Print this page
Saturday, 28 July 2012 11:09

የባዕድ ባህል ወረራ ኢትዮጵያዊነትን ሲፈታተን

Written by  በስለሺ ይልማ Sileshiyilma@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

የባዕድ ባህል በሀገራችን እንደ ሰደድ እሣት መስፋፋት ያስጨንቃል፡፡ ሀላፊነት የሚሰማቸው ውሱን የሚዲያ ተቋማት በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ፅሑፍ ባቀረቡ ቁጥር እኔም የበኩሌን ባልኩ እላለሁ፡፡ ለዚህ መጣጥፍ መነሻ የሆነኝ ሰሞኑን በአንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የተመለከትኩት ጉዳይ ነው፡፡ ስዋስቲካ በመባል የሚታወቀውን የናዚ ጀርመንን አርማ የላፕቶፑ ዩዘር አካውንት መግቢያ አነስተኛ ሣጥን ላይ ለጥፎ፣ በአደባባይ ሻይ ቡና የሚል የድህረ-ምረቃ ተማሪ መመልከቴ ነበር የመደንገጤም ሆነ የመገረሜ ምክንያት፡፡ ምንም እንኳን እ.ኤ.አ በ1930ዎቹ አዶልፍ ሂትለር የናዚ ፓርቲን ስልጣን ከመያዙ በፊት ስዋስቲካ፤ ቡዲዝምንና ሂንዱይዝምን በመሳሰሉ የጥንታዊ ሀይማኖቶች አርማነት ቢያገለግልም፤ የሁለተኛው የአለም ጦርነትን ተከትሎ ከናዚ ጀርመን ጋር በመቆራኘቱ የተነሣ የእኩይ ተግባር መገለጫ ሆኗል፡፡

በዚህም የተነሣ የጥላቻ ምልክትና ተምሣሌት ተቆጥሮ፣ አርማውን ለጥፈው የነበሩ ሕንፃዎች ሳይቀሩ እንዲያስወግዱት ተገደዋል፡፡ በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት የጀርመንና የኦስትሪያ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጎች ለትምህርታዊና ለምርምር ተግባር ብቻ ካልሆነ የስዋስቲካን አርማ በአደባባይ ማሳየት በህግ የሚያስቀጣ ወንጀል ነው፡፡

ታዲያ የሁለተኛ ዲግሪውን እየተከታተለ የሚገኘው ወጣት፣ ይህንን አርማ ደረቱን ነፍቶ በአደባባይ የሚያስተዋውቀው ትርጉሙን አውቆት ነው ወይስ ባለማወቅ? ባለማወቅ ከሆነ ለዚህ የትምህርት ደረጃ እንዴት ሊበቃ ቻለ? ምክንያቱም ይህንን አርማ ለማወቅ የታሪክ ምሁር መሆን አያስፈልግም፡፡ በዚህ የትምህርት እርከን ከፍተኛ ሀገራዊም ሆነ አለም አቀፋዊ እውነቶች ዙሪያ የበሰለና የዳበረ እውቀት ከመያዝም አልፎ ትንታኔና ማብራሪያ መስጠት ይጠበቅበታልና፡፡ ድርጊቱን አውቆ ነው የፈፀመው ተብሎ ቢታሰብ ደግሞ በአለም ታሪክ ተወዳዳሪ የማይገኝለትንና በርካታ ንፁሀንን የፈጀውን አረመኔውን ናዚ/ሂትለር ይወደዳል፣ ይደገፋል፣ በአደባባይም ይተዋወቃል የሚባል አይነት አይደለም፡፡ ወይንስ በአደባባይ የሚተዋወቅ ኢትዮጵያዊ ጀግና አሊያም ተቋምና ታሪካዊ ምልክት (አርማ) ጠፍቶ ነው? መልሱን ለግለሰቡና ለአንባቢያን እተወዋለው፡፡

ከላይ የጠቀስኩትን ገጠመኝ እንደምሳሌ አነሳሁ እንጂ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ኢትዮጵያዊ ባህላችንና ማንነታችን በማሽቆልቆል ላይ ይገኛል፡፡ የባዕድ ባህል ወረራ ጉዳዩ ያገባናል በሚሉ ሀገር ወዳድ ዜጎች በተለያዩ ወቅቶች በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ተወስቷል፡፡ ተደጋግሞ መነሳቱ መልካም ነው፡፡ በእኔ በኩል ጉዳዩ እንዳያሰለች በተቻለኝ መጠን ድግግሞሽን በማስቀረትና ከንድፈ-ሃሳባዊ ትንታኔ በመቆጠብ መሬት ላይ የወረዱ ማሳያዎች እጠቅሳለሁ፡፡

