Saturday, 10 October 2020 13:57

“ኮሮና ፊቴን ወደ ኢንቨስትመንት እንዳዞር አነሳስቶኛል”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

  "ሆፕ" የ7ሚ. ተመልካች ክፍያ (View) አልተፈፀመልኝም ዘፈኖቼን ከ “ሆፕ” ላይ አንስቼ በራሴ ቻናል ላይ ልጭን ነው

            ድምፃዊ ዳኘ ዋለ፤ “የጨነቀ እለት”፣ “ወይ ፍንክች” እና “ጣና ታሟል” በተሰኙ ነጠላ ዘፈኖቹ እውቅናና ተወዳጅነትን አግኝቷል፡፡ ከደብረ ማርቆስ ወጣ ብላ በምትገኝ የገጠር አካባቢ ተወልዶ ያደገው ድምፃዊው፤ በርካታ ነጠላ ዜማዎችን ቢለቅም አንድም የዘፈን አልበም አላወጣም፡፡ በአገራችን የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ በተገኘው ፋታ የአልበም ሥራ መጀመሩን ይናገራል፡፡ ኮሮና ፊቱን ወደ ኢንቨስትመንት እንዲያዞርም አነሳስቶኛል - ይላል አርቲስቱ፡፡  የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፈቆት ዮሴፍ ሰሞኑን ከርቲስቱ ጋር ባደረገችው ቃለምልልስ፤ ስለሙዚቃ ሥራዎቹ የጠየቀችው ሲሆን ከ “ሆፕ ኢንተርቴይመንት” ጋር ስለገጠመው ውዝግብም ነግሯታል፡፡


     ሰሞኑን አዲስ አበባ ነው ያለኸው… መሰለኝ?
ቀደም ሲል አዲስ አበባ ነበርኩ፡፡ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ወደ ክፍለ ሀገር ሄድኩ እንጂ፡፡ ሰሞኑን አዲስ አበባ የመጣሁት የአልበም ስራ ስለጀመርኩና  ከ“ሆፕ ኢንተርቴይመንት” ጋር የገጠሙኝን ችግሮች ለመፍታት ነው፡፡
ከተገናኘን አይቀር እስኪ ስለ ስራዎችህ አጫውተኝ… ይበልጥ የምትታወቀው “የጨነቀ ዕለት” በሚለው ዘፈንህ ነው። ነገር ግን ከዚያም በፊት ሌላ ነጠላ ዜማ አውጥተሃል አይደለ?
ወደ ዝርዝር ጉዳይ ከመግባታችን በፊት ግን መልካም ምኞቴን እንድገልጽ ፍቀጂልኝ…
መልካም ምኞት? እሺ ቀጥል…
እግዚአብሔር አምላክ የሀገራችንን ሰላም ያውርድልን፤ መዋደዱን፣ አንድነቱንና ፍቅሩን ይስጠን፣ ኮሮና ቫይረስ የተባለውን ወረርሽኝ ከአገራችን ይንቀልልን፤ እንዴ?… አሜን በይ እንጂ?
አሜን… አሜን… አሜን!...በእውነቱ… ጥሩ ነገር ነው የተመኘኸው…
አሁን ወደ ነጥባችን ስመለስ፣  “የጨነቀ እለት” ከሚለው በፊት “ውብ አበባ” እና “ልፎ ልፎ” የሚሉ ነጠላ ዜማዎችን ሰርቻለሁ፡፡ “የጨነቀ ዕለት”ን ከሰራሁ በኋላ ደግሞ የ“ፍቅር እስከ መቃብር”  ደራሲ ክቡር ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁን የተመለከተ አንድ ሙዚቃ ሰርቻለሁ፡፡
ኧረባክህ…እኔ ግን አላውቀውም…፡፡
እንደ አጋጣሚ ሆኖ ህዝብ ጆሮ በደንብ አልደረሰም፡፡ “ሀዲስ ዓለማየሁ” የሚል ነው ርዕሱ፡፡ እንደውም ቴዲ አፍሮ “ማር እስከ ጧፍ”ን ከመስራቱ በፊት ነበር የተሰራው፡፡ ከዚያ በኋላ “የጨነቀ እለት”፣ ወጣ፡፡ ቀጥሎ “ወይ ፍንክች፡፡ በመሀል ደግሞ ከድምፃዊ ሰለሞን ደምሴ ጋር  “ጣና ታሟል አሉ” የሚል አወጣን፡፡ በኮሮና ቫይረስ ዙሪያም አንድ ሥራ ሰርቻለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ሁለተኛ ስለ ጣና እና እምቦጭ “ጣና ታሟል” የተሰኘ ዘፈን ሰርቻለሁ፡፡
ለብቻህ የሰራኸውን በደንብ ሰምቸዋለሁ… እንዴት ለሁለተኛ ጊዜ ስለ ጣና አቀነቀንክ? የመጀመሪያው አላረካህም ወይስ ….
