Wednesday, 07 October 2020 16:53

ኢዜማ፤በሁከትና በጉልበት ወደ ሥልጣን ለመውጣት የሚደረግ እንቅስቃሴ አደገኛ መሆኑን አስገነዘበ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

መንግስት የለም# የሚል ቅስቀሳ በሚያደርጉ ወገኖች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቋል

መንግስት የኮቪድ -19 ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ «ሥልጣን ለማራዘም የሄደበት መንገድ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም፣ በዚህም ምክንያት ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም በኋላ መንግሥት የለም፣ ሕዝብና የመንግሥት መዋቅር ለፌደራልና የክልል መንግሥታት ሊታዘዙ አይገባም» የሚል ቅስቀሳ በተለያዩ አካላት ሲደረግ መቆየቱንና አሁንም እየተደረገ እንደሚገኝ የጠቆመው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፤ ቅስቀሳው የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት ከማወክና የዜጎችን ሕይወት አደጋ ላይ ከመጣል የዘለለ ፋይዳ እንደሌለው አስታወቀ፡፡ ይህንንም የኢትዮጵያ ሕዝብ በደንብ እንደሚገነዘብ እናውቃለን ብሏል - ፓርቲው፡፡
#መንግስት የለም የሚለውን ቅስቀሳ እያደረጉ ያሉ አካላት ከዚህ ተግባራቸው ተቆጥበው፣ የጋራ ሀገራችን ሰላምና የዜጎች ደህንነት ተጠብቆ በሰላማዊ መንገድ ችግሮቻችንን መፍታት ወደምንችልበት የውይይት መድረክ መምጣት እንጂ ከዚህ ውጪ በሁከትና በጉልበት ወደ ሥልጣን ለመውጣት የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ለራሳቸውም ቢሆን የማይጠቅም አደገኛ መንገድ መሆኑን ሊረዱ ይገባል።; ሲል አስጠንቅቋል፤ኢዜማ ትላንት ባወጣው መግለጫ፡፡
መንግሥትም እነዚህን ቅስቀሳዎች በንቃት እየተከታተለ አደጋ ከመድረሱ በፊት የመከላከልና አደጋ ለማድረስ የሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ፣ የሀገር ሰላምንና የዜጎችን ደህንነት የማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ ኢዜማ አሳስቧል፡፡
#ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ዘንድሮ እንዲካሄድ የተወሰነውን 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ ማድረግን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባውና ምርጫው እስከሚካሄድና የህዝብ ድምፅ ያገኘው ተለይቶ እስከሚታወቅ ድረስ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ፣ የሀገር ሉዓላዊነትን ማስከበርና ምርጫውን ነፃና ፍትሃዊ ከማድረግ ጋር በቀጥታ
ግንኙነት የሌላቸውን በተለይም በምርጫው የሚወዳደሩ ፓርቲዎች የተለያየ ፖሊሲ አቅርበው የሕዝብን ቅቡልነት ለማግኘት በሚወዳደሩባቸው ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ከማሳለፍና ከመተግበር እንዲቆጠብ እናሳስባለን።; ብሏል ኢዜማ፡፡
#እኛንም ጨምሮ በሀገራችን የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ በነፃነት ተንቀሳቅሰው ሃሳባቸውን መግለፅ እንዲችሉ፣ ከዚህ ቀደም በተስማማንበት የፖለቲካ ፓርቲዎች የቃል ኪዳን ሰነድ መሰረት፣ የምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሰላማዊ፣ ሕጋዊና የሌሎችን መብት ያከበረ መሆኑን እያረጋገጥን፣ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ እንዲሆን
የሚጠበቅብንን ሁሉ እንድናደርግ እንጠይቃለን። ;ሲልም ጥሪ አስተላልፏል፡፡
 የሲቪክ ተቋማትም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተስማሙበትን የቃልኪዳን ሰነድ እንዲያከብሩ ግፊት እንዲያደርጉና  በጋራ ሊሠሯቸውና ሊስማሙባቸው በሚገቡ ተጨማሪ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረግ የሚችሉበት መድረክ እንዲያዘጋጁ ኢዜማ ጠይቋል፡፡
መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም፣ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ፣ በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለምንገነባው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መደላድል የምንጥልበት ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን በመገንዘብ፣ የምርጫውን ሂደት ከአሁን ጀምሮ በንቃት እንዲከታተልና ምርጫው ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚጠበቅበትን ሁሉ ያደርግ ዘንድ ኢዜማ የአደራ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

Read 6000 times Last modified on Wednesday, 07 October 2020 17:55