Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 28 July 2012 11:03

የቱሪዝማችን አያ-አዎ !!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ሠዎች ከተለመደው መኖሪያ ቦታቸው ወጥተው ወደ ሌላ ቦታ (መድረሻ) ለጉብኝት ዓላማ ሄደው እና የቆይታ ወጪያቸውን ከፍለው ቢያንስ ለ24 ሠዓታት፣ ቢበዛ ለአንድ ዓመት በጎበኙት ቦታ (በጉብኝት ላይ ሲቆዩ) ቱሪስት (ጎብኚ) ይባላሉ፡፡ የጎብኚውን ጉዞ እና ጉብኝት በማስተባበር ማለትም ሆቴላቸውን፣ ምግባቸውን፣ መጓጓዣቸውን እና ሌሎች አሥፈላጊ ነገሮችን የሚያሟላላቸው የንግድ ተቋም ደግሞ አስጎብኚ ድርጅት (Tour Operator) ይባላል፡፡

ቱሪስት አስጎብኚ (Tour Guide) አገር ጐብኚዎችን ወደ ሀገር ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ሀገራቸው እስኪመለሡ ድረስ አብሮ በመጓዝ አጠቃላይ እንቅስቃሴአቸውን ፡- ትራንስፖርት፣ ማረፊያ ቦታቸውን (ሆቴል፣ ሎጂ፣ የካምፕ ቦታ)፣ የሚጎበኙ ቦታቸውን ወይም እንቅስቃሴዎችን የሚመራ ሲሆን በዘልማድ አስተርጓሚ ከሚባለው በጣም ይለያል፡፡

የቱሪዝም ጥቅም

ቱሪዝም አሉታዊ ጎኖች ቢኖሩትም የሚሠጠው ባህላዊ፣ ሣይንሳዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታው እጅግ ብዙ ነው፡፡

ሕዝቦች በባህላቸው እና ቅርሣቸው እንዲኮሩና እንዲጠብቁት ይረዳል

የትምህርትና የቴክኖሎጂ የልምድ ልውውጥ ይካሄድበታል፡፡

የኢኮኖሚ ጠቀሜታው ግን እጅግ የላቀ ነው፡፡ ከአረንጓዴው ወርቃችን ጋር ለማነፃፀር ያህል፡፡

ታዲያ በዚህ ጠቃሚ ዘርፍ ላይ ያለው ችግር ምንድን ነው?

ችግሮችን አንድ በአንድ ከመዘርዘሬ በፊት ሀሣቤን ለማጉላት የሚጠቅሙ ቃላትን እና ዘይቤን ልጥቀስ፡-

የአማርኛችን “አይ-አወ” ዘይቤ ሁለት ተቃራኒ ሀሳቦችን በአንድ ላይ ያስኬዳል፡፡ ምሣሌ፡- አቶ ከበደ ታሟል እንጅ ጤነኛ ነው፡፡

ከበደ ከታመመ ጤነኛ ሊሆን/ሊባል አይችልም ጤነኛ ከሆነ ደግሞ ሊታመም አይችልም፡፡ ይህ የዘይቤ ዓይነት ግን ሁለቱን ይዞ ይገኛል፡፡

ቱሪዝማችንም ሁለት ተቃራኒ ነገሮችን ይዞ እናገኘዋለን፡፡ ፅንፍ የደረሰ ተስፈኛነት (extreme optimism)- በዚህ ሁኔታ ላይ ያለ ሠው ወይም ድርጅት ከደስታ በቀር መከፋት፣ ከስኬት በቀር ውድቀት፤ሀብታም እንጂ ድሃ፣ ምቾት እንጂ ችግር አይታየውም አይሠማውም ፡፡

የቱሪዝም መ/ቤቶች ባህሪ

የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር “ላለው ይጨመርለታል ለሌለው ግን ያለውም ይወሠድበታል” የሚለዉን ጥሬ ቃል ከመፅሀፍ ቅዱስ   የወሰደ ይመስለኛል፡፡

