Saturday, 28 July 2012 12:18

xxx ኦሎምፒያድ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(18 votes)

በዝግጅት 7 ዓመት የፈጀውና  14.5 ቢሊዮን ዶላር ወጭ የሆነበት 30ኛው ኦሎምፒያድ ትናንት ተከፈተ፡፡ 205  አገሮችን የወከሉ 10500 አትሌቶች የሚሳተፉበት ኦሎምፒኩ በፉክክር ደረጃው፤ በመወዳደርያ ስፍራዎቹ ጥራት፤ በቴክኖሎጂ ግብዓቶቹ፤ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በተለይ በሶሻል ሚዲያ መድረኮች በሚኖረው ሽፋን ገዝፏል፡፡  ከ4 ዓመት በፊት ቤጂንግ ባስተናገደችው 29ኛው ኦሎምፒያድ 86 አገራት በሜዳልያ ሰንጠረዥ ገብተው በተለያዩ የውድድር መደቦች 43 የዓለም ሪኮርዶች እንዲሁም 132 የኦሎምፒክ ሪከርዶች ተመዝግበው ነበር፡፡ በለንደን ኦሎምፒክም ሜዳልያ የሚያገኙ አገራት ብዛት እንደሚጨምር ሲጠበቅ በተለይ በአትሌቲክስ ውድድሮች አዳዲስ የዓለምና የኦሎምፒክ ሪከርዶች እንደሚኖሩ ግምት በመሰጠት ላይ ነው፡፡

ሶሻል ኦሎምፒክስ የተባለው 30ኛው ኦሎምፒያድ በተለያዩ የሶሻል ሚዲያ መድረኮች በሚያገኘው ሽፋን በውድድሩ ታሪክ አስደናቂ ትኩረትንም አግኝቷል፡፡ በኦሎምፒኩ ከ218ሺ በላይ ጋዜጠኞች፤ ፎተግራፈሮች፤ ካሜራማኖች፤ የስቱዲዮ ቴክኒሽያኖች ከ180 አገራት ተሰባስበው ለንደን ገብተዋል፡፡

