Friday, 23 October 2020 14:55

ማራኪ አንቀፅ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ያገሬ ሽታ
               (በልብወለድ ትረካ)


        --መንገደኞቹ፤ የአራት መቶ ኪሎ ሜትር ጉዟቸውን ተጉዘው፤ ወደተነሱበት የዋግሹሞች ሠፈር የማታ ማታቸውን ይደርሳሉ፡፡ ለእንግድነታቸው፤ የወሎ ምድር ያፈራቸው፣ በእህትማማቾቹ ባለሟል እጆች ተዘጋጅተው የተጫኑት ገፀ በረከቶች ከመኪናዋ ይወርዳሉ፡፡ ዘመድ ከዘመዱ ተገናኘ፡፡ ደስታ ናኘ፡፡ እንደ አገር ቤቱ ወግ በእንግዳ ክፍሉ እርጥብ ተጐዝጉዞ፣ ረከቦት ተዘርግቶ፣ ስኒዎች ተደርድረው፤ ከፊት ለፊትም ጀበና ተገትሮ እንግዶቹን ተቀበላቸው። ቆሌውም የደስታቸው ተካፋይ እንዲሆን ደስ ደስ የሚለውን፣ “ወሎ መጀን!...የሚያስብለውን እጣን በረንዳቸው ላይ አጫጫሱለት፡፡
በነገራችን ላይ ሥፍራው ይኸን ስሙን ያገኘው፤ ዋግሹም ከበደ አዲስ አበባ መጥተው፤ ከራርመውም ሲበቃቸው ዓፄ ሚኒልክን “…ጃንሆይ አገሬ ልግባ ፈቃድዎ ይሁን ያሰናብቱኝ…” ብለው እሺታቸውን ቢጠይቁ፤ ንጉሱም ዋግሹምን ይወዷቸው ያከብሯቸውም ስለነበር “ምነው ባትርቀኝ፣ አጠገቤ ብትሆንልኝ…እዚሁ ከኔው ዘንድ ሆነህ ብትረዳኝ” ይሏቸዋል። ዋግሹም ከበደም “…እኔ እዚህ ቤት ንብረት የለኝ…ዘመድ አዝማድ አላፈራሁ…አገሬ ብገባ ከሕዝቤም መሀል ብሆን ጃንሆይ በተሻለ መልክ ለማገልገል እታደል ነበር…” ብለው ይመልሱላቸዋል፡፡
በመልሳቸው ብዙም ያልተደሰቱት ንጉሥ፤ ዋግሹምን መያዣ ማስገደጃ እንዲሆንላቸው “…ቤት ንብረት ካልክማ መላ ቀጨኔን ሰጥቼሀለሁ” ይሏቸዋል፡፡ ዋግሹም ስጦታውን ተቀብለው እንደ ንጉሡ ፈቃድ ሆነውና ከራርመው ሲያበቁ ሁኔታዎችን አመቻችተው ወደሚወዱት ዋግ አገራቸው፣ ሰቆጣም ቤት ንብረታቸው ይመለሳሉ፡፡
ከዚያም የዋግሹም ዝርያዎች አቤቶ ኢያሱ ያስተከሉትን የቀጨኔ መድኃኒዓለም ታቦትን ተጠግተው፣ እድሜ ጠገብ ዛፎች አካባቢውን የላስታ ላሊበላ አውራጃ አድባራትን ያስመሰሉት ጉብታ ላይ የእነሱም አምቻ ጋብቾች፣ አብሮ አደጐች እና አበልጆች ቦታ ቦታ ይዘው፣ ቤት ሠርተው ሠፈሩን መኖሪያቸው አደረጉት። እነወይዘርን የመሳሰሉት ዘመድና አዝማዱ ወዳጁም ሳይቀር አዲስ አበባ በመጡ ቁጥር የሚስተናገዱበት “ስንመጣ መግቢያችን” የሚሉት አለኝታ ሆነላቸው፡፡
በመሆኑም፤ መቶ አለቃና ወ/ሮ አባይነሽ በታላቅ እህታቸው ወ/ሮ የውብዳር ይማም ቤት፣ ወ/ሮ ኩሪ መልኬና ከሥጋ ዝምድናቸው በተጨማሪ የጁ ሐርቡ ላይ በወግ ሲዳሩ፣ ዋናዋ ሚዜ ከነበሩት ወ/ሮ ዘውድነሽ አመዴ ቤት ጓዝ አወረዱ፡፡ ለእንግዶቹ መስተንግዶ በየቤቱ ድግስ ተደጋገሰ፡፡ ሁሉም ያገሩን ትኩስ ወግ ባገር ቤቱ ዜማ ቃና ሲወጋ እንደወረደ መስማቱ፤ አገሩ ገብቶ ካገሬው የተገናኘ መስሎ ስለሚታየው “ቀጥሎ ከኔ ቤት ነው” እየተባባለ የግብዣውን ጥሪ ሰንሰለት አራዘመው፡፡
በየግብዣውም ለወይዘር፤ ቢናገሩ የሚያስፈሩ፣ ቢወዱ የሚያስከብሩ፣ ቢጠሉ የሚያስነውሩ መስለው የሚታዩዋት እንግዶች ይታደሙበታል፡፡ ከሁሉም በላይ የወይዘርን ቀልብ የሳቡበት፤ መደባቸውን ለይቶ ማወቁ የተሳናት ሁኔታቸው አገራዊ ያልሆነባት እንግዶቹ ነበሩ፡፡
