Tuesday, 20 October 2020 00:00

ዛሬ የት ነው ያለነው?

Written by  አያሌው አስረሰ
Rate this item
(2 votes)

  ‹‹በታሪካችን በተለያዩ አጋጣሚዎች አዲስ የፖለቲካ ምዕረፍ የመጀመር እድሎች አግኝተን ብዙዎቹን በወጉ ሳንጠቀምባቸው አምልጠውናል፡፡ አሁንም ይህ የሥልጣን ሽግግር አዲስ ምዕራፍ የምንጀምርበት ሌላ የታሪክ አድል ነው፡፡ በመሆኑም በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ልንጠቀምበት ይገባል›› - (ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ )
         
            አኔ በዚህ እድሜዬ የንጉሡን፣ የደርግንና የአቶ መለስ ዜናዊን የመንግሥት መሪነት ዘመን አሳልፌአለሁ፡፡ ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከሚመሩት መንግሥት ጋር መኖር ከጀመርኩ ደግሞ  ሁለት ዓመት ከስድስት ወር አለፈ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን መንግሥት እንዴት ነው የምረዳው? አራሴን መላልሼ የምጠይቀው ጥያቄ ነው፡፡
ደጃዝማች ተፈሪ መኮንን ለአልጋ ወራሽነት በኋላም ለንጉሠ ነገሥትነት በበቁበት የሥልጣን ጉዞ ላይ ያለፉበትን  መንገድ  የደባ አድርገው የሚያዩ ብዙ  ጸሕፍት አሉ፡፡ ሥልጣን በዘር በሚሸጋገርበት በዚያ ዘመን፣ ዘር ቆጥረው ወደ ሥልጣን የመጡ በመሆናቸው ንግሥናቸውን  ሕጋዊ አድርጎ መቀበል አይከብደኝም፡፡ መንግሥታዊ ሥርዓታቸው ቀጥሎ ቢሆን ኖሮ "አገር በዘውዳዊ አገዛዝ" ውስጥ በመሆኗ ሊኖር የሚችለው ትግል ልክ እንደ እንግሊዝና ጃፓን ዘውዱን ሕገ መንግሥታዊ አድርጎ፣ ለፓርላማውና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰፊ ሥልጣን መስጠት ነበር፡፡
ደርግ እጅግ አዝጋሚ በሆነ የመፈንቅለ መንግሥት ወደ ሥልጣን የመጣ አካል ነው። በግብጽ እንደሆነው ሁሉ የሕዝብን አመጽ ተጠቅሞ፣ የንጉሡን መንግሥት ያወረደው ደርግ የቀጠለው አምባገነን  ሆኖ ነው፡፡ በግብርና አሥራት በሚገኝ ገቢ  የቆመውን የንጉሡን መንግሥት አስወግዶ የተከለው ከሕዝብ ከተወረሰ  መኖሪያ ቤትና ፋብሪካ በተገኘ ገቢ  ክንዱን ባፈረጠመ መንግሥት ነው፡፡ በአዋጅ ከወረሰው ትርፍ ቤት ኪራይ በዓመት 38 ሚሊዮን ዶላር ያገኝ እንደነበር የሚጠቁም ሪፖርት ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡  በብር ያገኝ የነበረውን ገቢ ደግሞ እግዜር ይወቀው፡፡ በትርፍ ቤትነት ለወረሳቸው ቤቶች ካሳ ለመክፈል ቃል የገባው ደርግ አንዳች ነገር ሳያደርግ መውደቁ ይታወሳል፡፡
የመሬት ላራሹን አዋጅ በማወጅ ባላባትነትን ቢያጠፋም፣ ደርግ ያቋቋመው  መንግሥታዊ ባላባትነትን (ፊውዳሊዝም) መሆኑ ድብቅ አይደለም፡፡ የመንግሥት  የከተማና የገጠር መሬት ባለቤትነት በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ የተከለውን ደንቃራ ሁሉም ይገነዘበዋል ብዬ ተሰፋ አደርጋለሁ፡፡
ኢሕአዴግ ደርግን በውጊያ አሸንፎ ለሥልጣን የበቃ መንግሥት ነው፡፡ ደርግና እሱ የሚለያዩት ጦር ሜዳ በመግባትና ባለመግባት  ነው፡፡ ኢሕአዴግ የተቀመጠው ደርግ በመደመደው መደብ ላይ ነው፡፡ ደርግ የወረሰው ቤትና ፋብሪካ፣ አልፎም ያቋቋማቸው ልዩ ልዩ አስተዳደራዊና ኢኮኖሚያዊ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ የእሱ ፈቃድ ማስፈጸሚያ ነው የሆኑት። የተሸጠው ተሽጦ፣ የተዘረፈው ተዘርፎ የተረፈው የገባው በዶክተር ዐቢይ በሚመራው  መንግሥት እጅ ነው፡፡ይህ  የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት ባዶ ሜዳ ላይ እንዳልቆመ ያስገነዝበናል፡፡ የዐቢይ መንግሥት ባዶ ካዝና እንደጠበቀው ቢናገርም፣ መሬት ላይ የተትረፈረፈ  ሃብት እንዳገኘ ወይም እንዳለው መረዳት አይከብድም፡፡