በዚህ ዘመን የሳተላይት ዲሽ እንደ አሸን ፈልቷል፡፡ ሊፈርሱ አንድ ሐሙስ የቀራቸው ደሳሳ ጎጆዎች ሳይቀሩ የዲሽ ሳህን አናታቸው ላይ አንጠልጥለው መታየታቸው ተለምዷል፡፡ የሳተላይት ዲሽ መስፋፋት ጠቀሜታ እንዳለው አይካድም፡፡ ጠንካራ የሚዲያ አማራጭ በሀገር ውስጥ ያለመኖር ለዲሽ መስፋፋት በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡ ሆኖም የኛን ባህልና ወግ ክፉኛ በመፈታተን ላይ ይገኛል፡፡ ዘወትር የሚገርመኝን ነገር እንደማሣያ ልጥቀስ፡፡ በተለያዩ የአረብ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እየተላለፈ የሚገኘውና ምንጩ ከወደ ቱርክ እንደሆነ የሚነገርለት ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ፣ ከልጅ እስከ አዋቂውን በቁጥጥሩ ስር አውሏል፡፡ ቀን በቀን ከአመሻሹ አንስቶ እስከ እኩለ ሌሊት እነዚህን በመሰሉ ፊልሞች ደንዝዘው ኑሮአቸውን የሚገፉ ምስኪኖች አያሌ ናቸው፡፡ ሀገራቸውም ሆነች አለማቸው እንዴት ውላ እንዳደረች ለእነሱ ግዳቸው አይደለም፡፡

ሌላ የባዕድ ባህል ወረራን በማፋፋም ረገድ አስተዋፅኦ እያደረገ ያለው በሀገራችን የኤሌክትሮኒክስና የህትመት ሚዲያ እየተንሰራፋ የሚገኘው የ”ሴሌብሪቲ” ባህል ነው፡፡ ለማህበረሰቡ ወሣኝ የሆኑ ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ሰፊ ጊዜ ሰጥቶ ከማወያየት ይልቅ አደንዛዥ በሆኑ ተከታታይ ሙዚቃዎች እንዲሁም ለወጣቱ አርአያ ሊሆኑ በማይችሉ የፊልም፣ የሙዚቃና የስፖርት ሠዎች ታሪክ የታጨቁ ፕሮግራሞች፣ የኤፍኤም የአየር ሞገድን አጨናንቀውታል፡፡ እነዚህን ዝግጅቶች የሚያቀርቡት ወጣቶች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ራሳቸው ደንዝዘው አድማጩንም በእንቶ ፈንቶ ሊያደነዝዙት ቆርጠው የተነሱ ይመስላሉ፡፡

በግሌ ከልክ ያለፈ አትኩሮት ለእግር ኳስ (በተለይም ለባህር ማዶው) መመደቡን እቃወማለሁ፡፡ በታክሲ ውስጥ፣ በየካፍቴሪያው፣ በየመሸታ ቤት ውስጥና በሌሎች ስፍራዎች ሌት ተቀን ስለነማንቼና ስለነአርሴ መለፈፍ የጤና አይመስልም፡፡ አገራችን በርካታ አሳሳቢና ትኩረትን የሚሹ ጉዳዮች አሉባት፡፡ በጣም የሚያሳፍረው ደግሞ ለእነዚህ አሳሳቢ ጉዳዮች የመፍትሄ ማመንጫዎች ናቸው ተብለው የሚታሰቡት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጭምር በባህር ማዶ ኳስ የተለከፉ መሆናቸው ነው፡፡ ከነዚህ ሥፍራዎች የምንጠብቀው በአንገብጋቢ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በእውቀትና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ክርክርና ውይይት ነበር፡፡