እውነት ለመገር የጣና ጉዳይ የአንድ አካባቢ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ ነው፡፡ እኔ ጣና ዳር ቁጭ ስል የሚሰማኝ ስሜት በጣም ልዩ ነው። በዙሪያው ካሉ ደሴቶችና ገዳማት የሚወጣው የእጣን ጭስ፣ የሚያውደው የአየሩ መዓዛ… ህይወት የሚቀጥል ነው፡፡ ውሃው ራሱ እኮ ፀበል ማለት ነው፡፡ ዙሪያውን የሚፀለይበትና የሚቀደስ ስበት የተባረከ ውሃ ስለሆነ ፀበል ነው፡፡ ትኩረት ባንሰጠው እንጂ ጣና ለኢትዮጵያ ትልቅ ሀብት ነው፡፡ ከመንግስት ትኩረት ማጣቱ ግን ያሳዝነኛል፡፡ ብዙ ነገር ይባላል ቃል ይገባል፡፡ አንድ ሰሞን “ጣና ጣና… ሆይ ሆይ” ይባላል፡፡ ለጣና ግን ጠብ ያለለት ነገር የለም፡፡ በእምቦጭ ላይ ለመስራት የተቋቋመው ኤጀንሲም…ሌሎች አካላትም “ጢንዚዛ እያረባን ነው፣ ማሽን ተገዝቶ ገባ” ወዘተ ይላሉ፡፡  ውጤት ያመጣ ስራ ግን አላየሁም፡፡
እስካሁን መጠቀሚያ ሆነ እንጂ ጣና የተጠቀመው ነገር የለም፡፡ ይህንን በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ በአገራችን ያለው ያለመረጋጋት፣ የፖለቲካ ውጥረት፣ የዘርና ጐሳ ግጭት ደግሞ ማንም ስለ ጣና እንዳያስብና ትኩረት እንዳይሰጥ አድርጐታል፡፡ ይህንን የዘረኝነት እርኩስ መንፈስ ፈጣሪ ካላጠፋልን፣ እንኳን ጣና እኛም እንጠፋለን፡፡ ስለዚህ የጣና ጉዳይ በጣም ይቆጨኛል፤ ያንገበግበኛል፡፡ ለዚህም ነው ከአንዴም ሁለት ጊዜ በራሴ ወጪ ስለ ጣና የሰራሁት፡፡ ጣናን ለመታደግ መፍትሔው ምንድን ነው ካልሽኝ… ሁሉም ሰው በእውቀቱና በጉልበቱ መረባረቡ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ መንግስት ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት መስጠት አለበት፡፡ የጣናን ጉዳት ባለፈው “ሊቦ ከምከም” ላይ ተገኝተሽ… በአካል አይተሽዋል፡፡ ብዙ የውሃው ክፍል እየደረቀ ነው፡፡ በእንቦጭ ምክንያት “ጠናብኝ ህመሜ ታመምኩኝ ክፉኛ፤ በበሬ ታረስኩኝ የአሳዎች መዋኛ” ያልኩት፤ አሁን ያለበትን አደገኛ ሁኔታ እያየሁ ነው፡፡
እኔ አንዳንዴ በጣም የሚገርመኝ፣ መንግስት “ጣናን ለመታደግ ችግኝ መትከል ነው” የሚለው ነገር ነው፡፡ አዎ ችግኝ መትከል ጥሩ ነው፤ ችግኝ አይተከል አይደለም፤ ግን ጣናን እየበላው ላለው እምቦጭ አሁን ላይ ዛፍ ምኑ ነው፡፡ እምቦጩን እያጠፉ ጐን ለጐን፣ ዛፍ መትከል በጣም ጥሩ ነው፤ ግን ቅድሚያ ለሚሰጠው ነገር ቅድሚያ መስጠት ጥሩ ነው፡፡  እኔ አንዳንዴ ጣና እንዳይድን የሚሰራ የሆነ የተደበቀ ሴራ ያለ ይመስለኛል፡፡ ለህዳሴው ግድብ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንደተባበረና እጁን እንደዘረጋ ሁሉ ለጣናም ርብርብ ማድረግ፣ ድምፁን ማሰማት፣ ጉልበቱን እውቀቱንና ጊዜውን መስጠት አለበት፡፡ አባይ ከጣና 60 በመቶ ውሃ እንደሚያገኝ ነው በጥናትና ምርምር የተገለፀው፡፡ ጣና ከሌለ አባይ ግድብ የለም፡፡
አንድ ላይ ነው እንጂ ሞት ይርሳህ ማለት  
ለብቻ በማዘን አያስቀር ከሞት
የአባይ ውሃ ሞልቶ ይፈሳል ቦይ ለቦይ
እያሉ ያለኔ ማዜም ይቻላል ወይ?” ሲል ጣና መልዕክት እንደተናገረ፣ በሰውኛ ወክዬ ግጥም የሰራሁት ለዛ ነው፡፡ የጣና ጉዳይ ይሰማኛል ይቆጨኛል፤ ትኩረት ማጣቱ ይበልጥ ያበሳጨኛል፡፡ ለአባይ የተሰጠው ትኩረትና እርብርብ ለጣናም ይደገም እላለሁ፡፡
በጣም የተወደደው ዘፈንህ “የጨነቀ እለት” ወኔ ቀስቃሽና ፖለቲካዊ ብሶት የወለደው ነው ይባላል፡፡ ራስህን እንደ ፖለቲከኛ ታስባለህ እንዴ?
እኔ ድምፃዊና የግጥምና ዜማ ፀሐፊ ነኝ፤ በአገሬ ጉዳይ ከመጡብኝ ግን አዎ ፖለቲከኛ ነኝ፡፡ በአገሬ ጉዳይ አልደራደርም፤ ከወታደርም አልተናነስም፤ ልዋጋም እችላለሁ፡፡ ዘፈኑን በተመለከተ ግን ቃሉ “የጨነቀ እለት” ስለሚል ሰው ከወቅቱ የአገሪቱ ውጥረት ጋር አያይዞት ይሆናል እንጂ የጐጃምን ባህል… ጀግንነት፣ ወግና ሥርዓት፣ ሽለላና ፉከራ የሚያንፀባርቅ  ዘፈን ነው፡፡  እኔ ጐጃም ከደብረ ማርቆስ ወጣ ያለች የገጠር አካባቢ ነው ተወልጄ ያደግኩት፡፡ ሳድግም እየሸለልኩና እየፎከርኩ ነው ያደግኩት፡፡ አሁን ደግሞ ያንን ያደግኩበትንና የምኮራበትን የጐጃምን ባህል ነው ለማንፀባረቅ የሞከርኩት፡፡ ርዕሱ እንዴት ወጣ መሰለሽ… ይህንን ዘፈን ብዙ ሰው እንዲጽፈው ሰጥቼ ነበር፤ ከዛ የልቤ ስላልደረሰ እኔው ሌሊቱን ስጽፍ አደርኩና ለአቀናባሪው፤ “አንተዬ… ይሄ ነገር እኮ አስጨነቀኝ” እያልኩት… ቃሉ መጣልኝ፤ “የጨነቀ እለት” አልኩት፡፡ “ወይ ፍንክች” የሚለው ዘፈን ይልቅ ትንሽ ጠንከር ያለ፣ ኢትዮጵያዊነቱን ሳይለቅ የተሰራ አማራዊ ዘፈን ነው፡፡ የአማራን አጠቃላይ ሁኔታና ባህሪ የሚወክል ነው፡፡ በአሁን ወቅት አማራ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍና በደል እያሰብኩ፣ በዚያ ስሜት ውስጥ ሆኜ ነው ግጥሙን እኔና ሃብተማሪያም መንግስቴ ፃፍነው፡፡ ዜማውን እኔው ሰራሁት፡፡
ኮሮና ቫይረስ በሀገራችን ከተከሰተና የሁሉም ነገር እንቅስቃሴ ከተገደበ ወደ 7 ወራት ገደማ ተቆጥረዋል፡፡ በዚህ ምክንያት የሙዚቃ ዘርፉ በእጅጉ ተጐድቷል። ለመሆኑ አንተ ይሄን ወቅት እንዴት እያለፍከው ነው?
