Saturday, 10 October 2020 12:57

የ‘ግርግር’ ነገር!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

  "ልክ ነዋ...እንደ ድሮ ቢሆን አኮ ሰው ሲጣላ መገላገል የተለመደ ነበር፡፡ አሁን ዋነኛው ቡጢ ቀማሽ መሀል የገባው ገላገይ ነው የሚሆነው፡፡ ብቻ በዚህም፣ በዛም ‘ግርግር’ ነገር፣ “ጭር ሲል አልወድም” ነገር የሚመቸን የበዛን ነው የሚመስለው፡፡--"
              
          እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ...ዛሬ እኮ መስከረም 30 ነው። ማለቴ...ምንም ነገር ለማለት ሳይሆን ምናልባት የግድግዳ ቀን መቁጠሪያችሁ ካልተለወጠ ለማስታወስ ያህል ነው። (እንዲያው “ሲገርማችሁ ኑሩ” የተባልን ፍጡሮች!)
በከተማችን አንድ ክፍል ነው…ሰሞኑን። በርከት ያሉ ሰዎች የሆነ ነገር ለማየት አንዱ በሌላው ላይ ለመተዛዘል ምንም አልቀራቸው...ልክ፣ የትረምፕ ‘ማሪን ዋን’ ሄሊኮፕተር በስህተት እዚህ ያረፈች ይመስል፡፡ (ቂ...ቂ...ቂ...) እኔ የምለው... እሳቸው ሰውዬ ግን...አለ አይደል...የሆነች የእኛ ሀገርን ዘፈን ግጥምን የሆነ ሰው ተርጉሞ ሳይሰጣቸው አልቀረም... “ስለሰው፣ ስለሰው ቀድጄ ልልበሰው፣” የምትለዋን ዘፈን፡፡ አሀ...ነገራቸው ሁሉ እንደዛ ይመስላላ! ልብ በሉልኝማ ‘ዘ ሞስት ፓወርፉል ማን ኤን ዘ ወርልድ’ የሚሏቸው፤ እንዲህ ጠማማ ዓመሉን አላርቅ ያለ የሰፈር ጎረምሳ ነገር ሲያደርጋቸው ግርም ይላል፡፡
 አይ አማሪካን! ያቺ የሰብአዊ መብት አጠቃቀም ቁንጮ ነን፣ የጠንካራ ሞራላዊ እሴቶች ምሳሌዎች ነን፣ መንፈሳዊ ልቀት ከእኛ ሌላ ለአሳር...ምናምን ስትል የከረመችው ሀገር፤ የፈረንካው ጉዳይ ላይና እታች አድርጎን ነው እንጂ ለካስ ከእኛ በምንም አትሻልምና! ‘ቦተሊከኞቻቸውን’ ልብ ብላችሁልኛል...ጉሮሮ ለጉሮሮ እያስተናነቃቸው ያለው የአሜሪካ ህዝብ ጥቅም ሳይሆን የፓርቲያቸው ጥቅም ነው። የአቅም ጉዳይ ሆነና ነው እንጂ፣  በሆነ ባልሆነው “ዋ ማእቀብ ጥለን በእንፉቅቅ እንዳናስኬዳችሁ!” አይነት ነገር ሆነና ነው እንጂ...የእውነተኛው ፊልም ጽሁፍ ሌላ መሆን ነበረበት፡፡ የምር ግን...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ....ዘንድሮ በወረርሽኙ ምክንያት ስንቱ ነው ሲፋቅ ጉዱ እየወጣ ያለው!  
