Wednesday, 21 October 2020 06:23

COVID-19 አዲስ በተወለዱ እና ሌሎች ህጻናት……

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

 ገና የተወለዱ ህጻናት ወይንም በየትኛውም እድሜ ያሉ ህጻናት በኮሮና ቫይረስ ሊያዙ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን አብዛኞቹ በCOVID-19 የተያዙ ህጻናት በእድሜ ከፍ እንዳሉት ማለትም እንደታዳ ጊዎች ወይንም እንደወጣቶች ላይታመሙ ወይንም ምንም ምልክት ላያሳዩ ይችላሉ፡፡ ለመሆኑ ህጻናቱ በተለይ በኮሮና ቫይረስ እንዳይያዙ ለመከላከል ጥረት ማድረግ አስፈላጊ የሚሆንበት ምክንያት ምንድነው?
ህጻናት በኮሮና ቫይረስ ለመያዝ ቅርብ የመሆናቸውን ያህል ግን እንደወጣቶቹ ወይንም ትልልቅ ሰዎች በቀላል የማይታመሙ ሲሆን ምልክታቸውም ቀለል ብሎ የሚታይ ነው፡፡ በአሜሪካ የህጻ ናት ሆስፒታል እንደተገኘው መረጃ ከሆነ ከሚታከሙት ህጻናት 10 % የሚሆኑት ብቻ የኮሮና ቫይረስ እንደሚገኝባቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የተደረጉ ጥናታዊ ስራዎች እንደሚያመላክቱ ትም እድሜያቸው ከ20 አመት ጀምሮ ከፍ ከሚሉት ይልቅ ህጻናቱ በቫይረሱ እንደማይያዙ ብሎም እንደማይጎዱ ያመላክታል፡፡ በሆስፒታል አልጋ የሚይዙት ህጻናትም ቁጥር አነስተኛ መሆኑን አጥኚዎቹ ይናገራሉ፡፡ CDC እንደገለጸው ህጻናቱ በቫይረሱ ከተያዙ ሊረዱ የሚገባቸው በጽኑ ሕሙማን ክፍል መሆን አለበት፡፡  
ህጻናት ሲወለዱ የልብ ሕመም ያለባቸው ከሆኑ፤ሲወለዱ የተለያየ ተፈጥሮአዊ ችግር ያለባቸው ከሆኑ፤የነርቭ ስርአት ችግር ያለባቸው ከሆኑ በኮሮና ቫይረስ ለመያዝ እና ለመታመም ከፍተኛ ተጽእኖ የሚኖርባቸው ናቸው፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት አንዳድ ጊዜ ህጻናት ከኮሮና ቫይረስ ጋር ሊገናኝ የሚችል ከባድ የሆነ የሕመም ስሜት ሊታይባቸው ይችላል፡፡
ህጻናት ብዙም በCOVID-19 ላይጠቁ ይችላሉ ሲባል ምክንያቱን የሚገልጹ ተመራማሪዎች እንደሚሉት ህጻናት በሚኖሩበት ህብረተሰብ ውስጥ የተሰራጩ እና እንደጉንፋን ላለ ህመም የሚ ዳርጉ ሌሎች የኮሮና ቫይረሶች ባሉበት ስለሚኖሩ እና ሕመሙን በቀላሉ መለየት ስለማ ይቻል ነው ብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የህጻናቱ በሽታን የመቋቋም ኃይል አስቀድሞ በሽታን ለመከላከል ዝግጁ ስለሚሆን እና በቀላሉ እንዳይጎዱ ስለሚዳርጋቸው ነው፡፡
ከላይ የተገለጹት እንዳሉ ሆነው ነገር ግን አዲስ የተወለዱ ህጻናት በኮሮና ቫይረስ ሊያዙ እንደ ሚችሉ አስቀድሞ ማወቅም ተገቢ ነው ፡፡ እነዚህ ጨቅላዎች በቫይረሱ ሊየዙ የሚችሉባቸው የተ ለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ሲችሉ ከእነዚህም መካከል በሚወለዱበት ጊዜ ሊኖራቸው ከሚችል ተጋላጭነት ሲሆን ይህም ከእናቶቻቸው ወይንም ከተንከባካቢዎቻቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ልጆቹ ከተወለዱ በሁዋላም ቢሆን እናቶች የኮሮና ቫይረስ የያዛቸው ከሆኑ ወይም ደግሞ ይዞአቸው ወይንም አልያዛቸው እንደሆነ ለማወቅ ለምርመራ በመጠባበቅ ላይ ከሆኑ የመከላከያ ጭምብል (የአፍና የአፍንጫ) መሸፈኛ ሳያደርጉ ህጻኑን መንከባከብ እንደ ሌለባቸው ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ እናቶች ወይንም ተንከባካቢዎች ህጻኑን ከመንካታቸው በፊት እጃቸውን በሚገባ መታጠብ እንዳለባቸውም መዘንጋት የለባቸውም፡፡ አዲስ የተወለዱ ህጻናትን በሆስፒታል ውስጥ በራሳ ቸው አልጋ ላይ የሚተኙ ሲሆን ወደመኖሪያ ቤት ሲሄዱ ግን በተቻለ መጠን አቅም በፈቀደ እርቀታቸውን ጠብቆ ማስተኛት ተገቢ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ጥንቃቄ ከተደረገ አዲስ የተወለዱ ህጻናት በኮሮና ቫይረስ የመያዛቸው እድል እጅግ አነስተኛ ይሆናል፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት  የኮሮና ቫይረስ ካለባቸው እናቶች የተወለዱ ጨቅላዎች ከ2%-5% የሚ ሆኑት ብቻ  እንደተወ ለዱ ሲመረመሩ ቫይረሱ በደማቸው ተገኝቶአል፡፡ አንዲት እናት በኮሮና ቫይረስ ከፍ ባለ ሁኔታ የታመመች ከሆነች አዲስ ከተወለደው ጨቅላ ህጻን መራቅ ይገባታል፡፡
