Tuesday, 13 October 2020 14:58

የፍቅር ፀዳሎች

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(5 votes)

 የመስከረም ፀሐይ የዝናቡን ሃይል አሸንፎ ሲወጣ፣ ውበቱም ስሜቱም ደስ ይላል፡፡ ከአዲስነቱ ስሜት ከተስፋው ርችት ጋር ተያይዞ ሁሉ ነገር ይቆነጃል፡፡ ሰማዩ ብሩህ፣ ምድሩ ዐደይ አበባ መስሎ ሲታይ፣ ነፍስን የሚነሽጣት አንዳች ተፈጥሯዊ ሃይል አለ፡፡ ትዝታም ናፍቆትም ደስታም ሰቀቀንም ተቃቅፈው የሚሰነብቱባት ወር ናት፡፡ የትናንቱን አዝላ፣ የነገውን በጡቶችዋ ሥር አንጠልጥላ የምትታይ ነፍሰጡር ነገር ትመስላለች፡፡
ሰሞኑን የሥራ ፍላጐቴ ተነቃቅቷል። የቢሮ ሥራዬን ጨርሼ ስመለስ፣ “ራይድ” የምሠራባትን ኮሮላ ይዤ እከንፋለሁ፡፡ ጉርድ ሾላ ከሚገኘው ቢሮዬ ወጥቼ፣ መኖሪያ ሠፈሬ ጀሞ ሁለት እስኪደርስ ከራይድ ቢሮ ስልክ ተደውሎልኝ ያገኘሁትን ሸቃቅዬ ቤቴ እገባለሁ፡፡
ጉድለቴ አንድ ብቻ ነው፡፡ ሚስቴ አብራኝ እንድትኖር እፈልጋለሁ፡ አንድ ልጄ ከአጠገቤ መጥፋቱ ያንገበግበኛል፡፡ ዘመኑ በፈጠረው ቴክኖሎጂ ሁሉ ብንገናኝም፣ በዓይነ ሥጋ ተገናኝቶ፣ አንድ ላይ እንደ መኖር ያለ ፈንጠዝያ የለም፡፡ እርሷ ግን ገንዘቡ ጥሟታል፣ ዶላሩ አጓጉቷታል፡፡ እኔ ባለችን ተደሰተን እንኑር! ባይ ነኝ፡፡ ጀሞ ሁለት ባለሦስት መኝታ ኮንዶሚኒየም ከደረሰኝ ቆየ፡፡ ደሞዝ አለኝ፣ መኪናም ገዝቻለሁ። መኪና የገዛሁት በደሞዜ አይደለም፣ ወላጆቼ ያወረሱኝን ቤት ሸጠን ከወንድሞቼ ጋር ተካፍዬ በደረሰኝ ገንዘብ ነው፡፡ እርሷ ግን ቤት ሰርተን… የሆነ ካምፓኒ ከፍተን ትላለች፡፡ እኔ ልጄ አጠገቤ ሆኖ እየመከርኩ እያስጠናሁ ባሳድገው፣ ፍቅሬን ጠግቦ ቢኖር ጉጉቴ ነው፡፡ ሊዲያ ግን ችክ አለች፡፡ መቼም ቅንነቷ እንጂ የሃይሏ ነገር መላ ነው፡፡
በዚያ ላይ ዕድሜያችን እየገፋ እንደሆነ ለምን እንደማታስብ ይገርመኛል፡፡ ከተማሪነት ሴት ጓደኛዬ ቀጥሎ ሦስተኛዋ ናት፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦሎጂ ትምህርት ክፍል ተማሪ እያለሁ፣ ሠፈራቸው ዘመድ ጥየቃ ስሄድ፣ እርሷ ሱቅ ውስጥ ቆማ ሳያት ተማርኬ ነበር ያፈቀርኳት፡፡ ዐይኖቿ ያስደነግጣሉ፤ ዛጐል የመሰሉ ሆነው ሲንከባለሉ፣ ዙሪያቸውን በጥቁር የተኳሉ ናቸው፡፡ ወጥመድ ሆኑብኝ፡፡
