Friday, 23 October 2020 14:47

ጠይም ካራማ

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(8 votes)

                                              የአጭር አጭር ልብወለድ
                                 

          አንጀት የራቃት ጠይም ጉብል ናት። ሥጋ ቅብ ተክለ አቋሟ ከአንጀቴ ገብታ ለመጎዝጎዝ፣ ከስሜቴ ወለል ላይ ለመነጠፍ ተራድቷታል፡፡ አንኳኩ ይከፈትላችኋል የሚለውን መለኮታዊ ትእዛዝ በአፊጢሙ ተክላ፣ ድንገት የልቤን እልፍኝ በርግዳ ዘው አለች፡፡ ከእንስቶች መንደር ፀጉረ ልውጥ ሆና፣ ዐይኔን አጥበረበረችኝ። ግብብነታችን የጀመረው እኔ ፈረንካ ቆጣሪ፣ እርሷ አስቆጣሪ ሆና በንዋየ-ግምጃ ቤት /ባንክ ቤት/ ነው፡፡ ሞኝ ካመረረ እንዲሉ፣ አለወትሮዬ ጨከን አልኩ፡፡ ከጠይሟ ጋር ልወዳጅ ዕለት በዕለት ግስጋሴን ተያያዝኩት፡፡
የአነጋገር ዘይቤዋን የገጠር አማርኛ ይጫነዋል፡፡ ለአለባበሷ ብዙም ግድ የላትም። በሻሽ ቢጤ ሸብ ያደረገችው የሀር ነዶዋ፤ ለአመል ነው ብቅ ብሎ የሚታየው። ሁሉ ነገሯን ለአውደ ርዕይ ማቅረብ አትወድም። ጠይምነቷ ግን ገፍቶ ወጥቶ አላፊ አግዳሚውን በአፍዝ አደንግዝ ያደነዝዛል። ከጠይም ጸዳሏ ጋር የተላተመ ኮበሌ፤ እንደ ምርኮኛ እጁን ወደ ላይ ቢያንጨፈረር አይፈረድበትም፡፡
ሠርክ ማልዳ በኩርቱ ፌስታል የተሸከመችውን ገንዘብ ከፊት ለፊት ትዘረግፍና አቆጣጠሬን ኦዲት ታደርጋለች። ዳጎስ ያለ ገንዘብ ይዞ መጥቶ ከፊት ለፊቴ እንደ ጅብራ የሚገተር ወፍራም ደንበኛ፤ “ዳይ… ዳይ ፍጠን እንጂ የምን መጎምዠት ነው፡፡ ከጓሮ ተሸምጦ የመጣ መሰለህ እንዴ?” ብሎ ቀጭን ትዕዛዝ የሚያስተላልፍብኝ ስለሚመስለኝ፣ ባለጠጋ ባየሁ ቁጥር አፍንጫዬን እነፋለሁ። የእኔና የጠይሟ ጉብል ግብብነት፣ ከዚህ ዓይነት የአለቃና ምንዝር ጨዋታ የራቀ ነው፡፡
የምትሠራበት ሆቴል "እንባ" ሳትሆን አትቀርም፡፡ ይህ ሁሉ አመኔታ አላንዳች የሥጋ ዝምድና የሚሞከር አይደለም። ድንገት አንድ ቀን በኩርቱ ፌስታል ይዛ የመጣችውን ገንዘብ ስታቀብለኝ፣ እጇን ለቀም አድርጌ ያዝኳት። እንደ ማፈር ብላ አንገቷን ሰበረች፡፡ የሴትነት ውበቷ ተጋነነብኝ፡፡ የምታፍር ሴት ካየሁ ስንት ዘመኔ! ለንዋይ የሚንቀዠቀዡት የከተማ እንስቶች ዐይና-አውጣነት ከአንገቴ ደርሷል። የከተማ ሴትን ዳግም ላልከጅል ለራሴ ቃል ከገባሁ ሰንብቻለሁ፡፡ የገጠሯ ጉብል ዳግም የፍቅር ጠኔ ለቀቀችብኝ፡፡ እናም ጠይም ዓሳ መሳይዋን ከልቤ ማጀት ላደላድል ወደ ፍቅር ጫካ ለአደን ወጣሁ።
ከአንድ ወር በኋላ
ደጋግሜ ስከጅላት፤ ብዙም ሳታንገራገር ቀረበችኝ፡፡ አክስቷ ፍቃድ የምትሰጣት የሆቴሉ ሥራ ጋብ በሚልበት በሰንበት ተሲያት ላይ ነው፡፡ ቀኗን እየተጠባበቅን የፍቅርን ሃድራ ማጫጫሳችንን ተያያዝነው፡፡ አንሶላ ለመጋፈፍ መጣደፍ አላስፈለገኝም፡፡ ይህ አመሌ ለእርሷም ሳይደንቃት አልቀረም።
በሰንበት የጠሃይ ማማ ላይ በተገናኘን ቁጥር ከንፈር ለከንፈር ከመደባበስ በቀር ስለ ግል ሕይወታችን አንስተን ተጫውተን አናውቅም፡፡ አንድ ቀን ግን ስለ እርሷ የኋላ ታሪክ ለማወቅ ተገፋፋሁና ጥያቄዬን አስወነጨፍኩ፡፡
“ውዴ፤ ከሀገርሽ ከወጣሽ ምን ያህል ጊዜ ሆነሽ?”
“ዓመት ከመንፈቅ ”
 “አወጣጥሽ በሰላም ነው?”