እናማ...የከበበው ሰው ውጪያዊ አካላቸው ጢም የሚያስላጭ የሚባል አይነት ሁለት ‘ምን የመሳሰሉ’ ኋላና ፊት ተጠጋግተው የቆሙ መኪኖችንና ወርደው እየተንጎማለሉ የነበሩትን   ሁለት ‘ምን የመሳሰሉ’ ባለቤቶቻቸውን እያዩ ነበር...ጨረቃን ለመንካት “ምን ይሳነናል!” የሚሉ የሚመስሉ ሰዎች፡፡ ነገርዬው ግጭት አይነት መሆኑ ነው፡፡ (ወጣቶች ‘ይነሰነሳሉ…’ እንደሚሉት አይነት፡፡) ታዲያላችሁ....ለአቅመ ብልጭልጭ መኪናና ለአቅመ መንጎማለል ያልደረሱ መአት ሰዎች ከበዋቸዋል፡፡ 
እናማ… ከኋላ ያለውና ገጪ የተባለው መኪናም፣ ከፊት ያለውና ተገጨ የተባለው መኪናም ይቺን ታክል ጭረት አልነበረባቸውም፡፡ የኋለኛው መኪና ባለቤት “የታለ የገጨሁህ! አሳየኝ እስቲ፣ የቱ ላይ ነው የገጨሁህ?” ምናምን አይነት ነገር ይላል...በሸላይኛ፡፡ የፊተኛው መኪና ባለቤትም በውሀ ልክ አይነት ተኮሳትሮ…“ገጭተኸኛል፣ ትራፊክ ይምጣ…” ይላል... እሱም በሸላይኛ፡፡ እናማ… ትርኢቱ የሆነ ገና ስክሪፕቱ በመጻፍ ላይ ያለ የኮሜዲ ድራማ ምናምን ነገር ነበር የሚመስለው፡፡
ግን አሁን እንዲህ አይነት ፍሬከርሰኪ ነገር ለማየት ያ ሁሉ ሰው መኮልኮሉ ምን ይሉታል! ለነገሩማ…አለ አይደል...“ጭር ሲል አልወድም...” የሚመስል፣ ‘ግርግር’ የሚመስል አይነት ነገር ‘የሚመቸን’ በርከት እያልን መጥተናል፡፡  
የምር ግን፣ ነገሬ ብላችሁ ከሆነ...አሁን፣ አሁን የትኛውም የከተማው ክፍል ብትሄዱ፤ የሆነ ‘ግርግር፣’ የሆነ ከበባ አይነት ነገር አይጠፋም፡፡ ብቻ እዚህ ጋ አንድ፣ ሁለት ሰዎች የተሳተፉባት የሆነች ነገር ትፈጠር..እኛ ደግሞ በአራትና በአምስት ዙር ቀለበት ሠርተን አንከባለን፡፡
ደግሞላችሁ...አንዳንዶቻችን ጣልቃ ለመግባት እንሞክራለን፡፡ ሆኖም ዘንድሮ ‘ገላጋይነት’ የሚታየው እንደ ገለልተኝነት ሳይሆን፣ ነገርን እንደ ማብረድ ሙከራ ሳይሆን... ለአንደኛው ወገን እንደ ማገዝ ነው።
“በቃ ለዚች ብላችሁማ መጋጨት የለባችሁም፣” ምናምን ያለ ሰው ‘ወዮለት.‘... በቃ ምናምነኛውን የዓለም ጦርነት በራሱ ላይ የማስጀመሪያ ተኩስ በሉት፡፡
እናማ...በዘንድሮ የ“ወይ ከእኔ ጋር ነህ፣ ወይ ከእነሱ ጋር ነህ...” አይነት ‘ቦተሊካ’ “ምን አገባህ! አንተ ምን ቤት ነህ?” ሲባል ምን ቤት ነኝ ሊባል ነው፡፡ “አይ፣ መልካም ተግባር መፈጸምና መልካም ነገር መናገርን ከማዘር ቴሬዛ ወርሼ ነው...” አይባል ነገር! "ለመንግሥተ ሰማያት መግቢያ ሲቪዬ እንዲጠነክርልኝ ብዬ ነው...” አይባል!
ልክ ነዋ...እንደ ድሮ ቢሆን አኮ ሰው ሲጣላ መገላገል የተለመደ ነበር፡፡ አሁን ዋነኛው ቡጢ ቀማሽ መሀል የገባው ገላገይ ነው የሚሆነው፡፡ ብቻ በዚህም፣ በዛም ‘ግርግር’ ነገር፣ “ጭር ሲል አልወድም” ነገር የሚመቸን የበዛን ነው የሚመስለው፡፡
መሀል ከተማ ነው፣ አንድ ልብስ በቅናሽ ይሸጥ የነበረ ልጅን ደንብ ማስከበሮች ይዘውታል፡፡ ልጁ እየካደም አልነበረም፣ ‘ቡራ ከረዩ’ እያለም አልነበረም፡፡ እንባ፣ እንባ እያለው እየተለማመጣቸው ነበር። እናማ... ዙሪያቸውን ለእግረኛ መመላለሻ እስኪያቸግር ድረስ ከበባ ነበር …ግርግር፡፡
