Tuesday, 27 October 2020 00:00

የብልጽግና ፓርቲ እንዴት እየሆነ ነው?

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(1 Vote)

 ኢሕአዴግ፤ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና  የኢትዮጵያ ሕዝብ ዲሞከራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዲን) ያቋቋሙት የጋራ ግንባር ነው። በኋላ የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዲድ) እና የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ መኮንኖች ንቅናቄ (ኢዲመን) እንደተቀላቀሉት ይነገራል፡፡ ደርግን አሸንፎ የመንግሥት ሥልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ኢዲመን እንዲፈርስ ተደርጎ፣በምትኩ  ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ግንበር፣ የግንባሩ (ደኢሕዴግ)  አባል እንዲሆን ተደረገ፡፡
የፖለቲካ ኃይሎች አንድ የጋራ ግንባር የሚመሠርቱት፣ ግንባሩም አስፈለጊ የሚሆነው አንድን የታ ወቀ ግብ ለመጨበጥ ነው፡፡ የግንባሩ የመጀመሪያ   አስፈለጊነት የደርግን መንግሥት ከሥልጣን ለማስወገድ ነው ብንል ሁለተኛው በጦር የተያዘውን የመንግሥት ሥልጣን ለማደላደል ነው በማለት  መገመት እንችላለን። ሁለቱም በመጀመሪያው አምስት  የኢሕዴግ የሥልጣን ዘመን ተጠናቀዋል ብዬ አምናለሁ፡፡
ነሐሴ 15 ቀን 1987 ዓ ም የጸደቀው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ሕገ መንግሥት በመግቢያው ላይ ‹‹በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዲሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ እድገታችን እንዲፋጠን፣ . . . በሕግ የበላይነት እና በራሳችን ፈቀድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ አስፈለጊነቱን በማመንና ቆርጠን በመነሳት›› በማለት ከሰፈረው ሃሳብ ጋር ሲታይ፣  የግንባሩን ቀጣይነት አላስፈለጊ ያደርገዋል። ለዚህ ጸሑፍ ስል በየቦታ የተቀመጡ ሕገ መንግሥቱ መግቢያው ላይ   የያዛቸውን ሃሳቦች ወደ አንድ መምጣቴ  እንዲታወቅልኝ አሳስባለሁ፡፡
ከላይ የጠቀስኳቸው የሕገ መንግሥቱ ሃሳቦች ወይም አለማዎች በግንባር በተሰባሰበ የፖለቲካ ድርጅት ተግበራዊ የሚሆኑና ከታሰበላቸው ግብም የሚደርሱ አይደሉም። አሕአዲግ ለአረቀቀውና ላጸደቀው ሕገ መንግሥት ተግባረዊነት ቅን ልቡና ካለው የፖለቲካ ድርጅቱን ከግንባር ወደ ውሕደት መውሰድ ነበረበት። የውሕደቱ ሃሰብ  በ1995 ዓ ም ላይ በኢሕዴግ ቤት እየተብላላ እንደነበር በእርግጠኝነተ ቢታወቀም አልተገፋበትም። የግንባሩ አለመፍረስ ወይም ወደ ውሕደት አለመሄድ እየቆየ ብዙ ችግር አመጣ፡፡ ዋናው የአንድ ድርጅት የበላይነት ሲሆን ሌላው በአመራሩ መካከል ያለመተማመን መስፈንና ሁሉም በየአቅጣጫው እንደ ልመና በሬ  መሰሳብ መብዛቱ ነው፡፡ አሁን ላይ ስለ ሕዝቦች አንድነትና ቀጣይነት አልሠራንም ነበር እያሉ የሚነግሩን ሰዎቸ  ዘግይቶም ቢሆን የኢሕአዴግን ማለትም የግንበሩን ጎጂነት እያረጋገጡልን መሆኑን ልንገነዘብ  ይገባል፡፡
የኢሕአዴ ግን መፍረስ ከሚፈልጉ ሰዎች አንዱ እኔ ነኝ፡፡ ሕወሓት የትግራይ፣ ኦሕዴድ የኦሮሚያ ወዘተ ፓርቲ ሆነው እስከ መቼ ነው ኢትዮጵያ  የሚመሩት? የሚል ጥያቄ በአደባባይ የነሳሁበት ጊዜ እንደነበርም ሳላስታውስ አላልፍም፡፡
