Friday, 09 October 2020 00:00

ከአፍሪካ በ15 አመታት 836 ቢ. ዶላር በህገ ወጥ መንገድ ወጥቷል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 አህጉሪቱ በየአመቱ በግብር ማጭበርበርና ስርቆት 89 ቢ. ዶላር ታጣለች


         ባለፉት 15 አመታት ከአፍሪካ አህጉር 836 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ በህገ ወጥ መንገድ ወጥቶ ወደተለያዩ አገራት መሻገሩንና አህጉሪቱ በግብር ማጭበርበርና ስርቆት በየአመቱ 89 ቢሊዮን ዶላር ያህል እንደምታጣ ተመድ ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የንግድና ልማት ተቋም ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት እንዳለው፣ የተጠቀሰውን ያህል ገንዘብ ከአህጉሪቱ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ውጭ አገራት ሊሻገር የቻለው ወርቅ፣ አልማዝና ፕላቲኒየምን ከመሳሰሉ ውድ ማዕድናት ሽያጭ ጋር በተያያዘ በተፈጸሙ ሙስና፣ ዝርፊያና የግብር ማጭበርበር ድርጊቶች አማካይነት ነወ፡፡ ከአፍሪካ አገራት ለ15 አመታት የሰበሰበውን መረጃ መሰረት አድርጎ ተቋሙ ባወጣው ሪፖርት፤ከአህጉሪቱ በህገወጥ መንገድ የሚወጣው ገንዘብ እጅግ ከፍተኛ መሆኑ፣ የአፍሪካ መንግሥታት ጤና እና ትምህርትን ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት በሚያደርጉት ጥረት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ገልጧል፡፡
አፍሪካ በግብር ማጭበርበርና ስርቆት ሳቢያ በየአመቱ 89 ቢሊዮን ዶላር ያህል እንደምታጣ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ይህ ገንዘብ አህጉሪቱ በየአመቱ ከውጭ አገራት ለልማት ከምትቀበለው እርዳታ እንደሚበልጥ ገልጧል፡፡ መሰል ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርና የሙስና ድርጊቶች የአህጉሪቱን ልማት እያደናቀፉት እንደሚገኙ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ ለምርት አቅርቦት መቀነስ፣  ለንግድና ኢኮኖሚ ድቀት እንዲሁም ለድህነት መባባስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውንም አመልክቷል፡፡
በሌላ የአፍሪካ የሙስና ዜና ደግሞ፣ በስልጣን ዘመናቸው ከፍተኛ ሙስና ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩት የቀድሞው የሴራሊዮን ፕሬዚዳንት ኧርነስት ባይ ኮሮማ ከአገር እንዳይወጡ በወቅቱ የአገሪቱ መንግስት ዕገዳ እንደተጣለባቸው ቢቢሲ ዘግቧል። ከቀድሞው ፕሬዚዳንት ኧርነስት ባይ ኮሮማ በተጨማሪ በእሳቸው የስልጣ ዘመን በተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች ላይ ያገለገሉ በሙስና የጠረጠራቸው ከ100 በላይ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ የጉዞ እገዳ የጣለው የአገሪቱ መንግስት፣ ግለሰቦቹ በአፋጣኝ የመዘበሩትን ገንዘብ እንዲመልሱና ቤቶቻቸውን እንዲያስረክቡም ትዕዛዝ መስጠቱን ዘገባው አመልክቷል፡፡

Read 946 times