Saturday, 04 August 2012 10:56

የነፍስ ቅኔ

Written by  ኪሩቤል ሳሙኤል
Rate this item
(1 Vote)

… የድንጋዮቹ አጥንት ባለበት ነው … የቅጠሎቹ ትካዜ የባህሩ ወለል ላይ አረምሟል… አሸዋዎቹ ቅብጠታቸውን ትተው አንጋጠው የጉሙን  ዜማ ያደምጣሉ (ካላደመጡም የውበትን ለዛ ከፅንፉ ይበረብራሉ) … ንፋሱ መጀመሪያ ሲፈጠር ከነበረው ማንነቱ ጋር ነው ያለው … ምድር ርዝማኔዋን

ረስታለች … ብዙህነቷን ጥሳለች … በመረሳት ጣጣ ውስጥ ናት … በመተፋት ቁጭት፡፡ ባህሩ ማንነቱን ለማስታወስ ከአሸዋው ደጃፍ ሲደርስ ይለመጣል … ተለምጦ መልሶ ይወራጭና በሰቲ እግር ላይ ይለጠፋል፡፡ … ቅዝቅዝ፡፡ ሁሉም የተፈጥሮ ስርዓት ራሱን ችሎ በፀጥታ “ቢፈጠሩ ኖሮ…” የሚላቸውን በማስታወስ ውስጥ ነው… ትውስታው መደምደሚያው አይታወቅም… ትውስታ፡፡ ሰቲ ግን በዝታለች፡፡ ከትውስታ ጥረት ውስጥ አይደለችም፤ የሀሳብ ወንጭፏ ወደፊት ተለቋል… አውቃ ነው የለቀቀችው… ሀሳብ ወደፊት ሲለቀቅ አካል መሄጃ አይኖረውም፣ ባለበት ይደርቃል… ልክ እንደሰቲ አይኖች፣ ብብቶች፣ የሌባ ጣቶች … ባሉበት ይደርቃሉ፡፡ ሰቲ ግን በዝታለች፡፡ እራሷን ደግማ እያወጋች ነው፣ ቀጥላ ልትመጣ ካሰበችው ሌላኛዋ ሰቲ ጋር … ዳግማዊ ሰቲ፡፡ የሰቲ አይኖች ፈጠው ግለት ይተፋሉ፡፡ ሁለተኛዋ ሰቲን አልወደደቻትም፡፡
ሙግቷ ከራስ ድንገቴ ማንነት ጋር አልጣጣምም ብሏታል፡፡ ምክንያቱም ሙግቱ ውስጥ ሽረት አለ… መነጣጠል… የሆድን ስሌት ብቻ የሚያሰላ … ለስጋ መድከምን ብቻ ያጠጠ… ነገ ላለመፍረሱ አስተማማኝነት የሌለው … የዝምታን ርቀት ለማድመጥ ብቃቱን ያጣ … የምክንያታዊነት ጠርዙ በብር ኖታ የጠለሸ፡፡ አሁን ከባህሩ ወለል ላይ ዳግማዊ ሰቲ ተቀምጣ በአይኗ ሰቲን እየሞገተቻት ነው፡፡ “ፍርሀት ድንገት የሚመጣ ስጦታ አይደለም፡፡ እመኚኝ ልታሸንፊ ስትይ ነው የምትፈሪው፣ ነፍስሽን ደግሞ ከወዴት አግድም ስር ሆና እንደምታሰላስል የምታውቂው ስትፈሪ ብቻ ነው፡፡ ይዤልሽ የመጣሁትን አዲስ ስጦታ በፍጥነት እንድትቀበይኝ አልመክርሽም … መጀመሪያ ፍሪ፣ ደንግጪ፣ ከራስሽ ጋር ባለመገናኘት ውስጥ ሆነሽ አዳዲስ መጥፋቶችን ጥፊ፡፡”በሰቲ አይኖች ውስጥ ያሉት ርቀቶች ከወዴትም የመራቅ ብልሀት ያጡና፤ እንደው ዝም ብለው ይሄዳሉ… ወደየትም፡፡ ህይወቷ በሙሉ በመከራ የጨቀየ ሆኖ የተተየበው፣ በየትኛው አካል እንደሆነ ብትጠይቅም መልስ እንደማታገኝ ገብቷታል፡፡ አንገቷ ከዚህ በላይ ባይጎነበስ መልካም እንደሆነ ታውቃለች፡፡ በጣም ማጎንበሷና ማዘኗ ውስጥ ግን ጣፋጭ በሽታ አግኝታበታለች፡፡ ይህን ጥፍጥና ማንም እንዳያውቀው አድርጋ፣ ለራሷም እንኳን እንዳይታይ ደብቃዋለች፡፡ ደግሞ ታስብ ታስብና መልሳ ቀና ብላ ዳግማዊቷን ሰቲን … ራሷን ያልሆነች ራሷን ታያለች፡፡ የዳግማዊቷ ሰቲ ቃላቶች በመሉ ህይወት ከሆኑ ነገሮች ውስጥ ተፈልቅቀው የወጡ ናቸው፡፡ ለነዛ ቃላቶች በመገዛት የሚወጣውም አቅም፣ ህይወትነቱ የአንድ ነፍስ  ብዙ ድምርማሪ ውጤት ነው፡፡ “ሴተኛ አዳሪ የሚለውን ቃል ሙሉ ለሙሉ ከህሊናሽ ሰርዢው፣ እቺን ስሜተ-ብዙ ቃል ተደበቂያት፡፡ የምታደርጊው ነገር ከጠራኋቸው ቃላቶች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለውም፡፡ ቃላቶችም በራሳቸው ሙሉ እንዳልሆኑ ተረጂ፡፡ ቋንቋም ቢሆን የምድር ድብቅ ስሌቶች ውስጥ የገባ አንድ የሆነ ህልውና ነው እንጂ የምድር ነፍስ የለውም፡፡ መመረጥሽና መምረጥሽ ያለው ካንቺ ጋር ብቻ ላይነቃነቅ የዘላለምን ጫፍ የሙጥኝ ብሎ የያዘው ነፍስሽ ጋ ብቻ ነው፡፡ የምልሽ በሙሉ ግልፅ ነው፡፡ የማትሸሺው አይነት እውነት ሲጠምድሽ የሚመጣብሽ ፍርሀት ካለ  እኔነቴ ሆይ! ሳትለቂው ጨምቀሽ ያዢው…ልክ በዛ ተራራ ላይ እንዳሉት ዛፎች አለመውረድን---- በፍርሀታቸው እውነት እንዳደረጉት፡፡” ይች ዳግማዊ ሰቲ የተባለች የምትለው ነገር በሙሉ እውነት ላለመሆኑ የሚረዱ ሌሎች እውነቶች ካሉ ብላ በሀይል አሰበች… ሰቲ፡፡ ይሄ ውዥንብር የሚመስል የሀሳብ ልቀት ውስጥ መግባቷ የገባት ዳግማዊ ሰቲ ፈገግ ስትል ሰቲ ታያታለች፣ ልትስማማት ልትወስን ፈለገች፡፡ በዚህ ሰዓት ማንም ሊያስተምራትና ሊመክራት የመጣ የለም፡፡ የምታዋራትም ሰቲ እሷነቷ ብቻ ሳይሆን የሚገዛው፣ ከራሷ የሚልቁ ቃላቶችን ወደ እውነትነት የመለወጥ አቅሟን የተሸከመው ጠሊቅ ስሜቷ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ይገባኛል ብላ ማሰብ ስትጀምር፣ ሰቲ ወደ መስማማት አለም ተቀላቀለች፡፡ ባህሩን በርቀት አተኩራ ስትመለከት ከቆየች በኋላ፣ ፊቷን አዙራ ህይወትን በጥቂቱ ልትቀምሳት ወደ ከተማው አመራች፡፡ ወቅቱ ክረምት ስለሆነ ይበርዳል፡፡ ገላዋን ወደ እንጀራ ለመለወጥ ለምትጥር ሴት፤ ንፋሱ መራራቱን አቁሟል፡፡ እሱም ራሱ የራሱ ተልዕኮ አለው፡፡ ሰቲ እየተንዘፈዘፈች ነው፡፡ አስፓልቱ ሙሉ ሙዚቃ ነው፡፡ ሙዚቃው ነው ንፋሱን መታገል የሚችለው፡፡ ሙዚቃው ከሌለ ይበርዳል፡፡ ስዕልም ቢሆን አይን ካላገኘ የለም፡፡ ሰቲም ከዚህ ቀደም በመኪና ከጀርባዋ እየተከተለ፣ በቃላትና በተዝረከረከ ወንድነት ሲነዘንዛት የነበረው ወንድ ከጠቆማት ትልቅ ሆቴል በር ላይ ቆማ አፍጥጣለች፡፡ ይህን ተመልክቶ ትዕግስቱ ያለቀው ቀጭን ዘበኛ፤ በሀይል ተጠግቷትና ረቂቅነቷን በጥቂቱ በአፍንጫው ምጐ ካበቃ በኋላ…“ምን ፈልገሽ ነው…?”“ዳንኤልን ማግኘት እችላለሁ…?”
