Print this page
Saturday, 04 August 2012 09:56

የ“እኛ ተማሪነት” ዘመን ሌላኛው ገፅታ

Written by  ቻላቸው ታደሠ (ከሐዋሳ ዩኒቨርስቲ) chaltad2000@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

በጐ በጐውን ለመምረጥ ያለፈውን ማወቅ!

(ካለፈው የቀጠለ)

ባለፈው ሣምንት የ“እኛ ተማሪነት ዘመን ሌላኛው ገፅታ” በሚል ርዕሰ-ጉዳይ ላይ የጀመርኩትን ፅሁፍ ሌሎች ጉዳዮችን በማንሣት ዛሬ እቋጫለሁ፡፡ የአሁኑ ተማሪዎችን በተመለከተ መሠረታዊው ጉዳይ በትምህርት ቤት ውስጥ መተግበር ስለሚገባው ነፃነት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ በእርግጥም ነፃነት ለትምህርት እድገትና የራሱንና የሀገሩን እጣ ፋንታ መወሰን የሚችል ትውልድ በመፍጠር ረገድ የሚጫወተው ሚና ጉልህ ነው፡፡ የአሁኑ ዘመን ተማሪዎች እዚህ ላይ መርሣት የሌለባችሁ ግን ትምህርት ቤቶች ተቋም (institution) መሆናቸውንና በየትኛውም ሀገርና በማናቸውም ጊዜ የራሳቸውን ገደብ ማስቀመጥ የሚችሉ መሆኑን ነው፡፡

ስለሆነም እንደ ተማሪ የተወሰኑ ነፃነታችሁን ለተቋሙ ህግና ደንብ ማስገዛት የማይቀር ግዴታ ነው፡፡ አሁን በእኛ ሀገር የሚታየው አዝማሚያ ግን በተገላቢጦሽ የትምህርት ተቋማት ለተማሪዎች “ፍፁማዊ ነፃነት” በመገዛት ህግና ደንቦቻቸውን እያላሉ ብሎም እየተው መምጣታቸውን የሚያሣይ ነው፡፡ ይህ በብዙ የከተማ ትምህርት ቤቶች እየታየ ያለው ሁኔታ ከወዲሁ ዘላቂ መዘዝ እያስከተለ መምጣቱ መዘገብ ከጀመረ ቆይቷል፡፡ እናንተ አዲስ አበባዊያን የተማሪ ወላጆች፡- በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ሲዘገብ የሰማችሁትንና ያነበባችሁት አስጊ ጉዳይ አሳስቧችሁ በአስቸኳይ ከተማ-ዓቀፍ የወላጆችና የትምህርት ቤቶች ጉባዔ እንዲካሄድ አለመጠየቃችሁ ትዝብት ውስጥ አይጥላችሁም? በቶሎ ልታስቡበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

በነገራችን ላይ በሐዋሣ ዩኒቨርስቲ ውስጥ አንድ የሚገርመኝ ነገር አለ፡፡ ሁሌም ከ11፡00 ሰዓት በኋላ ድምፁ ግቢውን የሚያንቀጠቅጥ ሙዚቃ ይለቀቃል፡፡ ሙዚቃው የሚለቀቀው ከተማሪዎች ህብረት ቢሮ መሆኑ ደግሞ ትልቅ ግራሞት ይፈጥራል፡፡ የማታ ተማሪዎችን የሚያስተምሩ መምህራንን የሚሰማቸው አካል ያለ አይመስልም፡፡ ቤተ-መፅሃፍት ውስጥ ገብተው ማንበብ የሚፈልጉ ተማሪዎች ደግሞ የውስጣቸውን ስቃይ መረዳት አይከብድም፡፡ ይህ ስትራቴጂ ተማሪዎችን ወደ ከተማ እንዳይወጡ የማስቀረት ወይንስ የመገፋፋት ኃይል እንዳለው ለአንባቢያን እተወዋለሁ፡፡