ኮሮና ቫይረስ ብዙ ነገር አስተምሮኛል። እኔን ብቻ ሳይሆን ብዙ ሰው ያስተማረ ይመስለኛል፡፡ ሁሉም የጥሞና ጊዜ እንዲያገኝና ወደ ራሱ እንዲመለከት ያደረገ ይመስለኛል፡፡ እርግጥ ነው ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤ እኔ በግሌ ብዙ ጉዳት ላይ ባልወድቅም ኮሮና በአጠቃላይ ግን አርቱን በእጅጉ ጐድቶታል፡፡ እንደሚታወቀው አርት የማይገባበት ቦታ የለም፡፡ ኮሮናም ሲመጣ መንግስት ግንዛቤ ለመፍጠር እንደ መሳሪያ የተጠቀመው አርቱን ነው፡፡ ነገር ግን የዚያኑ ያህል ለአርቱ ትኩረት አልተሰጠም፡፡ በኮሮና ብዙ የአርት ሰው ነው ችግር ውስጥ የገባው። የአርቱ ማህበረሰብ ህይወት ተናግቷል፤ ገንዘብ እየተዋጣ ለባሰበት ቢሰጥም ከአቅም በላይ እየሆነ ነው፡፡ እኔ ባገኘሁት ፋታ አልበም እየሰራሁ ነው፤ ነገር ግን ወደ ኢንቨስትመንት ለመግባት እንዳስብም ዕድል ሰጥቶኛል፡፡
ምን አይነት ኢንቨስትመንት?
አንዱ ከሙያዬ ጋር የሚሄድ ነው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ክለቦችን ለመክፈት ነው ያሰብኩት፡፡ ሁለተኛ የአሜሪካ ላሞችን ለማርባት ፕሮጀክት አስገብቼ በሂደት ላይ ነኝ፡፡ ባህርዳርም ደብረማርቆስም ቦታ ጠይቄ ከሚመለከተው አካል መልስ እየጠበቅሁ ነው ያለሁት፡፡ ጊዜው ጥሩ ከሆነ፣ አገር ከተረጋጋ፣ መልካም ነገር ከመጣ… አዲስ አበባም ክለብ የመክፈት እቅድ አለኝ፡፡ ኮሮናው እንቅስቃሴ በመገደቡ የተነሳ አልበም መስራትም ጀምሬአለሁ፡፡  በዚህ ሁኔታ ነው ዘመነ ኮሮናን እያሳለፍኩ ያለሁት፡፡
ከ“ሆፕ ኢንተርቴይመንት” ጋር  ውዝግብ ውስጥ መግባታችሁን ሰማሁ ምን ገጠመህ?