“ላክቲክ አሲድ ባክቴሪያ (lactic acid bacteria) - እነዚህ የባክቴሪያ ዘሮች በሚያገኙት ህይወት ያለው ነገር ላይ ለምሣሌ እርጥብ ሣር ላይ መርዛማ አሲድን ያመርታሉ፡፡

በሣሩ ላይ ያሉ ፍጥረታት ሁሉ ይሞቱ እና ባክቴሪያዎች ብቻቸውን ይቀራሉ፡፡ እነሱም መርዛቸውን ያለማቋረጥ ያመርታሉ፡፡

በመጨረሻ ግን ያመረቱት መርዝ ሲበዛ ራሣቸውን ያጠፋቸው እና ያ የሣሡለት ነገር (ሣር) ከሁሉም ነፃ ሆኖ ይቀራል፡፡ በዚህ ጊዜ የከብቶች ገፈራ (silage) ሆኖ ለሌላ ሦስተኛ እና አራተኛ አካል ያገለግላል፡፡ ይህ ባህርይ የአስጎብኝ ድርጅቶችን ባህሪ ይወክላል፡፡

ለግንዛቤ የሚያግዙ ፅንሠ ሀሳቦችን ከያዝን ወደ ዋና ዋናዎች ነጥቦች  (ችግሮች) እንቀጥል፡፡የቱሪዝሙ ዘርፍ ካሉበት ዋና ዋና ችግሮች ውስጥ አንዳንድ ፣ አፈቅቤ በቱሪዝሙ ዘርፍ የተሠማሩ ባለ ሀብቶች እና ቱባ የዘርፉ ባለስልጣናት ለመገናኛ ብዙሃን ፍጆታ የሚውሉ ዲስኩራቸውን ሲደሠኩሩ እንደምንሠማው፤ ከፍተኛ የባለሙያ እጥረት ስላለ ለዘርፉ እድገት ማነቆ ሆኗል፡፡ ይህ ችግር እውነትም ከፍተኛ ችግር ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በዝቅተኛም ሆነ በከፍተኛ ደረጃ ውስን በሆነው የሀገራችን በጀት የሠለጠኑ ባለሙያዎች መግቢያ አጥተው ወደ ሌላ ዘርፍ ሲገቡ ወይም የተማሩ ቦዘኔዎች ሲሆኑ ማየት የተለመደ ሃቅ ነው፡፡ ይህንን ነው “አያ-አዎ” ዘይቤ ያልኩት::

ስለሆነም ሆቴሎች እና በተለይም አስጎብኚ ድርጅት ባልተማሩ ነገር ግን የባለሀብቶች የቅርብ ዘመዶች፣ የዘመድ የወዳጅ ልጆች ወይም የጎሣ እና የጎጥ ዘመድ በሆኑ ግለሠቦች ተይዞ ሲበላሽ እና መንግስት ስንት የዲፕሎማሲ ሥራ የሠራበትና ወጪ የፈሠሠበት ቱሪዝም አፈርድሜ ሲበላና የመልካም ገፅታችን ሣይሆን የመጥፎ ገፅታችን መግለጫ ሲሆን ይታያል፡፡

ይህችን ፅሁፍ ለመፃፍ ካነሣሡኝ፣ በስራ ካወቅኋቸው ሠዎች፣ ከጓደኞቼ እና ከእንግዶች (ጎብኝዎች) ከራሣቸው ከሠማኋቸው፤ እራሴም ካየሁት ለማሣያ ያህል በጣም ጥቂቱን ችግሮች ልጥቀስ፡፡

በሆቴሎች ውስጥ

እንግዳ መቀበያ ክፍል (Reception) - እንግዶች ሲደርሱ አልጋ አልተያዘላችሁም መባል፣ ዳብል (double) አልጋ ተይዞ ነጠላ (single) ተጠቀሙ መባል፣ የተከፈለበትን ትቶ ሌላ ያነሰ ወይም ከአቅም በላይ ለሆነው ክፍል ወይም አልጋ ተጨማሪ እንዲከፍሉ ማድረግ ወዘተ …

አስተናጋጆች ሙያዊና የቋንቋ ዝግጅት ስለሌላቸው የተረበሹ እና የተደናገሩ መሆን፣ ፒዛ ታዝዞ ላዛኛ፣ ፓስታ ታዝዞ ማካሮኒ፣ ኮካ ታዝዞ ፋንታ ማምጣት ወዘተ …