እኔ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ህብረት መሥራችና ሥራ አስፈፃሚ አባል በነበርኩበት ወቅት የነበረውን የተማሪዎች ህብረት ዓላማና አሰራር ሣስብ ግን ልዩነቱ የትየለሌ ይሆንብኛል፡፡ በእኛ ዘመን የዩኒቨርስቲው ህግ፤ ውጤት ተሳሳተብኝ የሚል ተማሪ ገንዘብ ከፍሎ ካስመረመረ በኋላ አቤቱታው የተሳሳተ ሆኖ ቢገኝ ውጤቱ የሚቀነስበት ፍፁም ኢፍትሃዊ የሆነ አሰራር የነበረበት ወቅት ነበር፡፡ ይህንን አሰራር ከብዙ ትግልና ግልምጫ በኋላ ማስቀረታችን ትዝ ይለኛል፡፡ ሙስናን ለመዋጋትም ዩኒቨርስቲው በጨረታ የሚገዛውን ዘይትና ቅቤ በየተራ እየቆምን እንፈትሽና እናስመዝን እንደነበር የሚረሣ አይደለም፡፡ በአንድ ወቅትም ሙዝ ከቅቤ ጋር ተመሣስሎ ተገዝቶ እንደነበር በወቅቱ የነበሩ ሁሉ ያስታውሱታል፡፡ ተማሪዎች በሀገራቸው ጉዳይ ንቁ ተሣታፊ እንዲሆኑ በህግ አውጭው ፓርላማ ሣይቀር የታዛቢነት ቦታ እንዲኖራቸው የታገልንበትን ሁኔታ ሣስታውስና የአሁኑ የሐዋሣ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ህብረት ምን እየሰራ እንደሆነ ስመለከት እጅጉን ይገርመኛል፡፡

ከላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን የሬጅስትራር ህግ ያነሣሁት፣ አቶ አንተነህ ይግዛው የተባሉት ፀሃፊ በድሮው ሥርዓት የትምህርት ዘመን ለ“ተማሪ መቶ አይሰጥም” የሚል ህግ እንደነበር ከኔ ቀደም ብሎ በዚሁ ጋዜጣ ላይ የፃፈውን በማስታወስ ነው፡፡ ሁለቱም ሁኔታዎች የትምህርት ሥርዓታችን ከድሮ እስከ ዘንድሮ፣ ከላይ እስከ ታች በበርካታ ችግሮች የተተበተበ ሆኖ የቆየ መሆኑን ያሣያሉ፡፡

መቼም የዛሬ ሣምንት የጀመርኩት ፅሁፍ መነሻ፣ ትዝታ ነውና ወደ ትዝታ እንመለስ፡፡ በእኛ የተማሪነት ዘመን ለሀገራችን በጐ ተግባራትን ያከናወኑ ሰዎችን ታሪክ የተማርን ይመስለን ነበር፡፡ የመረጃ ምንጫችን በጣም ውስን ስለነበር ወታደራዊው መንግስት በ“አብዮታዊ ማጥለያ” አጥልሎ ያስቀራቸውና ያልነገረን በርካታ ታሪኮች መኖራቸውን  ያወቅንበት ዘግይቶ ነው፡፡ ብዙዎቻችን የንጉሱን ዘመን አገዛዝ ያለ በቂ መረጃ ክፉኛ ስናብጠለጥል ከወላጆቻችን ጋር ቅራኔ ውስጥ መግባታችን አልቀረም፡፡ ወላጆቻችን የሚነግሩንን ታሪክ ላለመቀበል ትረካቸውን እየረገጥን እስከ መውጣት ደርሰን ነበር፡፡

ለአብነት ያህል እንኳን አንድ ጉዳይ ላንሳ፡፡ በንጉሱ ዘመን በ1920ዎቹ ለትምህርት ወደ አሜሪካ ተልኮ፣ የሰሜን አሜሪካ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ማህበር የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚዳንትና የፓን አፍሪካኒዝም (Pan-Africanism) ቀንደኛ አንቀሣቃሽ የነበረው ኢትዮጵያዊው ዶ/ር መላኩ በያን መሆኑን ያወቅነው እጅግ በጣም ዘግይቶ ነው፡፡  የተማሩ የውጭ ሀገር ጥቁሮችን እየመለመለ ኢትዮጵያን እንዲረዱ ይልክ የነበረው ዶ/ር መላኩ፤ በጣሊያን ወረራ ወቅት ከንጉሱ ጋር ተሰድዶ የነበረና በዓለም ዓቀፋዊ እውቅናው ምክንያት እኛ ሣናውቀው በሥሙ በርካታ ፋውንዴሽኖች የተቋቋሙለት ሰው ነው፡፡ የትምህርት ሥርዓታችን ግን ይህንና ሌሎች ለሀገራቸው በርካታ ቁም ነገሮችን ያከናወኑ ሰዎችን ጉልህ ሚና የማንኳሰስ ችግር ነበረበት፡፡