“ለምን?”የምትመልሰው ቃል ቀፈፋት፡፡ ነገር ግን ዳግማዊት ሰቲ ከውስጧ ሆና ብርታቱን መስጠቷን አላቋረጠችም፡፡ የመጨረሻ ፍርሃቷ ላይ ዳግማዊቷ ሰቲ አለች…ከዛ ውጭ ያለውን ህይወት ራሷ ትጨርስላት…ለሰቲ፡፡ “ስራ እቀጥርሻለሁ ብሎኝ ነበር፡፡”ዘበኛው ቋምጦ አይቷት ካበቃ በኋላ…“እዚህ ጋር ጠብቂኝ…” ብሎ ጥሏት ወደ ውስጥ ገባ፡፡ ብዙ ቆይቶ ከዳንኤል ጋር ተመለሰ፡፡ ዳንኤል ሰቲን ሲመለከት የሆነ…ሚስጥራዊ የሆነ ማንነቱ ይሁን ስሜቱ --- ብቻ የሆነ ነገሩ ከመቅጽበት አደገበት፡፡ ተደሰተ፡፡ ሰቲን የዳንኤል ደስታ ለጥቂት ደቂቃዎች አስደሰታት፡፡ መደሰቷን ግን ቶሎ ብላ ጠላችው፡፡ ዳንኤል ከመቅጽበት ኮቱን አውልቆ ከላይዋ ላይ ደርቦ ወደውስጥ ለማስገባት ሙከራ አድርጐ ተሳካለት…ሰቲ ገባችለት፡፡ ስትገባ ቶሎ መሞቅ፡፡ ያ የሙቀት ስሜት አሁንም አለ፤ የት ይሄዳል፡፡ ወዲያው ሰቲን በስስትና ከሱ በተናጥል እንዳትሆን ከወደ ስሩ አስጠግቷት ወደ ፎቅ ወጥተው ካበቁ በኋላ ወደ ስምንት የሚጠጉ ትላልቅ የሆኑ፤ ውድ በሆነ ጨርቅ እርቃናቸውን የደበቁ፣ አስተያየታቸው የተሰላ የመሰለ፣ ጥንቁቅ ሀብታሞች ያሉበት ክፍል ውስጥ ይዟት ጠለቀ፡፡ ወዲያው የሰቲ መምጣት ለባለ ከበርቴዎቹ እንደመዓት ሆነባቸው…አንድ መልዓክ ንጣቱን መግለጡ ሀይሉን እንደሚያበዛለት ሁሉ ሰቲም በዛ ጠቆርቆር ባለ ንፁህ ክፍል ውስጥ የበለጠ ብርሃንና ንፁህ ሆና ተገኘች…በቃ ይሄን ሲያዩ ደነገጡዋ!...ሀብታሞቹ…ሲያይዋት…በመታየት ብቻ የማትታየዋን፣ አይንን የምትበልጥ ፍጥረት ስለመጣችባቸው እንዴት አይደነግጡም፡፡ ዳንኤል ሀይል ያለው የደላላ ፈገግታውን ለባለ ሀብታሞች እያመለከተ…“ይህች ማለት…ሰቲ…ሰቲ…”ስሟን እየጠራ ተመሰጠ፡፡ የደላላ ምሰጣ ደግሞ ያስታውቃል፡፡ በተለይ ሀብታሞች እያወቁት ይዝናኑበታል፡፡ ውሸት ቢሆንም ይሁን እያሉ ቶሎ ቶሎ የሚዘርፉት አይነት ምሰጣ ነው…የደላላ ምሰጣ፡፡ “ሰቲ የመጀመሪያ ጊዜዋ ነው በሆቴላችን ስራዋን ስትጀምር፡፡”ሀብታሞቹ ቋመጡ፡፡ እርስ በርስ ተነካክሰው ቢጨራረሱና አሸናፊው ቢወስዳት አይነት ምኞት በእኩል ደቂቃ በሁሉም ውስጥ ተጋባ፡፡