የአስተዳደር ሠዎች:- በሀላፊነት የሚሰሩ ሠዎች የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የችሎታም ሆነ የሥነ-ምግባር ማነሥ ወይም አለመኖር ወዘተ …

በአስጎብኚ ድርጅቶች ላይ ያለው ችግር

ገና ሲጀመር ለእንግዶች የተገባላቸው ቃል /ውል አይተገበርም፡- ምሣሌ ዘመናዊ መኪና ተብሎ የወላለቀ፣ በግፊ የሚነሣ መኪና ይመደባል፤ በቦታው “አለ የተባለ ሆቴል ተብለው ከፍለው ሲገቡ የቁንጫ መራቢያ “ሆቴል ተብየ” ሆነው ያገኙታል፡፡ በሙያው የተካነ አስጎብኚ (professional guide) ተብለው ገና ሲታዩት ገፅታቸው የሚያስበረግግ ኢትዮጵያን ይቅርና ሠፈራቸውን እንኳ በቅጡ የማያውቁ፤ የአቡጊዳ ሽፍታ ይሆናሉ፡፡

እኔ ያየሁትንና ከእንግዶች የሠማሁትን ልጥቀስ፦

በ2003 ዓ.ም ከአዲስ አበባ አውሮፕላን የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል በባህዳር አየር ማረፊያ ተገኝቻለሁ፡፡ በዚሁ ቦታ አንድ እንከን የለሽ የተባለለት አስጎብኝም እንደኔው ተገኝቷል፡፡ ፀጉሩን ከተፈጠረ ውሃ እና ምላጭ አይቶት የሚያውቅ አይመስልም፡፡

ሱሪው በዘመናዊነት ሠበብ የተቀዳደደ ጉልበቶቹ ሙሉ ለሙሉ ይታያሉ፡፡

ያንን ውሃ፣ ማበጠሪያ እና ምላጭ አይቶት የማያውቅ ፀጉሩን አስር ጊዜ ይገምደዋል፣ ያሻሸዋል፡፡ ሰው ሁሉ ያፈጥበታል፡፡ የኔም የሱም እንግዶች ደረሱ፡፡ በግራ እጁ ሲጋራውን እያቦነነ፣ በቀኝ እጁ “እንኳን ደህና መጣችሁ” እያለ ሠላም ይል ገባ፡፡

ጠጋ ብዬ እንግዶቹን ተቀብሎ እስኪጨርስ ሲጋራውን እንዲጥል ስመክረው፣  በእንግዶች ፊት ሲጋራውን ከእነ እሣቱ ፊቴ ላይ ወረወረብኝ፡፡

እንግዶቹ ደነገጡ፡፡ እኔም ደንግጬ እዚያ ቦታ ላይ ምንም ማለት ስለማልችል ዝም አልኩኝ፡፡ አንድ ወዳጄ የነገረኝን ደግሞ ላጋራችሁ፡፡ ጊዜው 2002 ወይም 2003 ዓ.ም፡፡ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፍያ አንድ አስጎብኝ እና ወዳጄ በአንድ ቦታ ላይ እንግዶቻቸውን ይቀበላሉ፡፡

አስጎብኚው  ምን ቢያደርግ ጥሩ ነው ? እንግዶቹን ልክ ደርሰው፤ በእንግድነት ግራ በመጋባት ላይ እያሉ “እባካችሁ ብር አልቆብኝ ነው፤ ቅር ካላላችሁ ውስኪ ግዙልኝ” አላቸው፡፡ ወዳጄ ደንግጦ “እባክህ ተው ነገ ከነገ ወዲያ በየመንገዱ ህፃናቱና አረጋዊያኑ ይለምኑዋቸዋል፤ አንተ የአገርህ አምባሳደር መሆን ሲገባህ፣ በልመና ከተቀበልካቸው ስለ ሀገራችን ምን መልካም ገፅታ ይዘው ሊሄዱ ነው” ሲለው፤ “ያንተን እንግዳ አልነካሁም፣ አላስገደደኳቸውም፣ ደግሞም ድህነቴ የሚደበቅ አይደለም፤ እንኳን እኔ ጠ/ሚኒስትሩ አገር የሚመሩት በልመና በጀት ነው” እንዳለውና በተዋጣለት ገንዘብ፣ ከዚያው ከቀረጥ ነፃ ሱቅ አንድ እንግዳ ልኮ ሦስት ጠርሙስ ውስኪ በ40 ዩሮ እንዳስገዛ፤ ከተማ ወስዶ አንዱን በ80 ዩሮ እንደሚሸጠው እንደነገረው  አጫውቶኛል:: የችግሩን ስፋት ለማሣየት ይህን ያህል ካልሁ  ወደ ሌላ ነጥብ ልለፍ፡፡

