Saturday, 04 August 2012 10:12

በንጉሡ የልደት በዓል ምን ተባለ?

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

በጥንት ዘመን የሰው ልጅ አምስት ጣቶች “እኔ እበልጣለሁ፣ ለእኔ ለተየለ ክብር መስጠት አለባችሁ” በሚል እርስ በእርስ ይጣላሉ፡፡ አውራ ጣት በስያሜም በውፍረትም የተለየ አክብሮት የሚገባኝ እኔ ነኝ አለ፡፡ ሌባ ጣት እንዴት ሆኖ በማለት የራሱን መከራከሪያ ማቅረብ ጀመረ፡፡ ሌባ ጣት ባቀረበው ሐሳብ “የሰው ልጅ ሲጠቁም፣ ሲናገር፣ ሲያመለክት አብዝቶ የሚጠቀመው እኔን ነው፡፡ ስለዚህ የተለየ አክብሮት የሚያስፈልገኝ እኔ ነኝ” አለ፡፡ የመሐል ጣት በበኩሉ “የአፈጣጠሬን ልዩነት፣ የቁመቴን ከእናንተ በተለየ መርዘምና ማማር፣ ከዚህም ባሻገር ከግራና ቀኝ በሁለት ሁለት ጣቶች እንድታጀብ ተደርጌ የተፈጠርኩት፣ እኔ ከሁላችሁም ስለምበልጥ ነው” ሲል ተኩራራ፡፡ አራተኛው ጣት በተለየ ለመከበር ያበቃኛል ያለውን መከራከሪያ አቀረበ፡፡ “ሰዎች በብር፣ በወርቅ፣ በአልማዝ ቀለበት ሲያስሩ በአብዛኛው በእኔ ላይ ነው የሚያኖሩት፡፡ ጋብቻ ሲፈጽሙ እንኳን የቃል ኪዳን መለያ ቀለበታቸውን ለመያዝ መመረጤ ለታላቅነቴ መለያ ነው” አለ፡፡

ትንሹ ጣት “እኔ” ከማለት ይልቅ “እኛ” ብሎ ታላቅነታቸውን ለማሳየት ጥያቄ ማቅረብ ጀመረ፡፡ የመጀመሪያውን ጥያቄ ለአውራ ጣት አቀረበለት፡፡ “መሬት የወደቀውን ወረቀት ብቻህን አንሳው እስቲ?” አለው፡፡ አልቻለም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ሌሎችንም እንዲሞክሩ ጠይቆ አለመቻላቸውን ሲያይ እንደ ወረቀት ቀላል የሆኑ ነገሮችን ለማንሳት ሁለት ጣቶች መተባበር እንዳለባቸው፤ ከበድ ያለ ዕቃ ለማንሳት ደግሞ የ5ቱም ጣቶች መተባበር እንደሚያስፈልግ ተናግሮ ሁሉም የራሱ የሆነ ድርሻ፣ ኃላፊነትና ታላቅነት እንዳለው አመለከተ፡፡

***

ይህ ተረት ባለፈው እሁድ ሐምሌ 22 ቀን 2004 ዓ.ም በዋቢ ሸበሌ ሆቴል የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ 120ኛ የልደት በዓል በተከበረበት መድረክ የተነገረ ነው፡፡ መድረኩን ያሰናዳው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መታሰቢያ ማህበር ሲሆን በ1991 ዓ.ም በ24 አባላት የተቋቋመ ነው፡፡ የንጉሱን አስከሬን በክብር ማሳረፍ፣ ለችግረኛ ልጆች የትምህርት ስኮላርሽፕ ለመስጠት፣ በንጉሱ ሥም ሙዚየም ለማቋቋምና የመሳሰሉ ዓላማዎችን ነድፎ መንቀሳቀስ የጀመረው ማህበር፤ ባቀደው መሠረት መንቀሳቀስ አለመቻሉ በተነገረበት ወቅት ነበር ለችግሩ አንድ መፍትሔ መተባበርና መተጋገዝ ነው በሚል ከላይ የቀረበው ተረት የተነገረው፡

