Sunday, 25 October 2020 15:34

“ምርጫ ሕይወቴ፣ ዲሞክራሲ ነፍሴ” …የፖለቲካ በሽታ ምልክቶች!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

       - መጪው ምርጫ፣ የሚያጓጓ ወይስ የሚያሰጋ? ተስፋ ወይስ አደጋ?
         - ዲሞክራሲ በሌጣው፣ “ምርጫ” ለብቻው፣ ወደ ቀውስ ይቸኩላል፡፡
              
       ምርጫው፣ “ከሁለት ጥሩ ፖሊሶች መካከል አንዱን” የመምረጥ ጉዳይ መሆን ነበረበት። የጥበቃ ሰራተኛ እንደመቅጠር ማለት ነው፡፡ ምርጫው፤ ከቀይ ወጥ እና ከአልጫ፣ ከፔፕሲና ከኮካ፣ አንዱን የመምረጥ ጉዳይ ሲሆን ነው፣ ችግር የማይፈጠረው፡፡ አለበለዚያ፣ ምርጫው ሰላማዊ ሊሆን አይችልም፡፡
ምርጫው፣ “በፖሊስ እና በሌባ” መካከል የሚደረግ ፉክክር ነው ብለን የምናስብ ከሆነ፣ እንዴት ሰላማዊ ይሆናል? “የኛ ሌባ እና የነሱ ሌባ”፣ ወይም “ነባር አምባገነን እና አዲስ አምባገን” የሚፎካከሩበት ነው ብለን የምናምን ከሆነስ? ምርጫው፣ የሞት ሽረት ትንቅንቅ መስሎ አይታየንም? ከጦርነትስ በምን ይለያል?
“ምርጫ” በሚል አዲስ ስም የሚመጣ፣ በአዲስ መልክ የሚጀመር ጦርነት ነው -የኋላቀር ፖለቲካ ምርጫ፤ ማለትም የኢትዮጵያ ምርጫ፡፡  
የፖለቲካ ብልሽትና  የአደገኛ ምርጫ፣ ቁጥር 1 ምልክት - “የማር የእሬት ምርጫ”።
“አንተ ነህ ሰይጣን!... አንተ ነህ ዲያብሎስ” እየተባባሉ የሚወጋገዙ ፓርቲዎች፣ የሚወነጃጀሉ ፖለቲከኞች ከበዙ፣ የአገሪቱ መከራ ይበረታል። የአገሪቱ ፖለቲካ ጤናማ እንዳልሆነ፣ በሽታ እንደፀናበት ከሚያረጋግጡ ምልክቶች መካከል አንዱ፣ ይሄ ነው፡፡
ራሳችሁን ጠይቁ፡፡ የአገሪቱ ምርጫ፣ “አገር ገንቢ እና አገር አፍራሽ” የሚፎካከሩበት፣ “ቅኝ ገዢ እና ነፃ አውጪ” የሚቀናቀኑበት ነው? እንደዚህ ከሆነ፣ ወይም ከመሰለን፣ ወይም ካስመሰልን፣ ነገርዬው ሰላማዊ ምርጫ ሳይሆን፣ የቀውስ ምድጃ፣ የጦርነት አውድማ እንደሚሆን አትጠራጠሩ፡፡
አልያም፣ ምርጫው፣ አንድ “አውራ ፓርቲ” የገነነበት ድራማ ይሆናል፡፡ ፉክክር የሌለው ሰላማዊ ምርጫ ደግሞ፣ የይስሙላ ምርጫ ማለት ነው፡፡ ችግሩ ግን፣ የይስሙላ ምርጫ፣ ለጊዜው እንጂ ሰላማዊ ሆኖ አይዘልቅም፡፡ ውሎ አድሮ፣ ወደ አጥፊ አመጽና ወደቀውስ አዘቅት እንደሚያስገባ፣ በተግባር አይተነዋል፡፡ ፉክክር አልባ፣ የገናና ፓርቲ ድራማ፣ ወይም የይስሙላ ምርጫ፣ እንደመሸጋገሪያ ቢጠቅም እንኳ፣ አያዛልቅም። እና ምን ተሻለ?
