Tuesday, 06 October 2020 08:17

አንድዬ እና ምስኪኑ ሀበሻ

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(0 votes)

"-እንደው፣ ለትንሹም ለትልቁም እኔን መውቀሳችሁን መቼ ነው የምታበቁት! ችግር ፈጣሪዎች ራሳችሁ፣ የተቃናውን የምታጣምሙት፣ የቆመውን የምትገነድሱት፣ የተደፈነውን የምትሸነቁሩት ራሳችሁ፣  አደራችሁን የበላችሁ፣ ሃቃችሁን ያፈረሳችሁ ራሳችሁ! የእኔን ስም ገንዘብና ጥቅም መሰብሰቢያ ያደረጋችሁ ራሳችሁ! እና… እኔን ምን አድርግ ነው የምትሉኝ?!--"
            


           እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪኑ ሀበሻ በአስቸኳይ እንዲመጣ ተነግሮት አንድዬ ዘንድ ደርሷል፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ! አንድዬ!
አንድዬ፡— ማነህ አንተ በጠዋት እንዲህ የምትጮኸው?
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እኔ ነኝ፡፡ ምስኪኑ ሀበሻ ነኝ፡፡ "አንድዬ ይፈልግሀል፣ በአስቸኳይ ና ተብለሀል" ሲሉኝ ጊዜ፣ ጠቅልዬ አፌ ያደረኩትን እንጀራ እንዲህ ትሪው ላይ ቁጭ አድርጌ ነው ሮጬ የመጣሁት፡፡
አንድዬ፡— እየው እንግዲህ፣ ገና ከመድረስህ ጀመርክ ደግሞ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡— ምን አጠፋሁ!?
አንድዬ፡— እኔ አፍህ ያደረስከውን እንጀራ ሳትጎርስ ና ብያለሁ! እንደሱ ብለው ነው እንዴ መልእክቱን የነገሩህ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አይ አንድዬ፣ እንደሱ ሳይሆን…ፈጥኜ ነው የመጣሁት ለማለት ፈልጌ ነው፡፡
አንድዬ፡— እንደሱ ከሆነ ሌላ ምሳሌ አጣህና ነው! አፌ ያደርኩትን እንጀራ ሳልጎርስ መጣሁ ብሎ ነገርን ምን አመጣው!
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አይ አንድዬ፣ ለክፋት አስቤው ሳይሆን ነገር ማሳመር ልማድ ሆኖብን ነው፡፡
አንድዬ፡— ልማድ ነው ያልከው! ልማድ የሆነባችሁን እኔ እነግርሃለሁ፡፡ አፌ ያደረስኩትን እንጀራ ሳልጎርስ መጣሁ አይደል ያልከው?
ምስኪኑ ሀበሻ፡— እኮ አንድዬ፣ ነገር…
አንድዬ፡— ቆይ፣ ቆይማ…አፌ ያደረስኩትን እንጀራ ሳልጎርስ ነው መጣሁ ብለሀል፡፡ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ይርብሀል። ያን ጊዜ "እሱ ነው አንከውክዎ ጦሜን ያዋለኝ" ብለህ አኔን ሰበብ ልታደርግ፣ እኔ ላይ ጣትህን ልትቀስር ፈልገህ ነው፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— ኸረ አንድዬ እንደሱ አይደለም! ምን ቆርጦኝ፣ እንዴትስ ብዬ ነው አንተ ላይ እንደዛ የማስበው!
አንድዬ፡— እኔ ላይ ብቻ ሳይሆን ማን የሚቀራችሁ አለና ነው! አሁን እኮ የያዛችሁት ትልቁ ነገራችሁ ለሁሉም ነገር አንዳችሁ ሌላኛችሁ ላይ ማሳበብ ነው፡፡ በእናንተ ቤት ሁሉንም ስህተት የሚሠራው ሌላኛው ሰው ነው፡፡ እናንተ ግን ሁልጊዜም ከደሙ ንጹህ ናችሁ፡፡ የራሳችሁን ጥፋት “እኔ ነኝ ያጠፋሁት፣” ብሎ ሀላፊነትን መውሰድ የሞት ፍርድ ነው የሚመስላችሁ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— ቢሆንም አንድዬ፣ ቢሆንም…
አንድዬ፡— ምንም ቢሆንም ብሎ ነገር  አያስፈልግም፡፡ ነገርኩህ፣ ለሁሉም ነገር ሌላ ላይ ማሳበብ ቁጥር አንድ ባህሪያችሁ ሆኗል። እናንተ እኮ ከቋሚዎች የምታሳብቡበት ብታጡ እንኳን መቃብር እየቆፈራችሁ በሰላም ያረፉት ላይ ሁሉ ጣታችሁን የምትቀስሩ ናችሁ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ዛሬ በጣም ነው የተበሳጨኽብን፣ ሀጢኣታችን ይህን ያህል ከፍቷል እንዴ፣ አንድዬ!
