Saturday, 28 July 2012 11:08

ጫጩት በአየር ላይ መፈልፈል…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(0 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ብርዱም ከፋ፤ ዝናቡም ሲያሰኘው እየከፋ ነው…ጊዜውም ከፋ፡፡ ነገሩ ሁሉ…ይሄዳል ባልንበት መንገድ መሄዱ ቀርቶ ባልጠበቅነው አሳባሪ መንገድ እየተቀየሰብን…ሁሉን ነገር ከሐምሌ ደመና በባሰ እያጨለመብን ነው፡፡ (ይባስ ብሎ ይሄን ሰሞን ደግሞ በየሰፈሩ መብራት እንደፈለገው ይጠፋል፡፡ “ኧረ የእኛም ጠፍቷል” መባባል እየተለመደ ነው፡፡ ያውም “ውሃ ባልጠፋበት”፡፡ አንዳንድ ጊዜ…”ይቺ አገር በእውነት የማናት?” ብንባባል ወደን አይደለም፡፡)እናላችሁ…ሰሞኑን ወሬው ሁሉ…አለ አይደል…የምጽአት ቀን ከሌሎች አገሮች ቀድሞ ወደ እኛ እየተቃረበ የሚያስመስል ሆኖብን ግራ ገብቶናል፡፡

የምር ግን…ምንም አይነት ቅጽል የማያሻሽለው ደባሪ ሰሞን ነው፡፡ (ስርዝ ከራሴ፡፡) ምንም አይነት ምርምር፣ “ሲኒየር ፔፐር” ቅብጥርስዮ ሳያስፈልገው…በመንገዱ የሚመላለሰውን ሰው በማየት ድብርት፣ ስጋት፣ ያለመተማመን፣ “ጌታዬ ምኑን ልታመጣው ይሆን!” አይነት ፀሎት ምን ያህል የእኛነታችን አካል እንደሆኑ ማወቅ ይቻላል፡፡

ይሄን ደባሪ ሰሞን የባሰ ሳያጨልምብን ወደፀሐዩዋ ብርሃን ፊታችንን ያዙርልማን!

ስሙኝማ…የእውነትና የውሸት ትርጉም ላይ የሚነጋገር ወርክሾፕ፣ የ”ጂ ምናምን” ምክክር ይካሄድልን፡፡ ግራ ገባና ፋክትና ፊክሺን ከምንም ጊዜ በላይ መንታ ነገር የሆኑባት አገር የእኛዋ ሳትሆን አትቀርም፡፡

በዓይናችን እያየን ያለውን ቀይ መብራት “ቢጫ ነው ብለናል ቢጫ ነው!” አይነት ነገር ስንባል…አለ አይደል ቀሺም ነገር ነው፡፡ ስምንትና ዘጠኝ “ዲጂት” የባንክ አካውንትና ወፍራም የጭቃ ሹም ወንበር ላይ መቀመጥ ውሸትን እውነት አድርጐ የመናገር “ሊቼንሳዎች” ከሆኑ ይነገረንማ!...ሃሳብ አለን፣ ቦሶቻችን መናገር፣ ማብራራት፣ “ግንዛቤ ማስጨበጥ” ምንም አይነት ነገሮችን አቁመው ለትንሽ ጊዜ “ሳባቲካል ሊቭ” ምናምን እንደሚሉት ወደዛው ወደ ሸንኮራ ጠበል ይወሩድልንማ፡፡ ያኔ “ከእንትና ሚስት ጋር ለጥ ብሎ እንትን ሲያደርግ ነው የያዝኩት” ምናምን ብሎ ሲያስለፈልፍ ችግሩን ደረስንበት ማለት ነው፡፡ መፍትሔም ሊመጣ ይችላል! ቂ…ቂ…ቂ…

ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…አንድ ሰውዬ አሉ “ስጥ ሲሰጥ” በአምስተኛ ማርሽ ነው በቁልቁለት የሚያንድረድረው አሉ፡ እናማ፣ ምን አለ አሉ መሰላችሁ…”እኛ አገር ትያትር ቤቶች በጣም ሰፊ ከመሆናቸው የተነሳ ሁዋላ የተቀመጠው ሰው እንቁላል ቢወረውር መድረኩ ከመድረሱ በፊት ጫጩት አየር ላይ ይፈለፈላል፡፡” ሸላይ ስጥ አይደል!

