Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 04 August 2012 09:51

“ተንኮለኛ ገደል ዝንጀሮ ይጥላል…”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

እኔ የምለው…ብርዱ አልበዛባችሁም! እንደ ድሮ (‘ጉድ ኦልድ ዴይስ’ እንደማለት) እስቲ አንድ ኪሎ ሻኛ ለሁለት እንቃመስና እንከላከለው ምናምን እንል ነበር፡፡  (በብዙ ነገሮች ‘ነበር’ የሚለው ቃል አልበዛባችሁም!) እናላችሁ የእነ ቁርጥ ነገር ቁርጥ ሆኖ ተለያይተናል፡፡ ሌላ ‘ብርድ መከላከያ’ መፈለግ ነው፡፡ እሱም አሁን መደብ ለይቷል፡፡ስማ ወዳጄ… እንግዲህ ብርድ ለመከላከል የቀረህ ነገር …ያው ለምታውቀው እሱ ላይ ‘በርታልኝማ!’ የወንዶችና የሴቶች ቁጥር መሳ ለመሳ ሳታደርግማ…እንዴት ይሆናል፡፡ ስማኝማ…ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ አይነት የአባት ስም ያላቸው (የእናት አላልኩም!) ሁለት የወንዶችም የሴቶችም ታዳጊ መረብ ኳስ ቡድኖች ሊኖሩህ ይችላሉ ብዬ እንደምጠረጥር ነግሬህ አውቃለሁ? እንግዳውማ ይኸው ነገርኩህ፡፡
ስሙኝማ…ከኮምፒዩተር ነገሮች ሁሉ አንዱ አሪፉ ምን መሰላችሁ…የማይሆን ፋይል ምናምን ሲጫን ‘ቫይረስ ተገኝቷል’ ብሎ “እሪ!” የሚለው ነገር፡፡ ሀሳብ…አለን፣ ‘ቦሶች’ ምናምን ሊቀመጡባቸው የሚዘጋጁ ወንበሮች ላይ አንቲ ቫይረስ ይገጠምልን፡፡ አጅሬ ቁጭ ሲል ኮምፒዩተር ሆዬ እሪታውን ዳር እስከ ዳር ያስነካዋላ! (ያኔ የሚጮኸው ወንበር ከመብዛቱ የተነሳ በድምጽ ብክለት ቦነስ አይረስን አልፈን ቁጭ ነው የምንለው!)
እናላችሁ…‘በዓይናችን በብረቱ ስር’ ብዙ ነገር እየተበላሸ ነው፡፡
ልክ ነዋ…አንዴ ከተቀመጠ በኋላ ጂ ፕላስ ምናምኑን፣ ሌክሰሱን፣ ሰባት የ‘ዋይፍ’ ምትኮችን ምናምን ካከማቸ በኋላ “እኛ እኮ አላወቅንም ነበር” ምናምን ቀሺም ነው፡፡
እኔ የምለው… አገር ሁሉ በየቢሮው እንደተቀመጠ የዓመት እረፍት ወስዷል እንዴ! አሀ…ግራ ገባና! አንድ ሰሞን ሀያ ቀን ነገር ይወስድብን የነበረው ነገር ሁሉ በአምስት ደቂቃ እያለቀልን አሁን ገና ሥራ ተሠራ ምናምን ስንል ከርመን ጭራሽ ብሶ ቁጭ ይበል! አንዳንዴ ሳስበው ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…አንድ ጊዜ አካፋውን ተደግፈን እንዳንቆም መሀል፣ መሀሉ ላይ ቆረጡብን ተብሎ የሚወራላቸው ቻይኖቹ አሉ እንደተባለው ሁላችንም የየራሳችንን ሌላ አገር አመቻችተን ይቺኛዋን “እንደ ፍጥርጥሯ!” ያልን ነው የሚመስለኝ፡፡
እናላችሁ…‘በዓይናችን በብረቱ ስር’ ብዙ ነገር እየተበላሸ ነው፡፡
ነገር ሁሉ ደነዘዘብና! የየቢሮው ሥራ የደነዘዘ፣ ንግዱ የደነዘዘ፣ ወዳጅነት የደነዘዘ፣ እኛ የደነዘዝን…ብቻ ምን አለፋችሁ…ግርም የሚል ነገር ሆኖብናል፡፡