እንደው ብዙ አስለፈለፍሽኝ እንጂ ዋናው የተገናኘንበት ጉዳይ የዚህን ድርጅት በደልና ግፍ ሰው እንዲያውቀው ቅሬታዬን ለማቅረብ ነበር፡፡ “ሆፕ ኢንተርቴይመንት” እንደሚታወቀው፤ የብዙ ዘፋኞችን ቪዲዮ ዩቲዩብ ላይ በመጫን የሚታወቅ፣ ብዙ ሰብስክራይበር ያለው አንጋፋ ድርጅት ነው፡፡ እኔም ላለፉት 6 ዓመታት ከሆፕ ኢንተርቴይመንት ውጪ ደንበኛ የለኝም፡፡ ስራዎቼ  እስካሁን የሚታዩት በዚሁ ድርጅት አማካኝነት ነው፡፡ አሁን በርግጥ የራሴን ዩቲዩብ ከፍቻለሁ፡፡ አንድ ዘፋኝ ግጥምና ዜማ ገዝቶ፣ ከአቀናባሪ ጋር መከራውን በልቶ፣ ቪዲዮ ፕሮዳክሽን ለመስራት ወጥቶ ወርዶ ገንዘብ ተበድሮ ሰርቶ፣ ስራውን ለ“ሆፕ ኢንተርቴይመንት” ይሰጣል፡፡ እኔስ መቼም ግጥምም ዜማም ራሴ እጽፋለሁ፤ በርካታ ዘፋኞች በ “ሆፕ” በኩል የድካም ዋጋቸውን ሳያገኙ እየቀሩ ነው፡፡
በምን ምክንያት? ችግሩ ምንድነው?
አንደኛ፤ በተገቢው ጊዜና ሰዓት አይከፍልም፤ በስንት ጭቅጭቅ ቢከፍል እንኳን ተገቢውን ክፍያ አይሆንም፡፡ ዛሬ ቴክኖሎጂው ምቹ ነው፡፡ አንድ ዘፋኝ ስራው ሆፕ ላይ ተጭኖ፣ ስንት ተመልካች እንዳየው በግልጽ ቢታወቅም ድርጅቱ ተገቢውን ክፍያ አይከፍልም፡፡ ስንቶቹን መሰለሽ ተስፋ ያስቆጠረው! 5 እና 6 ሚሊዮን ሰው ስራሽን እንደተመለከተው አያወቅሽ 30 ሺህ ሰው ብቻ ነው ያየው ይልሻል፡ ይህንን የሚያደርገው ደግሞ በአብዛኛው በክፍለ ሀገር ዘፋኞች ላይ ነው፡፡ እኔ በተፈጥሮዬ ሰው ሲያታልለኝ አልወድም፤ ማንም ይህንን የሚወድ ያለ አይመስለኝም፡፡ በ“ሆፕ ኢንተርቴይመንት” ምክንያት ብዙ ዘፋኝ እያለቀሰ ተስፋ ቆርጦ ተቀምጧል። አሁን ብዙ የማውቃቸውን አርቲስቶች እዚህ ልጠራልሽና ልትሰሚያቸው ትችያለሽ (ይህ ቃለ ምልልስ እየተደረገ 4 ድምፃዊያን ለጋዜጠኛዋ ቅሬታቸውን በስልክ  ነግረዋታል) እስከ 2 ሚ ተመልካች ያገኙ ዘፋኞች፣ በተለይ የክፍለ ሀገር ልጆች… እያለቀሱ ነው ያሉት፡፡ ከኔ ይልቅ ለእነሱ ድምጽ ለመሆን ነው ይህንን ቅሬታ ወደ ሚዲያ ያመጣሁት፡፡ እኔ ለምሳሌ እስካሁን በዘፈኖቼ ወደ 20 ሚሊዮን ተመልካች አግኝቻለሁ፤ ገንዘቡን በአግባቡ ቢከፍልሽ አንድ ቁም ነገር ይሰራበት ነበር፡፡ አሁን ግን ምን ያህል አገኘህ ብትይኝ፣ እየቦጫጨቀ ስለሚሰጠኝ አላውቀውም፡፡
