Saturday, 28 July 2012 11:00

ሐረርን በበዓሏ ሰሞን!

Written by  መልካሙ ተክሌ
Rate this item
(0 votes)

በአሚሮች ትተዳደር የነበረችው ከተማ እና ትንሿ የኢትዮጵያ ክልል ሐረር ከቅርብ አመታት ወዲህ ከፍተኛ የውሃ እጥረት ያለባት ከተማ በመሆን ነው የምትታወቀው፡፡ ከተማይቱ የዛሬ አምስት ዓመት የተመሠረተችበትን አንድ ሺህኛ ዓመት ስታከብር፣ በየአምስት አመቱ የሚከበር በዓል አሰናዳች፡፡ ስያሜውን በሐረሪኛ “ዓለም ሑቁፍ ሐረር ሞይ” አለችው፡፡ “ዓለም አቀፍ የሐረር ቀን” ማለት ነው፡፡ በዓሉ ለአንድ ወር የሚከበር ነው፡፡ ባለፈው ሐምሌ 1 ቀን 2004 ዓ.ም በዓሉ በይፋ መከበር የጀመረ ሲሆን ታዳሚዎቹ አውስትራሊያን፣ ካናዳንና ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተሰባሰቡ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ዜጐች ነበሩ፡፡

“ሐረር ታመሠግናለች”

የድሮው ሃረማያ ሐይቅ ቀስ በቀስ እየነጠፈ ሄዶ የእርሻ ማሳና ቤት መስርያ ከመሆኑ በፊት ለሐረር ከተማ የውሃ ምንጭ ነበር፡፡ ሃረማያ ሲደርቅ ከተማይቱና አጐራባቾች በውሃ እጥረት ተቸገሩ፡፡ ይሄኔ ነው “ሐረር ተጠምታለች” የተባለው፡፡ ነዋሪው ለአመታት ተንገላታ፡፡ ሆኖም የፌደራል መንግስትና አበዳሪዎች 530 ሚሊየን ብር መደቡ፡፡ ከ70 ኪሎ ሜትር በላይ በመጓዝም አዲስ የውሃ ምንጨ ተገደበ፤ ድሬዳዋ አካባቢ፡፡ የከተማዋ ነዋሪም መንግስትን፣ አበዳሪዎችንና ድሬን ከውሃ ጥማችን ታደጋችሁን በማለት “ሐረር ታመሠግናለች” አለ፡፡ ዝገው ተቀምጠው የነበሩ የመናፈሻ ፏፏቴ ቧንቧዎች አሁን በውሃ ተሞልተው “ፊኒኒኒ…ን” እያሉ ነው፡፡ ሐረር ለጊዜውም ቢሆን እፎይ ብላለች፡፡ ውሃው ከተሟላ የሚያሳስበው የሰንጋው ጉዳይ ነው፡፡

የሐረር ሰንጋ

የሐረር ሰንጋ ድልብ ነው፣ ጮማ ነው…ብሎ መደስኮር የጥሬ ሥጋ አፍቃሪዎችን እውቀት ማሳነስ ነው፡፡ በሐረር ዙሪያ ያሉ ከተማ ቀመስ ገበሬዎች ብዙ ከብቶች አያረቡም፡፡ ብዙ ከብቶች ካልረቡ ብዙ የሐረር ሰንጋ ከየት ይመጣል? ገበሬዎቹ በነፍስ ወከፍ አንድ አህያ፣ አንድ ላም፣ አንድ ፍየል (ወይንም በግ) አንድ ወይፈን ብቻ ያረባሉ፡፡ ወይፈኑ በደንብ ይቀለባል፡፡ ይደልባል፡፡ በብዙ ሺህ ብርም ይሸጥና ላሚቷ ካልወለደች ጥጃ ይገዛል፡፡ ለአርቢዎቹ ረብጣ ብር ለኛ ሙዳ ሥጋ!