ኢትዮጵያና የኦሎምፒክ ገድሎቿ

የመጀመርያው ኦሎምፒክ በግሪኳ አቴንስ ከ116 ዓመታት በፊት 14 አገራት ተሳታፊ ሆነውበት ሲጀመር አንድ ወር ቀደም ብሎ ኢትዮጵያ በዳግማዊ ምኒልክ እየተመራች በቅኝ ለመያዝ የወረረቻትን ጣሊያን በአድዋ ድል አድርጋ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ 60 ዓመታት አልፈው ኢትዮጵያ  በታላቁ የኦሎምፒክ መድረክ በ1956 እኤአ ላይ በአውስትራሊያዋ ከተማ ሜልቦርን ለመጀመርያ ግዜ ለመሳተፍ በቅታለች፡፡ ከአፍሪካ ተሳታፊ የሆኑት ሌሎቹ አገራት ጋና፤ ላይቤርያና ደቡብ አፍሪካ ነበሩ፡፡ በወቅቱ እንደነገሩ ተመስርቶ የነበረው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ተሳታፊ ኦሎምፒያኖቹን የመለመለው ከጦር ሃይልና ከተለያዩ የስፖርት ክለቦች ነበር፡፡ ከመጀመርያዎቹ የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች በብስክሌት ውድድር ተሳታፊ የነበሩት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የተገኙት ምርጡ ብስክሌተኛ ገረመው ደንቦባ እና የማራቶን ሯጩ ባሻዬ ፈለቀ ይታወሳሉ፡፡ በማራቶን ኢትዮጵያን በመወከል እንዲወዳደሩ የተመረጡ እና አስገራሚ ታሪክ ያላቸው ሁለት ኦሎምፒያኖችም የታሪክ መዛግብት ያስታውሳቸዋል፡፡ እነዚህ ሁለት ማራቶኒስቶች የአዲስ አበባው ጋሻው እና ከማይጨው የተገኘው ብርሃኑ ነበሩ፡፡ ሁለቱ አትሌቶች በንጉሳዊ ስርዓቱ ለኦሎምፒክ እንዲዘጋጁ በተሰጠ መመርያ ለአገራቸው የሜዳልያ ክብር ካስገኙ ብሄራዊ ጀግኖች ተብለው ትልቅ የክብር ሽልማት እንደሚያገኙ ቃል ተገብቶላቸው ነበር፡፡ ስለሆነም ሁለቱ ኦሎምፒያኖች ለኦሎምፒኩ ዝግጅት ሲያደርጉ በታላቅ ወኔ ነበር፡፡ ጋሻው ከደብረዘይት ናዝሬት በተጨማሪም በሰበታ የገጠር መንገዶች አያሌ ኪሎሜትሮችን ሲሸነሽን ይታይ ነበር፡፡ ብርሃኑ በበኩሉ በማይጨው መስኮች ሰፊ ርቀት እየሸፈነ ሲለው ደግሞ የአምባላጌ ተራራን ሽቅብ እየጋለበ ዝግጅቱን ያጧጡፍ ነበር፡፡ ጋሻውና ብርሃኑ ከሜልቦርን ኦሎምፒክ ተሳትፏቸው በተያያዘ ሁለት ጓደኞቻቸውን ተዋወቁ፡፡ እነሱም አበበ ቢቂላ እና ማሞ ወልዴ ነበሩ፡፡ አበበ እና ማሞ በማራቶን መወዳደር ቢኖርባቸው በሜልቦርን ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን ወክለው ለመሰለፍ የበቁት በ100ሜትር ውድድር ነበር፡፡ በማራቶን የተወዳደሩት ጋሻውና ብርሃኑ 17ኛና 19ኛ ደረጃ አግኝተው በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ የመጀመርያ ተሳትፎ አመርቂ የሚባል ወጤት አገኙ፡፡ ከ4 ዓመታት በኋላ በ1960 እኤአ ላይ ኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ተሳትፏዋን በወርቃማ ድል ጀመረች፡፡ በወቅቱ የክቡር ዘበኛ ታማኝ ወታደር የነበረው አበበ ቢቂላ ሮም ባስተናገደችው ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ ሮጦ ማራቶንን አሸነፈ፡፡ አፍሪካ ዓለምን በአትሌቲክስ ማሸነፍ የጀመረችው በዚህ ታሪካዊና ፈርቀዳጅ የኢትዮጵያ ኦሎምፒያን ድል ነበር ፡፡አበበ በሮም ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ በታላቅ ግርማ ሞገስ መሮጡ ብቻ ሳይሆን የዓለም ሪከርድን መስበሩ ያስገረመ ነበር፡፡ በወቅቱ ውድድሩን ካሸነፈ በኋላ 42 ኪሎሜትር የሮጠ ሳይመስል አስደናቂ ጅምናስቲክ በመስራት በስታድዬም የነበረ ስፖርት አፍቃሪን ልብ የገዛ  ትእይንት ያሳየ ጀግና አትሌት ነበር፡፡  ከ4 ዓመታት በኋላ በ1964 እኤአ ላይ በቶኪዮ ኦሎምፒክ አበበ ቢቂላ በማራቶን በድጋሚ አሸንፎ ክብሩን አስጠበቀ፡፡  እስከዛሬም ድረስ በሁለት ተከታታይ የኦሎምፒክ ውድድሮች በማራቶን ያሸነፈ አትሌት አልተፈጠረም፡፡ በቶኪዮ ማራቶን በድጋሚ የዓለም የማራቶን ሪከርድን በመስበር ለሁለተኛ ግዜ በማራቶን ያሸነፈው አበበ ቢቂላ ይህ ድሉን በትርፍ አንጀቱ ላይ ቀዶ ጥገና ካደረገ ጥቂት ሳምንታት በኋላ በማስመዝገቡ መላው ዓለምን  ጉድ ያሰኘ ነበር፡፡

