Saturday, 10 October 2020 16:10

የሥነ ጥበብ ቴራፒና የአዕምሮ ጤንነት

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

  ሰዓሊያን ‹‹የዓለም የአዕምሮ ጤና ቀን"ን በአማኑኤል ሆስፒታል ያከብራሉ
                     
             ዛሬ በመላው በዓለም የሚከበረውን ‹‹የዓለም የአዕምሮ ጤና ቀን››  ምክንያት በማድረግ ታዋቂ ሰዓሊዎች የተሰባሰቡበት ቡድን፤ በአማኑኤል የአዕምሮ ጤና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ግድግዳዎችን በቀለማት የሚያስውቡ ሲሆን የጓሮ አበባና አትክልት ይተክላሉ.፤ ታካሚዎችንም  ያዝናናሉ ያጫውታሉ ተብሏል፡፡ የሰዓሊዎቹ ቡድን በ “ኦዳ መደመር አፍሪካ የስነጥበባት ስፍራ” የሚሰሩ ሲሆን ከአማኑኤል ሆስፒታል ጋር በመተባበር ታካሚዎች ፤ የህክምና ባለሙያዎችና ሌሎች ሰራተኞችን በሚያሳትፉ ተግባራት የዓለም የአእምሮ ጤና ቀንን እንደሚያከብሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡  
የአለም ጤና ድርጅት በ130 አገራት ያሉትን ሁኔታዎች በሚዳስስ ጥናቱ  እንዳመለከተው፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ 93 በመቶ በሚሆኑት አገራት ውስጥ ወሳኝና አስፈላጊ የአእምሮ ጤና አገልግሎቶችን እያስተጓጎለ ነው፡፡ ወረርሽኙ በአእምሮ ጤና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ  አስከፊ እንቅፋት መጋረዱም ተጠቁሟል፡፡
የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) የዘንድሮ የዓለም የአዕምሮ ጤና ቀንን ምክንያት በማድረግ የዓለም መሪዎችን፣ ታዋቂ ሰዎችንና የመብት ተሟጋቾችን ከያሉበት በኦንላይ መድረክ እንደሚያወያይም ታውቋል፡፡ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ገብረየሱስ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ‹‹ጥሩ የአእምሮ ጤንነት ለአጠቃላይ ጤና እና ደህንነት ፍፁም ወሳኝ ነው፡፡ የዓለም መሪዎች ሕይወት አድን በሆኑ የአእምሮ ጤንነት ፕሮግራሞች ላይ የበለጠ ኢንቨስት ለማድረግ፣ በፍጥነትና በቆራጥነት መንቀሳቀስ አለባቸው›› ብለዋል፡፡
የታዋቂ ሰዓሊዎቹ ቡድን፤ ከሁለት ሳምንት በፊት በአማኑኤል የአዕምሮ ጤና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተገኝተው ሰፊ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ በጉብኝታቸው ወቅትም ከሆስፒታሉ ዋና ሜዲካል ዳይሬክተር፤ ከተለያዩ የህክምና ባለሙያዎች እንዲሁም የአስተዳደር ሰራተኞችና ታካሚዎች ጋር ተገናኝተው፣ በሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡ የሆስፒታሉን ግቢ ግድግዳዎች በቀለማት ማስዋብ፣ ከታካሚዎች ጋር አብሮ ማሳለፍ፣ የጓሮ አበባና ዕጽዋት መትከል እንዲሁም መዝናናትና መጫወት የሚለው ሃሳብ የመነጨውም ከዚያ በኋላ ነው ብለዋል፤ የሰዓሊዎቹ ቡድን፡፡  