እናላችሁ…እኛ ዘንድ እንቁላልን በአየር ላይ ከመፈልፈል የባሰ “ስጥ እንግዲህ” ሞልቶላችኋል፡፡ ውሸት የሚያሳፍር መሆኑ ቀርቶ እንደውም ማንነታችንን የሚወስነው የውሸቱ “ጥበባዊ አቀራረብ” ሆኗል፡፡

እግረ መንገዴን…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ሰውየው አንድ ጓደኛውን “ለመሆኑ ለሚስትነት የምትፈልጋት ሴት ምን አይነት ናት?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ጓደኝየውም፣ “መልካም ጠባይ ያላት፣ ብልህና ቆንጆ፣” ሲል ይመልሳል፡፡ ሰውየው ምን አለው መሰላችሁ…”እንግዲያውስ አንተ የምትፈልገው አንድ ሳይሆን ሦስት ሴት ነው፡፡” እናማ…እንኳን ሦስቱንም ማጣመር፣ የአንዱን ሩብ እንኳን ያጣን ሰዎች እየበዛን ነው፡፡

ውጪው አገር ላይ “ዲቴክተር” የሚሉት ሰው ሲዋሽ “እጅ ከፍንጅ” የሚያሲዝ ነገር አላቸው አሉ፡፡ ሰው እንኳን ይበል፣ ይበል ብሎ ቢቀበል መሣሪያው…አለ አይደል…”አንተ ቀጣፊ!” “አቤት ውሸት!” “ወራጅ አለ…” ምናምን አይነት ምልክት እየሰጠ ያጋልጣል አሉ፡፡

(በነገራችን ላይ ብዙዎቻችን መለስ ብለን እውነተኛ እኛነታችንን እንዳናይ የሚያደርገን ዙሪያችንን “ይበል፣ ይበል” የሚሉ ስለበዙብን ነው፡ የዘንድሮ ወዳጅነት እንደሁ “ማን እውነቱን ተናግሮ ይቀያየማል!” ሆኗል፡፡ ‘ፊልመኞቻችን’… ልብ በሉማ!)

እናላችሁ … አንድ ‘እንደ ጉድ’ የሚረግጥ ሰውዬ አለ፡፡ ታዲያማ ምንም ያህል ‘ቢረግጥ’ ሚስቱን ማታለል አልቻለም፡፡ ግራ ሲገባው ምን ቢል ጥሩ ነው …”የመጀመሪያው ውሸትን መለያ መሣሪያ የተሠራው ከወንድ ግራ ጎን ነው፣ እስከ ዛሬ ድረስም ምንም አይነት ማሻሻያ አልተደረገለትም፡፡”

እናማ …ውሸትና አጉል የ‘ርጥብ ብልጥነት’ ሲበዛ ሁሉንም ነገር እንጠረጥራለን፡፡ “ፀሐይ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ትጓዛለች” ሲሉን “አይ አጅሬ፣ ይሄኔ እኮ በእሱ ቤት እኛን ማቃለሉ ነው!” ምናምን ልንል እንችላለን፡፡

ስሙኝማ … የጥርጣሬ ነገር ካነሳን … ሰውየው ቀዶ ጥገና ሊካሄድለት ነበር፡፡ እናላችሁ …ወደ ኦፕሬሽን ክፍል ከመግባቱ በፊት ምን አለ አሉ መሰላችሁ ... “መጀመሪያ ውስጤ ያሉት አካሎቼ ኢንቬንትሪ ይካሄድልኝ፡፡” ልክ ነዋ!...በሁሉም ነገር ምንተፋ በዝቷል ይባላላ! እኔ የምለው…የምር እዚህ አገር “ኪድኒ” ምናምን ምንተፋ አለ እንዴ! እንደሱ አይነት ነገር ከተጀመረ እኮ…”ኪሳችሁን ጠብቁ…” በሚለው ማስታወቂያው ቦታ “ኩላሊታችሁን ጠብቁ…” ልንል ነው!

እናላችሁ አስቸጋሪ ጊዜ ነው፣ አንድም የውሸት እንዲህ “የእከሌ ኮንሰርት” አይነት “ፖፑላር” የሆነው ይቺ በየሙያው ያለች ኤቲክስ የሚሏት ነገር ስለጠፋች አይመስላችሁም? ሀኪም ዘንድ ሄዳችሁ በአምስት ሽልንግ “አንቲባዮቲክስ” ምናምን ለምትገላገሉት ነገር ለአሥራ ምናምን አይነት ምርመራ ሦስትና አራት መቶ ብር ስትጠየቁ፣ ውሸት ስንት መልክ እንደሚይዝ ታውቃላችሁ፡፡

በአንዲት ምርመራ ለሚታወቅ የጤና ችግር ሀኪሙ ከኤንዶስኮፒ እስከ ምንምን ስካን ድረስ ሲያዝላችሁ ከዚህ የባሰ “መቅጠፍ” የት ይኖራል!