ጤናማ ያልሆነ የፉክክር ፖለቲካና ምርጫም፣ ለአገራችን እንዳልበጀ በተግባር አይተነዋል፡፡ የሞት ሽረት ትንቅንቅ የበዛበት፣ እየተሰዳደቡ የመወንጀል እሽቅድምድም የተካረረበት፣ የጥላቻ ስሜት የጦዘበት ምርጫ፣ አያዋጣም፡፡ ደርሶብን አይተነዋል፡፡ ሞክረነው መከራ አብልቶናል፡፡ ከማጥ ወደለየለት ረመጥ ሆኖብናል፡፡
የአደገኛ ምርጫ፣ ቁጥር 2 ምልክት፡፡ “ያልፍልናል? ያልቅልናል?”፡፡
ይሄኛው ፓርቲ ካሸነፈ፣ “እኛ ያልፍልናል፣ እነሱ ያልቅላቸዋል” የሚያስብል ከሆነ ወይም እንዲህ አይነት ስሜት ካሳደረብን፣ ምርጫው፣ ለጤና አይደለም፡፡
ያኛው ተቀናቃኝ ፓርቲ ካሸነፈ፣ “እነሱ ያልፍላቸዋል፤ ለኛ ግን ሞት ይሻላል” እንደማለት ነው - የሞት ሽረት ምርጫ፡፡ ፉክክሩ “የሞት ሽረት” መስሎ የሚታየን ከሆነ፣ከመሰለን፣ ወይም ካስመሰልን፣ የጦርነት ግጥሚያ እንጂ ሰላማዊ ምርጫ አይሆንም፡፡
የአደገኛ ምርጫ፣ ቁጥር 3 ምልክት - “ለምሳ ያሰቡንን ለቁርስ”፡፡
እንዲጠፋ የምትፈልጉት ፓርቲ አለ? አንዱ ፓርቲ በተንኮልም ሆነ በጉልበት፣ በአመጽም ይሁን በምርጫ፣ ሌላኛውን ፓርቲ እንዲያስወግድና እንዲያጠፋላችሁ ትመኛላችሁ? ይሄ፣ የአገራችን ፖለቲካ ባህርይ ነው - የአደገኛ ምርጫ ምልክትም ነው፡፡
አሳዛኙ ነገር፣ የአገራችን ፖለቲካ፣ በጠላትነት ስሜት የጦዘ፣ በመጠፋፋት ምኞት የሰከረ ፖለቲካ ነው፡፡ ነባሩ ፖለቲካችን፣ ክፉ የኋላቀርነት ፖለቲካ ነው፡፡ “ወይ ትጠፋለህ፤ ወይ ታጠፋለህ” ነው - ኋላቀር የመጠፋፋት ፖለቲካ፡፡
“ማን አሸንፎ ማንን ይረግጣል? ማን ቀድሞ ማንን ይበላል?” የሚል ነው - የመበላላት ፖለቲካ፡፡ “ለምሳ ያሰቡንን ለቁርስ አደረግናቸው” ተብሎ የተፎከረው ለምን ሆነና!! የምርጫ ፉክክሩ፣ አደገኛ የሞት ሽረት ትግል ነው - በአገራችን ኋላቀር ፖለቲካ፡፡
እንዲያም ሆኖ፣ የፖለቲካ በሽታ ወይም አደገኛ ምርጫ፣ ልክፍት አይደለም፡፡ ማርከሻ የሌለው፣ መንስኤው የማይታወቅ ዱብዳ እርግማን አይደለም፡፡ መንስኤዎች አሉት፤ መፍትሔዎችም አሉት፡፡
የአደገኛ ምርጫ፣ ቁጥር 4 ምልክት - ምርጫ እንደ ቁማር ጨዋታ፡፡
ወደ መፍትሔ ለመራመድ ከፈለግን፣ ከሁሉም በፊት፣ ሁለት ቁምነገሮችን መገንዘብ አለብን፡፡
“ዲሞክራሲ” እና “ምርጫ” እያልን የምንደጋግማቸው ቃላት፣ ተዓምረኛ የምትሃት ወይም የአስማት ሃይል የላቸውም፡፡ “በአንዳች ተዓምር፣ በራሳቸው ጊዜ፣ ሰላማዊና ስኬታማ ይሆናሉ” ብለን ራሳችን ከማሞኘትመላቀቅና ከቅዠት መባነን፣ ወይም ሌሎችን ከማሞኘት አባዜ መላቀቅና መንፃት አለብን፡፡