የንጉሡ መንግሥት፣ የዜጎቹን ዲሞክራሲያዊ መብት ማክበሩን፣ ሃሳባቸውን ለመግለጽ ገደብ የሌለባቸው መሆኑን ሲናገር ኖሯል፡፡ ይህን የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም መንግሥት ለአስራ ሰባት ዓመታት አስተጋብቶታል፡፡ ቅድመ ምርመራን ያስቀረው የኢሕአዴግ መንግሥት፣ ስለ መንግሥቱ ዲሞክራሲያዊነት ተናግሮ ባይጠግብም፣ በመንግሥቱ የመጀመሪያ ዓመታት እንደ እንጉዳይ የፈሉት ጋዜጦችና መጽሔቶች ቀስ በቀስ እየተመናመኑ እንዲሄዱ ማድረጉ  ድብቅ አይደለም፡፡ ከ1997 ዓ.ም አገር አቀፍ ምርጫ በኋላ ደግሞ ፊት ለፊት ሳይሆን በጀርባ በተዘረጋ መረብ (ኔትወርክ) እጅግ በጣም ጥቂት ጋዜጦችና መጽሔቶች ሲተርፉ ሌሎች እንዲጠፉ ተደርገዋል፡፡ በዚህ የሕዝብ ድምጽ መታፈን  በገሃድ በሚታይበት ጊዜ መንግሥቱ እራሱን የሕዝብን መብት አክባሪ፣ ለዲሞክራሲ ተቆርቋሪ አድርጎ ያቀርብ እንደነበር መግለጽ ግድ ነው፡፡
"ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የሚመሩት መንግሥት፣ በሕዝብ አመጽ ወደ ስልጣን የመጣ መንግሥት ነው፡፡ ደርግና የዐቢይ መንግስት  ለእኔ አንድ የሚሆኑት ለዚህ ነው። ደርግ የሕዝብን አመጽ ተጠቅሞ ንጉሡን ከሥልጣን አሰወገደ፣ ዐቢይ ከ2008 ዓ.ም መጨረሻ እስከ 2010 ዓ.ም አጋማሽ የቆየውን የሕዝብ አመጽ ድጋፍ አድርገው፣ የአገር መሪነቱን ሥልጣን ጨበጡ፡፡ በአገራችን የሕዝብ ድጋፍ ያለው ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ ቢኖር ኖሮ፣ የመንግሥቱ ሥልጣን በአመጽ በተሸነፈው በኢሕዴግ እጅ ባልገባ ነበር፡፡  
ዐቢይና  መንግሥታቸው እንደ ቀደምት አዳዲስ መንግሥታት ሁሉ የሕዝብን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንደሚያከብሩና እንደሚያስከብሩ ቃል ገቡ። ከሕወሓት መገፍተር በስተቀር የተለየ ነገር አለመኖሩን የተረዱ ክፍሎች ‹‹ጉዟችን ወዴት እንደሆነ  አመልካች ነገር ይሰጠን›› ለሚለው  ጥያቄአቸው፤  የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልስ ቃል በቃል ባይሆንም፣ ‹‹የምንላችሁን ስሙ›› የሚል ነበር፡፡ የሚከተሉትን መንገድ አለመናገራቸው፣ ‹‹ኧረ መንገድ ልቀቁ ወይም ቃልዎን እያጠፉ ነው››  እንዳንል እያደረገን ነው ማለት ይቻላል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት የሰጠው መስፈርት ኖሮ እሱን ይዘን ለመከራከር ባንታደልም፣ የፍትሕ መጽሔት ማኔጂንግ ዲሬክተር ጋዜጠኛ ተመስጌን ደሳለኝና ዋና አዘጋጁ ምስግና ዝናቤ   የታሰሩት፣ ‹‹በአንድ የኦዴፓ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የነበረው ብርሃኑ ፀጋዬ‹፣ በአዳነች አበቤ የባንክ አካውንት ምንጩ ያልታወቀ 40 ሚሊዮን ብር መግባቱን ጠቅሶ በማስረጃ ሲያፋጥጣት (የማፋጠጡ መንስዔ እንደተጠበቀ)፣ ገንዘቡ በግል አካውንቷ ያለ እርሷ እውቅና መግባቱን ካመነች በኋላ ማን እንዳስገባው አላውቅም የሚል መልስ ሰጥታለች›› የሚል ጽሑፍ (ፍትሕ መጽሔት፤ ሶስተኛ ዓመት፤ ቁጥር 101፤ መስከረም 2013 ዓ.ም) በማተማቸው እንደሆነ  የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡
ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል ነው ሲባል፣ ወይዘሮ አዳነች አበቤ፣ እንደኔና እንደ ሌላው ሰው ሁሉ ሰው በመሆናቸው የተለየ ነገር አይደረግላቸውም‹፣ በመንግሥት መዋቅር ያላቸው ቦታ የተለየ ጥቅም አያስገኝላቸውም  ማለት ነው፡፡ እኔ ተመሳሳይ ጉዳይ ቢያጋጥመኝ መጽሔቱ ማስተባበያ እንዲጽፍ፣ ላደረሰብኝ የሞራል ጉዳት (ካለ ማለት ነው) እንዲክሰኝ ማድረግ እንደምችል ሁሉ፣ ወይዘሮ አዳነችም ክስ የመመሥረት መብቱ አላቸው፡፡ እንዲህ አይነቱ ጥፋት ለስር የሚደርግ አለመሆኑ እየታወቀ፣ የመጽሔቱ ሰዎች መታሰርና መፈታት ነገሩን የበለጠ አነጋጋሪ ያደርገዋል፡፡ "አገር ለውጥ ላይ ነች፤ የተለወጠ መንግሥት ነው ያለው" እየተባለ የትናንቱ አሠራር መቀጠሉ የተስፋ ጭላንጭልን ያዳፍናል፡፡
በእውነት ግን የት ላይ ነን? ለውጡና የለውጡ መንግሥት አሉ? ትክክለኛ መልስ ያሻናል፡፡


Read 2068 times