የሀኪሞች ነገር ካነሳን አንድ ነገር ትዝ አለኝማ…እዚቹ ከተማችን አንድ ክሊኒክ መአት በሽተኛ ተራውን እየጠበቀ ነው፡፡ እና በወቅቱ አንድ ዶክተር ብቻ ነበር የነበረው፡፡

እናላችሁ…ያ ሁሉ በሽተኛ በየአግዳሚው ወንበር ተቀምጦ እያቃሰተ በመሀል ዶክተሩ ጋዋኑን አውልቆ ወደ ውጪ ይወጣል፣ ምን ብሎ ወጣ መሰላችሁ…“ሙዝ ገዝቼ መጣሁ” ይሄ ነው የምር “ሮማንቲክ ኮሜዲ” ማለት፡፡ አሀ…ያንን ሁሉ በሽተኛ አስቀምጦ አትክልት ቤት የሚሄደው ከሙዝ ጋር የሆነ አይነት “ሮማንስ” ቢኖረው ነው፡፡

ስሙኝማ…ከሀኪሞች ወሬ ሳንወጣ የሆነች ነገር ትዝ አለችኝ፡፡ ሰውየው ምርመራ ክፍል ከሀኪሙ ጋር እየተነጋገረ ነው፡፡ ሚስቱ ደግሞ ውጪኛው ክፍል ሆና ትጠብቀዋለች፡፡

ዶክተሩ የሰውየው የጤና ችግር ግራ ስለገባው ይጠይቀዋል፡፡ “ለመሆኑ እንዲህ ጤናና ሰላምህን ያሳጣህ የተረገመ ነገር…” ብሎ ሳይጨርስ ባል ሆዬ አፉን እየተመተመ “ቀስ ብለህ አውራ፣ ትሰማሃለች…” አለው አሉ፡፡

ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ባል ከከተማ ወጣ ሲል “እንግዳ” በመስኮት የምታስገባ እንትናዬ ያው “ማሬጇ” ላይ “ቅጥፈት” እየፈፀመች አይደል! ለነገሩ…ዘመኑ እየተለወጠ በመስኮት መግባት ቀርቶ መኪና ኋላ ወንበር…ምን እያወራሁ ነው! ይኸውላችሁ…ባልታሰበው መንገድ መቀየስ ማለት ይሄ ነው፡፡ እናማ…ውሽሜ ሆዬ ባል ፊልድ ይወጣበታል በተባለበት ቀን በጓሮ በኩል ሹክክ ብሎ ይመጣል፡፡ ግን ነገርዬው ባልታሰበለት መንገድ ሄደና ባል ሆዬ ሀሳቡን ለውጦ ለካስ ቤቱ ኖሯል፡፡ ውሽሜ ሆዬ እንደ ተለመደው በጓሮ ሆኖ እንደ በግና ፍየል አይነት ድምጽ እያሰማ ምልክት ይሰጣል፡፡ ያው ድምጾቹ “ዲኮድ” ሲደረጉ “መስኮቱን ክፈቺልኝ” አይነት መሆናቸው ነው፡፡ ቀኑ ደግሞ የሆነ የጠበል ጠዲቅ ቀን ነው፡፡ እናላችሁ…እሷዬዋ ምን አለች አሉ መሰላችሁ…አንተ የጓሮ ፍየል ብትስል ብታነጥስ

ዛሬ ባል ነውና ቅጠልም አልበጥስ!

የዘንድሮ እንትናዬዎች ከቅኔ ምናምን “ገላግሏቸው” ነገርዬው…አለ አይደል…”ዕድሜ ለቴክስት ሜሴጅ” ምናምን ነው፡፡ ሀሳብ አለን…የሰማንያ ሰርተፊኬት ላይ “በየሞባይላችን የሚደርሱንን ቴክስት ሜሴጆች በሙሉ አንዳችን ለሌላችን ልናሳይ ቃል ገብተናል!” ምናምን የሚል ሀረግ ይካተትማ፡፡ ዘመኑ ተለውጧላ!

አባትየው ለልጁ “እኔ ልጅ ሳለሁ አንድም ቀን ውሸት ተናግሬ አላውቅም” ይለዋል፡፡ ልጁ ምን ብሎ ጠየቀ መሰላችሁ…”ታዲያ ስንት ዓመት ሲሞላህ ነው የጀመርከው?”

እናላችሁ…በብዙ ነገር ጫጩቱ አየር ላይ እየተፈለፈለ ግራ ገብቶናል፡፡ በቃላችን የምንገኝ በጣም፣ እጅግ በጣም እየተመናመንን ነው፡፡

ድብርቱን ይዞ የሚሄድ ተአምር አንድዬ ይላክልንማ!

ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

 

Read 1805 times Last modified on Saturday, 28 July 2012 11:19