Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 04 August 2012 09:30

የጨው ክምር ሲፈርስ ሞኝ ያለቅስ፤ ብልህ ይልስ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

እንደ “ናብሊስ” መጽሐፍ አገላለፅ፤ “ሩቢኮንን ማቋረጥ” የሚለው አባባል ዛሬ ያነጋገር ፈሊጥ ሆኗል፡፡ ወደ ማይመለሱበት ወይም ወደማይሻገር ውሳኔ ላይ ተደረሰ እንደማለት ነው፡፡ ይህ አነጋገር ዕውነተኛ የታሪክ መሠረት አለው፡፡ እነሆ፡-

ጥንት የሮማንና የፈረንሣይን ድንበር የሚለይ ሩቢኮን የሚባል ወንዝ ነበር፡፡ ይህንን ወንዝ ተሻግሮ ወደ ሮም ለመግባት ለራሳቸው ለሮማውያን ጀነራሎች እንኳ ከጠቅላይ ምክር ቤቱ ልዩ ፈቃድ ያስፈልግ ነበር፡፡ ይህ ፈቃድ ሳይኖር የሩቢኮንን ወንዝ ማቋረጥ ማለት በሮም ላይ ጦርነት እንደማወጅ ይቆጠራል፡፡ ስለዚህ በጥንት ዘመን ጁሊየስ ቄሣር ሠራዊቱን ይዞ ሩቢኮንን በማቋረጡ ከራሷ ከሮም ጋር ፍጥጫ ውስጥ ገብቶ ነበር ይባላል፡፡

ሮማ በዚያን ዘመን ገናና ነበረች፡፡ ብዙ አገሮችን በጦር አስገብራለች፡፡ ጁሊየስ ቄሣር የተባለው ጀነራል ለዚህ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ በርካታ ያውሮፓ አገሮችን በሮም ቁጥጥር ሥር አውሏል፡፡ ሠራዊቱም ኃይለኛ ነበር፡፡ ቄሣርና ሠራዊቱ ሮምን ለዘጠኝ ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ሆኖም ቄሣር በሮማ ብዙ ጠላቶች ነበሩት፡፡ ጀግንነቱንና በህዝቡ ዘንድ መወደዱን የፈሩ ነበሩ፡፡ ገናናነቱ ከፍተኛውን ስልጣን እንዲያስብ ያደርገዋል በሚል የሚሰጉ ነበሩ፡፡ ከነዚህ አንዱ የሮም የአንደኛው ሠራዊት አዛዥ ፖምፔ የሚባለው ነው፡፡ ሆኖም የፖምፔ ሠራዊት ምንም ሳይሠራ ከተማ ውስጥ የሰፈረ በመሆኑ በሮማውያን አይከበርም ነበር፡፡ በዚህ በመናደዱም ፈጣር እርምጃ ካልተወሰደ በሚቀጥለው ዓመት ቄሣር ወደ ሮም ተመልሶ የሮም ገዢና የእሱም የበላይ አዛዥ ሆኖ በህዝብ ይመረጣል የሚል ሥጋት ገባው!

ስለዚህ በምክር ቤቱ ካሉ ሌሎች የቄሣር ተቀናቃኞች ጋር ሆኖ ደባ አውጠነጠነ፡፡ በአስቸኳይ ቄሣር ወደ ሮም እንዲመለስ ተላከበት፡፡

ቄሣር ግን ደባው ገብቶታልና በአስቸኳይ የሚወዳቸውን ብርጌዶች ጠራና የጠረጠረውን ነገራቸው፡፡ የሠራዊቱን አባላት ሮም ውስጥ የተሸሸጉት ጥቂት ሐሞተ-ቢስ ቢሮክራቶች ያውጠነጠኑት ደባ ደማቸውን አፈላው፡፡ የሩቢኮንን ወንዝ ካቋረጡ በፖምፔና በሸንጎው ላይ ጦር እንደ መምዘዝ መሆኑን ያቃሉ፡፡ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ሊለወጥም ይችላል፡፡ ይህ ደሞ ሮማን ለባሰ ጥፋት ሊዳርግ ይችላል፡፡ ቄሣር ሆዬ “በሉ እንግዲህ ጎበዝ ምረጡ! ሩቢኮንን እናቋርጥ አናቋርጥ?” ሲል ጠየቀ፡፡ “እናቋርጣለን!... ከእንግዲህ ወደ ኋላ መመለስ የለም!” አለ ቄሣር፡፡ ዜናው ለህዝቡ ደረሰ! ህዝቡ የሚወደውን ጀግና ለመቀበል ወጣ፡፡ “ቄሣር ሩቢኮንን አቋረጠ!” የሚለው ቃል ከዳር ዳር አስተጋባ! የተፈራው ሽኩቻ ይመጣል የተባለው ሮም ደጃፍ ላይ ነበር፡፡ ሆኖም አንድም ተቀናቃኝ ጠፋ! ፖምፔና ተከታዮቹ እንደጉም በንነዋል!