አንድዬ፡— ስማ፣ ተበሳጭተኸል አይደል ያልከኝ! ብበሳጭ ይሻል ነበር። አየህ እሱ አንደኛውን የለየለት ነገር ስለሚሆን  አያስቸግርም፡፡ ወይም እዳው ገብስ ነው አይደል የምትሉት! ይልቅ አሁን አንተን ወዳስጠራሁበት ጉዳይ እንግባ፡፡ ለምን ያስጠራሁህ ይመስልሀል?
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ቸኮልክ አትበለኝና “በቃ ያስቀየማችሁኝን ሁሉ ይቅር ብያችኋለሁ፡፡ እርግማኑንም አንስቼላችኋለሁ። ከእንግዲህ ምንም አይነት መከራና ችግር አይደርስባችሁም የሚል መልእክት አድርስ፣” ብለህ ልትልከኝ ይመስለኛል፡፡
አንድዬ፡— እውነት! ለካስ እንዲህ ነገርን ብትንትን አደርጎ ሰሙንም፣ ወርቁንም የሚፈታ አእምሮ አለህና! እኔ እኮ አንደኛውን ይሄ መሬት ወረራ ነው ምናምን እንደምትሉት የአእምሮ ወረራ  ተደርጎባችሁ የተነጠቃችሁ ነበር የሚመስለኝ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ…
አንድዬ፡— አሁን እሱን ተወውና… ስማ፣ እናንተ ሰዎች ምንድነው የምትፈልጉት? ንገረኛ ምን ሁን እያላችሁኝ ነው!
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አ…አንድዬ፣ ግራ አጋባኸኝ እኮ…
አንድዬ፡— እኔ ምን ግራ አጋባሀለሁ፣ እናንተ ናችሁ እንጂ እኔኑ ግራ ያጋባችሁኝ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ…
አንድዬ፡— ቆይ፣ ቆይ… እስቲ ንገረኝ፣ እናንተ ሰዎች ምንድነው የምትፈልጉት! ለእናንተ ተብሎ ዓለም እንደገና ተጠፍጥፋ ትሰራላችሁ! ንገረኛ1
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ..
አንድዬ፡— ቆይ፣ ቆይ አልኩህ እኮ! እናንተም እንደ ማንኛውም የሰው ልጅ  ነው የተፈጠራችሁት፡፡ ሌላው ላይ የሌለ፣ እናንተ ላይ የተገጠመ ባእድ አካል የለ፡፡ እናንተ ብቻ ተለይታችሁ የተላከባችሁ መቅሰፈት የለ! እና ምን እንሁን ነው የምትሉት!
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ይሄን ያህል  ተናደህብናል? በጣም ስትቆጣ አስፈራኸኝ እኮ!
አንድዬ፡— ጭራሽ የተገላቢጦሽ! እወነቱን ንገረኝ ካልከኝ አሁን፣ አሁን ሳያችሁ መፍራት ያለብኝ እኔ ነኝ፡፡ ለማንንም የማትመለሱ ነው የሆናችሁት እኮ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡— ኸረ አንድዬ፣ እንደሱ አትበል! በጣም ነው ያስደነገጥከኝ፡፡
አንድዬ፡— ድንጋጤ ነው ያልከው! ድንጋጤ እኮ አንዳንዴ ጥሩ ነው፡፡ መለስ ብላችሁ እውነተኛውን ነገር እንድታዪ ያደርጋችሁ ነበር፡፡ የምትደነግጡ ብትሆኑ ኖሮማ፣ አሁን የደረሳችሁበት ቦታ ባልደረሳችሁ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— እሱስ ልክ ነህ…
አንድዬ፡— አዲስ ዓመት ሲገባ እስቲ እስካሁን ራሳችሁ በራሳችሁ ላይ ያመጣችኋቸውን ችግሮች ሁሉ ስትፈቱ አያለሁ ስል፣ እኔም እያገዝኳችሁ እንደ አብዛኛው ዓለም ተረጋግታችሁ መኖር ትጀምራላችሁ ስል፣ ጭርሱን ይባስባችሁና ይረፈው!