አይኦኤም ኢትዮጵያ ሰዓሊዎቹ በሆስፒታል ቅጥር ግቢው ለሚያከናውኗቸው የሥነጥበብ ሥራዎች የስዕል መስሪያ ሸራዎች፣ ብሩሾች፤ ቀለማትና ሌሎች ቁሳቁሶችን በማሟላት ድጋፍ አድርጎልናል ይላሉ፤ ሰዓሊያኑ፡፡ የዘንድሮ “የዓለም የአዕምሮ ጤና ቀን” በዛሬው ዕለት በአማኑኤል የአዕምሮ ጤና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚከበር ሲሆን የአገሪቱ ትልልቅ መገናኛ ብዙሃን የዜና ሽፋን እንደሚሰጡት ይጠበቃል፡፡ የሰዓሊዎቹ ቡድን በሆስፒታሉ ዙርያ ገብ ባሉ ግድግዳዎች፤ በማረፊያ ስፍራዎችና በግዙፍ ሸራዎች ላይ ልዩ የስዕል ስራዎችን ከሆስፒታሉ ታካሚዎች እንዲሁም የህክምና ባለሙያዎችና የአስተዳደር ሰራተኞች ጋር ይሰራሉ፡፡ በሆስፒታሉ የሴቶች ዋርድ አካባቢም ልዩ ልዩ የጥበብ ስራዎችና የጓሮ ልማቶች ያካሂዳሉ ተብሏል፡፡
ሰዓሊና ዲዛይነር ዳዊት ሙሉነህ ለ20 ዓመታት በአፈር ቀለማት ስዕሎችን በመስራት ለ20 ዓመታት የዘለቀ ሲሆን ሥነጥበብ ያለውን የመፈወስ ሃይል በገጠመኝ አስደግፎ ይናገራል፡፡
‹‹ባንድ ወቅት ከአንድ ኢትዮጵያዊት ጋር ተገናኘን፡፡ ኢትዮጵያዊቷ በፅኑ ታማ፤ ምንም የማትናገር፤ በዊልቼርና በሞግዚት ድጋፍ የምትንቀሳቀስ ነበረች። ስዕል ልታሰራኝ እንደምትፈልግ ተነገረኝ። የምትፈልገው ስዕል ጥቅጥቅ ያለ ደን ቢሆንም፣ ያንን በምልክት  ልታስረዳኝ እጅግ ከብዷት ነበር፡፡ እኔ ግን የፈለገችውን ስለተረዳኋት ስዕሉን ሰራሁላት፡፡ ስዕሉን እንድታይ ተጠርታ  የመጣች ቀን የሆነ ለውጥ… ፊቷ ላይ አስተዋልን፡፡ እንደ ምንም ብላ ስዕሉ ላይ እንዲጨመር የምትፈልገውን በምልክት ነገረችኝ። በሚቀጥለው ጊዜ ያለችኝን አስተካክዬ ስዕሉን ወሰድኩላት። በሚያስገርም ሁኔታ ልክ እንዳየችው ማውራት ጀመረች፡፡ ከረጅም ጊዜ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ነበር በአማርኛ ያወራችቀው፡፡ ለስዕሉ ፍሬም ሲገዛም ራሷ ነበረች የመረጠችው፡፡ ከዚያ በኋላ “ፀጉር ቤት ልሂድ”፤ “ካፌ ሻይ እንጠጣ” ማለት ሁሉ ጀመረች፡፡ ይህ ገጠመኝ ስዕል የፈውስ ሃይል እንዳለው ያረጋገጥኩበት ነው፡፡” ብሏል፤ ሰዓሊው ለአዲስ አድማስ፡፡
“ስዕል የአዕምሮ በሽተኛን ብቻ ሳይሆን ጤነኛ ሰውንም እንደሚያድን ነው የማምነው።  ለብዙ ዓመታት በተሰማራሁበት የስዕል ሙያዬ፤ “ለምን ትስላለህ?” ተብዬ ስጠየቅ፤ “በሽተኛ ላድንበት” ብዬ ነው የምመልሰው፡፡ በዚህ ረገድ ሰፊ ልምድ አለኝ፡፡ አሁን ደግሞ የስነጥበባት ሥራዎችን ለማከናወን በሆስፒታሉ ቀጠሮ መያዛችን አስደስቶኛል፡፡ በተፈጠረው አጋጣሚ ከሙያ አጋሮቼ ጋር የስዕል አቅምን ለማሳየት እጥራለሁ፡፡ በእርግጠኝነት ስዕል ያድናል፤ ከህመም ይፈውሳል፡፡” በማለት ሰዓሊ ዳዊት አብራርቷል፡፡
ሰዓሊ መምህርና ገጣሚ አስናቀ ተገኝ በበኩሉ፤ “በአዕምሮ ህክምና ዙርያ በርካታ ጥናቶች፤ ፊልሞችና ዘጋቢ ፊልሞች የተሰሩ ቢሆንም ሁሉም ሰው ሊመለከተው የሚገባው በብራዚላዊቷ የስነልቦና ባለሙያ ዶክተር ኒስ ዳ ሲልቬይራ የተሰራው  “Nise: The Heart of Madness (2015)” የተሰኘው ፊልም ነው፡፡ ፊልሙ በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ሲሆን የሥነ-ልቦና ባለሙያዋ ከባልደረቦቿ ጋር  ለአዕምሮ ታማሚዎች የሚደረገውን የኤሌክትሮሾክ ቴራፒ (ህክምና) በስነጥበብ በመታገዝ ስትሰጥ ነው” ሲል ተናግሯል፡፡