ታዲያ በመንግስትና በግልም ተቋማት የሠለጠኑ ሙያና ሥነምግባርን የተላበሡ ባለሙያዎች ሥራ ፈተው ወይም ያለቦታቸው እየገቡ ሣለ፣ እንደዚህ ያሉትን የቀለም እና የሥነ-ምግባር ሽፍቶች እየመደቡ፣ የሀገርን ገፅታ ማበላሸትን ምን አመጣው ብሎ መጠየቅ ከማንኛውም ጤናማ እና ቀና ዜጋ ይጠበቃል፡፡ ለዚህ ጥያቄ ብዙ መልሶች ቢኖሩም ከተረዳሁትና ከሠማሁት ጥቂቱን እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡-

ሀ. ግለሠቦች ገንዘብ እንጅ ሙያ ሳይኖራቸው ድርጅቱን ስለሚከፍቱ እና ስለሀገር ገፅታ እና ስለሙያው መቀጨጭ ባለማሠብ /ባለመገንዘብ፣ ዘመድ ወዳጅ ያሏቸውን ግለሠቦች ለመጥቀም በማሠብ ስለሚመድቡበት፣

ለ. አንዳንድ ባለሀብቶች የሙያው ግንዛቤ ቢኖራቸውም ስለ ሀገርና ሙያ ክቡርነት ግዴለሽ በመሆን ከላይ የተጠቀሰውን ያደርጋሉ፣

ሐ. በተፈጥሮአቸው ተጠራጣሪ፤ ጥላቸውን እንኳ የሚፈሩ ስለሆኑ በእነሱ አመለካከት ዘመድ ያልሆኑ ሠዎች ቢመድቡ የሚከሥሩ፤ ድርጅታቸዉ የሚዘጋ ስለሚመስላቸው ፣

መ. አንዳንዶች በብቃት እና ተወዳዳሪነት ማነስ ደንበኞቻቸው ጥለዋቸው ሲሄዱ እና ሲከስሩ አይተው ወይም ሠምተው ይሆናል፡፡ አንዳንዴም ሥነ-ምግባር የጎደለው ባለሙያ እውነትም ሥራ ጉድቶ ወይም ገፍቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ “እባብ ያየ በልጥ” እንዲሉ ባለሙያዎችን በመፍራት ሆን ብለው ያልተማሩትን ያሠራሉ፡፡

ሠ. ሌሎች ደግሞ “ሌባ እናት ልጇን አታምንም” ሆኖባቸው፣ የተማረና ባለሙያ ሠው እጅግ አደገኛ ሆኖ ይታያቸዋል፡፡ ስለዚህ ከየትም ፈልገው ቋንቋ ብቻ የሚችል ሙያውን ግን ፈጽሞ የማያውቅ ይፈልጋሉ፡፡

ረ. ሌሎች ደግሞ ባለሙያውን ካሠራነዉ ገንዘብ ይኖረዋል፣ ነገ ከነገ ወዲያ የራሱን ድርጅት ይከፍታል፤ ተወዳዳሪ (ባላንጣ ይሆንብኛል) ብለው ስለሚያስቡ፡፡ ላክቲክ አሲዶችን እዚህ ጋ አስታውሱ!