ከአበበ  ቢቂላ በኋላ የኢትዮጵያ የማራቶን ክብር በሶስተኛው ተከታታይ ኦሎምፒክ ያስጠበቀ አትሌት ማሞ ወልዴ ነበር፡፡  በ1968 እ.ኤ.አ በሜክሲኮ ከተማ ማሞ ወልዴ የአበበን ዱካ በመከተል በማራቶን የወርቅ ሜዳልያ ሲያሸንፍ በ43 አመቱ መሆኑ አነጋጋሪ ነበር፡፡ ከእነዚህ ሶስት ተከታታይ የኦሎምፒክ ማራቶን ድሎች በኋላ ኢትዮጵያ ማራቶን ልእልቷን እየዘመረች ለሌላ የኦሎምፒክ ወርቃማ ገድል የበቃች ከ3 የኦሎምፒክ ውድድሮች በኋላ ነበር፡፡ በ1980 እኤአ ላይ ደግሞ በሞስኮ ኦሎምፒክ በረጅም ርቀት ሩጫ አዲስና ፈርቀዳጅ ታሪክ ተሰራ በወቅቱ ምሩፅ ይፍጠር በ10ሺና 5ሺ አሸንፎ ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን በመጎናፀፍ አዲስ ምእራፍ ሊከፍት በቃ፡፡ በአስደናቂ የአጨራረስ ብቃቱ ማርሽ ቀያሪው በሚል ስያሜ ለመወደስ የበቃው ምሩፅ ይፍጠር በኦሎምፒክ ታሪክ በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር ውድድሮች ድርብ የወርቅ ሜዳልያዎችን በማግኘት የመጀመርያው አትሌት ነበር፡፡

ከምሩፅ በኋላ የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ታሪካዊ ውጤታማነት ከበርካታ ዓመታት በኃላ 1992  እኤአ ላይ ባርሴሎና ላይ ነበር፡፡ በዚህ ኦሎምፒክ  ላይ ኢትዮጵያዊቷ ኦሎምፒያን ደራርቱ ቱሉ በ10 ሺ ሜትር አሸንፋ በርቁ የመጀመርያውን የወርቅ ሜዳልያ ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ በመውሰድ ታሪክ ሠራች፡፡

ከ4 ዓመታት በኋላ በ1996 እኤአ ላይ  በአትላንታ ኦሎምፒክ ሌላ አዲስ ታሪክ  በኢትዮጵያዊቷ ኦሎምፒያን ፋጡማ ሮባ ተመዘገበ፡፡ ፋጡማ ሮባ በማራቶን አሸንፋ የወርቅ ሜዳልያውን በመጎናፀፍ  ለኢትዮጵያና ለአፍሪካውያን ፈርቀዳጅ ሆኖ የሚጠቀስ ታሪክ ሰራች፡፡ በአትላንታ ሌላ ትልቅ ኦሎምፒያንም ከኢትዮጵያ ወጥቷል፡፡ በዓለም አቀፍ የረዥም ርቀት አትሌቲክስ ውድድሮች የምንግዜም ምርጥ  አትሌት ለመሆን የበቃው ኃይሌ ገብረስላሴ ነበር፡፡ ኃይሌ በአትላንታ ኦሎምፒክ የ10 ሺ ሜትር ሪኮርድ በመስበር አሸንፎ የርቀቱን ክብር ከሶስት ኦሎምፒኮች በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሊመልሰው ለወርቅ  በቃ፡፡ በ2000 እኤአ ላይ በሲዲኒ አውስትራሊያ በተካሄደው ኦሎምፒክ  ኢትዮጵያ በታሪክ ከፍተኛ የሆነውን ውጤት አስመዘገበች፡፡ በ10ሺ ሜትር ዓለም ምንግዜም በማይረሳው ትንቅንቅ ኬንያዊውን ፓልቴርጋት እስከመጨረሻው የድል መስመር ተፎካክሮ በ9 ማይክሮ ሰከንዶች ልዩነት በመቅደም ለሁለተኘ ተከታታይ ኦሎምፒክ ኃይሌ ገብረስላሴ የወርቅ ሜዳልያውን ተጎናፀፈ፡፡ ደራርቱ ቱሉ በአስደናቂ የአሯሯጥ ውበት በ10ሺ ሜትር ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳልያ ወሰደች፡፡ በዚሁ የሲድኒ ኦሎምፒክ ግን ሌሎች ትልልቅ ታሪኮችም ነበሩ፡፡ ከ42 ዓመታት በኃላ የማራቶንን ክብር  ሊመለስ የበቃው በገዛሀኝ አበራ ድል ነበር፡፡ ሚሊዮን ወልዴ በኩሉ በ5 ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ሀገሩን አስጌጠ፡፡