ከላይ የጠቀስነው ታሪክ ከሁለት ሺ ዓመታት በላይ ሲነገር ኖሯል፡፡ ዛሬ ተረት ይምሰል እንጂ የሰው ልጆች ብዙ ሩቢኮኖች ከፊታቸው መደቀናቸውንና ወይ በድፍረት መሻገር፡፡ አሊያም በፍርሃት ወደ ኋላ መመለስ ምርጫቸው መሆኑን ያፀኸይልናል! ጀምስ ባልድዋን የተባለው ደራሲ ይህንን ታሪክ የመልካም ሥነ ምግባር የቆራጥነት መማሪያ አድርጎ ነው የፃፈው፡፡ ለህይወት ውጣ-ውረድ ዝግጁ እንድንሆን ነው የሚያሳስበን፡፡ ቤት ተቃጠለ ብለን ከምንጮህ እሳቱን ለማጥፋት ምን እናድርግ? አልጠፋ ብሎ እኛ ቤት ቢደርስስ ምን እናደርጋለን? በተቀጣጠለው እሳት ላይ ቤንዚን መጨመር ወዴት ያደርሰናል? እያልን እንድንመካከር እንድንወስን ነው የሚጠቁመን፡፡ ለዚህስ ምን ያህል ዝግጁ ነን? ብሎ ነው የሚጠይቀን፡፡  “ያባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ” ማለት ተገቢ ነውን?” ብሎ ማውጠንጠን የመልካም ዜጋን ኃላፊነት ማስተዋል ነው፡፡

ባህር ዳር ከተማ አንድ “ባህል ቤት” (አዝማሪ ቤት እንደ አዲሳባው አጠራር) አንዱ አዝማሪ ተጫወቶ ሲጨርስና የሚተካው አዝማሪ ሊተካው ሲመጣ፤ “በሉ እንግዲህ እኔ ልሰናበት - ምቀኛዬ መጣ!” ይላል አሉ፡፡ በሰላም መሰነባበት ቀላል እንዳልሆነ የሚነግረን ነገር አለው ይሄ አባባል፡፡ ወደ አገር ሰፋ አድርገን ማየት ነው፡፡ ሀገራችን ብዙ ሩቢኮኖችን ሰንጥቃ ማለፍ አለባት፡፡ ለዚህም እኛ ልጆቿ አርቀን ማስተዋል ይገባናል፡፡ እኛ አገር፤ በሰላም ተጨባብጦ መለያየት ከባድ መሆኑን መናገር ብቻ ሳይሆን ከእኛስ ምን ይጠበቃል? ብሎ መጠየቅ ያባት ነው፡፡ “በንፋስ የሚሰራ ወፍጮ ተፈለሰፈኮ!” ሲሏት “ለእኔ ምን ለውጥ ያመጣል - እኔ እንደሁ መሸከም አይቀርልኝ!” ካለችው የፈረንሣይ አህያ የተሻለ ማሰብ ይጠበቅብናል፡፡ “አምሣም ታለበ መቶ ያው በገሌ ነው” ከምትለው ኢትዮጵያዊ ድመት የተሻለ የባለቤትነት ስሜት ሊኖረን ይገባል፡፡ ምሬትና ብሶት በብስለት ሊያዝ ይገባል እንጂ ያለቀልብ በትኩሳት (emotionalism) ቢያደነባብረን ከቶም ማጣፊያው እንዲያጥረን ነው የሚያደርገው፡፡ “አትሩጥ እንጋጥ!” ማለት ይበጃል፡፡ ምዝበራ ሲበዛ ምን መደረግ አለበት? ማለት፣ ፕሬስ አደጋ ላይ ቢወድቅ ምን መደረግ አለበት? ማለት፤ በሥልጣን መባለግ ቢበዛ ምን ይሻላል ጐበዝ? መባባል፤ የሚለውን የገጣሚ ኑረዲን ኢሣን ግጥም ያስታወሷል፡፡ አስተዋይ ዜጋ ሁኔታዎችን በውል ያጤናል፡፡ የሚያልፍ የሚመጣውን ይመረምራል፡፡ በሚሆነው ውስጥ ከኔ ምን ይጠበቃል? ለዚያስ ምን ያህል ዝግጁ ነኝ ይላል፡፡ በማንኛውም ነገር ሳቢያ ምንም ዓይነት ነገር ቢከሰት ሳይደነጋገሩ ለመጓዝ ቆም ብሎ የሥነ ምግባር ጥንካሬ፣ የፖለቲካ ሱባዔና የኢኮኖሚ ማረጋጊያ ስልትን ማጤን ዛሬም ተገቢ ነው፡፡ “የጨው ክምር ሲፈርስ ሞኝ ያለቅስ፤ ብልህ ይልስ!” የምንለው ለዚህ ነው!!

 

 

Read 4616 times Last modified on Saturday, 04 August 2012 09:42