ከጠላት መልስ በነፃነት፤ ኢትዮጵያ በዕድሜ ልኳ ምንም እንዳልነበራት፤ ውርስና ቅርስም እንደሌላት ተደርጋ፣ ዘመናይ ተብየው ዜጋዋ አገሩን በአውሮፓ መነጽር በማየቱ ሥልጡን ያሰኘው ስለነበር፣ በሥልጣኔ ስም የአገሩ ባህላዊ ሕግና ሚዛናዊ አስተዳደር እየተሻሩና እየተሸረሸሩ በመሄዳቸው፣ አገሬው በአገሩ ባይተዋር መምሰሉን በመምረጡ “ፈረንጅ አገር በነበርኩ ጊዜ” እያለ ስለ ምዕራቡ ዓለም በሰፊው ማውራቱ በዕውቀቱም መኩራራቱ፤ በያጋጣሚውም የፈረንጁን ታሪክ በምሳሌ መተረኩ ከብቃት ተቆጥሮለት ማዕረግ ያሰጠው ስለነበር፣ ዓለሜ ዋሴ “እኔን አድነህ ጠላቶቼን አዋርደህ፣ ልዑልነትህን ግለጽ” እያሉ እግዜሩን የሚያስቸግሩ፤ ከሥረ - መሠረታቸው የተላቀቁ ራስ ወዳዶች ለአገር እንግዳ፣ ለዘር ባዳ የሆኑ ናቸው የሚላቸውን መስለው ይታይዋት ጀመር።
እየደመቀ የሚሄደው ጨዋታቸው ዞሮ ዞሮ አገር አዳርሶ ሲመለስ…ቢፌው ተነስቶ፣ ተበልቶ ተጠጥቶ፣ ማእድ ከፍ ብሎ፣ ብርጭቆ ተለውጦ በሌላም ተሞልቶ…እንግዳው ሞስቮልድ ሶፋ ወንበር ላይ ተዝናንቶ፣ የወቅቱን ሁኔታ አስሮ ሊፈታ፣ ለታሪክ ትረካው፣ ለፖለቲካ ዳኝነቱም ሁለንተናውን ያሾራል፡፡
ወይዘርም፤ በመዲናይቱ መኳንንትና ወይዛዝርት፣ በዘመናዮቹም መሀል ሆና በማታውቀው ዓለም ውስጥ ገብታ፣ ዓይኖቿን አውጥታ የሚታየውን እያየች ትታዘባለች፡፡ ጆሮዎቿን ቀስራም የሚባለውን ታዳምጣለች፡፡
እነ ወ/ሮ አባይነሽ ወይዘርን እቴጌ መነን ትምህርት ቤት ለማስገባት አዲስ አበባ በመምጣታቸው፤ የግርማዊት ስምና የትምህርት ቤታቸው ገድል የምሽቱ መነጋገሪያዎች ይሆናሉ። አብዛኞቹ የግብዣው ወይዛዝር፣ ደሴ ወ/ሮ ስሂን ትምህርት ጀምረው፤ ለከፍተኛ ትምህርት አዲስ አበባ መጥተው መነን ገብተው፣ ተመርቀው ሥራ ይዘው፤ ትዳርም መሥርተው ወልደው የከበዱ ናቸው፡፡
በመሆኑም በሰው ልጅ ሥጋ ባህርያት፣ ማለትም በውሀው (ጐልማሳው) እና በመሬቱ (አረጋዊው) እድሜ እርከን ላይ ሆነው የሚገኙቱ እንግዶች፤ ከተቀመጡበት ወንበር ላይ ተመቻችተው አቀማመጡንም አሳምረው ስለመነን ትምህርት ቤት በያጋጣሚው ማንሳቱና ማውሳቱ፤ ወደነበሩበት የነፋስ (ልጅነትና ቅብጥብጥነት) እና የእሳት (ያለመረጋጋት የችኩልነት) እድሜ ወስዶና አድርሶ ስለሚመልሳቸው፣ ሁኔታዎች ሲመቻቹ፣ ለሳቅ ጨዋታ ለትዝታ ትውስታም የሚደጋግሙት ልዩ ወጋቸው ነው፡፡
ወ/ሮ የውብዳር ለመስተንግዷቸው “መቼም” ብለው ወጋቸውን ጀመሩት፡- “መቼም ቢሆን ጃንሆይና እቴጌ አብረው ሆነው ነው የሚታዩት…ቤተክርስቲያን ቢሄዱ አብረው…በየማህበራዊው ሥፍራም ባንድ ላይ ሆነው በየዘመነኛውም እንዲሁ ተያይዘው ነው የሚታዩት…አንድ ጊዜ ነው ታዲያ! ቲያትር ቤት በክብር ተጋብዘው ሄዱና ትወናው ሴት ልጅ በሴትነቷ የሚደርስባትን ባህላዊ ጭቆና እያጐላ የሚያሳይ፣ የእሮሮና አቤቱታ ትርኢት ነበር፡፡ የሚያዩትም ሆነ የሚሰሙት ጌቶቹን አልጥም አልዋጥ ይልባቸዋል፡፡--
(ከጌታቸው ጳውሎስ ብርሃኔ "ያገሬ ሽታ፤ በልብወለድ ትረካ" አዲስ መጽሐፍ የተቀነጨበ)

Read 2662 times