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ፣ አንድ በወረዳ ደረጃ ያለ ግብር ሰብሳቢ ቢሮ ሰሞኑን ያየኋት ነገር ነች፡፡ ከሰብሳቢዎቹ በስተጀርባ ከማንኛውም የአማርኛ ማስታወቂያ ጉልህ ሆኖ በላቲን ፊደላት ‘ዘ ወርልድ ኢዝ ቼንጂንግ…’ The world is changing…) ምናምን ተብሎ ተጽፎ ከስር ያለው ምን መሰላችሁ… ግብር ክፈሉ ምናምን የሚል ነገር፡፡ ግራ የገባኝ አንደኛ ነገር በአማርኛ የተጻፉት አንስው የእንግሊዝኛ የጎላው ምክንያቱ ምንድነው…ነው፣ ወይስ እዛ ቤት ሰሞኑን ግራጁኤት ያደረገ ‘የፈረንጅ አፍ አዋቂ’ ገብቷል!  እኔ የምለው…እንዲህ መላ ቅጣችን ይጠፋል እንዴ! በጣም የሚገርመው ነገር በዛ ሰዓት በአካባቢው የነበሩት አብዛኞቹ በዕድሜ የገፉ ጉስቁል ሴቶች… አይደለም እንግሊዝኛውን አማርኛውን በሚገባ ለማንበብ የሚቸገሩ ነበሩ፡፡
ይሄ አሁን፣ አሁን ‘የፈረንጅ አፍ’ እንደ ‘ፍርፍር ቃሪያ’ ቁጭ ቁጭ (ቂ…ቂ…ቂ…) ማድረግ መንግሥታዊ በምንላቸው ተቋሟት በርከት ማለቱ ያደናግራል፡፡ አንድ የከተማችን አካባቢ በኮንቴይነር የተሠራች እንደ ፖሊስ ጣቢያ የምታገለግል ነገር አለች…እናላችሁ የወረዳው ስም ከፊት ተጽፎ በኋላ …“ፖሊስ ስቴሽን” ተብሎ በአማርኛ ፊደላት ተጽፎላችኋል፡፡ እኔ የምለው…‘ስቴሽን’ ማለት… ልክ ባለከረባት ማኪያቶ ምናምን ነው እንዴ! በቃ…በ‘ውሃ ላይ ዘይት’ አይነት ‘የፈረንጅ አፍ’ አይገባንማ!
ታዲያላችሁ…‘በዓይናችን በብረቱ ስር’ ብዙ ነገር እየተበላሸ ነው፡፡
እናላችሁ… አስቸጋሪ ነገር ነው…“ኮንፊዴንሻል ነኝ…”  “ሬስፔክሽን አለኝ…” “ዋይኔ ሩኒ…” “የኒውዘርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር…” ምናምን አልበቃ ብለውን ጭራሽ  “ዘ ወርድል ኢዝ ቼንጂንግ” ወረዳ ገበታ ቁጭ አለች! እንዴ…የምር ማስታወቂያውን መጀመሪያ ስታዩት እኮ የሆነ የአዲስ ፊልም ‘መፈክር’ ምናምን ቢመስላችሁ ከኃጢአት አይቆጠርባችሁም፡፡  (በነገራችን ላይ…በፊልም ኢንዱስትሪው “ሀይ ኮንሴፕት”፣ “ቲም” ምናምን ሳይሆኑ ዘንድሮ በየፊልሙ ፖስተር የምናያቸው “ኢምፔሪያሊዝም ይውደም” አይነት መፈክሮች ናቸው፡፡ ጨረስኩ፡፡)
እናማ…ነገሩ ሁሉ ሲለዋወጥ፣ ያስቀመጡት ሰው ቦታው ሳይገኝ፣ “ለእራት ይተርፋል…” ያሉትን ለምሳ እንኳን ማብቃቃት ሲቸግር የሆነ የተበላሸ ‘ቸርኬ’ ምናምን አለ ማለት ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
ሀሳብ አለን…“የደወሉላቸውን ደንበኛ አሁን ማግኘት አይችሉም” የሚለው መልእክት ላይ ተጨማሪ እንዲሆን የምንፈልገው አለን…“ደግመው ባያገኟቸውም ይመረጣል” ምናምን የሚባል ነገር ይጨመርልንማ፡፡
እናማ ዘንድሮ…‘ሰዉ ሁሉ ሄዶ መለስ’ ሲል ምን አይነት ጡንዥት ምናምን እንደሚያጨሱበት እንጃ…ሙሉ ለሙሉ ተለውጦ ይመጣል፡፡ እየተለወጠብን ተቸግረናል፡፡ ወይም ደግሞ ስልኩ ሲያዝ “የደወሉላቸው ደንበኛ መስመሩን እርሶን እያሙበት ነው…” ይባልልን፡፡ እንትናዬ…በቃ ታምተን ‘አጨብጭበን’ መቅረታችን ነው!
እግረ መንገዴን…የሀበሻ ሀገር እንዲሀ ‘እንዳሁኑ ባልሰለጠነበት’ ዘመን (“ይሉሽን በሰማሽ የሚለውን ተረት ‘ታሪካዊ ጠላቶቻችን’ እንኳንም አላወቁት!) ያሙናል ማለት ልክ እንደ ዘንድሮ ቮድካ በኦሬንጅና የእንትና ቤት ክትፎ ‘ካዝና መክፈቻ’ ቁልፍ በሉት፡፡ (አንዳንድ ነገሮች ‘ቅኔ ያስመስልብኝ ይሆን!’ የሚል ቆዳ ግልባጭ አበዛሁሳ…!)
