Print this page
Tuesday, 27 October 2020 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

                   ትላንት ታሪክ ነው፤ ነገ ደግሞ ሌላ ቀን ነው
                    
         ስካርለት የደማቅ ቀይ አበባ ቀለም ነው - ደስ የሚል!! ስካርለት ኦሃራም እንደዚያ ናት - ዓይን የምትስብ፣ ልብ የምትሰርቅ ውብ፡፡ ሶስት ባሎችን በየተራ አግብታለች። ወይም እንዲያገቧት አድርጋለች፡፡ ሶስቱንም አላፈቀረችም፡፡ ከሶስቱም ግን ወልዳለች። ስታገባቸው ልቧ አብሯት አልነበረም። የነበራት ሃሳብ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም… የመጀመሪያ ባሏ ቻርልስ ሐሚልተን መልከ ቀና፣ ሃብታምና የተማረ ወጣት ቢሆንም ለሷ “ከብት” ነበር። በቅናት ለወጠችው። ሁለተኛው ባሏ ፍራንክ ኬኔዲ፣ የእህቷ ፍቅረኛ ነው፡፡ አታለለችውና አገባት፡፡ ከሱ የምትፈልገው ሶስት መቶ ዶላር ብቻ ነበር፡፡ ሃሳቧን ሞላችበት፡፡ ሌላው ከብት!
ሶስተኛው ባሏ የዋዛ አይደለም፡፡ በልጅነቱ በመገፋቱ መከራን ተለማምዷል፡፡ በህገ ወጥ ንግድ በሰበሰበው ገንዘብ የሃብት እርከን ጫፍ ላይ የደረሰና የሰዎችን ባህሪ በቀላሉ ሊረዳ የሚችል ነበር፡፡ በአፉ ባይናገርም በስካርለት ኦሃራ መውደድ ተሰቃይቷል። ቀናተኛ እንደነበረም ትዳራቸው ያበቃ በመሰለበት ምዕራፍ ላይ ለመጀመሪያ ባሏ እህት ለሜላኒ አጫውቷታል፡፡
ጋብቻቸው ፍቅርን ሳይሆን ነፃነትን፣ እምነትን ሳይሆን አጋርነትን መሰረት ያደረገ፣ እነሱ እንደሚሉት “Fun” ነበር፡፡ የልጃቸው ቦኒ እና የሜላኒ በሞት የመለየት አጋጣሚ ግን የትዳራቸውን ደም ስር በጣጠሰው፡፡
“ብንለያይ ምን ይመስልሻል?” ሲል ጠየቃት… ሜሊ በሞተችበት ቀን፤ ተስፋ በቆረጠ ድምጽ፡፡
“ፍቺ?...ለምን?”
“ወደ ሩቅ አገር እሄዳለሁ”
“እኔ ፍቺ አልፈልግም፡፡ እንደምትወደኝ አውቄአለሁ፡፡” ሜሊ ነግራኛለች”
“እና?”
“እኔምኮ ወድሃለሁ” አለችው…እንደዘገየ ዜና ሁሉ ስሜት አልሰጠውም፡፡ እንዳልሰማ ሆኖ ሻንጣውን ማስተካከል ጀመረ፡፡ “ጋቢው ተፈትሎ ሲያልቅ፣ ሰውየው ብርዱን ለምዶታል።” እንደማለት ነው፡፡
*   *   *
ስካርለት ኦሃራና አሽሊ ዊክስ አብሮ አደግ ነገር ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜያቸውን አብረው ያሳልፋሉ፡፡ አንድ ቀን በትዳር እንደሚጣመሩ የአካባቢው ቤተሰቦች ግምት ነበር፡፡ ሳይረጋገጥ የቀረ ግምት፡፡
“ለማንበብ የተፈጠረ” የሚባለው አሽሊ ዊክስ፤ ከስጋ ጋብቻ ይልቅ የአእምሮ ጋብቻ በለጠበት፡፡ ለነገሩ የቤተዘመዱ እርስ በርስ የመጋባት ባህልም እንደ ምክንያት ይጠቀሳል። ከሁሉም በላይ ግን የሜሊ ባለመሆን ገነትን በቁም እንደ መውረስ ያህል ነው፡፡ ሜላኒ ሰው የማሳስታት፣ አሉባልታ የማይበግራት…፣ ቅን፣ ርህሩህና ደግ ልጅ ናት፡፡ ከመንገዷ የማትዛነፍ ደፋር!