የኦሎምፒክ ጀግኖችን በማፍራት የማትነጥፈው ኢትዮጵያ በ2004 እኤአ ላይ  አቴንስ ባዘጋጀችው 28ኛው ኦሎምፒያድ  አዳዳዲስ ኦሎምፒያኖች አስተዋወቀች፡፡ የመጀመርያው በሴቶች 5 ሺ ሜትር በአትሌት መሠረት ደፋር አማካኝነት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ነው፡፡ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ደግሞ በሁለት ተከታታይ ኦሎምፒኮች በኃይሌ ገብረስላሴ የተገኘውን የወርቅ ሜዳልያ ክብር ባስጠበቀ የበላይነት ለራሱ የመጀመርያን የኦሎምፒክ ሻምፒዮናነት ክብር ተጎናፀፈ፡፡ ጥሩነሽ ዲባባም የአክስቷን ደራርቱ ቱሉ ዱካ ተከትላ በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ወሰደች፡፡

ከ4 ዓመት በፊት ደግሞ በ10ሺ እና  በ5ሺ ሜትር ውድድሮች ቀነኒሳ በቀለና ጥሩነሽ ዲባባ እያንዳንዳቸው ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን በመውሰድ በኦሎምፒክ ታሪክ በምሩፅ ይፍጠር የተሰራውን ክብረወሰን በመስተካከል ኢትዮጵያዊ ብቸኛ የዓለም አትሌቶች ሆኑ፡፡

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በ11 ኦሎምፒኮች በ4 የአትሌቲክስ ስፖርቶች በ44 ውድድሮች ላይ ተሳትፎ ነበሯት፡፡ 185 ኦሎምፒያኖቿን ባሰለፈችባቸው በእነዚህ 11 ኦሎምፒያዶች  38 ሜዳልያዎች (18 ወርቅ 6 ብርና 14 ነሐስ) ሰብስባለች፡፡ ከእነዚህ የሜዳልያ ድሎች ብዙዎቹ ለአፍሪካውያን ፈር የቀደዱና በዓለም የአትሌቲክስ ስፖርት አዳዲስ ክብረወሰኖችን የፈጠሩ  ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ተስፋዎች

በ30ኛው የለንደን ኦሎምፒያድ ላይ የተለመደው ፈርቀዳጅ እና ታሪካዊ ጀግንነት ከኢትዮጵያውያኑ ኦሎምፒያኖች ይጠበቃል፡፡ ኢትዮጵያ በለንደን ኦሎምፒክ ተሳትፏዋ በታሪኳ ከፍተኛውን ውጤት ልታስመዘግብ እንደምትችል ግምት ተሰጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ 4 የወርቅ 4 የብርና 4 የነሐስ ሜዳልያዎችን ለማግኘት በማቀድ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በለንደን ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ በመካከለኛ ርቀት የ800 እና የ1500 ሜትር ውድድሮች  ለሜዳልያ ተፎካካሪነት ብቁ የሆኑ አትሌቶች ማሰማራቷ ተሳትፏዋን ልዩ ያደርገዋል፡፡ በኦሎምፒክ ቡድኑ አንጋፋ እና ከሁለት በላይ ኦሎምፒኮችን የሚሳተፉ፤ በኦሎምፒክ የመጀመርያ ተሳትፏቸወን የሚያደርጉ አዳዲስና ወጣት አትሌቶች መኖራቸውም የተለየ ነው፡፡