ለባዕድ ወረራው መስፋፋት እንደማሳያ የሚሆኑኝን ሌሎች ምሳሌዎች ልጥቀስ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከሀገር ውስጥና ከባህር ማዶ እየተሰሩ በኢቢኤስ፣ በኢቴቪና በቅርንጫፎቹ የሚተላለፉ የሙዚቃ ክሊፖች፤ ቅጥ አምባሩ በጠፋ አለባበስና በከፊል እርቃንነትና ፀረ-ኢትዮጵያዊነት ባህል የታጀቡ መሆናቸው የቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ ሃይ ባይ የላቸውም ወይም ያስብላል፡፡ እዚህ ጋር መጤን ያለበት እነዚህ የመሠልጠንና የአራዳነት ምልክት ተደርገው የሚወሰዱት የሙዚቃ ክሊፖች፤ ከየት ተኮረጁ የሚለው ነው፡፡ ምንአልባትም ብዙዎች ልብ የማይሉት ኤምቲቪ የሚባል የማደንዘዣና የባህል ብረዛ ምንጭ መኖሩን ነው፡፡

ዋና መቀመጫውን በሀገረ አሜሪካ ያደረገው ይህ የቴሌቪዥን ጣቢያ፤ ክፉኛ ተፅዕኖ በሀገሬ ታዳጊዎች ላይ እያሳደረ መሆኑን ዘወትር እመለከታለሁ፡፡ ተፅዕኖው ከአለባበስ አንስቶ እስከ አረማመድ፣ የፀጉር ስታይል፤ ከአኗኗር ዘይቤ እስከ ልቅ ያጣ ፆታዊ ግንኙነት፣ ጭፈራና ሌሎችም ተግባሮች ይገለፃል፡፡ ጣቢያው የሚያቀርበውን ቅጥ አምባሩ የጠፋ የልደት አከባበር እንደምሣሌ እንመልከት፡፡ “ስዊት 16” በሚሉት በዚህ ፕሮግራም ልጆች 16 ዓመታቸውን ሲያከብሩ፣ የናጠጡ ሀብታም ወላጆቻቸው እነሱንና ጓደኞቻቸውን ለማስደሰት ፓርቲ ያስጨፍራሉ፣ ለመስማት የሚከብድ ገንዘብ አውጥተው ውድ ስጦታዎችን ያበረክታሉ፡፡ ይህንን የሚያዩ የኛዎቹ ታዳጊዎች፤ ወላጆቻቸውን ቁምስቅላቸውን ሲያሳዩዋቸው እየታዘብን ነው፡፡ ከእንደዚህ ዓይነቱ ፕሮግራም ታዳጊዎች፤ አባካኝነትና አስረሽ ምቺውን ካልሆነ በስተቀር ምን ሊማሩ ይችላሉ?

ኤምቲቪ በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች (ኤምቲቪ ዩሮ፣ ኤምቲቪ ሚድልኢስት… ወዘተ በማለት) ሥርጭቱን በማስፋፋት የባህል ብረዛውን ቀጥሏል፡፡ እርግጥ ነው ጣቢያው አሜሪካንና አሜሪካዊነትን ከነግሳንግሱ በሚገርም ስልት አስተዋውቋል፡፡ ማስተዋወቅም ብቻ አይደለም በርካታ የሀገሬን የኔን ትውልድ፤ አሜሪካንን ቀን በእውናቸው ማታ በህልማቸው እንዲናፍቋትና የራሳቸውንም ባህል እንዲፀየፉ አድርጓቸዋል፡፡ በነገራችን ላይ ይህ የቴሌቪዥን ጣቢያ ሥጋት የሆነው ለኛ ብቻ ሳይሆን ለራሳቸው ለአሜሪካውያኑም ጭምር ነው፡፡ ስለ ኤምቲቪ አሉታዊ ተፅዕኖ በሚገባ ተብራርተው የተፃፉ መጣጥፎችን በኢንተርኔት ማግኘት በጣም ቀላል ነው፡፡