ስልጢና ሐረር

በሐረር ዙሪያ ሐረሪዎች፣ አርጐቦች፣ ኦሮሞዎች፣ አማሮች፣ አፋሮች እና ሶማሌዎች ይኖራሉ፡፡ ድሬዳዋን ጨምሮ ኦሮሚያ፣ አፋር፣ ሐረሪ እና ሶማሊ ክልሎች “አምስቱ የምስራቅ ኢትዮጵያ አጐራባች ክልሎች” በሚል ይታወቃሉ፡፡ እንደ ጉርብትናቸውም ሐረር ዓለምአቀፍ ቀኗን ስታከብር “እንኳን አደረሰሽ” በማለት ጠበል ጠዲቅ መቅመሳቸው የተለመደ ወግና ባህል ነው፡፡ ስለዚህ በእንግድነት ተገኝተው ነበር - በበዓሏ፡፡ እንግዶቿ ግን ጐረቤቶቿ ብቻ አልነበሩም፡፡ ከሰባት መቶ ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት ላይ የሚኖሩትም የስልጢ ተወላጆች በበዓሉ ታድመዋል፡፡ ስልጢና ሐረሪ ግን ያን ያህል የተራራቁ ሕዝቦች አይደሉም፡፡ ርቀታቸው በመልክዓምድር ብቻ ነው፡፡

የእስልምና ሐይማኖት ከሚያቀራርባቸው በተጨማሪ በጋብቻም ከሌሎች በበለጠ እንደተዛመዱ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ ስሊጢዎች በጨለንቆ አደባባይ (የድሮው ፈረስ መጋላ) ባህላዊ ጣዕመዜማ እያሰሙ ነበር፡፡ በነገራችሁ ላይ በርካታ የፌደራል መንግስቱና የክልሎች ባለስልጣናትም በዓሉን ታድመዋል፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር አቶ አሚን አብዱልቃድር፣ የሐረሪ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሙራድ አብዱልሃዲ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣኖች ከተማዋ መሃል በሚገኝ አደባባይ ላይ በስልጢና በአርጐባ ዜማዎች ጨፍረዋል፡፡ ከዚህ ቦታ ትንሽ እልፍ ብሎ አንድ የከተማዋን የጥንት ባለውለታ የሚያስታውስ ሃውልት ቆሟል፡፡

የባለፈረሱ ሐውልት

ከአንድ ሺ ዓመት በላይ ታሪክ እንዳላት የሚነገርላት ሐረር የአሁኑን ቅርጿን እንድትይዝ ከፍተኛ ሚና ከነበራቸው ባለስልጣናት መካከል የቀዳማዊ ሐይለስላሴ አባት እና የዳግማዊ ምኒልክ ከፍተኛ ባለሥልጣን ራስ መኮንን አንዱ ናቸው፡፡

ራስ መኮንን ሐረር፤ ከአዲስ አበባ ቀጥሎ አንዳንዴም ቀድማ ዘመናዊነትን ቀምሳ እንድትራመድ አድርገዋል፡፡ ለዚህ መታሰቢያም ፈረሳቸው ላይ ሆነው አድዋ ሲዘምቱ የሚያሳይ ሐውልት ሐረር ከተማ እምብርት ላይ ቆሞላቸዋል፡፡

ሆኖም ይኼ ሃውልትና በዙርያው ያለው አደባባይ አጥር ስለሌለው ለመኪና ግጭት የተጋለጠ ነው፡፡ የሐውልቱ ጽሑፍም በእርጅና ተላልጦ የእድሳት ያለህ እያለ ነው፡፡

እንግዳ ተቀባይነት

ከአዲስ አበባ ከመነሳቴ በፊት ሐረር ላይ አልጋ እንደተያዘልኝ ቢነገረኝም ስደርስ የተባለው አልጋ አልነበረም፡፡ ያደርኩት በአንድ የሕክምና ተቋም መታከሚያ አልጋ ላይ ነበር፡፡ እንደተመቸኝ እርግጠኛ የነበሩት አስተናጋጆቼ፤ በማግስቱ ስለአልጋው ምቾት ሲጠይቁኝ፤ ግሉኮስ የለውም እንጂ ጥሩ የሐኪም ቤት ስትሬቸር ነው ብያቸዋለሁ፡፡ የሕክምና ታሪክ (Clinical data) መመዝገቢያ፣ ከፍና ዝቅ የሚል አልጋ፣ ፕላስቲክ ሽፋን ያለው ፍራሽ፣…ያሉበት ክፍል ሌላ ምን ሊባል ይችላል!