በለንደን ኦሎምፒክ በአትሌቲክስ ከሚጠበቁ ውድድሮች ፈታኙ እና አስቸጋሪው የ10ሺ ሜትር ውድድር ነው፡፡ በዚሁ የውድድር ርቀት በሁለቱም ፆታዎች የተመዘገቡት የኦሎምፒክ ሪከርዶች የኢትዮጵያውያኑ ኦሎምፒያኖች ጥሩነሽ ዲባባ እና የቀነኒሳ በቀለ ናቸው፡፡ በ2004 እኤአ በአቴንስ፤ በ2008 እኤአ በቤጂንግ በ10ሺ ሜትር አከታትለው በማሸነፍ የኦሎምፒክ ሻምፒዮናነታቸውን በማስጠበቅ ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎን የወሰዱት ጥሩነሽ ዲባባ እና ቀነኒሳ በለንደን ኦሎምፒክ በ10ሺ የወርቅ ሜዳልያ ሃትሪክ ለመስራት ያነጣጥራሉ፡፡

ለንደን ላይ በ10ሺ ሜትር ሴቶች ውድድር ለሜዳልያ በሚኖረው ትንቅንቅ ዋናዎቹ ተፎካካሪዎች የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች ናቸው፡፡ በተለይ በጥሩነሽ ዲባባ እና በቪቪያን ቼሮይት የሚደረገው ፉክክር በጉጉት የሚጠበቅ ይሆናል፡፡ በ10ሺ ሜትር ውድደሩ ኢትዮጵያን የሚወክሉት ሌሎቹ ሴት ኦሎምፒያኖች ደግሞ ወርቅነሽ ኪዳኔ እና በላይነሽ ኦልጅራ ናቸው፡፡

በወንዶች 10ሺ ሜትር ለንደን ላይ ለሚኖረው የሜዳልያ ትንቅንቅ ቀዳሚ ግምቱን የወሰደው ቀነኒሳ በቀለ ነው፡፡ መላው ዓለምን ያጓጓው ግን በርቀቱ ቀነኒሳ ከታናሽ ወንድሙ ታሪኩ በቀለ ጋር የሚገባው ፍጥጫ ሆኗል፡፡ አዘጋጇን እንግሊዝ በመወከል የሚሰለፈው ትውልደ ሶማሊያዊው ሞ ፋራህም ወንድማማቾቹን በሜዳውና በደጋፊው ፊት ጉድ ለመስራት እንደተጠበቀ ነው፡፡ በ10ሺ ሜትር ውድድሩ የዘንድሮውን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን በመምራትና በመወከል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገው ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም በተቀናቃኝነት ይሰለፋል፡፡

በ5ሺሜትር ሴቶች ያለፈው ኦሎምፒክ ሻምፒዮና ጥሩነሽ ዲባባ ተጠባባቂ መደረጓ አስጨናቂ ቢሆንም በ2004 እኤአ በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ታሪክ የመጀመርያውን የ5ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ በማስገኘት ፈርቀዳጅ ታሪክ የሰራችው መሰረት ደፋር ለሁለተኛ የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያዋ ስኬት ከባድ ተጋድሎ ማሳየቷ አይቀርም፡፡ በ5ሺ ሜትር ውድድሩ ለኢትዮጵያውያኑ ኦሎምፒያኖች የሜዳሉ አደን ስጋት የምትፈጥረው በዋናነት የኬንያዋ የአለም ሻምፒዮን ቪቪያን ቼሮይት ትሆናለች፡፡

በወንዶች 5ሺ ሜትር ምንም እንኳን የቀነኒሳ ተሳታፊ አለመሆን በለንደኑ ኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያው እድል ወደ ኬንያ አትሌቶች ፤ወደ አሜሪካዊው በርናንድ ላጋትእና ወደ እንግሊዛዊው ሞ ፋራህ  ያጋደለ ቢመስልም የመጀመርያ የኦሎምፒክ ተሳትፏቸውን የሚያደርጉት ሁለት አዳዲስ የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች ግምት እያገኙ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለት አትሌቶች በዘንድሮው የዳይመንድ ሊግ ውድድር 1ኛ እና ሁለተኛ ደረጃ የያዙት ደጀን ገብረመስቀልና ሃጎስ ገብረህይወት ናቸው፡፡ ሁለቱ የኢትዮጵያ አዳዲስ ኦሎምፒያኖች እና ከሌላው አዲስ ኦሎምፒያን የኔው አላምረው ጋር በማራኪው የ5ሺ ሜትር ውድድር በድንቅ የቡድን ስራ እና የአጨራረስ ብቃት ታሪክ መስራታቸው የሚጠበቅ ይሆናል፡፡