 አንድ የዜን መምህር በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ነበሩት፡፡ ታዲያ ሁሉም በየእለቱ በተወሰነ ሰዓት ጸሎታቸውን ያደርሳሉ›፡፡ አንዱ ብቻ ነበር ዘወትር በመጠጥ ጥምብዝ እያለ የሚመጣው፡፡ መምህሩም እድሜው እየገፋ ነበር፡፡ ታዲያ ተማሪዎቹ መምህሩ ህይወቱ በሚያልፍበት ጊዜ ከመሀላቸው ቡድኑን ለመምራት የሚታጨውና፣ የልማዱን ምስጢሮች የሚነገሩት ማን ሊሆን እንደሚችል ይጋራሉ፡፡
ሆኖም መምህሩ ህይወቱ ሊያልፍ በዋዜማው ሰካራሙን ተማሪ ያስጠራውና፤ ሁሉንም ምስጢር ለእሱ ይዘከዝክለታል። በዚህ ጊዜ ሊሎቹ በብሽቅ ጨርቃቸውን ሊጥሉ ምንም አልቀራቸውም፡፡ አደባባይ ወጥተውም “እንዴት አሳፋሪ ነገር ነው! ለካስ እኛ ራሳችንን መስዋእት ስናደርግ የቆየነው ችሎታችንን ማየት ለማይችል ለተሳሰተ ሰው ነው፣” አሉ፡፡
መምህሩም ይህንን ተቃውሞ ሲሰማ ምን ቢል ጥሩ ነው... እነኚህን ምስጢሮች አበጥሬ ለማውቀው ሰው ማሰተላለፍ ነበረብኝ። ሁሉም ተማሪዎቼ መልካም ባህሪይ ያላቸው ናቸው፤ የሚያሳዩትም መልካም ባህሪያቸውን ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አደገኛ ነው፡፡ ምክንያቱም የደግነት ባህሪይ በራሱ እብሪትን፣ መታበይንና አለመቻቻልን መሸሸጊያ ሊሆን ይችላል፡፡ ለዚህ ነው ጠንቅቄ የማውቀውን ብቸኛውን ተማሪ የመረጥኩት፣ ምክንያቱም አሉታዊ ጎኑ ስካር እንደሆነ አውቃለሁ፡፡” አሪፍ አይደል!   
ስሙኝም...እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... ይሄ የ‘ግርግር’ ነገር እኮ ለሁሉም ነገር ‘ኮምፐልሰሪ’ የሚሉት አይነት እየሆነ ነው የሚመስለው፡፡ ቦተሊካችን ይኸው እንደምታዩት ነው፡፡ ይሄ ቢያጥቡት፣ ቢፈትጉት በቀላሉ አልጠራ የሚለው የከብቱ የሆድ እቃ ክፍል አለ አይደል...የአንዳንዶቻችን ቦተሊካ እንደዛ ነው የሚመስለው፡፡ ልክ ነዋ...ከዘመንና ከጊዜ ጋር በሚጢጢው እንኳን እየተስተካከሉ መሄድ ማንን ገደለ! ኸረ እባካችሁ በሀያ አንደኛው ክፍለ ዘመን፣ አሁንም አስራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን የከሰል ባቡር ላይ ልትጭኑን አትሞክሩ! (ሄይ! ወራጅ አለ፡፡)  
ስሙኝማ...ይሄ የ‘ታሪክ ትረካ’ ነገር የምር ቅልጥ ያለው ‘ግርግር’ ያለው እዛ ነው፡፡ ልክ ነዋ....አንደኛው ወገን ጀግና ያደረገውን ሌላኛው ውጉዝ ከመአርዪስ ይለዋል፡፡ አንዱ  ሀገርን ያለማ፣ ሀገር ወዳድ የሚለውን፤ሌላኛው ሀገር ያጠፋ ባንዳ ይለዋል፡፡ እናላችሁ...አለ አይደል...እንደዚህ አይነት ነገሮች ከዘጠነኛው ድራፍት በኋላ የሚመጣ ንትርክ ሳይሆን የበቁ፣ የነቁ በእውቀት ‘ቃ’ ያሉት የሚባሉት በጽሁፍ የሚያስቀምጡትና በየሚዲያው ሊታበዩ የሚሞክሩበት ነው፡፡ የ‘ግርግር’ ነገር ሆኖ ነው እንጂ ልማትም ሆነ ጥፋት በዓይን የሚታዩ ነገሮች ሆነው ሳለ...አለ አይደል... እንዴት “አንተ፣ አንቺ” ሊያባብሉ ይችላሉ?
ስሙኝማ....አንድ ግን ዓለም እውቅና ሊሰጠን የሚገባ ነገር አለ፡፡ አለ አይደል...ታሪክ የሚባል ነገር ከተጀመረ አንስቶ ከዜጎቿ 92.5% የታሪክ ሊቅ የሆነባት ብቸኛዋ ሀገር ማን ትመስላችኋለች? - የእኛይቱ ነቻ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1905 times