መቼም የአሁኑ ዘመን ተማሪዎች ሀገራችን አህጉራዊና የዓለም አቀፍ ድርጅቶችን መምራት የሚችሉ ዜጐች ባለማፍራቷ ይቆጫችሁ ይሆናል፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሠረት የመጀመሪያው የሽግግር ዘመን ዋና ፀሃፊ ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ተስፋዬ ገብረ እግዚ መሆናቸውን ግን ሰምታችኋል? እኔን ካላመናችሁ እድሜያቸው ገፋ ያሉ የታሪክ መምህር ካሏችሁ ጠጋ ብላችሁ በትህትና ጠይቋቸው፡፡ እኒህን ታዋቂ ሰው ግን የእኛው ዘመን መንግስት “አብዮታዊ እርምጃ” የወሰደባቸው ሥልጣን በያዘ ማግሥት ነው፡፡ በእኛ የተማሪነት ዘመን በሀገር-በቀል ሰዎቻችን ፋንታ የሌኒንንና የማርክስን ሐውልቶች በብዛት መገንባታችን እውነት ነው፡፡ ይህ የእኛ ዘመን እብደት ነው፡፡

ለነገሩ ከምንጊዜውም በላይ የ“ሐውልቶች ዘመን” ተብሎ መጠራት በሚገባው የእናንተ ዘመን እንኳ ቻይናዎች ለአፍሪካ ህብረት በሰሩት ህንፃ ቅጥር ግቢ ውስጥ ብቻውን የቆመ ሃውልት አለ፡፡ ይህ የ“መደለያ” ይሁን የ“ወንድማማችነት” መገለጫ ገና በቅጡ ያለየለት ህንፃ ቅጥር ግቢ ውስጥ የመጀመሪያው የጋና ጥቁር ፕሬዚዳንት የክቡር ክዋሜ ንክሩማ ሃውልት ቆሟል፡፡ ከጐኑም የአንጋፋው የአፍሪካ አባት የአፄ ኃ/ሥላሴ ኃውልት ሣይቆም በመቅረቱ በርካታ የእኛ ዘመን ሰዎች ያኮረፉ ይመስላል፡፡ ግን ጋናዊያን ራሳቸው ምን ያህል ይታዘቡን ይሆን? መቼም የሁለቱን መሪዎች አስተዋፅኦ በመጠኑም ቢሆን ለመዳሰስ ከኢቲቪ ጀርባ ወደሚገኘው መወዘክር ቤተ-መፅሃፍት ብቅ ማለት ይበቃል፡፡

የኮልፌ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ሆይ! የደቡብ አፍሪካው የነፃነት ታጋይና የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ፤ ከትምህርት ቤታችሁ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኝ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያ መሠልጠናቸውን ሰምታችኋል? በእርግጥ እሳቸውም Long Walk to Freedom በሚለው መፅሃፋቸው በኩራት ይጠቅሱታል፡፡ እስኪ በሚቀጥለው ዓመት የ95ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ሲያከብሩ “መልካም የልደት በዓል”  ብላችሁ ካርድ ላኩላቸው፡፡ ይህንን ካደረጋችሁ በቀላሉ የታሪክ አካል መሆናችሁ አይቀርም፡፡ የመልካም ምኞት ካርዳችሁ የዓለም ህዝብ በሚጐበኘው ሙዚየም ውስጥ መቀመጡ አይቀርምና፡፡ በነገራችን ላይ ኔልሰን ማንዴላ ከሀገራችን ጋር ካላቸው ጥብቅ ትስስር አንፃር በሥልጣን ዘመናቸው ሥድስት ወር ያህል የቆዩበትን ተቋምና በአጠቃላይ የሚወዷትን ሀገራችንን ሳይጐበኙ የቀሩት ለምን ይሆን?