በ800 ሜትር ወንዶች ለኢትዮጵያ የሜዳልያ ተስፋ የሰነቀው  በርቀቱ በዓለም ሶስተኛ ደረጃ ያለው መሃመድ አማን ነው፡፡ ከ4 መት በፊት ቤጂንግ ላይ በርቀቱ የወርቅ ሜዳልያ ያስገኘውን ኬንያዊ ዊልፍሬድ ቦንጊ ታሪክ ለመድገም ከፍተኛ ግምት የተሰጠው የዓለም ሪከርድን የያዘውና የወቅቱ ያለም ሻምፒዮን  ዴቪድ ሩዲሻ ነው፡፡ በሜዳልያ ትንቅንቁ ለወርቁ ቅድሚያ ግምት ከተሰጠው የኬንያው ዴቪድ ሩዲሻ ባሻገር ኢትዮጵያዊው መሃመድ አማን፤ ሱዳናዊው አቡበከር ካኪ፤ የአሜሪካው ኒክ ሳይመንድስ የእንግሊዙ አንድሪው ኦሳጌ እና የደቡብ አፍሪካና የራሽያ አትሌቶችም ተጠብቀዋል፡፡በኦሎምፒክ የኢትዮጵያ ተሳትፎ ታሪክ የመጀመርያ የሜዳልያ ድል ለማስመዝገብ ከባድ ትንቅንቅ የሚጠብቀው መሃመድ አማን የኬንያውን ዴቪድ ሩዲሻ ያሸነፈ ሲሆን ለንደን ላይ ይህን ስኬቱን ለመድገም ተስፋ ያደርጋል፡፡ በ800 ሜትር ሴቶች ውድድር ላይ በለንደን ለሜዳልያ ድል ከፍተኛ ግምት የተሰጣት ፋንቱ ሚጌሶ ናት፡፡ በዚህ ርቀት ከ4 መታት በፊት ቤጂንግ ላይ ያስመዘገበችውን የወርቅ ሜዳልያ ድል ለማስጠበቅ ከፍተኛ ግምት የተሰጣት የኬንያዋ ፓሜላ ጄሊሞ ናት፡፡ የዓለም ሻምፒዮኗ ሩስያዊት ማርያ ሳቪኖቫ እና የደቡብ አፍሪካዋ ካስተር ሴማንያም ከወርቅ እሰከ ነሐስ ለሚኖረው ድል ግምት ያገኙ አትሌቶች ናቸው፡፡ በዘንድሮው የዳይመንድ ሊግ በዓለማችን አሉ የተባሉ ምርጥ የ800 ሜትር ሴት ሯጮችን በማሸነፍና የደረጃ ሰንጠረዡን በመምራት ድንቅ ብቃት ላይ የምትገኘው የኢትዮጵያዋ ኦሎምፒያን ፋንቱ ሚጌሶ በለንደን ማንኛውንም ሜዳልያ ለማግኘት ከቻለች ውጤቷ በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ተሳትፎ ታሪክ አዲስ እና ፈርቀዳጅ ስኬት ሆኖ ይመዘገባል፡፡

በ1500 ሜትር በሁለቱም ፆታዎች ለንደን ላይ የሜዳልያ ስኬት ለኬንያ እና ለራሽያ አትሌቶች ቅድሚያ ሲሰጥ ቢሰነብትም በተለይ በሴቶች ምድብ ኢትዮጵያውያኑ ኦሎምፒያኖች የዘንድሮውን ዳይመንድ ሊግ በነጥብ የምትመራው አበባ አረጋዊ እና ገንዘቤ ዲባባ ለወርቅ ሜዳልያው ዋና ተፎካሪ መሆናቸው አይቀርም፡፡