አሽሊ እና ሜሊ በተጫጩበት ዕለት በቅናት የበገነችው ስካርለት፤ እዛው ግብዣ ላይ ቻርልስ ሃሚልተንን ጠብሳ ለጋብቻ እንዲጠይቃት አደረጋቸው፡፡
እሱም ወዲያውኑ አባቷን አስፈቅዶ በሁለኛው ሳምንት ተጋቡ፡፡
ስካርለት ኦሃራ እንደ ሜሊ የምትጠላው አልነበረም፡፡ ከእናቷ ሌላ ከልብ የወደደችውና ያከበረችው ሰው ቢኖር ደግሞ እሷው ናት - ሜላ ኒሃሚልተን።  ስካርለት የሜሊና የአሽሊ  ትዳር ፍፁም እንደነበር የገባት ከመሸ በኋላ ነው። ታላቁ ግብዣ በተደረገበት ዕለት፣ ስካርለት አሽሊን ለብቻው ስታገኘው “የሴትነት ክብሯን” ትታ፤
“እወድሃለሁ፤ እንዴት ሌላ ሰው ታገባለህ?” ብላው ነበር፡፡
“እኔና እሷ‘ኮ አንድ ነን” በማለት ሊያስረዳት ሞከረ፡፡  አልተዋጠላትም፡፡ በላይብረሪው አንደኛው ጥግ በነበረው ሶፋ ላይ ተጋድሞ፣ የሁለቱን ንግግር ሲያዳምጥ የነበረውን እንግዳ አላዩትም፡፡ ሰውየው ቀና ብሎ ስካርለትን ያናገራት አሽሊ ከወጣ በኋላ ነው፡፡
“ባለጌ ነህ!” አለችው በብሽቀት፡፡
“አንቺ ትብሽያለሽ” በማለት በሃፍረት አሸማቀቃት፡፡ ሶስተኛው ባሏ የሚሆነው እሱ ነው፡፡ ሬት በትለር!!
*   *   *
በግብዣው ሰሞን ዳር ዳር ሲል የነበረው የአሜሪካውያን የእርስበርስ ጦርነት እያየለ በመምጣቱ አሽሊዊክስና ቻርለስ ሃሚልተን እንደ ሌሎች ጓደኞቻቸው በወዶ ዘማችነት ተመዘገቡ። የደቡቡን ጦር ተቀላቅለው ዘመቱ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ቻርልስ ሃሚልተን በማሰልጠኛው ካምፕ ውስጥ እንዳለ በወባ በሽታ ሞተ፡፡ የመጀመሪያ ትዳሯ አበቃ፡፡
በጦርነቱ የአንድነት ሃይሎች አሸነፉ። የባርነት ስርዓት አከተመ፡፡ ግርግር ለሌባ ያመቻል እንደሚባለው፤ የአሸናፊው ፓርቲ ደጋፊ የሆኑ አንዳንድ ጋጠወጥ ወታደሮች ግን ባሪያ አሳዳሪ የነበሩትን የሃብታም ገበሬዎችን ንብረት እየተሹለከለኩ መዝረፍ ጀመሩ፡፡ የጥጥ እርሻዎቻቸውንና መኖሪያ ቤቶቻቸውን አቃጠሉ፡፡ በየአንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ ሞት፣ አካለ ጐዶሎነት፣ ችግርና መፈናቀል ተዳበለ፡፡ ስካርለት ኦሃራ ሁለተኛው ባሏን ያገባችው በዚህ ቀውጢ ጊዜ ነው፡፡
ፍራንክ ኬኔዲ ለኮንፌዴሬት ወታደሮች የሚላከውን ስንቅና ትጥቅ ከሚያደራጁ፤ ከሚያስተባብሩና ባዛር በማዘጋጀት ገንዘብ ከሚያሰባስቡ ኮሚቴዎች አንዱ ነበር። ጦርነቱ ሲያልቅ ባለቤት ያልነበረው የኮንፌዴሬት ሃይሎች ገንዘብ የራሱ ሆነ፡፡ ከስካርለት ጋር ሲገናኙ ዕድል እንደሳቀችለት አጫወታት፡፡ የዛን ቀን ስካርለት ወደ አትላንታ የመጣችው ከተለኮሰበት እሳት የተረፈው የቤተሰቦቿ ቤት፤ በሶስት መቶ ዶላር የግብር ዕዳ ሊወረስና ሊሸጥ በመሆኑ የጆሮ ጌጦቿን አስይዛ ከሬት በትለር ገንዘብ ለመበደር ነበር፡፡
