Saturday, 24 October 2020 00:00

በመላው ዓለም በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የአእምሮ ህመምተኞች በሰንሰለት ታስረው ይገኛሉ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

አለማቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ በአለም ዙሪያ በሚገኙ 60 አገራት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የአእምሮ ህመምተኞች ንጽህና በጎደላቸው ጠባብ ክፍሎች ውስጥ በሰንሰለት ታስረውና ታጉረው እንደሚገኙ አስታወቀ፡፡
ተቋሙ የአለም የአእምሮ ጤና ቀንን በማስመልከት በ110 የአለማችን አገራት የሰራውን ጥናት መሰረት አድርጎ ከሰሞኑ ይፋ ያደረገውን አለማቀፍ ሪፖርት ጠቅሶ አልጀዚራ እንደዘገበው፣ አንዳንድ የአእምሮ ህመምተኞች በእንስሳት በረቶችና ጋጣዎች ውስጥ ሳይቀር እዚያው እየበሉ እዚያው እንዲጸዳዱ እየተገደዱ አስከፊ ኑሮን እየገፉ ይገኛሉ፡፡
የአአምሮ ህመምተኞቹ በብረት ሰንሰለት እንዲሁም በገመድ ታስረው የሰቆቃ ኑሮን እየገፉ ይገኛሉ ያለው ሪፖርቱ፣ አብዛኞቹ ምንም አይነት የህክምና ወይም የዘመድ ወዳጅ ክትትል እንደማያገኙም አመልክቷል፡፡
በርካታ ቁጥር ያላቸው የአእምሮ ህመምተኞች በሰንሰለት ታስረው ህይወታቸውን ከሚገፉባቸው የአለማችን አካባቢዎች መካከል የአፍሪካና የእስያ አገራት ይገኙበታል ያለው ሪፖርቱ፣ በዋናነት የሚጠቀሱት አገራትም ላይቤሪያ፣ ሞዛምቢክ፣ ሴራ ሊዮንና የመን እንደሆኑ ገልጧል፡፡ በሰንሰለት ታስረው ከሚገኙት የአእምሮ ህመምተኞች መካከል ህጻናትም እንደሚገኙበት የጠቆመው የአልጀዚራ ዘገባ፣ የአለም የጤና ድርጅትም በቅርቡ ባወጣው መረጃ ከአለማችን ህጻናት መካከል 20 በመቶ ያህሉ የአእምሮ ህመም ተጠቂዎች መሆናቸውን መግለጹን አስታውሷል፡፡

Read 3683 times