ዋናው የሆፕ ባለቤቱ ውጭ አገር ነው የሚኖረው፤ ሰለሞን ይባላል፡፡ እዚህ ተወካይ ሆኖ የሚሰራው ብሩክ ይባላል፡፡ እኛ እዚህ ያለውን ተወካይ አፋጠን ይዘን ገንዘባችንን ስጠን ስንለው፣ ውጪ ይደውልና “እንዲህ ሆኖ፣ በዚህ ወጥቶ” ይለናል፡፡ እውነት ለመናገር “ሆፕ ኢንተርቴይመንት” ገንዘቡን በአግባቡ ቢከፍልና ዘፋኞች እንዲበረታቱ ቢያደርግ ጥሩ ነበር፡፡ ሁሉ ነገር በተቆላለፈበት በዚህ ጊዜ፣ ብዙዎችን ለእውቅና በማብቃት እየቦጫጨቀም ቢሆን ገንዘብ በመስጠት፣ አንዳንዶች ህይወታቸውን እንዲመሩ በማድረግ በኩል፣ የሰራውን ውለታ የሚክድ የለም፡፡ ግን የክፍለሀገር ልጆችን “ምንም አያውቁም” ብሎ ማሰቃየቱ ያበሳጫል፡፡ ሰውን ቀጥረው ቢሮ ዘግተው ይጠፋሉ፡፡
አርቲስቶች ስራቸውን ለሆፕ ሲሰጡ የውል ስምምነት ይኖራቸዋል… ብዬ አስባለሁ፡፡ አንተም ከድርጅቱ ጋር ትንቅንቅ እየገጠምክ የተቆራረጠም ቢሆን ክፍያ እንደምትወስድ ነግረኸኛል፡፡ ጉዳዩን በህግ ለመፍታት ወደ ፍርድ ቤት ለምን አትሄዱም?       
ምን መሰለሽ… ልጁ (ብሩክ) ለታዋቂና ለከተማ አርቲስቶች እየቆራረጠም፤ ቀኑን እያሳለፈ ቢሆን ይከፍላል፡፡ አሁን ግፍ እየሰራ ያለው በክፍለሀገር ዘፋኞች ላይ ነው። ብዙ ጊዜ እየታሰረ ወዲያው ቶሎ ይፈታል። በፍትህ አካላት በኩል ያለው ችግር ምን እንደሆነ አላውቅም፡፡ ወዲያው ዘፋኞቹ ይህንን ሲያዩ ብንከሰውም ምንም አናመጣም በሚል ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ እኔ ለምሳሌ ወደ 7 ሚ. ተመልካች ያየው ያልተከፈለኝ ገንዘብ አለ፡፡ ድርጅቱ በጣም ከፍተኛ በደል ነው የሚፈጽመው፡፡ በዚህ የተነሳ እኔ ለምሳሌ አሁን የራሴን ዩቲዩብ ከፍቻለሁ፡፡ ከሆፕ ጋር ያለኝን ውል በማቋረጥ ዘፈኖቼን በራሴ ቻናል ላይ ልጭን በዝግጅት ላይ ነኝ፡፡ ደብዳቤም አስገብቼላቸዋለሁ፡፡ እስካሁን ስሜቴን በመቆጣጠር ነበር እዚህ የደረስኩት፡፡ በዚሁ ከቀጠለ ሌላ ያልተፈለገ ነገር ውስጥ ለማስገባት ስለሚገፋፋ ከወዲሁ ብንለያይ ይሻላል የሚል ውሳኔ ላይ ደርሻለሁ። ስለ ክፍለሀገር ልጆች ብነግርሽ… በዚህ ሙያ ለማደግና ፍላጐታቸውን ለማሳካት የአባታቸውን በሬ ሸጠው፣ ተበድረው፣ ከዘመድ ወዳጅ ገንዘብ ወስደው… የዘፈን ቪዲዮ ይሰሩና ለሆፕ ይሰጡታል፡፡ እነሱ ከክፍለሀገር ወደዚህ መመላለስ ይቸገራሉ። እሱ ከምንም አይቆጥራቸውም፡፡ እስከ 2 ሚ. ድረስ ተመልካች ያላት ያልተከፈላትን ዘፋኝ፣ በስልክ አገናኝቼሽ፤ አውርተሻታል። ሽራፊ ሳንቲም አልተከፈላትም፡፡ የግፍ ግፉ ደግሞ “ኑ አከፍላችኋለሁ” ብሎ ጠርቷቸው፤ ከክፍለሀገር የትራንስፖርት ተበድረው ይመጡና፣  ሳይከፍላቸው እንደገና ለመመለሻ ተበድረው የሄዱ አውቃለሁ፡፡ አሁን ይሄ አግባብ ነው? ወደ አገራቸው ለመሄድ ገንዘብ አጥተው እዚሁ የትም የሚቀሩም አሉ፡፡
አንተ በትክክል ምን ያህል ክፍያ ነው የቀረብህ?