ባለፈው ስዊዘርላንድ ደርሰህ የመጣኸው ወዳጄ፡- ስዊዘርላንድ ውስጥ በምትገኘው በርን ከተማ በሚገኝ ሆቴል ውስጥ ኔልሰን ማንዴላና አፄ ኃ/ስላሴ ለጉብኝት በሄዱ ጊዜ የተኙባቸው አልጋዎች እንደ ቅርስ ተጠብቀውና ለጐብኝዎች (tourists) ብቻ ክፍት እንደሆኑ የነገርከኝ ሁሌም ይገርመኛል፡፡ የእኛን ሞኝነት ጭምር ለመዘከር የተቀመጡ ይመስሉኛል - የቀድሞ ገዥዎቻችን በማውገዝ የተጠመድን በመሆናችን፡፡

ለማንኛውም የአሁኑ ዘመን ተማሪዎች የመረጃ ምንጫችሁ በርካታ በመሆኑ ስለ ውጭ ሀገራት አብዝታችሁ ከምታስቡ የእኛው ዘመን “ቆራጥ” መሪ ከዚምባቢዌ ሆነው “ትግላችን” በሚል የፃፉትን መፅሃፍ ገዝታችሁ አንብቡ፡፡ የሦስት ቀን የባቅላባ ወጭ ብትቆጥቡ ትገዙታላችሁ፡፡ ለእናንተም ሣይቀር መዘዙ የተረፈላችሁን የመጠላለፍ፣ የድብቅነትና የመጠራጠር ብሎም የመናናቅ ፖለቲካዊ ባህል ታሪካዊ አመጣጡን ትረዱበታላችሁ፡፡ የትምህርት ሥርዓታችን ቀውስ ምንጩም ይገለጥላችሁ ይሆናል፡፡ በጐ በጐውን ጐዳና ለመምረጥ ያለፈውን ማወቅ ይጠቅማል፡፡ one who doesn’t remember history is bound to live through it again  ብሏል አንድ ፀሃፊ፡፡

ይህንን የምላችሁ በእኛ የተማሪነት ዘመን እንደነበረው ሁሉ ቅጥአምባሩ በጠፋባቸው ሃሳቦች ከመወናበድ እንድትድኑ ነው፡፡ የመረጃ ምንጫችሁ በመብዛቱ ጥሩውንም መጥፎውንም እንደወረደ እያከታተለ የሚግታችሁ መሣሪያ በኪሣችሁ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ጥሬ እና የማይረባ መረጃ የታጨቀባቸውን የሀገራችን ኤፍ ኤም ሬዲዮኖች መስማት የሰለቸው አንድ ታዋቂ ፀሃፊ “ኤፍኤሞቻችንን መልሱልን!” ብሎ የፃፈው ለምን እንደሆነ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ በቅርቡ የፓርላማችን ቋሚ ኮሚቴም “አደገኛ” እና “ባህል በራዥ” የሆኑ ፕሮግራሞችን የሚያስተላልፉ ኤፍ ኤፍ ጣቢያዎች መኖራቸውን እንደደረሰበት መግለፁ የሚታወስ ነው፡፡

በእኛ ዘመን ባዕድ ኃሣቦች የሚወርዱት ከላይ ወደ ታች ነበር፡፡ ከመንግስት ወደ ዜጐች ማለቴ ነው፡፡ በእናንተ ዘመን ግን የጐንዮሽ (horizontal) መልክም ይዟል፡፡ እንዲያውም የከፋው ይኸው ነው፡፡ በጐንዮሽ በኩል የሚመጣውን አንቅሮ ለመትፋት የሚያስችላችሁ ሙሉ ነፃነት ግን በእጃችሁ ነው፡፡ ወደ ተግባር ለመቀየር ግን ብዙ ኃላፊነት ያለባቸው ተቋማት መኖራቸው አይካድም፡፡

ያደግንበትንና ትዝታው ከህሊናችን ሊፋቅ የማይችለውን ቀያችንን በኃይል በመሣሪያ እየታገዘ ሲፈርስና ወደ አንድ መንደር ስንኮለኮል የተማርነው ሁሉ ዋጋ ቢስ መሆኑን ተረድተነዋል፡፡ ቢያንስ ወላጆቻችን የዚያን ድርጊት ምክንያታዊነት ሲጠይቁን ለመግለፅ አለመቻላችን በወቅቱ የነበረውን የ“ችኮላ” ዘመን ያስታውሰናል፡፡