ታዲያ እዚህ ላይ ይህን ችግር የሚፈታ፣ የሚመራ፣ የሚያስተዳድር አካል የለም ወይ ሊባል ይችላል፡፡ መልሱ አዎ አለ፤ ለዚያውም እንደ ድሮው ጽ/ቤት ወይም ኮሚሽን ሳይሆን በሚኒስቴር ደረጃ የተዋቀረ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አለ፡፡ ችግሩ “ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም” እንዲሉ ወይም ደግሞ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ “ከታላቅም ይወለድ ከታናሽ ሠውን ታላቅ የሚያደርገው ሥራ ነው” እንዳሉት፤ ኮሚሽንም ሆነ ጽ/ቤት አሊያም ሚኒስቴር መ/ቤት ችግርን የሚፈታው ስሙ ሳይሆን ሥራው ነው፡፡

ከዚህም ባሻገር ሙያዊና ስነ-ምግባራዊ ብቃት ያላቸው ወደ ዘርፉ ገብተው በውድድር እንዳያሻሽሉት “ላለው ይጨመርለታል ለሌለው …” እንዲሉ በባለሙያዎች ላይ ከራስ ዳሽን ተራራ የበለጠ መመዘኛ እያስቀመጠ ያርቃቸዋል፡፡ እጣ ፈንታቸውም ከልምድ አዋላጆች / ካልተማሩ አስጎብኚዎች የሚተራረፍ ሥራ እየጠበቁ መኖር ብቻ ይሆናል፡፡ ይህም ሁኔታ መማርን በማጥላላት፣ አለመማርን /መሃይምነትን በማበረታት የትምህርት ሚኒስቴርን ዓላማ በአዋጅም ባይሆን በተግባር ይቃወማል፡፡

የቱሪዝማችን ጉድ

ምንም እንኳ አፈፃፀሙ  ላይ ከፍተኛ ችግር ቢኖርም የክልል እና የወረዳ ቱሪዝም ጽ/ቤቶች እና ቢሮዎች የተሻሉ ሙከራዎችን አድርገዋል፡፡ “ከፈረሱ ጋሪው ቀድሞ” እንዲሉ ፈረሱ ሚ/ር መሥሪያ ቤት ያላወጣውን /ያልፈፀመውን ህግ ከታች ያሉት ለመፈፀም ሞክረዋል፡፡

በየቱሪስት መዳረሻው ያሉት ወጣቶች በትምህርታቸው ቢያንስ 10ኛን ክፍል ያጠናቀቁና በአካባቢው መልካም ሥነ-ምግባር ያላቸውን፣ አወዳድረው በመመልመል ለአጭር ጊዜ በማሠልጠን መታወቂያ/ ባጅ ሠጥተው እንዲሠሩ አድርገዋል /ሞክረዋል፡፡ ልብ በሉ! እነዚህ የአካባቢ አስጎብኚዎች ከእንግዳው  ጋር የሚቆዩት ለአጭር ጊዜ ሲሆን ለዚያም ቢሆን እውቀትና ሕጋዊነት እንዲኖራቸው ተሞክሯል፡፡ ውጤታማ ከሆኑት ቦታዎች መካከል 1ኛ ደረጃ ጎንደር፣ ሠሜን ተራራ ብሔራዊ ፓርክ፣ አክሱም እና ላሊበላ በከፊል ይገኙበታል፡፡ እንግዳው የሀገራችንን መሬት ከረገጠበት ጊዜ ጀምሮ ተመልሶ እስከሚሄድ በመልካምም ሆነ በመጥፎ አብሮ የሚከርመውን “ብሔራዊ አስጎብኚ”  ግን የጠየቀው የለም፡፡ አይገርምም?