ብልጭ ድርግም የሚሉ ተቃወሞች በኢሕዴግ መንግሥት ላይ በተደጋጋሚ የታዩ ቢሆንም  በአዲሱ፣ የአዲሰ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን እንደተቀሰቀሰውና የአማራንና የደቡብ ክልልን እንዳዳረሰው ተቀውሞ ማዕበል አይሆንም፡፡ ወደ ሁለት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ የቆየው ይህ ተቃውሞ የኢሕአዴግን መንግሥት ለማንገዳገድ በቅቷል፡፡ ኢሕዴግ ገዥ ፓርቲነቱን እንደቀጠለ ሆኖ በፓርቲው የሊቀ መንበርነት ቦታ ለውጥ ተደረገ፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም ወርደው ዶር ዐብይ አሕመድ ተተኩ፡፡
ከጣት ጣት ይልቃል እንዲል ተረቱ ከሰውም ሰው ስለሚለይ፣ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ለያዙት የመንግሥት ሥልጣን የሚመቹ እርምጃዎችን በተከታታይ መውሰድ ጀመሩ። የፖለቲካ አስረኞችን እንደፈቱት ሁሉ የፖለቲካ ምሕዳሩንም አሰፉት፡፡ አሸባሪ ተብለው ለተፈረጁ የፖለቲካ ድርጅቶች ፍረጃው እንዲቀርላቸው ሲያደርጉ፣ አገር ቤት ገብተው እንዳይንቀሳቀሱ የተከለከሉትን  ድረጅቶችም መግባት ፈቀዱላቸው፡፡
አቶ መለስ፤ አብዮታዊ ዲሞክራሲን ለመተግበር ከሚያበቃ ኢኮኖሚያዊና ማኅበረዊ መሠረት አልደረሱም በማለት በአጋርነት እንዲቆዩ ያደረጓቸውን የአምስቱ ክልል ገዥ ፓርቲዎችን፣ በኢሕዴግ ጠቅላላ ጉባኤ በመገኘት፣ ከመልካም ምኞት መግለጫ አንባቢነት አውጥተው  በኢሕአዴግ የሥራ አሰፈጸሚው ስብሰባ እንዲሳተፉ  አደረጉ፤ ድምጻቸውም የሚሰማ ሆነ፡፡
የመጋቢት 2010 ዓ.ም ለውጥ ካሰገኛቸው በጎ ነገሮች አንዱ፤ የኢሕአዴግ ፣ የብልጽግና ፓርቲ መመሥረት ነው፡፡ለእኔና እኔን ለመሰሉ ሰዎች እርምጃው የሚወደስ ነው። በውዳሴያችን  ለመቀጠል ግን ‹‹እሳት ካየው ምን ለየው›› የሚያሰኙ ሁኔታዎች እየተስተዋሉ ናቸው፡፡
ሊሆን ሰለማይችል  ብልጽግናን "ከዘር የነጻ ሰው" ካላመጣህና አባል ካላደረግህ  ልንል አንችልም፡፡ ጅማ፣ ነቀምት፣ ሮቤ ወዘተ ላይ የሚገኙ የብልጽግና ፓርቲ መሠረታዊ ድርጅቶች፤ በዘር ኦሮሞ የሆኑ ሰዎችን፡ የእንጅባራና የሆሣህና መሠረታዊ ድርጅቶች አገዎችንና ሐድያዎችን በብዛት  በፓርቲ አባልነት ቢመለምሉ ኃጢያት ሊሆን አይችልም። ኃጢያት የሚሆነውና የብልጽግና ፓርቲን ኅብረ በሔራዊነት የሚያጠፋው ጅማ፣ ነቀምት፤ ሮቤ፣ እንጂባራና ሆሣህና የሚኖሩ ጉራጌዎች፣ ትግሬዎች፣ አማራዎች፣ ወላይታዎች ወዘተ የመደራጀት መብታቸውን  ተነፍገው አባል እንዳይሆኑ፣ በየምክንያቱ ሲገፉ፣ በአካባቢው እንደሚገኝ የፓርቲው አባል በሁሉም ጉዳይ እኩል  እንዳይሳተፉ ሲከለከሉ ነው፡፡ የፓርቲው አባል መሆን የሚፈልጉ ሰዎች የሚሞሉት ቅጽ፤ ከመረጃ ክፍሉ አንዱ አድርጎ የያዘው የብሔር ማንነት ጥያቄ መሆኑ ደግሞ #ብልጽግና በስም ነው፤በግብር ከኢሕአዴግ አይለይም#  ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል፡፡
‹‹ወደ ባሕር ዳር ተጉዘን ምን ሠርተን እንደመጣን አታውቁም፡፡ የቻልነውን አሳምነን፤ ያልቻልነውን አደናግረን ተመልሰናል፡፡ ብልጽግናን የመሠረትነው እኛ ለእኛ ነው›› የሚለው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዜዳንት የአቶ ሽመልስ አብዲሳ ንግግር (ቃል በቃል አልተጠቀሰም) ፤ፓርቲውን በጥርጣሬ ዓይን እንዲታይ እንዳደረጉው አምናለሁ፡፡ እባብ ያየ በልጥ ይበረግጋል  ሊባል አይገባም፡፡ አእምሮ ያላሰበው በአንደበት አይገለጥም፡፡በመሆኑም አፍ ተልብ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ የንግግሩን አላማ ዘርዝሮ የሚያስረዳ ወይም በአደባባይ ወጥቶ ‹‹አፍ ወለምታ ነው›› የሚል (ሆኖ ከተገኘ) አንድ ሰው እንኳ መጥፋቱ ፣የብልጽግና ፓርቲ እንዴት እየሆነ ነው? የሚል ጥያቄ እንድናንሰላስል ግድ አድጎናል።
ብልጽግና፤ ‹‹ከዝንብ ማር አትጠበቁ›› የሚሉንን  ሰዎች፤ ;ልክ ናችሁ እንዳንል;  ያስብበት!!!


Read 7491 times