ለባዕድ ባህል ወረራ ማሳያነት ከምጠቅሳቸው ምሳሌዎች መካከል አስደንጋጭ ነው የምለውን ሌላ ጉዳይ ልጥቀስ፡፡ የግብረ ስጋ ግንኙነት ሲፈፅሙ እራስን በቪዲዮ ካሜራ መቅረፅ ሳያንስ በአደባባይ እዩልኝ ብሎ በኢንተርኔት መልቀቅ ከውጪ የተወረሰ እንጂ ኢትዮጵያዊ ባህል አይደለም፡፡ እንደዚህ አይነቱን ልቅ ተግባር አይተናል፤ እያየንም እንገኛለን፡፡ በስማ በለውም ቢሆን የዚህ ድርጊት ሰለባ የሆነች ኢትዮጵያዊት ወጣት፣ እራሷን እንዳጠፋች ይነገራል፡፡ ድርጊቱ እኩይ መሆኑን ተዘንግቶ እንደ ጀብዱ ተቆጥሮ የተኮረጀው ደግሞ ምንአልባትም እነ ፓሪስ ሂልተንን ከመሳሰሉ ሥራ ፈት የምዕራቡ አለም የመዝናኛው ኢንዱስትሪ የባህል ብረዛ “አምባሳደሮች” ነው፡፡ ይህች ግለሰብ በአንድ ወቅት ከጓደኛዋ ጋር ወሲብ ስትፈፅም በግልፅ የሚያሳይ ቪዲዮ በኢንተርኔት ተለቆ ነበር፡፡ ይህ አለምን ጉድ ያሰኘው ተግባር ምንም ደንታ ያልሰጣት ፓሪስ ሂልተን፤ ድርጊቱን ራሷን ለማስተዋወቅና ዝናዋን ከፍ ለማድረግ ተጠቅማበታለች፡፡ በነገራችን ላይ ታዋቂው የኒውስዊክ መፅሔት ይህችን ጋጠ-ወጥ ግለሰብ ጨምሮ ሌላኛዋን ነውጠኛ ዘፋኝ ብሪትኒ ስፒርስን ጨምሮ በፊት ሽፋኑ ላይ አውጥቶ “The Girl Gone Wild” በሚል ሰፊ ዘገባ ሰርቶ ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ በዚህም ዘገባ የአገሬውን ታዳጊዎች እንዴት ክፉኛ እየመረዙት እንደሆነ ተወስቷል፡፡

ከባህር ማዶ መጥተው በሀገራችን ሚዲያዎች (በዋነኝነት በኢቴቪና በቅርንጫፎቹ) የሚተላለፉ ፕሮግራሞች ሁሉ ጎጂ ናቸው ወደሚል ጉንጭ አልፋ ክርክር ውስጥ መግባት አልፈልግም፡፡ መልካም ትምህርትን የሚያስተላልፉ ዝግጅቶች ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ የኔ ትውልድ ታዳጊ በነበረበት ወቅት እያየናቸው ካደግንባቸው ተከታታይ ፊልሞች መካከል መልካም ተፅዕኖ ያሳደሩብን እስካሁን ድረስ በአእምሯችን ተቀርፀው ይገኛሉ፡፡ “The Bill Cosby Show” ከተሰኘው ፊልም የቤተሰብ ፍቅር፣ ማህበራዊ ህፀፆችን በዘዴ ነቅሶ ስለማውጣት፣ እንዲሁም የዘር መድሎን በብልሃት ስለመታገል ተምረናል፡፡ “Matlock” ከተሰኘው ሌላ ተከታታይ ፊልም ደግሞ ስለ ፍትህና ርትዕ እውቀት ቀስመናል፡፡ በዋናው ገፀ ባህሪ ቤን ማትሎክ (ነፍሳቸውን ይማርና! ሰሞኑን መሞታቸውን ሰምተናል) ተማርከን ስናድግ በሣል የወንጀል መርማሪና ጠበቃ ለመሆን ተመኝተናል፡፡ “Space 1999” በሚባለው ተከታታይ ሳይንሳዊ ፊልም ተመስጠን ስናድግ ሳይንቲስት እንሆናለን ስንል ተመኝተናል፡፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን ምስሉ ሌላ ነው፡፡ አባባ ተስፋዬን የመሳሰሉ ትውልድ ቀራጮች፣ ኢትዮጵያዊ ባህልና ስነ ስርዓት የሚያስተምሩ ድንቅ አባቶች ከሚዲያው ማግኘት ብርቅ ሆኗል፡፡ እናም ኢትዮጵያዊነትን ከባእድ የባህል ወረራ እንከላከል እያልኩ ፅሁፌን እቋጫለሁ፡፡

 

 

Read 3377 times Last modified on Saturday, 28 July 2012 11:19