“የጨነቀለት” ከተሰኘው ዘፈን ብጀምርልሽ… 6 ሚ ተመልካች አግኝቷል፤ ገና 2 ሚ ተመልካች ላይ እያለ ነው ክፍያ የፈፀሙልኝ፡፡ የ4 ሚ አልተከፈለኝም፡፡ ጐንደርኛው 3 ሚ ተመልካች ደርሷል፤ የ1 ሚ ከምናምን ከፍለው ግማሹ በእንጥልጥል ቀረ። እንደገና “ለፎ ለፎ” የሚል ዘፈን አለኝ፤ 500 ሺህ ተመልካች አለው፡፡ በአጠቃላይ የ6 እና 7 ሚ ቪው ገደማ አልተከፈለኝም። እኔ እንኳ በመድረክም በሌላም ገንዘብ አገኛለሁ። እነዛ ሚስኪኖች ግን የትናየት መድረስ እየቻሉ፤ ተስፋ ቆርጠው ሲቀሩ፣ እንዴት ዝም እላለሁ ብዬ ነው አሁንም ወደ ሚዲያ የመጣሁት፡፡ አዲስ አድማስ የመጀመሪያዬ ነው፤ ገና በሬዲዮም በቴሌቪዥንም ጩኸቴን እቀጥላለሁ፡፡
ሆፕ ኢንተርቴይመንት እንደዚህ የሚያንገላታ ከሆነ… ዘፋኞች ለምን ለሌላ አማራጭ አይሞክሩም?
እውነቱን ልንገርሽ አይደለ… ብዙ ሰብስክራይበርና ተመልካች ስላለው ነው - ሌላ ታሪክ የለውም፡፡ ስለዚህ ሁሉም ወደ ሆፕ ይሄዳል፡፡ እንደኔ እንደኔ ግን አሁን የምመክረው፣ ዘፋኞች የራሳቸውን ቻናል ሰርተው፣ ሰብስክራይብ ማድረጉ ላይ ትብብር እንዲጠይቁ ነው፡፡ ጥሩ ስራ ከሰራሽ የትኛውም ቻናል ላይ ብትጭኚው መታየቱ አይቀርም፡፡ አሁን ሁሉም ዘፋኝ የሆፕ መቀለጃ መሆኑን ማቆም አለበት፡፡ እኔ በጣም ነው እያዘንኩ ያለሁት፡፡ እንዳልኩሽ ፍርድ ቤት ብትከሺው ነገ ይወጣል፤ ትርፉ ድካምና ጊዜ ማባከን ነው፡፡ ስለዚህ እሱ በዘፋኞች ነው ገንዘብ የሚያገኘው፡፡ ሁሉም ተማርሮ ሲቀር፣ ጥቅምና ጉዳቱን ያየዋል። ሁሉም የየራሱን ዩቲዩብ ከፍቶ ራሱ ተጠቃሚ እንዲሆን ነው ጥሪ የማቀረብው፡፡  እኔ በቅርቡ ዘፈኖቼን ከሆፕ ላይ እንደማነሳ ነግሬሻለሁ፡፡
ቀሪ ክፍያህስ ይቀልጣል ማለት ነው?
እሱንማ እንተሳሰባለን፡፡ አየሽ፤ ብስጭት ውስጥ ገብተሽ፣ አጉል ነገር ከማድረግና ሌላ ችግር ውስጥ ከመግባት በሰላም መለያየቱ ይሻላል ብዬ አስባለሁ፡፡  


Read 922 times