“አረ አወጣጤስ በጠብ ነው፡፡ ሀገሬ፣ አረግሚት ሚካኤል ነው፡፡ አንድ ፍሬ ጉብል ሆኜ ነበር ለወንድ የዳሩኝ፡፡”
“ታጭተሻል ማለት ነው?” አልኩኝ፤ ግራ በተጋባ ስሜት፡፡
“ሀረገኝ፣ ሙጫይቱ ምን ዶሎኝ ነው? አለአቻዬ የምንጠራራ? እርሱ ባለጠጋ። በይሂ ላይ ዕድሜያችንም ተነጣጣሪ አይደለም”
“እና ጥለሽው መጣሽ?"
“እምቢኝ ብዬ በጠፍ ጨረቃ በርሬ ከሀገሬ ወጣሁ፣ እርሱ የፈለገው ሕጌን ነበር። እኔ ልጅት ሴትነቴን ሳላስነካ  ነፍስያዬን በእጄ እንደያዝኩ፣ ተአዲስ አበባ ሀክስቴ ቤት ተሰበሰብኩ”
“አሀ ወንድ አታውቂም ማለት ነው!?” በውስጤ አጉተመተምኩ፡፡ ምራቄን ስውጥ የሰማች ስለመሰለኝ ደንገርገር አልኩ፡፡  
የቀን ጎዶሎ
ከውሃው እየወሳሰድን ለዐይን ያዝ አደረገ፡፡ ጠይሜን ዛሬ ከጉያዬ ወሽቄ ማደር አስፈልጎኛል። ደመነፍሳዊው ፍላጎቴ በውስጤ አለቀጥ ሲዘል ይሰማኛል። ልገስጠው ሞከርኩ፡፡ አልቻልኩም። በአክስቷ የተሰጣት የሰዐት እላፊ ገደብ እንዳለፈ ያወቅነው ከንፈር ለከንፈር ተጣብቀን፣ አቅላችንን በሳትንበት ቅጽበት አስተናጋጁ “ሒሳብ” በሚል ድምጽ ሲያስበረግገን ነበር፡፡ ውቧን የገጠር አማልክት፣ እኔ መደዴው ከተሜ፣ የስሜት ምህዋሯን እያሳትኳት እንደሆነ በገባኝ ቁጥር ራሴን እረግማለሁ፡፡ በአደባባይ መቃበጥ የእርሷ ወግም ልማድም አይደለም፡፡
ተያይዘን ወደ ቤርጎ አመራን፡፡ የቀማመሰችው መጠጥ አናቷ ላይ ወጥቶ ያስቀባጥራት ጀምሯል። ለመጀመሪያ ጊዜ እንደምትወደኝ ከአንደበቷ ደጋግሜ ሰማሁ፡፡ ቀዝቃዛዋን አልቤርጎ እንደ እቶን በሚንቀለቀለው አፍላ ስሜታችን ንዳድ አደረግናት፡፡ ጥምጥም አለችብኝ፡፡ የእኔም የአጸፋ ምላሽ የዋዛ አልነበረም፡፡ በፍቅር ደሴት ላይ መንሸራሸር ጀመርን፡፡ ጦረኛ ጡቷን ደጋግሜ ጨመኳቸው፡፡ በስሜት ተሰቅዛ አይኗ ተስለመለመ፡፡ ሴትነቷን ለመቃረም የስሜቴ ልጋግ እያደነቃቀፈኝ ነው። ድንገት የእጅ ሥልኳ ጠራ፡፡ ሁለታችንም በርግገን ተላቀቅን፡፡
“የታታዬ ስልክ ነው--” አለችና ፈጥና አነሳችው፡፡
ከወዲያኛው ጫፍ የሚሰማው ዜና ጥሩ አይደለም:: ከመቅጽበት ፊቷ ደረመን ለበሰ። መርዶ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የሰዎች ዋይታና ጩኸት ይሰማኛል፡፡ ትንሽ እንደ መነፋረቅ አለችና ዝልፍልፍ ብላ እጄ ላይ ውሃ ሆነች። እውነትም የቀን ጎዶሎ። በቅጽበት ውስጥ በጉራማይሌ ዓለም ከአጽናፍ አጽናፍ ተላጋሁ። ከአፍታ በፊት ከወጣሁበት የስሜት ራስ ዳሽን በግዴታ እንጦሮጦስ ወረድኩ፡፡
ከአንድ ዓመት በኋላ
ንጹህ ፍቅሯን ልታስረክበኝ ድንገት በሕይወቴ እንደ መስቀል ወፍ የተከሰተችው ጉብል አሁን የእኔ አይደለችም፡፡ እናቷን ለመቅበር ወደ ሀገሯ ባመራችበት ወቅት ባለጠጋው ቀራፎ በኃይል አስጠልፎ ከእልፍኙ እንዳኖራት ሰማሁ፡፡ መራራ እውነት። በጠራራ ጠሐይ ጠይሜን ተዘረፍኩ፡፡ ለእኔ ያቆየችውን ሕግ ጉልበተኛ በኃይል ገረሰሰው፡፡ ወትሮም የእኔ ምስ ከእርሷ ገላ ጋር አልነበረም፡፡ ጠይም ካራማዋ እላዬ ላይ አርፎ ቢያስቀባጥረኝ እንጂ። ካራማ አንዴ ነው የሚያርፈው፡፡ ብከጅልም አይዳላኝም፡፡ በአቋሜ እንደጠናሁ ይህቺን ባተሌ ዓለም ለመገርመም ወስኛለሁ፡፡ ምን ነበር ያለው ያ- አዝማሪ……
አረ ጠይም ጠይም ጠይም አትውደዱ፣
ጠይም ወድጄ ነው የጠፋኝ መንገዱ፣
ጠይም የወደደ ኮረኮንች ያረሰ፣
ዘላለም ይኖራል ደም እንዳላቀሰ፤

Read 2169 times