Monday, 19 October 2020 00:00

የኢዜማና የአዲስ አበባ አስተዳደር ጉዳይ ጥቅምት 25 በፍ/ቤት ይዳኛል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

    ኢዜማ ህገ መንግስታዊ መብቴን ተጋፍቷል ሲል በአዲስ አበባ አስተዳደር ላይ መስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 12ኛ ፍትሐብሔር ችሎት የመሠረተው ክስ ጥቅምት 25 ይታያል፡፡
“ህገ መንግስታዊ የሆነው የመሰብሰብ መብቴ በከተማ አስተዳደሩ ተጥሷል” ያለው ኢዜማ፤ “ፍ/ቤቱ ይህን ተገንዝቦ የከተማ አስተዳደሩ የስብሰባ እግድ ደብዳቤ መፃፉና የፓርቲውን የመሰብሰብ መብት መንካቱ ህገ ወጥ ነው” ብሎ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት  እንደሚጠይቅ ነው የፓርቲው ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ ለአዲስ አድማስ የገለፁት፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በደብዳቤው በመሬት ወረራና ተያይዞ ባሉ ጉዳዮች ምርመራ እያደረገ መሆኑን በመግለጽ፣ የምርመራ ውጤቱ መጨረሻ ሳይታወቅ በፊት ውይይት ማድረግ አይቻልም በሚል መግለፁን ያስረዱት አቶ ናትናኤል፤ ይህ የደብዳቤው ይዘት አስተዳደሩ ውጤት ላይ ሳይደርስ ሌላ ስብሰባ እንዳይደረግ እግድ የሚጥል በመሆኑ ይህ እግድ እንዲነሳና ከአሁን በኋላም አስተዳደሩ እንዲህ ያለ ድርጊት መፈፀም እንደማይችል ትዕዛዝ እንዲሰጥ መጠየቁን ነው ያስረዱት፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ አሁንም የመሬት ወረራ እየተፈፀመ መሆኑን የሚገልፁ ጥቆማዎች  እየደረሱት መሆኑን አስረድተዋል - አቶ ናትናኤል፡፡
ቀደም ሲል ኢዜማ፤ በአዲስ አበባ የመሬት ወረራ ጉዳይ የደረሰበትን የምርመራ ውጤት ከከተማ አስተዳደሩ በተጨማሪ ለፌደራል ፖሊስ፣ ለፌደራል የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንና ለጠቅላይ አቃቤ ህግ “የወንጀል ይጣራልኝ” አቤቱታ አስገብቶ የነበረ ቢሆንም፤ ከተቋማቱ ምንም አይነት ምላሽ እንዳለተሰጠውም አቶ ናትናኤል አስረድተዋል፡፡

Read 980 times