የአካባቢ አስጎብኚዎች ተግዳሮት

በትክክል አለመመልመል እና በቂ ሥልጠና አለመስጠት፤ በዚህም ምክንያት እውቀትም ሆነ ምግባር የሌላቸው ልጆች መብዛት፡፡ ምሳሌ፡-

ሠንበቴ እና ባቲ ገበያ ጅንካ እና ቱርሚ ላይ ያሉ አስጎብኚዎች የእውቀት ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የሥነ-ምግባር ችግር ይታይባቸዋል፡፡ የሁሉም የጋራ ችግሮች፡-

ሁሉም እውቀት የላቸውም፣ ሁሉም ውጫዊ ገፅታቸው ማራኪ አይደለም፣ ላልሠሩበት ሥራ ክፍያ ይጠይቃሉ:! በዚያ መስመር እንግዳው ስለደረሠ ብቻ፣ ጉንጫቸው በጫት ተወጥሮ፣ አይናቸው በአልኮል ቀልቶ፣ ትንፋሻቸው ጫት ጫት እና አተላ አተላ እየሸተተ ይመጣሉ፡፡

የሠንበቴና ባቲዎች ለአንድም ሁለትም እንግዳ አራት አምስት አስጎብኚ ነኝ ባይ መጥቶ “እኔ ነኝ እኔ” እያሉ ይጣላሉ፡፡ የክፍያቸውም መጠን ደሥ እንዳላቸው ከፍና ዝቅ ያደርጉታል፤ በህጋዊ ማህተም ህገወጥ ሥራ ይሠራሉ ፡፡

ጃንካ እና ቱርማ ያሉት መንደር ላይ ከታወቀው ክፍያ ውጭ የመንደሩ ሠዎች ተጨማሪ ክፍያ እንዲጠይቁ በማድረግ ይካፈላሉ፤ በተለይም ጂንካ ላይ፡፡

ሀውዜን ማርያም ቆርቆሮ እና አቡነ የማታ ጉህ ገዳማት ላይ ያሉት በተለይ ቆርቆሮ ላይ በጣም ብልሹዎች ናቸው፡፡ ህጋዊው እና ህገወጡ አይታወቅም፡፡ ለአንድ ቡድን እንግዳ አሥር አሥራ አምስት አስጎብኝ ነኝ ባይ ይመጣል፤ እርስ በእርሳቸው ይጣላሉ፣ ከአዲስ አበባ የሄደውን አስጎብኚ “እኔን ውሰድ እኔን” በማለት ይጣሉታል፡፡ ለዚህም ሲባል ጠባቂ ተመድቦ ይጠብቃል፤ ያም ሆኖ ግን ችግሩ አልተፈታም፡፡ ከአንደኛ ደረጃ ተማሪ ህፃናት መካከልም፣ ሠዓት ባልሞላ ጊዜ 150 ብር ከተገኘ በማለት ትምህርታቸውን ያቋረጡም እንዳሉ ሠምቻለሁ፡፡

ላሊበላ ላይ ያሉ ጥቂት አስጎብኚዎች መጠነኛ የሥነ-ምግባር ችግር ቢታይባቸውም ለክፉ የሚሠጥ አይደለም፡፡

የውጭ ዜጋ የሆነ/ች ሠው በመንገድ ሲሄድ፣ ብዙ ህፃናትና ጎረምሶች ያዋክቡታል፡፡ የልመናው ዓይነት ተዘርዝሮ አያልቅም::

ሌላም ነገር አለ!

በቅርቡ በጣም ደስ የምትል ወሬ በዚህም በዚያም ተናፈሠች፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡- መንግስት የሀገራችንን ሕዳሴ ለማፋጠን፣ የበቃና የነቃ የሠለጠነ የሠው ሐይል በበቂ ሁኔታ እንዲኖረን፣ ከተቻለም እንደ ህንድ እና ቻይና የሠው ኃይል ወደ ውጭ ሀገር በመላክ ጠቀም ያለ ገቢ ለማግኘት የብቃት ማረጋገጫ ምዘናን (certificate of competency) በት/ት ሚኒስቴርና የምዘና ኤጀንሲ አማካኝነት አጠናክሯል ተባለ፡፡

ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርም አንድ የመንግስት መ/ቤት ነውና በዘርፉ የሚሠማሩና የተሠማሩትን እንዲመዘኑ አውጇል ብሎ አንድ ወዳጄ ሲነግረኝ፣ የተሠማኝ ደስታ በጣም ከፍተኛ ነበር፡ ምክንያቱም ለዘርፉ ትኩረት ሊሰጠው ነው፤ ሊያድግ ነው ብዬ ስላሰብኩ፡፡