በወቅቱ ከስድስተኛ ወይንም ከስምንተኛ ክፍል በኋላ ትምህርት ለመቀጠል ወደ ሩቅ ከተማዎች ሄዶ ዘመድ ጋ መማርን ይጠይቅ ነበር፡፡ በወቅቱ “ኮብልስቶን” የማንጠፍ ቴክኖሎጂ ባለመታወቁ በርካታ ብሩህ አዕምሮ የነበራቸው ተማሪዎች ወደ አባቶቻቸው ግብርና ተመለሱ፡፡ እኔ የተማርርኩባት ትንሿና በደቡብ ጐንደር የምትገኘው ሽሜ ማርያም ትምህርት ቤት ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃን መክፈት የቻለችው እኛ ከወጣን ከሃያ ዓመታት በኋላ ነው፡፡

ከእኔ ጋር ለሥምንት አመታት ከገጠር ተመላልሰው የተማሩት መንግስቱና ጌትነት፤ ገበሬ ሆነው በአሁኑ ጊዜ የገጠር ቀበሌያችን ሊቀመናብርት ሆነው ሲሰሩ አገኘኋቸው፡፡ እስከ ስምንተኛ ድረስ የተማሩት ትምህርት እንኳ የአኗኗር ዘይቤያቸውን እንዳልቀየረው እርግጠኛ ነኝ፡፡ እስካሁንም በዚህ ደረጃ ላይ የምንማረው ትምህርት ካልተማሩ ገበሬዎች በምን እንደሚለየን ለማወቅ ያስቸግራል፡፡ በዚያን ወቅት እነዚህ ሁለት ወጣቶችንና ሌሎች ጓደኞቼንም የሚያጋጥማቸው ሌላ ችግርም ነበር፡፡ ከትምህርት ቤት ሲመለሱ በሸለቆ ውስጥ ተደብቀው የቆዩ እጩ ወታደር መልማይ ሚሊሻዎችና ሊቀመንበሮች በድንገት ያሳድዷቸዋል፡፡ የግዳጅ ወታደር ምልመላ ባልተጠበቀ ጊዜ የሚከሰትና በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዲሰወሩ የሚያደርግ ድርጊት ነበር፡፡ በእርግጥ ከበላይ አካል የእጩ ምልምል ኮታ የተጣለባቸው ካድሬዎችና ሚሊሻዎች በትምህርት ቤታችን ቅጥር ግቢ ገብተው ተማሪዎችን ለመያዝ አይደፍሩም ነበር፡፡  ይህንን አስከፊ ትዕይንት የቀመሱት መንግስቱና ጌትነት አሁን የአካባቢያችንን ገበሬዎች በምን ሁኔታ እያስተዳደሯቸው ይሆን? የቀበሌ ገበሬ ማህበር ስብሰባ ላይ በተደጋጋሚ ቀርታችኋል ብለው ማዳበሪያ እንዳይገዙ ይከለክሏቸው ይሆን?

የሶሻሊዝምን ሥርዓት ሣነሣ አንድ ገጠመኝ ትዝ አለኝ፡፡ በ1970ዎቹ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሣለሁ የክፍል ሥም ጠሪያችንና የህብረተሰብ መምህራችን ጋሽ ገበየሁ ለክፍላችን በር መቆለፊያ የሚሆን “ጓጉንቸር” ቁልፍ ለመግዛት በነፍስ ወከፍ ሃምሣ ሣንቲም እንድናዋጣ አዘዙን፡፡ በዚያን ወቅት ወላጆቻችንን ሣንቲም ስጡን ብሎ መጠየቅ ያስፈራን ነበር፡፡ እንደ ነውርም እናየው ነበር፡፡ በመሆኑም የተባለውን መዋጮ በተባለው ወቅት ሳልይዝ ሄድኩ፡፡ ጋሽ ገበየሁ የተባለውን ሣንቲም ለምን እንዳላመጣሁ ሲጠይቁኝና ተማሪዎች ፊታቸውን ወደኔ ሲያዞሩ ክው ብዬ ቀረሁ፡፡ የትምህርት ሥርዓቱ ተማሪዎች ከሚገባው በላይ ዓይን አፋር እንዲሆኑ የሚያደርግ እንደነበር አቶ አንተነህ ቀደም ሲል የገለፀውም እውነት ነው፡፡ ይህ የራሱን ሌላ ችግር ማስከተሉ አልቀረም፡፡ ጋሽ ገበየሁ ቀጠል አድርገው “አንተ ሃምሣ ሣንቲም ካጣህማ ኢትዮጵያ ነጠፈች ማለት ነው” ብለው ተናገሩ፡፡ በትምህርት ቤት ታሪኬ ክብረ-ወሰን የሰበረ እንባ አነባሁ፡፡ እጅግ የምወደው የህብረተሰብ ትምህርት እስኪጠናቀቅ ድረስ መራር ለቅሶ አለቀስኩ፡፡ የአሁኑ ዘመን ተማሪዎች ለምን ብላችሁ መጠየቃችሁ አይቀርም፡፡ ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ በተማርኩት ትምህርት መሠረት ድህነት በነገሰባት፣ ወዛደሩ በገነነባትና የግል ሃብት እንደ “ጭራቅ” በሚታይባት ህብረተሰባዊት ኢትዮጵያ የገጠር “ከበርቴ” እና የ”አድሃሪ” ልጅ መሆኔ ሲነገረኝ እንዴ አላለቅስ?