አልተሳካላትም፡፡ ሬት በነፍስ ግድያ ተጠርጥሮ በመታሰሩ ገንዘብ በጁ አልነበረም፡፡
ፍራንክ ስካርለትን እንዳያት ሰረገላውን አቁሞ፡፡
“አንቺ መሆንሽን አላምንም” አላት፡፡
በርግጥም እሷ አይደለችም፡፡ የምትይዝ የምትጨብጠው የጠፋት፣ ተስፋ የቆረጠች ሌላ ሴት ነበረች፡፡ ከሰላምታ በኋላ እህቷ ሱለን ደብዳቤ መጻፍ እንደማይሆንላት እያወቀች፤
“ሱ ፃፈችልህ አይደል?” ስትል ጠየቀችው።
“ስለ ምኑ?”
“ከጥቂት ቀናት በኋላ እንደምታገባ”
“እ?” ፍራንክ ደነገጠ፡፡ ዋሸችውና እንዲያገባት አደረገች፡፡ ግብሩ ተከፈለ፡፡ ሁለተኛ ልጇን ወለደች፡፡
ፍራንክ የ “KKK” አባል ነበር፡፡ እንደነ አሽሊ ዊክስ አንድ ቀን ስካርለትን ሊዘርፉ የሞከሩትን ወሮበሎች ሲበቀሉ በተኩስ ልውውጥ ተገደለ። አሽሊ ቆስሎ ተረፈ፡፡ የስካርለት ሁለተኛ ትዳር ተደመደመ፡፡
ሬት በትለር “ሁለተኛ አላገባም” ስትል የነበረችው ስካርለትን በምኞት አስክሮ አገባት፡፡ ቦኒን ወለዱ፡፡ ቦኒ የአባቷ ጌጥ ሆነች፡፡ መሰናክል ስትዘል ከፈረሷ ወድቃ ተቀጨች፡፡ ትንሽ ሰንብቶ ደግሞ ወዳጁ ሜሊም በወሊድ ሰበብ ሞተች፡፡ ልቡ በሃዘን ተኮማተረ፡፡ ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ ተነሳ፡፡ እናም የፍቺ ጥያቄ አቀረበ፡፡
በዚህ ላይ ለአሽሊ ያላት ፍቅር ውስጥ ውስጡን ያስቀናዋል፡፡ ቅናትና ፍቅር አሸፈተው። ሜላኒ የሞተች ዕለት፡-
“የነገረችሽ ነገር የለም?” ብሎ ጠየቃት
“አሽሊን አደራ ብላኛለች” ትለዋለች፡፡
ሰውየው ስካርለት መለወጧን አላወቀም። አሽሊ ለስካርለት ወንድም እንጂ ሌላ መሆን እንደማይችል አልገባውም፡፡ ስካርለትም የገባት አሁን ነው፡፡
ለስካርለት ልከኛ ባል ሬት በትለር ነው። እነሱም እንደ ኦሽሊና ሜሊ ይመሳሰላሉ፡፡
“ካንተ መለየት አልፈልግም” ስትለው አላመናትም፡፡ እሷ ደግሞ መኖር ትፈልጋለች። ምክንያቱም ያለፈው አልፏል። ነገ ደግሞ ሌላ ቀን ነው!!
“”…Because the past is history and tomorrow is mistry; what we have at hand is this moment, this very now!” ይሉሃል ሊቃውንቱ! ትስማማለህ ወዳጄ?!
ሠላም!

Read 1226 times