የኮሮና ቫይረስ የያዛቸው ጨቅላ ህጻናት ቫይረሱ ይያዛቸው አይያዛቸው ለመለየት እንዲቻል በተለያየ ምክንያት ምርመራ ሊደረግላቸው ካልቻለ እና ጨቅላዎቹም ምንም ምልክት የማያሳዩ ከሆነ እንደጤነኛ ህጻን ከሆስፒታል ሊወጡ ይችላሉ፡፡ በእንደዚህ ያለው አጋጣሚ በሆስፒታል ያሉ አገልግሎት ሰጪዎች ከጨቅላው ልጅ ቫይረሱ ሊተላለፍባቸው እንደሚችል ምንም ጥር ጥር የለውም፡፡ ስለዚህ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያስችሉትን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ እንዲሁም እጅን በሚገባ መታጠብን አዘውትረው መተግበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የህጻኑን ጤንነት ለ14 ቀን የመከላከል ስራም በስልክ ወይንም በኮምፒዩተር በመታገዝ እና ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ በማድረግ ህጻኑ ጤነኛ መሆኑ ሲረጋገጥ ወደቤቱ መሄድ እንደሚችል ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
ህጻናት ኮሮና ቫይረስ ሲይዛቸው የሚያሳዩት ምልክት፡-
ምንም እንኩዋን ህጻናትና አዋቂዎች በኮሮና ቫይረስ ሲያዙ ተመሳሳይ ምልክት ቢያሳዩም ህጻናቱ ላይ ግን የሚታየው በአነስተኛ ደረጃ ሊሆን ይችላል፡፡ አብዛኞቹ ህጻናትም በአንድ ወይንም በሁለት ቀን ከህመሙ ሊያገግሙ ይችላሉ፡፡ ሊኖሩ የሚችሉት የህመም ምልክቶችም እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል፡፡
ትኩሳት….በአፍንጫ ፈሳሽ (ንፍጥ) መታየት
ሳል…የጉሮሮ ሕመም
የትንፋሽ ማጠር ወይንም ለመተንፈስ መቸገር
የአቅም ማነስ…..ራስ ምታት…..የጡንቻ ሕመም
ተውከት….ተቅማጥ…..የምግብ ፍላጎ ማጣት
የማሽተት ወይንም የማጣጣም ችግር
የአይን መቅላት….የሆድ ሕመም
አንድ ህጻን ከላይ የተጠቀሱትን ምልክቶች ካሳየ በኮሮና ቫይረስ የመያዝ ምልክት ሊሆን ስለሚችል በአስቸኳይ የህክምና ባለሙያ እንዲጎበኘው ማድረግ ይገባል፡፡ ህጻኑ በቤት ውስጥ ክትትል ሊደረግለትና በተቻለ መጠን ከህክምና ባለሙያ በስተቀር ከሌሎች መራቅ አለበት፡፡ ከተቻለ ህጻኑ ከሌላው የቤተሰብ አካላት ተለይቶ ለብቻው አንድ ክፍል ቢሰጠው ጥሩ ነው፡፡ ባጠቃላይም የአለም የጤና ድርጅት ወይንም የአገሩ መንግስት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በሚያወጣው ራስን የማግለል አሰራር መሰረት ሁሉም መተግበር ይገባዋል፡፡    
ሕጻናት የኮሮና ቫይረስ ሲይዛቸው አፋጠኝ የሆነ የህክምና እርዳታ የሚያስፈልጋቸው የህመም ሁኔታ አለ፡፡ በሰውነታቸው ወይንም በእንቅስቃሴአቸው አለዚያም በአመጋገባቸው ላይ ትልቅ ልዩነት ይታያል፡፡ ለምሳሌም፡-
ለመንቃት መቸገር ወይንም እንደነቁ መቆየት ሊያቅታቸው ይችላል፡፡
መተንፈስ ሊያቅታቸው ይችላል፡፡
ደረት ላይ ሕመም ወይንም የማይለቅ ጫና ያለው ስቃይ ሊኖር ይችላል፡፡
ህጻኑ ያለመረጋጋት እና የመነጫነጭ ባህርይው ግራ በሚያጋባ መልክ ሊሆን ይችላል፡፡
ከንፈር ወይንም ፊት ሰማያዊ ቀለም ሊኖረው ይችላል፡፡
ህጻናት ኮሮና ቫይረስ በሚይዛቸው ወቅት የሚኖራቸው ትኩሳት የመሳሰለው ስሜት በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ ሊከሰት የሚችል መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ለምሳሌም በልብ ላይ፤ በደም ስሮች፣በኩላሊት፣በአእምሮ ወይም በአይኖች ፤በቆዳ ላይ ሁሉ ሊገለጽ ወይንም የህመም ስሜቱ ሊታይ ይችላል፡፡ ይህ የሚያሳየው ምናልባትም ችግሩ በታየበት ወቅት ብቻ ሳይሆን ቀደም ሲል ቫይረሱ ይዞአቸው ቆይቶ ሊሆን እንደሚችል ነው፡፡
ወላጆችም ሆኑ እንክብካቤ አድራጊዎች በተለይም እናቶች ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የወጡትን ህጎች ማለትም እጅን መታጠብ፤ማህበራዊ እርቀትን መጠበቅ እና በአፍና አፍንጫ ላይ ጭም ብል Face Mask መጠቀምን እንዳይዘነጉ እነዚህ የWHO እና የCDC የምርምር ወረቀቶች ያስ ረዳሉ፡፡

Read 8412 times