ምስኪኑ ሀበሻ፡— በእርግጥ ብዙ ችግሮች አሉብን፡፡ እኔም አኮ ወደ አንተ ስመላለስ የከረምኩት አጠገባችን ሆነህ እንድታግዘን ነው።
አንድዬ፡— እንዴት! እንዴት ብዬ፣ በየትኛው ተአምር ነው ላግዛችሁ የምችለው!
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ አሁን እኮ አግዛችኋለሁ ብለህ ነበር፡፡
አንድዬ፡— ታዲያ መጀመሪያ ራሳችሁን ስታግዙ ሳይ ነዋ! መጀመሪያ ራሳችሁን አጥርታችሁ ንጹህ ልብ ሲኖራችሁ ነዋ! እሩቅ ያለው ወገናችሁ ይቆይና…መጀመሪያ ጎረቤታችሁን እንደ ራሳችሁ ማየት ስትጀምሩ ነዋ! ሞፈርና ቀንበር ተሸክማችሁ ማረሱን ትታችሁ፣ ብረት አንግባችሁ ማጥፋቱን ስተተዉ ነዋ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡— እየሞከርን ነው እኮ አንድዬ፣ በየመንገዱ መሰናክሉ በዝቶብን፣ አላራምድ እያለን ነው እንጂ እኛማ እየሞከርን ነው፡፡
አንድዬ፡— እና መሰናክሉ ከየት መጣ?! ንገረኛ! መሰናክሉን ማነው መንገዳችሁ ላይ የሚበትንባችሁ?! እኔው እርግማን አውርጄባችሁ ነው?
ምስኪኑ ሀበሻ፡— ኸረ አንድዬ እንደሱ አይደለም!
አንድዬ፡— ስማ እናንተን በተመለከተ አንድ ስልችት ያለኝ ነገር ምን እንደሆነ ታውቃለህ!  እንደው፣ ለትንሹም ለትልቁም እኔን መውቀሳችሁን መቼ ነው የምታበቁት! ችግር ፈጣሪዎች ራሳችሁ፣ የተቃናውን የምታጣምሙት፣ የቆመውን የምትገነድሱት፣ የተደፈነውን የምትሸነቁሩት ራሳችሁ፣  አደራችሁን የበላችሁ፣ ሃቃችሁን ያፈረሳችሁ ራሳችሁ! የእኔን ስም ገንዘብና ጥቅም መሰብሰቢያ ያደረጋችሁ ራሳችሁ! እና… እኔን ምን አድርግ ነው የምትሉኝ! ንገረኛ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ፣ አንተ እንዲህ ስትቆጣ እኮ እኛም ሆድ ይብሰናል፡፡  
አንድዬ፡— አሁን ሌላ ሌለውን ነገር ተወውና፣ ገና አዲሱ ዓመት እንደገባ አንዳንድ አዝማሚያችሁ አላምር ስላለኝ፣ እኔን አግዘን የምትሉኝ ከሆነ ከመንገድ እየወጣችሁ ያላችሁትን ነገር አስተካክሉ፡፡ አይ አሁን እንደያዝነው እንዳሰኘን እንሆናለን ካላችሁም፣ ምርጫው የራሳችሁ ነው፡፡ ደግመህ ግን በሬን እንዳታንኳኳ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ…
አንድዬ፡— በቃ ተናግሬያለሁ! ራሳቸው ለችግሮቻቸው መፍትሄ ለማግኘት እየሞከሩ ያሉና የእኔን እገዛ የሚሹ ብዙ አሉና ቅድሚያ ለእነሱ ነው፡፡ ሂድና እንዲህ ብሏል ብለህ ንገራቸው፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— ግን አንድዬ…
አንድዬ፡— ጨረሰኩ፣ ደህና ሁን፡፡ በሰላም ግባ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አ…አ…አሜን አንድዬ! አሜን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 854 times