በማግስቱ ቁርስ ለመብላት አንድ ምግብ ቤት ሄድኩኝ፡፡ አስተናጋጁንም የፆም ፍርፍር እንዲያመጣልኝ ነገርኩት፡፡ ይህን ምግብ ሥጋ የማይወድ ሰው ወይም ጿሚ ሊያዘው እንደሚችል ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ ምግቡ መጣ፡፡ በላሁ፡፡ ላጠናቅቅ ስል ግን ሥጋ አገኘሁበት፡፡ አዘንኩኝ፡፡ ከዛም ሥነሥርዓቱ ወደሚካሄድበት ስቴድየም አመራሁ፡፡ እዚያ ደግሞ ፍቃዴን ሳይጠይቅ የደረት ባጄን መንጭቆ ያነበበ አስተናጋጅ ነው የገጠመኝ፡፡ ማታ ራት ፍለጋ የሔድኩበት ሐረር ቤተመንግስት የምሥራቅ እዝ ምግብ ቤት ከፈተሸ በሁዋላ ለጓደኛው “ማንጐ ብቻ ነው የተገኘበት ይለፍ” ብሎ የአካባቢውን ተመራጭ ፍራፍሬ በብልሃት በማስተዋወቅ አስደምሞኛል፡፡

የማድርበት አልቤርጐ ያለው አስተናጋጅ ደግሞ ክፍሉ ሳሙናና ፎጣ እንደሌለው ስነግረው “ሄደህ ውሰድ!” በማለት የእንግዳ ተቀባይነት ትህትና የጐደለው ትዕዛዝ ሰጥቶኛል፡፡ እዚያ ክፍል ከመግባቴ በፊት አልተከራየም ተብሎ የተሰጠኝን ክፍል ከፍቼ ስገባ ራቁቷን እየታጠበች ያለች ሴት ማየቴም አስደንግጦኛል፡፡ የተሻለ ነው ተብሎ ከሁለተኛው ቀን ጀምሮ ያደርኩበት ቤት የገጠመችኝ አስተናጋጅም የባሰባት ናት፡፡

አስተናጋጇን በዚሁ ሆቴል አልጋ የያዝኩ መሆኔን አስታውሼ የምግብ መምረጫ (Menu) እንድታመጣልኝ ስጠይቃት “ሂድና ባለቤቶቹን ጠይቅ” ብላኛለች በጠየመ ፊት፡፡ በአንፃሩ ሐረር ራስ ሆቴል የገጠመኝ አስተናጋጅ የፈለግሁት ምግብ ለጊዜው ባይኖርም በፍጥነት እንደሚሰናዳልኝ ተሽቆጥቁጦ ነግሮኝ ወዲያው አሰርቶ አምጥቶልኛል፡፡ በማግስቱና በሦስተኛው ቀንም ሞቅ ባለ ፈገግታና በተቀላጠፈ መስተንግዶ ተቀብሎኛል፡፡

ሐረርን በድረ ገጽ

በርካታ የአካባቢው ተወላጅ ዳያስፖራዎች እና የሐገር ውስጥ ነዋሪዎች እንዲሁም የውጭ ሀገር ዜጐች በዓለም አቀፍ የሐረር ቀን አማካይነት ይበልጥ ከተማዋን እየጐበኙ ነው፡፡ በዳያስፖራ እና በእህትማማች ከተሞች መድረክ አማካይነት ሐረር ላይ ሙዋለ ንዋይ እንዲያፈሱም ተጋብዘዋል፡፡ ይህን እያደረገ ያለው መንግስት ብቻ አይደለም፡፡ በከተማዋ ታዋቂ ምግብ ቤት ያለው የዲኒ ምግብ ቤት ባለቤት ወጣት ቢኒያም አብዱረሽድ የራሱን ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ወጣቱ ሐረርን ብቻ የሚያስተዋውቅ እንደ ዩቱዩብ አይነት ማህበራዊ ድረገጽ ከፍቶ ቪዲዮ በመጫንም ጭምር ሐረርን እያስተዋወቀ ነው፡፡ ለዚህ አጋዥ የሆነ ዶክመንታሪ ፊልምም ከአጋሮቹ እና ከሐረር ማዘጋጀ ቤት ጋር በመተባበር ሰርቶ በዲቪዲ ያከፋፍላል፡፡ ማህበራዊ ድረገፁ ቀስበቀስ የተመልካች አትኩሮት መሳቡንም ወጣቱ ተናግሯል፡፡

 

 

Read 1293 times Last modified on Saturday, 28 July 2012 11:04