Monday, 19 October 2020 00:00

“አንድ ወደፊት ሁለት ወደ ኋላ” One step forword two step back

Written by 
Rate this item
(3 votes)

    ከዕለታት አንድ ቀን ይመክትበት ጋሻ፣ ይሰብቀው ጦር፣ ይመለቅቀው ቃታ ያለው አንድ ጀግና አርበኛ ወደ ጦርነት ሊሄድ ይዘጋጅ ነበር አሉ፡፡
መሣሪያውን ይወለውላል፡፡ ዝናሩም ይሞላል፡፡ ጦርና ጋሻውን ያመቻቻል፡፡
በሠፈሩ ታዋቂው ጀግና እሱ በመሆኑ፣አሁንም አሁንም የሰፈሩ ሰው መልዕክተኛ ይልክበታል፡፡
“ኧረ ጠላት ደረሰ እኮ” ይሉታል፡፡
“እየተዘጋጀሁ ነው እኮ” ይላል፡፡
አሁንም ገንባሌውን ያጠልቃል፡፡ ጫውን ያሳስራል፡፡ ሁሉን ነገር ረጋ ብሎ እያዘጋጀ ነው፡፡
ሠፈርተኛው ደግሞ አሁንም መልክተኛ ይልክበታል፡፡
“ጠላት እየገሰገሰ ነው እኮ፤ ምነው ዝም አልክ?” ይሉታል፡፡ እንደገና ሌላ ሰው ይልካሉ፡፡ እባክህን ውጣ ይሉታል፡፡
“እሠፈራችን ሳይደርስ በአጭር እንቅጨው እንጂ” ብለዋል፤ እነ ፊታውራሪና እነ ደጃዝማች ይሉታል፡፡  
“ጐበዝ እየተዘጋጀሁ ነው አልኳችሁ፤ በቃ መምጣቴ ነው አይዟችሁ”፡፡
ትንሽ ቆይቶ ሌላ መልዕክተኛ መጣ፡፡ “አሁን የመጨረሻው ሰዓት ላይ ነን ፤ጠላትም በየቤታችን እየገባ ነው፡፡ እባክህ አሁኑኑ ናልን!’’
ትንሽ መልዕክት ይዞለት ደሞ ሌላ ሰው መጣ፡፡
አርበኛውም፤ “ጐበዝ ምን አድርግ ነው የምትሉኝ? ያላችሁኝን ጠላት ሞቼ ልጠብቀው ወይ?” ሲል መለሰ ይባላል፡፡
*   *   *
ይህ የአርበኛ ንግግር ከባድ መልክት ያለው ነው፡፡ በቤት፣ በመንደር፣ በቀዬም ሆነ በአገር ደረጃ ለህዝብ ህልውና ቅድሚያ እንስጥ ካልን፣ መሠረታዊ ጉዳይ ዝግጅት ነው፡፡
ዝግጅት ቢሉም አንድም የልቦና አንድም የአካል ነው፡፡ የስነልቦና ዝግጅት ሳይኖር፣ አካላዊ ብቃትን ማደራጀት አዳጋች ነው፡፡
ገና ጥንት ጠዋት፡-   
“ከማዕበል በፊት የባሕር እርጋታ
ከጦርነት በፊት የዝግጅት ፋታ
ከንግግር በፊት የአርምሞ ፀጥታ
ዛሬም ያው ሕዝባችን የአንደዜ ዝምታ
ነገር ግን “ይዋጋል መታገሉ አይቀርም፤ ታግሎም ያቸንፋል አንጠራጠርም።” ብለን የነበረው ዝግጁነት አንድም የሕዝብ ስነ አእምሮ መቅረጽን፣ አንድም ነባራዊና ህሊናዊ ሁኔታን ማመቻቸትም፤ (Objective and subjective Conditions) እንዲሉ ይጠይቃል፡፡ እኒህ ሁለት ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ ሳይጠናቀቁ በአንድ አገር ላይ መሠረታዊ ለውጥ አመጣለሁ ብሎ መፍረምረም፣ ግማሽ - ጐፈሬ፣ ግማሽ ልጭት ሆኖ አደባባይ እንደ መውጣት ነው፡፡
ያልተሸራረፈና ምሉዕነት ያለው ጉዞ ነው፡፡ ለውጥም ሙሉ ለሙሉ አሳክቶ (a change is ats equal to rest) (ለውጥ ላወቀበት እፎይታ ነው እንዲሉ) እዛ ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ መፍጋትን ይጠይቃል፡፡ ለውጥ አመጣለሁ እያልን፣ በወርቅ አልጋ፣ በእርግብ ላባ ላይ ተኝተን አይሆንም። ለውጥ እየተሰናሰለ ትግል ውጤት ነውና፡፡ የምንፈልገው ለውጥ የፖለቲካ ነው በምንል ጊዜ ፣ሁሌም ማስተዋል ያለብን አስኳል ቁም ነገር፤ ፖለቲካ ማለት የተጠናቀረ ኢኮኖሚ ነፀብራቅ መሆኑን ነው፡፡ (Politics is the concentranted expression of Economic) እንዲሉ ማርክሳዊ ልሂቃን! ይህ ማለት ደግሞ የሕዝባችን ኖሮ ከየት ወዴት ተለውጧል ወይም ተሸጋግሯል ማለታችን ነው፡፡ ለውጥን በእድገት መነጽር መመርመር ተገቢ ነው፤ የሚባልበትም አንዱ መሠረታዊ ምክንያት ይሄ ነው፡፡ የኑሮ ሂደት ወሳኝ የእድገት ፍሬ ነገር ላይ ደረሰ የምንለው የሰው ህይወት መለወጡን የሚያሳይ ፍንጭ ሲፈነጥቅ ነው፡፡ አለበለዚያ በመሄድና በመዳከር መካከል በልዩነት የማናይና ወደ ንቅዘት የምንጓዝ የዋሀን፣ አሊያም አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይነቃም የምንባል እንሆናለን፡፡
አንድ እርምጃ ወደ ፊት፣ሁለት ወደ ኋላ ማለት ይኸው ነው፡፡ One step forword two steps back የሚባለው ሌኒናዊ ብሂል ላይ ነው የምንወድቀው! ከዚህ ይሰውረን!


Read 12574 times