እናም ከወዳጄ ጋር ለመመዘን የሚያበቁንን ነገሮች ሁሉ አሟላንና በዝግጅታችን ጊዜ በትምህርትም በሥራም ላይ በልምድን የተማርነውንና ያነበብነውን ሁሉ በዓይነ ህሊናችን ዳሰስንና ምዘናው እንዲህ ይሆናል ብለን ተነጋገርን:

መሠረታዊ የሆነ የሀገራችን ተፈጥሮአዊ ሀብቷን በተመለከተ፣

መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ወንዝ፣ ሐይቅ፣ ተራሮች፣ እፅዋት፣ እንስሳት፣ የአየር ንብረት ወዘተ …

መሠረታዊ ታሪኳን፤ ቅድመ ታሪኳን፣ ድህረ-ታሪኳን ቢያንስ ዳማት፣ አክሱም ላሊበላ፣ ጎንደር፣ ሀረር፣ ጅማ፣ አዲስ አበባ ወዘተ…

ስለ ህያው ባህሏ (living culture) የብሔር ብሔሮችን አኗኗር ወዘተ…

ስለ ኪነጥበብ - በየገዳማቱ የሚያስጎበኘው ድንጋይና ውሃ ስላልሆነ…

ስለ ምጣኔ ሀብታችን ቢቻል ስለ ኢንቨስትመንት አማራጮችም ማስተዋወቅ…

ስለ መንግስት አወቃቀርና ስለ ፌደራሊዝም፣ ዲሞክራሲያችን (ያለንበት ሀቅ ስለሆነ) …

እና የመሣሠሉትን ብለን ሥንጠብቅ፤ በብሄራዊ ሙዚየም አንድ ትንሽዬ ክፍል ውስጥ  ከዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ እስከ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም የነበሩ መሪዎቻችን ከፊሉ ፎቶና የነገሱበት ጊዜ የተፃፈበት ክፍል ገብተን፣ እንደምታዩት አፄ ቴዎድሮስ ከ1855-1868 ዓ.ም ስልጣን ላይ ነበሩ፤ ከዚያ አፄ ዮሃንስ ተተኩ እያልን ስናስረዳ… እንዴት ዙፋን ላይ እንደ ወጡ፣ ምን እንደሰሩ፣ ለምን እንደወደቁ፤ አፄ ተክለጊዮርጊስ ፎቶአቸው ስለሌለ ልጅ እያሱን እንዲሁ እየዘለልን እንደነገሩ ተወጣነውና እንከንየለሽ ብቁዎች ተብለን የብቃት ማረጋገጫ ወረቀት ተቀበልን እላችኋለሁ:፡

ከዚያም እኔ በግሌ እነዚህ ጥያቄዎች በአእምሮዬ ተመላለሱብኝ:-

መንግስት ባለሙያዎችን በትክክል መዝኖ፤ ብቁውን ወደ ሥራ ለማሠማራት፣ ያልበቃውን ለማብቃት ካልሆነ ለምን ምዘናው አስፈለገ?

ምናልባት ለመገናኛ ብዙሃን ፍጆታ ካስፈለገም፣ የምዘና ማዕከሉ ብቁ የሚለውን ወረቀት እያተመ ለምን አያሰራጭም? የመዛኝም ተመዛኝም ጊዜ ሳይበክን?

በሆቴል እና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ተቋም/ ማዕከል ስም የተሰሩ ዲፕሎማዎች እና ሌሎች ወረቀቶች በሀሰት እየተፈበረኩ እየቀረቡ መሆኑንም በተደጋጋሚ ሰምቻለሁ:: በዚህ ዙሪያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ምን እየሰራ ነው?

ምናልባት ለምዘና የሚከፈለው ገንዘብ ካስፈለገ፣ በሌላ መንገድም መሰብሰብ የሚቻል ይመስለኛል:፡ እባካችሁ ለጥያቄዎቼና ለተጠቀሡት ችግሮች ማብራሪያ የሚሠጥ አካል  ከተገኘ ጠይቁልኝ፡

 

 

Read 1965 times Last modified on Saturday, 28 July 2012 11:07

Latest from