Saturday, 10 October 2020 11:55

አርቲስት ዳኜ ዋለና "ሆፕ ኢንተርቴይመንት" ፍጥጫ ላይ ናቸው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

 የ7 ሚሊዮን .ተመልካች ክፍያ አልተፈጸመልኝም ብሏል
                             
             "ሆፕ ኢንተርቴይመንት" በሙዚቀኞች ላይ የሚያደርሰውን ግፍና በደል በአስቸኳይ እንዲያቆም አርቲስት ዳኜ ዋለ አስጠነቀቀ፡፡ ድምፃዊው እ.ኤ.አ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ከድርጅቱ ጋር ለስድስት ዓመታት በደንበኝነት መዝለቁን ገልፆ፤ ባለሙያ የደከመበትን ሥራ በውሉ መሰረት በአግባቡ ካለመክፈሉም በላይ በተለይ ከክፍለ ሀገር የሚመጡ ሙዚቀኞችን ክፍያ ሙሉ በሙሉ በመከልከል በቀጠሮ በማመላለስና ተስፋ በማስቆረጥ የውንድብድና ሥራ እየሰራ ነው ሲል አማሯል፡፡
“እኔ እስካሁን ወደ 7 ሚሊዮን የሚደርስ ተመልካች ክፍያ አልተከፈለኝም፡፡ በዚህም ትዕግስቴ እያለቀ ነው" ሲል አርቲስት ዳኜ ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡
አዲስ አድማስ በሆፕ ኢንተርቴይመንት በደል ደርሶብናል የሚሉ የተለያዩ አርቲስቶችን ያነጋገረ ሲሆን አብዛኞቹ “ሆፕ” እንደ ስሙ ተስፋ ነው ብለን ሥራችንን ብንሰጠውም፣ ምንም አያመጡም በሚል ክፍያም አልፈጸመልንም ሲሉ ከስሰዋል፡፡  
በሆፕ ኢንተርቴይንመንት ከ2.ሚ በላይ ተመልካች እንዳላት የገለፀችውና ስሜ አይጠቀስ ያለችው አንዲት ድምፃዊት፤ ድርጅቱን ምን እንደማደርገው ግራ ገብቶኝ ቁጭ ብያለሁ ብላለች። ያነጋገርናቸው በርካታ ድምፃዊያን በቀጣይ ተሰብስበው ብሶታቸውን ለተለያዩ ሚዲያዎች እንደሚገልፁም አስታውቀዋል፡፡ አቶ ብሩክ ለተባሉ የሆፕ ኢንተርቴይመንት የአገር ቤት ተወካይ ስልክ ደውለን ስለ ጉዳዩ ብንጠይቃቸውም፣ በስልክ ሳይሆን ቢሯችን ድረስ መጥታችሁ አነጋግሩን የሚል ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ በተሰጠን ቀጠሮ መሰረትም፤ ቦሌ ሞሪኒንግ ስታር ሞል የሚገኘው ቢሯቸው ብንሄድም፣ ቢሮው ዝግ በመሆኑ ልናገኛቸው አልቻልንም፡፡ የሆፕ ኢንተርቴይመንት ሃላፊዎችን ምላሽ በማንኛውም ጊዜ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናችንን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡  


Read 1597 times