ተጋብተን ግን በትዳር አልኖርንም፡፡ አንድ ቀን አንሶላ ተጋፍፈን ልጃችን ተፀነሰ፡፡ እኔም ተመርቄ ወጣሁና ሥራ ያዝኩ፡፡ ልጁን ካላስወረድኩት ብላ ጮኸች፡፡ ለመንኳት፡፡ “አብረን እንኖራለን” ብዬ የኔ ደሞዝ ለጊዜው እንደሚበቃን ብነግራት “ሞቼ እገኛለሁ” ብላ በየሀኪሙ ቤት ተንከራተተች፡፡ ለጉዱ ልጁ እምቢ አለና ተወለደ፡፡ “ጥገኛ ሴት መሆን አልፈልግም” ስትለኝ “የኔ ያንቺ ነው፤ ተጋብተን መማር ትችያለሽ” ምክሬን አልሰማችም፡፡ ብቻ በሆነ ተዓምር ልጁ ተወለደ፡፡ ከዚያ ልጁን አስቀምጣ ጂዳ ወዳለው ወንድሟ ጋ ሄደች፤ ሰምቼ አዘንኩ። ጭራሽ እንደ ባዳ ሸሸችኝ፡፡ እንጋባ ይለኛል ብላ እንደሆነ ገባኝ፡፡ እርሷን ባሪያ ለማድረግና እኔ ገዢ ሆኜ ለመኮፈስ ያሰብኩ ሳይመስላት አልቀረም፡፡ በርግጥ አልተረዳችኝም። ዓመታት ቆይታ ስትመጣ ደውላልኝ ተገናኘን፡፡ ሳያት ብዙ ተስማምቷታል፡፡ ደስ አለኝ፡፡ ልጃችንን ይዘን ብዙ ነገር አወጋን። ጥሩ ጊዜ ካሳለፍን በኋላ ወደ አሜሪካ ልትሄድ እንደሆነ ነገረችኝ። ደስ አለኝ፡፡ የልቧ ምኞት እንዲሠምር ይሁን ብዬ ተቀበልኩ። ልዩነታችን እኔ ከኢትዮጵያ ውጭ መኖር የማልፈልግ መሆኔ ነው፡፡ “አሜሪካ ገብቼ ዛፍ ልሁን” የሚሉ ህልመኞችን ባየችበት ዐይን፣ የኔ ፈጽሞ ዝግ መሆን እየገረማት ተለያየን፡፡ ናፍቆቷና ትዝታዋ እስካሁን ያምሰኛል፡፡ ይህ ዓመት ግን የምንገናኝበትና በቬሎ የምንታይበት እየመሰለኝ ነው፡፡ ልጃችንን ሻማ ያዥ አድርገን መናፈሻ ውስጥ በወዳጆቻችን ፊት ሽር ብትን ማለታችን አይቀርም!...
ከፀሐይዋ ውበት ከሰማይ ፍካት ጋር ተያይዞ ልቤን ናፍቆት ጠበቅ አድርጐ ሳማት -  ትዝታ ከንፈሮቼን ነከሳቸው፡፡ ዝምታ የመኪናዬን ቁልፎች ጨበጠ፡፡ ሳላስበው አፏጨሁ!
የተለያዩ ድምፃውያን ዜማ በጆሮዬም በልቤም ተንቆረቆረ፡፡ በተለይ እሷ ታዜማቸው የነበሩ ሙዚቃዎች፡፡ እኔ ግን…
ተስለሻል እንዴ ከዐይኔ ከመሀሉ
አንቺ ብቻኮ ነሽ የሚታየኝ ሁሉ
…ይላል ውስጤ፡፡
መስከረም ቀድሞም ሆዴን ያባባዋል። እንቁጣጣሽ ሲደርስ በዋዜማው ጳጉሜን ሳምጥ መክረም ልማዴ ነው፡፡ የትውልድ መንደሬ ትዝታ ከጓደኞቼ ጋር ያሳለፍኳቸው የችቦ ለቀማ ጊዜያት፣ የሆያሆዬው… የሠፈራችን ልጃገረዶች አስረቅራቂ ድምፆች… እቴ አበባሽ እቴ አበባዬ ሲሉ፣ እኛ ስንከተላቸው፤ ችቦ ሲለኮስ አባቶች ሲመርቁ፣ እናቶች የጥበብ ቀሚሳቸውን ለብሰው ቄጠማ ተጐዝጉዞ ሙሽራ መስለው ወዲያ ወዲያ ሲሉ… ውስጤ በትዝታ ጅራፍ ይዠለጣል፡፡ የሚያም ጅራፍ! የሚጣፍጥ ግርፊያ!
መስከረም ሳቂ፣ መስከረም ልቅሶ ነው፡፡ ሁለቱ ተቃቅፈው ልቤ ጀርባ ላይ ይደንሳሉ። ዐይኖቼ እንባ ተሸክመው፣ የሰማይ ምድሩን የውበት ሥዕል ያንከባልሉታል… ሆያ ሆዬ!