የኛ አገር ምርጫ፣ በጣም አደገኛ እንደሆነ፣ በቅጡ ለመገንዘብና አይናችን ከፍተን ለማየት መድፈር አለብን፡፡ ይሄ አንድ ቁምነገር ነው፡፡ ከጭፍንነት ጋር ተጣብቀን ለመኖር ከመረጥን ግን፤ የምርጫ አደጋዎችን ማባባስ እንጂ ማቃለል አንችልም፡፡
ሁለተኛው ቁምነገር፤ ……. “የመበላላት ፖለቲካን በመከባበር ፖለቲካ” ለመተካት መትጋት እንጂ፣ ሌላ አቋራጭ መፍትሔ የለም። እዚያው የመበላላት ፖለቲካ ውስጥ ተዘፍቀን፣ ከሌሎች ለመብለጥና ለመብላት መመኘትስ? እንዲህ ዓይነት ምኞት የቁማርተኛ ምኞት ነው፤ የቁማር ብልጫም ቀሽም ብልጠት ነው፡፡ ቀሽም ብልጣብልጥነትም፣ ከሞኝነት አይለይም፡፡
የፖለቲካ ምርጫዎች፣ አደገኛ ጨዋታዎች እንዳይሆኑ መፍትሔ ከማበጀት ይልቅ፤ በብልጠትም ሆነ በጉልበት ለማሸነፍና ለመብላት መራኮት፣ ሌላ ትርጉም የለውም። ትርጉሙ፣ የቁማርና የመበላላት ሱስ ውስጥ ተዘፍቆ መቅረት ነው፡፡
የፖለቲካ ምርጫዎች፣ “በብልጣብልጥነት የመተላለቅ የቁማር ውድድር” መሆን አልነበረባቸውም፡፡ አመጽ ለመቀስቀስ ወይም ተቀናቃኝን ለመደምሰስ የሚያገለግሉ፣ የቁማር ጨዋታዎች መሆንም የለባቸውም፡፡ ምርጫዎች፣ የቁማር ጨዋታዎች ከሆኑ፣ ከመሰሉን፣ ወይም ካስመሰልን ግን፣ የበሽታ ምልክት አየን ማለት ነው፡፡
በዚህም ተባለ በዚያ፣ መንግስት ለመገልበጥም ሆነ፣ ተቃዋሚን ለመርገጥ፣ የቁማር ጨዋታ፣ ልዩነት የለውም፡፡ የቁማር ብልጣብልጥነት፣ አገርን የሚያሳጣ ቂላቂልነት እንደሆነ መገንዘብ አለብን፡፡
አለበለዚያ፣ እዚያው ነባር ኋላቀር ፖለቲካ ውስጥ፣ “በላሁ፣ ተበላሁ” እያልን፣ በአደገኛ የምርጫ ቁማር ተጠምደን፣ የመጠፋፋት ረመጥ ውስጥ ሰምጠን ለመቅረት ፈልገናል ማለት ነው፡፡
በአጭሩ፣ የአገራችን “ዲሞክራሲ” እና “ምርጫ”፣ እጅግ አደገኛ የመበላላት ቁማር ነው።
“ከመበላት አመልጣለሁ፤ ሁሌም መብላት እችላለሁ” የሚል የቁማርተኛ ቀሽም ብልጣብልጥነት ደግሞ፤ አያዋጣም፡፡ መፍትሔ ሳይሆን፤ የበሽታው ምልክት ነው፡፡
5ኛ የበሽታ ምልክት  - “ምርጫ ሕይወቴ፣ ዲሞክራሲ ነፍሴ”
 “ዲሞክራሲ” እና “ምርጫ“ በሚሉ ቃላት ያልተጥለቀለቀ የፓርቲ መግለጫ ወይም የፖለቲከኛ ዲስኩር የለም ማለት ይቻላል፡፡
ከዲሞክራሲ በስተቀር ሌላ፣የሕይወት ቁምነገር የሌለ ይመስላቸዋል ወይም ያስመስላሉ - ብዙ ፖለቲከኞች፡፡  
ከፖለቲካ ምርጫ በስተቀር፣ ሌላ የኑሮ ጉዳይ በሙሉ፣ እንደ ትርፍ ጉዳይ ይቆጥሩታል፡፡
ይሄ፣ ትልቅ የፖለቲካ ብልሽት ነው - ዋና የበሽታ ምልክት፡፡ ከሕይወትና ከኑሮ የሚልቅ ነገር እንደሌለ እንዴት ይሰወርባቸዋል? የሕይወትና የኑሮ ልዕልና፣ እለት በእለት ብቻ ሳይሆን፣ ደቂቃ በደቂቃ፣ ሁልጊዜና በሁሉም ቦታ በግላጭ የሚታይ ዘላለማዊ እውነት ነው። እንዲያውም፣ “ዲሞክራሲና ምርጫ”፣ ዋጋ የሚኖራቸው፣ ለሕይወትና ለኑሮ በሚኖራቸው ፋይዳ ልክ ብቻ ነው፡፡