“ለማንኛውም… አብራችሁ ብትሆንና ብትጫወት አይከፋም ብዬ ነው ያመጣኋት፡፡” ያ ደላላ ለመጨረሻ ጊዜ የሰቲን ፍርሀት ማደሪያውን ያደረገ አይን አይቶ ቤቱን ለቆ ወጣ፡፡ ሰቲ በሁኔታው የባሰ ደነበረች፡፡ ሁሉም በክፍሉ ያሉት ትላልቅ ሰዎች በአትኩሮት ነው የሚያይዋት፡፡ ከመሀል ግን በጥ ያለው ከሌሎቹ ለአይን መጠነኛ ስሜት የሚሰጥ መልክ ያለው ሰውዬ ከጠረጴዛ ላይ ቀለሙን በውል መናገር የሚያቅት ጠርሙስ አንስቶ ብርጭቆ ውስጥ ከቀዳ በኋላ ቀና ብሎ ወደ ሰቲ በማየት ግብዣን አስቀደመ… “እባክሽ ሰቲ ተቀላቀይን… ይሄ ደግሞ ለብርዱ?” ብሎ ብርጭቆውን ከፍ አድርጎ አነሳላት፡፡ ጣቱን ተመለከተችው፤ የብር ቀለበት አለበት፡፡ ትልቅ የብር ቀለበት፡፡ ዳንኤል ቀድሞ ነግሯት ነበር - ባለ ቀለበቱ የሆቴሉ ባለቤት እንደሆነ፡፡ ሰቲ ከመቀፅበት ደመነፍስ ብቻ ሆነች፡፡ መጠጡን ሊቀበሉ የተራመዱት እግሮች የሷ አልነበሩም፡፡ ልክ የያኔ ቅፅበት ነበር ዳግማዊቷ ሰቲ መሰስ ብላ ሰቲን ከወዲያ አሽቀንጥራ ራሷን ማኖር የጀመረችው፡፡
የዛን ምሽት ሀያል የሆነ ሳቅና ደስታ አለፈ፡፡ ያን ቀን ሰቲ ትዝ የምትላት አንዲት የእንባ ዘለላ አምልጣታለች፤ አሁንም ቢሆን ከቦታዋ ሆናንደማትደርቅ ታውቀዋለች፡፡ ያቺ እንባ የዘላለም ነበረች፡፡ ከዛን እለት አንስቶ አልቅሳ አታውቅም ነበረ፤ ያኔ ነበር አልቅሳ የጨረሰችው፡፡
ያቺ ክብርት ነፍስያና ክቡር ስጋ በገንዘብ ቁጥር ውስጥ ሆነው የምድር ዘመን ውስጥ ገብተው አንቀላፉ፡፡ ያንቀላፉት ነፍሶች ሁሌ በህልማቸው ይገናኛሉ፡፡ እነሱነታቸውን የቀሟቸውን ብዙሀን ደመነፍሶች (ዛሮች) ሊበቀሉ ለሁልጊዜ ይነጋገራሉ፡፡ አቤት ግን የመራራቁ ርዝመት፡፡ ስጋን እያዩ
በነፍስ ማልቀስ … ዘመናት ድቅቅ ሲሉና ሲያጎነብሱ ደግሞ እየደጋገሙ ማዘን…
ሰቲ የዛን ቀን ሳቋ እስካሁን አለ፡፡ አሁን ግን ድምጿ በመጠጡ ቅዝቃዜ ቢዘጋም ከስሜቱ ተከፍቶ ከጉሮሮዋ እየተንሰረረሰረ በየሆቴሉ ባሉ ሙዚቃዎች ውስጥ ይሰማል፡፡ ሳቋ ግን ብቻውን ሆኖ የማያቃትን፣ ሰቲን አስተውሏት አያውቅም፣ የሷ እንደሆነ እያሰበ በመላ ሰውነቷ ውስጥ ይኖራል፡፡
የተራራቁ ነፍሶች ናቸው… ሳቋና እሷ፡፡ አሁንም ቢሆን ብዙ ዳግማዊ ሰቲዎች እራሳቸውን እያበዙ፣ እንደ ሰቲ ያሉ ንፁህ ነፍሶች ውስጥ
ያድራሉ፡፡ በነፍስ ሆነው የሚያለቅሱት ግን በአንደኛው ቀን ተነስተው ዳግማዊ ሰቲዎችን ማጥፋታቸው አይቀርም፡፡ ሰርክ ከነፍስ እያደሩ ማልቀስም አመፅ አለው ውስጡ … ያ አመፅ ደግሞ …
ያ አመፅ ደግሞ…

 

 

Read 2638 times Last modified on Saturday, 04 August 2012 11:17