤት በሚያስቀምጧቸው አቅጣጫዎች መሠረት፤ የሚወሰዱት ህጋዊ እርምጃዎች ይወሰናሉም ተብሏል፡፡
የፌደሬሽን ም/ቤት የመጨረሻው ውሣኔ በጀትን ማቋረጥ ሲሆን የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በበኩሉ፤ የም/ቤቱ የትግራይ ተወካዮች ከም/ቤቱ ስብሰባ በመቅረታቸው ህጋዋ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል። ክራይሲስ ግሩፕ በበኩሉ፤ የፌደራል መንግስቱ የወሰደው በጀትን የማቋረጥ እርምጃ፤ ችግሩን የበለጠ ከማወሳሰብ ባለፈ ሁነኛ መፍትሔ እንደማይመጣ ነው ያመለከተው፡፡
ውጥረቱን ሊያረግቡ የሚችሉ አማራጮች እንዲፈለጉም ተቋሙ መክሯል።

Read 6224 times