ከዲሞክራሲና ከምርጫ በላይ እጅግ የላቁ፣ “በጣም ውድና ክቡር ጉዳዮች፤ ሞልተዋል። እውቀትና ሙያ፣ ማሰብና ማምረት፣ በራስ መተማመንና የሰዎችን ብቃት በፍቅር ማድነቅ፣ እነዚህን የመሳሰሉ ዋና ዋና ጉዳዮች፣ ውድና ድንቅ ነገሮች እንኳ፣
ከሕይወትና ከኑሮ በታች ናቸው። የውድነታቸውና የክብራቸው ትልቅነት፣ ለሕይወት በሚፈይዱት ልክ ነው፡፡
ዲሞክራሲና ምርጫ ግን፣ በሰዎች ሕይወትና ኑሮ ውስጥ ይቅርና፣ በፖለቲካ ጉዳይ ውስጥ እንኳ፤ ዋና ቀዳሚ ነገሮች አይደሉም፡፡ በፖለቲካ ውስጥ፣ ከዲሞክራሲና ከምርጫ የላቁ መሰረታዊ ነገሮች አሉ፡፡
አገርና መንግስት፣ ሕግና ስርዓት የተሰኙ ነገሮች ከሌሉ፣ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም። እንዲያውም፣ በተወሰነ ደረጃ፣ የግለሰብ ነፃነት ካልተከበረና በትንሹም ቢሆን የሕግ የበላይነት ደልደል ካላለ፣ የፖለቲካ ምርጫ ትርጉም የለውም፡፡ ለልምምድ ይጠቅማል ሊባል ይችላል፡፡ ግን ግርግርን መቆስቆስ፣ ትርምስን መጋበዝ፣ ወይም መንግስትን ወደ ባሰ አምባገነንነት መገፋፋትም ሊሆን ይችላል፡፡
የሆነ ሆኖ፣ የአገርና የመንግስት፣ ማለትም የሰላምና የዳኝነት፣ ማለትም የሕግና የስርዓት መደላደል፣ ከዚያም ለግለሰብ ነፃነትና ለሕግ የበላይነት የተወሰነ ክብር መስጠት፣… እጅግ መሰረታዊ የፖለቲካ ፋይዳዎች ናቸው - ከዲሞክራሲና ከምርጫ የሚቀድሙ የሚልቁ፡፡  
ሕይወትና ኑሮ ደግሞ፣ ከፖለቲካ ፋይዳዎች በሙሉ ይልቃሉ፤ ይቀድማሉ፡፡ የብዙ ወላጆች የሌት ተቀን ሃሳብና ጥረትን ተመልከቱ። ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው እህል ውሃ ለማሟላት፣ የአቅማቸውም ያህል ሕይወትን ለማለምለም፣ ኑሮን ለማሻሻል አይደለም የሚጣጣሩት?
ልጆቻቸውን ለማስተማር፣ ለወደፊት ሕይወታቸው የሚበጅ እውቀትና ሙያ እንዲያገኙ አይደለም የወላጆች ጥረት?
የወላዶች ሃሳብና ጥረት ብቻ ሳይሆን፣ የብዙ ልጆች ዋና ምኞትንና ጉጉትንም ተመልከቱ፡፡ የስኬት ኑሮና የፍቅር ሕይወት አይደለም ወይ የልጆች ዋና ምኞት?
ወይስ፣ የእለት ተእለት ምኞታቸው፣ የዲሞክራሲ ተዋናይ ለመሆን ነው? 18 ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ በጉጉት የሚጠብቁት፣ በመራጭነት ለመሳተፍ ነው? እንደዚያ ከመሰለን ወይም ካስመሰልን፣ …ይሄ ትልቁ የበሽታ ምልክት ነው፡፡  


Read 2351 times