በለንደን ኦሎምፒክ ማራቶን ውድድር በሁለቱም ፆታዎች ከፍተኛ የበላይትነት እንደሚያሳዩ የተጠበቁት የኬንያ አትሌቶች ናቸው፡፡ ከኦሎምፒክ ዋንኛ ውድድሮች አንዱ በሆነው ማራቶን የውድድር ታሪክ ግን የየትኛውም አገር አትሌት ባልተጠበቀ ብቃት እና እድል የማሸነፍ እድል ይኖረዋል፡፡ ይሄው ሁኔታም ለኢትዮጵያውያኑ ኦሎምፒያኖች በድል ማንፀባረቅ ምክንያት ይሆናል፡፡ በለንደን ማራቶን ልእልቷን ወደ አገሯ ለመመለስ የሚጠበቁት የኢትዮጵያ ማራቶኒስቶች በውድድር ዘመኑ ትልልቅ የማራቶን ውድድሮችን ያሸነፉ፤ የዓመቱን ፈጣን ሰዓቶች ያስመዘገቡ፤ በወቅታዊ ብቃታቸውና በወጣትነታቸው ጥንካሬ የሚታይባቸውና በኦሎምፒክ መድረክ ለመጀመርያ ግዜ የሚሳተፉ አትሌቶች ናቸው፡፡ በለንደን የኦሎምፒክ ማራቶኒስቶች ሆነው ኢትዮጵያን በወንዶች የሚወክሉት በዱባይ ማራቶንን ከ1 እስከ 3 የወጡት   አየለ አብሽሮ፤ዲኖ ሰፈርና ማርቆስ ገነቴ፤ በሮተርዳም ማራቶን 2ኛ የሆነው ጌቱ ፈለቀ እንዲሁም በዱባይ ማራቶን አምስተኛ የወጣው  ታደሰ ቶላ ናቸው፡፡ በሴቶች ደግሞ የሮተርዳም ማራቶን አሸናፊዋ ቲኪ ገላና፤ በዱባይ ማራቶን ያሸነፈችው አሰለፈች መርጊያ 3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ያገኙት ማሩ ዲባባና የፓሪስ ማራቶንን ያሸነፈችው ትርፌ ፀጋዬ ተይዘዋል፡፡ ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ የሳትፎ ታሪኳ በማራቶን 5 ወርቅና 3 የነሐስ ሜዳሊያዎች መሰብሰቧ የሚታወስ ሲሆን የዘንድሮው የማራቶን ቡድን ሜዳልያዎች ለማግኘት ሰፊ ዕድል ይኖረዋል ተብሎ ይገመታል፡፡

የሜዳልያ ሰንጠረዡን አሜሪካ ወይስ ቻይና?

በዎልስትሪት ጆርናል ትንበያ መሰረት በ30ኛው ኦሎምፒያድ የሜዳልያ ሰንጠረዡን በመሪነት ለማጠናቀቅ ዋናው ፉክክር በቻይና በአሜሪካ መካከል ነው፡፡ ትንበያው ቻይና 40 የወርቅ ሜዳልያዎች በአጠቃላይ 108 በማግኘት አንደኛ ሆና እንደምታጠናቅቅ ሲገመት አሜሪካ በ38 የወርቅ ሜዳልያ በአጠቃላይ 92 በማግኘት ሁለተኛ ደረጃ ይኖራታል፡፡ በዩኤስኤቱዴይ በተሰራው ትንበያ አሜሪካ በ41 የወርቅና በአጠቃላይ በ88 ሜዳልያዎች ስብስብ  የመጀመርያ ደረጃ ሲተነበይላት  በ34 የወርቅ እና በአጠቃላይ 94 ሜዳልያዎች ቻይና ሁለተኛ ደረጃ ተገምቶላታል፡፡  የሆላንድ የስታትስቲክስ ኩባንያ ኢንፎስትራዳ በሰራው ትንበያ አሜሪካ በለንደን ኦሎምፒክ 36 የወርቅ በአጠቃላይ 83 ሜዳልያዎችን  በመሰብሰብ የሜዳልያ ሰንጠረዡን በመሪነት ልታጠናቅቅ ትችላለች፡፡ ቻይና በ32 የወርቅ በአጠቃላይ በ85 ሜዳልያዎ ሁለተኛ ደረጃ ታገኝም ይሆናል፡፡ በ30ኛው ኦሎምፒያድ አሜሪካ በ25 ስፖርቶች የሚሳተፉ 530 ኦሎምፒያኖችን ስታሳትፍ ቻይና በቤጂንግ ኦሎምፒክ 29 የወርቅ ሜዳልያዎችን ያገኙ አትሌቶችን ጨምሮ 396 ኦሎምፒያኖችን በ23 ስፖርቶች ታቀርባለች፡፡