መኪናዬ ከቤት ይዤ ወጣሁ፡፡ ስልሳ ሰባት ማዞሪያ ጋ መንገድ ተዘጋግቶ ስለነበር ቀኙን ታጥፌ በለቡ በኩል በመብራት ሃይል፣ ወደ ጀርመን አደባባይ ለመውጣት መስመሬ ውስጥ ገባሁ፡፡ ገና ብራይት ሆኜ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅን እንዳለፍኩ ከራይድ ስልክ ተደወለ፡፡
መልዕክት ተቀበልኩና በተሰጠኝ ስልክ ደወልኩ፡፡ ደስ የሚል ዜማ ያለው ድምጽ ነው፡፡
“የት አካባቢ ነዎት?” አልኩ፡፡
“ሴፍ ዌይ ሱፐር ማርኬት ፊት ለፊት”
ነዳሁት፡፡
የጠበኳት ዓይነት ሴት አይደለችም። ሙሉ ለሙሉ የሙስሊሙን አለባበስ ሥርዓት ጠብቃ ራሷን ሸፍናለች፡፡ በሩን ከፍታ ገባች፡፡ ወደ ቦሌ መሄድ ፈልጋለች። ሽቶዋ የመኪናዋን ሁለንተና አጠመቀው። በመስከረም አበባ ውስጥ የዚህ ዓይነት ሽቶ ሲርከፈከፍ፣ ሁለንተናን በተስፋ ቀለም ይነክራል፤ በደስታ ዘይት ይቀባል፡፡
“ሸገር 102.1 ላይ ብታደርገው ደስ ይለኛል…”
በጣም እየተገረምኩ “ይቻላል… ደንበኛ ንጉሥ ነው” አልኳት፡፡
ደስ የሚል ሳቅ ሳቀች፡፡
“ብዙ ቁም ነገሮች የሰማሁበት ሬዲዮ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከመጣሁ በኋላ የመረጥኩት ጣቢያ ነው፡፡ በርግጥ ሌሎችም ይኖራሉ፡፡ ግን ሸገር ካፌ ምናምን ደስ ይለኛል…፡፡
 “እርሱ ሁልጊዜ አይኖርም!” አልኳት፡፡
“ኦኬ! ሌሎቹም ጥሩ ናቸው፡፡”
“የአንተንም ድምጽ የሆነ ቦታ የማውቀው ወይም የሰማሁት ይመስለኛል፡፡ ምናልባት ሬዲዮ ላይ ሠርተህ ነበር እንዴ?” ጠየቀችኝ፡፡
“በፍፁም! ጂኦሎጂስት ነኝ!”
“ደስ ይላል! ጂኦሎጂስት… ታዲያ አዲስ አበባ ምን ይሠራል? ፊልድ አይሄድም”
“እዚህ ጉርድ ሾላ ዋና ቢሮ ውስጥ ነው የምሠራው! እዚህም አንዳንድ የሚሠሩ ሥራዎች አሉ፡፡”
“ይቅርታ ለጨዋታው ነው!”
እየነዳሁ እያለ “…የት ሀገር ኖረሃል?” ስትል ጠየቀችኝ፡፡
“ከኢትዮጵያ ውጭ?”
“ኖ ኖ እዚህ ኢትዮጵያ!”
“ሃዋሳና ደሴ”
“ደሴ ኖረሃል?...የት ሠፈር?”
“ወደ ቧምቧ ውሃ መውረጃ፣ በሆጤ በኩል ሳይሆን በፔፕሲ በኩል ስትሄጂ… ቀኙን ከኩታ በር መታጠፊያ ወረድ ብሎ፡፡”
“ማነው ስምህ?”
“እርስቱ ቦጋለ!”
“ኡኡኡኡኡ….”
ደንግጬ ፍሬኑን ያዝኩት፡፡
“I cant believe!...ሶፍያ ዐሊን አታውቃትም?”
ፊቷን ስትገልጠው ትንሽ አሻራ ቀርቷል፡፡ ጠይም፣ ደመ ግቡ፣ ፀባየ መልካም ልጅ፡፡ ያኔ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነበረች - ፍቅረኛዬ!
ተለቃቀስን፡፡
“እናቴም ሞተች፤ አባቴም ሞተ፡፡ ከዚያ ወደ ፈጣሪ ልጠጋ ብዬ ብቻዬን እኖራለሁ፡፡”
“አንተስ?” አለች ወዲያው፡፡
“እኔም ለብቻ ከመኖር የተለየ ሕይወት የለኝም!”
ተቃቅፈን፣ ተለቃቀስን፡፡
“ምነው ታዲያ ሳትፈልጊኝ!”
“ላገኝህ ያላደረግሁት ጥረት የለም፡፡ አዲስ አበባ ግን ውቅያኖስ ናት፡፡ ተስፋ ቆርጬ ተውኩት!”
“አሁን የት ነሽ?”
“ወደ ለንደን ልበርር ነው!...እመለስና እንገናኛለን!”
“ደስ ይለኛል!”
“ኢንሻ አላህ!”
የዛሬዋ ፀሐይ ናፍቆትና ትዝታዋ አሠከረኝ፡፡ እስከ አውሮፕላኑ ድረስ ሸኘኋት። እጅዋን አውለበለበች፡፡ በሩቁ ተለየኋት፡፡ ሁለቴ መለየት፡፡
“አግብተሃል?”
መልስ አልሰጠኋትም ነበር፡፡  


Read 2154 times