“ወደ አማኑኤል ሆስፒታል የምንሄደው የምንገናኝበትን ሚዲየም ይዘን ነው፤ የፈለጉትን እንደፈለጉ ተሳትፈውና ተጫውተው እንዲያሳልፉ እንሻለን። በነገራችን ላይ ሚስጥርም ይነግሩናል። አዕምሮ የምስጢር ቤት ጓዳ ነው፤ ዝም ብሎ ለማንም አይነገርም፡፡ ሰው ሲታመም የሚናደደው አዕምሮ ነው፡፡ መጠበቂያው ግንብ አዕምሮ ነው፡፡ ስለዚህም  የኦዳ መደመር አፍሪካ ሰዓሊዎች፣ ወደ አማኑኤል ሆስፒታል ስንሄድ፣ ይህን የመጠበቂያ ግንብ ለማጠናከር ነው፡፡ ምክንያቱም የኛም ነውና። ስናያቸው እኛን ይመስላሉ፡፡ እኛም እነሱን እንመስላለን፡፡ ባላለቀ ጊዜ ውስጥ እከሌ ታማሚ ነው፤ እከሌ ጤነኛ የሚለው ቋንቋ መቆም አለበት# በማለት አስረድቷል።
ወጣት ሰዓሊ ዳሪዮስ ኃይለሚካኤል በበኩሉ ሲናገር፤ “ከአዕምሮ ጤና ጋር የስዕል ሙያን በማገናኘት ለመስራት የመጀመርያው መልካም አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡ ስነ ጥበብ የመፈወስ ጉልበትና አቅም እንዳለው በሳይንስ ተረጋግጧል፡፡ ስለዚህም በአማኑኤል ሆስፒታል ልዩ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ልንሰራ ያሰብነው ሁሌም ሊደረግ እንደሚገባው ነው የምረዳው፡፡ ሆስፒታሉ በሳምንት ቢያንስ ሁለት ጊዜ የእኛን የመሰለ ድጋፍ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ሰዎች እየዳኑበት በመሆኑ የሆስፒታሉ ሰራተኞች በዘላቂነት ውጤቱን እንዲያዩት የስነጥበብ ባለሙያዎች ደጋግመው ሊተገብሩት ይገባል፡፡ ስነጥበብ በአዕምሮ መታወክ ውስጥ ላሉ ሰዎች ፈዋሽነቱ አያጠራጥርም፡፡ በአማኑኤል ሆስፒታል የምናከናውነው ተግባርም አሪፍ ጅማሮ ነው..›› ብሏል፡፡
ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ በመላው ዓለም ከአራት ሰዎች አንዱ በሕይወቱ በተወሰነ ደረጃ በአእምሮ መታወክ ይጠቃል፤ የአእምሮ ፣ የነርቭና የአደንዛዥ ዕፅ አጠቃቀም ችግሮች በጤና ውጤቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላሉ፤ ይህም ከጠቅላላው የዓለም የጤና ችግር 13 በመቶ ያህል ነው (WHO, 2012)፡፡ በሌላ በኩል፤ የዓለም ጤና ድርጅት በ2018 ባወጣው ሪፖርት፤ በየ40 ሰከንዱ አንድ ሰው ራሱን ያጠፋል ብሏል፡፡ ይህም በየአመቱ የራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎችን ብዛት ከ800 ሺ  በላይ ያደርሰዋል፤ በዓለማችን  በጦርነትና በግድያ ከሚሞቱት ሰዎች የበለጠ ማለት ነው፡፡  
የዓለም የአእምሮ ጤና ቀን፣ በየአመቱ ኦክቶበር 10 ላይ የሚከበርበት አጠቃላይ ዓላማ፣ በዓለም ዙሪያ ያሉ የአእምሮ ጤና ጉዳዮችን ግንዛቤ ለማሳደግና የአእምሮ ጤናን የሚደግፉ ጥረቶችን ለማጠናከር ነው፡፡ በዓሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረው እ.ኤ.አ. በ1992 በዓለም አቀፍ የአእምሮ ጤና ፌደሬሽን አማካኝነት ነበር፡፡



Read 1147 times