ማህበሩ የገጠመውን የገንዘብ ችግር ለመቅረፍ ንጉሳዊ አስተዳደር ላላቸው መንግስታት፣ በአገር ውስጥና በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ለመንግስት የትብብር ጥያቄዎች ቢቀርቡም በተጠበቀው መጠን ምላሽ አልተገኘም፡፡ በታቀደው መሠረት ማህበሩ የስኮላርሽፕ ትምህርት ዕድል ለመስጠት ያሰበው ተማሪዎች ቁጥር 500 መድረስ የነበረበት ሲሆን እስካሁን ማሳካት የተቻለው የእቅዱ ግማሽ መሆኑ በቀረበው ሪፖርት ተመልክቷል፡፡

የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ ናሁሰናይ አርአያ፤ ችግሩ የቱን ያህል የሰፋ መሆኑን ሲያመለክቱ ለቤት ኪራይ መክፈል የሚገባቸውን እየከፈሉ እንዳይደለ፣ የቢሮው አራት ሠራተኞችም በዝቅተኛ ደሞዝ እያገለገሉ መሆኑን፣ በዚህ መልኩ ዋጋ እየከፈሉ ያሉት አካላት ለአፄ ኃይለሥላሴና ለማህበሩ ዓላማ ካላቸው አክብሮት የተነሳ ነው ብለዋል፡፡ በሰው ኃይልና በገንዘብ እጥረቱ የተነሳም ቃል የተገባልንንም ዞረን ለመሰብሰብ ተቸግረናል ሲሉም አክለዋል፡፡

የልዑላን ቤተሰቦች፣ የማህበሩ መሥራቾችና አባላት፣ ብዙ ታላላቅ ሰዎች በተገኙበት መድረክ በክቡር ዘበኛ ሙሉ ልብስ፣ በንጉሡ ዘመን የፓርላማ ተመራጮች የሚለብሱትን ካባ ደርበው የመጡ እንግዶችም ነበሩ፡፡ ለማህበሩ ሥራ በተለይ የስኮላርሽፕ ተማሪዎችን ለመርዳት በተለያየ መልኩ እገዛ ያደረጉ ተቋማትና ግለሰቦች የሰርተፊኬት ሽልማት በተሰጠበት መድረክ፤ ማህበሩን ያለ ደሞዝ አንድ ዓመት በነፃ ላገለገሉት አቶ አበራ ሞልቶት ልዩ ምስጋና ቀርቧል፡፡ መድረክ ይመሩ የነበሩት አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ አፄ ኃይለሥላሴ በሕይወት እያሉ ብቻ ሳይሆን ከህልፈታቸው ከብዙ ዓመታት በኋላ በሰዎች ልብ ውስጥና በብዙ ቤቶች ግድግዳ ላይ ምስላቸው ተሰቅሎ እንደሚገኝ አመልክተው፤ በንጉሡ ሥራዎች ታላቅነት የተነሳ ጥቂት በማይባሉ የአፍሪካ አገራት መንገድና ትላልቅ ተቋማት ሰይመው የአፄ ኃይለሥላሴን ሥም ይዘክራሉ ብለዋል፡፡

ንጉሡ ፍጡር ስለሆኑ እንደማንኛውም ሰው የሰሯቸው ስህተቶች ይኖራሉ ያሉት አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ፤ በደርግ ዘመን የአፄ ኃይለሥላሴን ሥምና ሥራዎች ለማጥፋት ብዙ ተለፍቷል፡፡ ሥራና ታሪካቸው ሕያው ስለሆነ ግን አልጠፋም፡፡ ዛሬም ቢሆን መንግሥትን አጥብቆ የሚጠይቅ አልተገኘም ይሆናል እንጂ ደርግ ያፈረሰው መታሰቢያ ሐውልታቸውን መልሶ የማቆም ዕድሉ አለ፡፡ ለሥማቸው መታሰቢያ የሚሆን ሌሎች ነገሮችንም ማሰየም ይቻላል ብለዋል፡፡ ለአፍሪካ ባከናወኑት ተግባር በተለያዩ አገራት መታሰቢያ የተሰራላቸው አፄ ኃይለሥላሴ፤ በአገራቸው ግን የሚገባቸውን ክብር እንዳላገኙ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩ አንድ ተሰብሳቢ፤ ለንጉሡ በአዲስ አበባ ከተማ ሐውልት መቆም እንዳለበትና ሐውልቱም ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ሕንፃ ፊት ለፊት (የሌኒን ሐውልት የነበረበት ቦታ ላይ) መሠራት ቢችል ከንጉሡ ታሪክና ሥራ ጋር ተያያዥነት እንደሚኖረው አመልክተዋል፡፡ ማህበሩ የገጠመውን የገንዘብ ችግርንም ለመቅረፍ በቅርቡ ለኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን በሞባይል ስልክ ብዙ ብር ማሰባሰብ እንደተቻለው የሕዝቡንም እገዛ በዚህ መልኩ ማግኘት ይቻላልና ይታሰብበት ብለዋል - አስተያየት ሰጪው፡፡

