Print this page
Monday, 19 October 2020 00:00

የግለሰቦችን ፎቶግራፎች በማቀናበር በማህበራዊ ገጾች ላይ ለቋል የተባለ ተጠርጣሪ ግለሰብ ተያዘ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(0 votes)

የግለሰቦችን ፎቶግራፎች በማቀናበር አስነዋሪ ድርጊቶችን እንደ ፈጸሙ በማስመሰል በተለያዩ ማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ ለቋል የተባለ ግለሰብ በፖሊስ  በቁጥጥር ሥር ውሎ እተየመረመረ መሆኑ ተገልጿል ።
ግለሰቡ ከፌስቡክ፣ ከቴሌግራምና ከሌሎች ማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ የግለሰቦችን ፎቶ በመውሰድ የማቀናበሪያ መተግበሪያዎችን በመጠቀም ከአንገት በላይ ያለውን ገጽታ ቆርጦ ከሌላ ሰው አካል ጋር በማቀናበር፣ ግለሰቦቹ የወሲብ ድርጊቶችንና ሌሎች ክፉ ነገሮችን  እንደፈጸሙ በማስመሰል  በፌስቡክ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ለቋል፤ ብሏል ፖሊስ ።   የድርጊቱ ሠለባ ከሆኑ ግለሰቦች በደረሰው ጥቆማ መሰረት፤ፖሊስ ተጠርጣሪው ድርጊቱን ሲፈጽም ሲጠቀምባቸው ከነበሩ ኮምፒውተርና ሞባይል ስልክ ጋር በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እያደረገ መሆኑን  የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በድረ ገፁ የሠፈረው ሪፖርት ያመለክታል ።
ተጠርጣሪው ላይ  ተጨማሪ ማስረጃ በማሰባሰብ ፖሊስ በፍ/ቤት የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆ ጉዳዩን እያጣራ ሲሆን በርካታ ተበድለናል የሚሉ አቤቱታ አቅራቢዎች-፡  ጥቆማ እየሠጡ መሆኑን አስታውቋል።   
  ግለሰቡ ድርጊቱን መፈጸም ከጀመረ መቆየቱን፣ለዚህም ዓላማው ከ200 በላይ የግለሰቦችን ፎቶዎች መጠቀሙን ያስታወቀው ፖሊስ ፤ ወጣት ሴቶች፣ አባወራዎችና  እማወራዎች የድርጊቱ ሰለባ መሆናቸውን ጠቁመዋል ።
  በተጠርጣሪው አስነዋሪ ድርጊት የተነሳ በርካቶች ለማህበራዊና ስነልቦናዊ ጉዳት ተዳርገዋል ያለው ፖሊስ፤ በቤተሰብና ጓደኞቻቸው አመኔታ፣ እንዲያጡ ትዳራቸው፣ እንደፈረሰባቸው፣ ከስራ እንደተባረሩና የተደፈረች ወጣት እንዳለችም ፖሊስ አመልክቷል።
ግለሰቡ ድርጊቱን ሲፈጽም የነበረው በማህበራዊ ድረ ገጾች የተመልካች ቁጥር በመጨመር በህገ ወጥ መንገድ ገቢ ለማግኘት በማሰብ መሆኑን የጠቆመው ፖሊስ ፤ሌሎች ጉዳት ደርሶብናል የሚሉ ግለሰቦችም  እንዲጠቁሙ ጠይቋል።

Read 1186 times