በጊዜው የተወሰኑ ተማሪዎችን በዚህ መንገድ ማሸማቀቅ የተለመደ ቢሆንም የሀዘኔ ምክንያት ግን የእኔ አምሣ ሣንቲም ማጣት ለምወዳት ሀገሬ ካዝና መራቆት ምክንያት የሆነ ስለመሰለኝ ነበር፡፡ ጋሽ ገበየሁ ሆይ! ያን ጊዜ መዋጮውን እንድናዋጣ የጠየቁን ተማሪዎች እኮ ብዛታችን ሃምሣ ሁለት ነበር፡፡ ከእነ ጋሽ ይብሬ ሱቅ ግን የአንድ “ጓጉንቸር” ቁልፍ ዋጋ ሁለት ብር ከሃምሣ ሣንቲም እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ መቼም የአሁኑ ዘመን ተማሪዎች በዚያ ዘመንም ሙስና የሚባል በሽታ ነበር እንዴ ብላችሁ ማሰባችሁ አይቀርም፡፡ እኔ ግን በአይኔ ባላይም ትርፉ ሣንቲም ወደ ትምህርት ቤታችን ካዝና እንደገባ ያኔም አሁንም አልጠራጠርም፡፡ የሙስና ነገር ከተነሣ አይቀር ግን ሌላ ገጠመኞች ነበሩን፡፡ በከተማዋ ለሚገኙ ባለሀብቶች ከገጠር ለማገዶ የሚሆን የባህር ዛፍ ፍልጥ እየተሸከምን እናመላልስ የነበረበት ሁኔታ አይረሳኝም፡፡ ከገጠር የተገዛውን ፍልጥ ከሰዓት በኋላ ትምህርት ተዘግቶ እንድንሸከም ይደረጋል፡፡

የምንወስደው ደግሞ አስተማሪዎቻችን በየወሩ እየከፈሉ ለሚቀለቡበት ምግብ ቤት ባለቤት ለሆኑት ወይዘሮ ነው፡፡ ደረቅ ሣርም ቢሆን ከተገዛበት ቦታ ተሸክመን ለጋሽ ይብሬ እናደርስ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ጋሽ ይብሬ የትምህርት ቤታችንን ሣር ከመግዛት አልፈው የመምህራን ደመወዝ ቢዘገይ እንኳ ሣሙና፣ ለኩራዝ ማብሪያ የሚሆን ላምባ (Kerosene) ለማበደር የሚነፍጉ አልነበሩም፡፡ በመሆኑም ትምህርታችንን ትተን የእነሱን ሥራ እንሰራላቸዋለን፡፡ እነዚህ ድርጊቶች ሙስና መሆናቸው ተገልጦልን ነው መሠለኝ በወቅቱ ብዙዎቻችን ማጉረምረማችን አልቀረም፡፡ ከእኔ ቀደም ብሎ በጉዳዩ ላይ የፃፈው አቶ አንተነህ እንደ “ግዴታ” እና “ጉልበት ብዝበዛ” አድርጐ ካስቀመጣቸው ነገሮች ይልቅ ይኸኛው ለጉዳዩ የሚቀርብ ነው፡፡ ቸር ሰንብቱ፡፡

 

 

Read 1947 times Last modified on Saturday, 04 August 2012 10:10