ለትምህርት የተለየ አክብሮት ነበራቸው የተባሉት አፄ ኃይለሥላሴ፤ “የሚንቋችሁ የሚያከብሯችሁ ስትማሩ ነው” በማለት ሌሎችን ለትምህርት ያተጉ እንደነበርም በተለያዩ ሰዎች መድረኩ ላይ ተነግሯል፡፡ የአንዱ ተናጋሪ የልጅነት ገጠመኝም ይህንኑ እውነት የሚያጠናክር ነው፡፡ በአንዱ ትምህርት ቤት ንጉሡ ተገኝተው ጉብኝት ሲያደርጉ፣ ተማሪዎቹ በምግብ ቤት ውስጥ ነበሩ፡፡ ከተማሪዎቹ መሐል አንዱ አለመብላቱን ያዩት አፄ ኃይለሥላሴ፤ ምክንያቱን ሲጠይቁት እፆማለሁ ሲላቸው “ብላ ግዴለም እኛ እንፆምልሃለን” ማለታቸውም በምስክርነቱ ቀርቧል፡፡ በንጉሡ 120ኛ የልደት በዓል ላይ ንግግር እንዲያቀርቡ የተጋበዙ ምሁራንም ነበሩ፡፡ አቶ ሰይፈ ሀብተማርያም ባቀረቡት ጽሑፍ፤ የ13 ዓመት ልጅ ሳሉ ጀምሮ የመንግሥት ሥራ ኃላፊነት የወሰዱት አፄ ኃይለሥላሴ፤ በትምህርት፣ በባህል፣ በሃይማኖት፣ በጤና፣ በኢኮኖሚ … ያከናወኗቸውን ታላላቅ ተግባራት በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ ለ345 ጊዜያት በአገር ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸውንና ከ1916 ዓ.ም ጀምሮ ለሥራ ጉዳይ ብዙ የዓለም አገራትን መጎብኘታቸውንም አብራርተዋል፡፡

“በአሁኑ ጊዜ ዓለም ስለ ማንዴላ ያወራል፡፡ ማንዴላ በበኩላቸው ስለ አፄ ኃይለሥላሴ ይናገራሉ” በማለት ንግግር የጀመሩት ሌላኛው ተጋባዥ አቶ መኮንን ተገኝ በበኩላቸው፤ አፄ ኃይለ ሥላሴ ንጉሥ ከመሆናቸው በፊትና በኋላ ያከናወኗቸውን ተግባራት አመልክተዋል፡፡ ንጉሡ ነጋዴዎችን ለማበረታታት “ቀኛዝማች” እና መሰል ሽልማት ይሰጡ እንደነበርም በምሳሌነት በመጥቀስ፡፡

“ዛሬ ብዙ የውጭ አገር የእርዳታ ድርጅቶች የእኛን ልጆች ለመርዳት ወደዚህ ይመጣሉ፡፡ በተቃራኒው አፄ ኃይለሥላሴ ችግረኛ ልጆችን ለመርዳት ወደ ውጭ መጓዝ ችለው ነበር” ያሉት አቶ መኮንን ተገኝ፤ በኦስትሪያ (ቪየና) ችግረኛ ልጆችን ይረዱ እንደነበር፤ በኢየሩሳሌም በችግር ላይ ያገኟቸውን 40 ልጆችን ወደ አዲስ አበባ በማምጣት ይረዷቸው እንደነበር ገልፀው፤ ለንጉሡና ለአገራቸው መፈራትና መከበር እነዚያ ተግባራት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ኬክ በመቁረስ የአፄ ኃይለሥላሴ 120ኛ የልደት በዓል ተከብሮ የዕለቱ ዝግጅት ከመጠናቀቁ በፊት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በዘለቀው ገንዘብ የማሰባሰብና ቃል የመግባት ሂደት ፍፃሜ 72 ሺህ ብር መገኘቱ ተበስሯል፡፡

 

 

 

Read 1611 times Last modified on Saturday, 04 August 2012 10:24