ስኑፕ ላየን እምነቱን ወደ ራስተፈርያኒዝም በመቀየር ለቤተሰብ የሚሆኑ ሬጌ ሙዚቃዎችን በመጫወት መቀጠል እንደሚፈልግ ተነግሯል፡፡ የራስተፈርያኒዝም እምነቱን በጃማይካ ባደረገው ጉዞ የተቀበለው ስኑፕ፤ በዚሁ ለውጡ ዙርያ ልዩ ዶክመንታሪ ፊልም እንደሰራም ታውቋል፡፡ ስኑፕ ላየን ሰሞኑን ለኤምቲቪ በሰጠው አስተያየት፤ የቦብ ማርሌይ ሬጌ ሙዚቃዎችን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያደንቅ ገልፆ ፒተር ቶሽ፤ በኒ ዌለር፤ ግሪጎሪ አይዛክስ እና ጂሚ ክሊፍንም እንደሚወዳቸው ተናግሯል፡፡ካሊቭን ኮርዶዘር ኮሮዬስ በሚል የመዝገብ ስሙ የሚታወቅው ስኑፕ፤ በራፕርነት፣ በሙዚቃ ፕሮዲውሰርነትና በተዋናይነት ሲሰራ ከ20 መት በላይ ሆኖታል፡፡ አሁን 40ኛ ዓመቱን የያዘው ስኑፕ፤ ከአዲሱ የሬጌ አልበሙ በፊት በራፕ እና ሂፕ ሆፕ የሙዚቃ ስልቶች 11 አልበሞችን ሰርቶ በዓለም ዙርያ እስከ 10 ሚሊዮን ቅጂዎችን መሸጥ ችሏል፡፡