እናም…የተበላሹ ነገሮች እየበዙ ነው፡፡ ገና ሎሊፖፕ ምናምን መጥጦ ያልበቃው ታዳጊ ቪያግራ ላይ ‘ተግባራዊ ምርምር’ ሲያደርግ…አለ አይደል… “ዳግም ሰዶምና ገሞራህ መጣ እንዴ” ብሎ ከማዳነቅ የተበላሸውን ማቃናቱ ሳይሻል አይቀርም፡፡
እናላችሁ…የታዳጊዎቹ ባህሪይ የምር ሊያሳስበን ይገባል፡፡ የአዲስ አበባን መሀል ከተማ መንገዶች የሞሉት ህፃናት ልጆች በተለይ ሴቶች ሳንቲም ቢጤ ካልሰጧቸው የሚሳደቡት ስድብ ዘግናኝ ነው፡፡ “ምን አይነት ትውልድ እየተፈጠረ ነው!” ብለው የሚሰጉ ሰዎች የምርም ጭንቀታቸው ‘የባዶ ሜዳ ማካበድ’ አይደለም፡፡ ችግሩ ምን መሰላችሁ… የሆነችውን ሰላማዊ መንገደኛ ህጻናቱ ከፍ ዝቅ አድርገው ሲሰድቧት የተቀረነው ማስታወቂያ ያልተደረገበት ‘ሮማንቲክ ኮሜዲ’ ቆመን የምናይ ነው የሚመስለን፡፡ (‘ሮማንቲክ ኮሜዲ’ ያልኩት ከእንደዛ አይነት ፊልም በስተቀር ሌላ እንዳይሠራ የሚከለክል ‘ኢን-ሀውስ ሰርኩላር’ ምናምን ይኖራል የሚል ጥርጣሬ ስላለኝ ነው፡፡)
እኔ የምለው…ሰሞኑን ኮብልስቶን እንኳን መነጋገሪያ ሆና ሰነበተችሳ! በነገራችን ላይ… ዲግሪያቸውን ይዘው ኮብል ስቶን የሚሠሩትን ልጆች ማድነቅ ያስፈልጋል፡፡ ምንም እንኳን እንዲህ የሚሆኑት እንደ ‘መጨረሻ አማራጭ’ እየተወሰደ ቢሆንም፡፡ ነገር ግን… ቦሶች ሲፎክሩበት ስንሰማ “ኧረ ወዴት እየተሄደ ነው!” ያሰኛል፡፡ የወጣትነታቸውን አብዛኛውን ክፍል በትምህርት አሳልፈው፣ ቤተሰቦቻቸው አንጀታቸውን አስረው ካስተማሯቸው በኋላ “ትምህርታችንን በተግባር የምናውልበትና ራሳችንን የምንለውጥበት ጊዜ ላይ ደረስን” አይነት ስሜት ሊያድርባቸው ሲገባ “ግፋ ቢል ኮብልስቶን ነው…” አይነት ሀሳብ እንዲጫናቸው ሲገፋፉ አሪፍ አይደለም፡፡
እናላችሁ…‘በዓይናችን በብረቱ ስር’ ብዙ ነገር እየተበላሸ ነው፡፡ “ተማርከ አልተማርክ ጋዋን ከመልበስ በስተቀር ምን ታመጣለህ!” አይነት መንፈስ ሲሰፍን…አለ አይደል…ቀሺም ነው፡ አሁንም የሆነ ሰው “ኮሌጅ እኮ በጠሰ!” ምናምን ሲባል “ግፋ ቢል ኮብልስቶን መጥረብ ነው፣ ሌላ ምን የሚያመጣ መሰለህ!” አይነት ነገር እንዳይለምድብን ፍሩልኝማ፡፡እናላችሁ…‘በዓይናችን በብረቱ ስር’ ብዙ ነገር እየተበላሸ ነው፡፡የምንናገረው አርባ ቦታ እየተመተረ፣ ከሳቃችን ጀርባ ድብቅ ትርጉም እየተፈለገ…ቆም እያልን ስናወራ ከባቢ ‘ጸጉረ ልውጥ’ እየበዛ…ምን አይነት የጠለቀ አስተሳሰብ እንዳለን ሳይሆን ወዳጃቾቻችንና ‘ጎድፋዘራችን’ እነማን እንደሆኑ እየታየ ‘የምናገኝ የምናጣበት’… አይነት ነገር እየተለመደ ሲሄድ አሪፍ አይደለም፡፡ስሙኝማ…የኮሌጅ መበጠስ ምናምን ነገር ስናወራ የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ…ድሮ ምን ይባል ነበር አሉ መሰላችሁ፡፡
ቢሆንም ይሆናል ባይሆንም አይሆንም
ቢማር ቄስ ነው እንጂ ሰው መላክ አይሆንም..
እናላችሁ…‘በዓይናችን በብረቱ ስር’ ብዙ ነገር እየተበላሸ ነው፡፡
ዘመኑ ራሱ “ተንኮለኛ ገደል ዝንጀሮ ይጥላል በሬ ያሳልፋል…” እየሆነብን ተቸግረናል፡፡
ሁሉንም ወደ በጎ ይመልስልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

 

Read 1920 times Last modified on Saturday, 04 August 2012 10:09