የወርቅ ሜዳልያ ክብርና ዋጋ

ኦሎምፒክ የዓለም አገራትና ህዝቦቻቸውን በአንድ መንፈስ የሚያስተባብር መድረክ ነው፡፡ በስፖርት መድረኩ በድህነት የተጎሳቆሉ፤ በበቂ የስፖርት መሰረተ ልማት ዝግጅታቸውን ያላከናወኑ፤ በየአገራቸው ባሉ የፖለቲካ አለመረጋጋቶች የተረበሹ፤ በጦርነት እና በኢኮኖሚ ቀውስ የሚገኙ አገሮቻቸውን የወከሉ ኦሎምፒያኖች ሲሳተፉ ሁሉም አንድ ዓላማ ይኖራቸዋል፡፡ ይህ ዓላማ በሜዳልያ ክብር አገራቸውን ማኩራትና  ሰንደቅ አለማቸውን ማውለብለብ ነው፡፡ የኦሎምፒክ የሜዳልያ ክብር መጎናፀፍ  ደግሞ የየትኛውም የዓለም ስፖርተኛ ህልም እንደሆነ ይታወቃል፡፡በኦሎምፒክ ታሪክ ሙሉ ለሙሉ ከወርቅ የተሰሩ ሜዳልያዎች ለአሸናፊዎች ለመጨረሻ ግዜ የተሰጠው በ1912 እኤአ ላይ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ የኦሎምፒክ ሜዳልያዎች ገፅታ በአዘጋጅ አገራት የዲዛይን ፍላጎት እንዲሆን ቢፈቀድም ሜዳልያዎኙ የሚሰሩበት ማእድን በኦሎምፒክ ቻርተር መሰረት የሚዘጋጅ ይሆናል፡፡ በኦሎምፒክ ለ1ኛ እና ሁለተኛ ደረጃ የሚሸለሙት የወርቅና የብር ሜዳልያዎች 92.5 በመቶ የሚሰሩት ከብር  እንዲሁም 6 በመቶ ከመዳብ ነው፡፡ ለ3ኛ ደረጃ ተሸላሚዎች የሚሰጡት የነሐስ ሜዳልያዎ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ከነሐስ የተሰሩ ናቸው፡፡ የወርቅ ሜዳሊያዎች በ6 ግራም ወርቅ መለበጣቸው ግድ ነው፡ሁሉም ሜዳልያዎች ውፍረታቸው 3ሚሜ  ዲያሜትራቸው 60 ሚሜ መሆን አለበት፡፡ አንድ የወርቅ ሜዳልያን አቅልጦ ይሸጥ ቢባል ከ706 ዶላር ጀምሮ ዋጋ ይኖረዋል፡፡ በ30ኛው ኦሎምፒያድ 4700 ሜዳልያዎች ለተሸላሚዎች የተዘጋጁ ሲሆን በሜዳልያዎቹ ስራ 802 ሰራተኞች ተሳትፈዋል፡፡  ለኦሎምፒክ ሻምፒዮኖች የቀረቡ 302 የወርቅ ሜዳልያዎች 400 ግራም ይመዝናሉ፡፡

 

 

Read 12398 times Last modified on Saturday, 28 July 2012 12:34