Sunday, 04 October 2020 00:00

“የአንድ ክ/ዘመን የታሪክ ምዕራፍ ተዘጋ”

Written by  አለማየሁ አንበሴ እና መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(2 votes)

 “ሰው ሆነን ለመሞት ከፈለግን፤ ሰው ሆነን እንኑር”
                            
        በኮቪድ 19 ምክንያት በ91 አመታቸው ባለፈው ሳምንት መስከረም 20 ያረፉት አንጋፋው ምሁር፣ ፖለቲከኛና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም፤ ታላቅነታቸውንና ክብራቸውን በጠበቀ መልኩ ስርአተ ቀብራቸው በአዲስ አበባ ቅድስት ስላሴ ካቴድራል እንደሚካሄድ የቀብር አስፈፃሚ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡
የፕሮፌሰሩን ህልፈት ተከትሎ የቀብር ስርአታቸውን የሚያስፈጽም፤ (አርቲስት ደበበ እሸቱ፣ የህግ ባለሙያና የሰብአዊ መብት ተሟጋች አመሃ መኮንንና ረዳት ፕ/ር ነብዩ ባዬ የተካተቱበት) ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን ኮሚቴው በቀብር ስርአት አፈፃፀሙ ዙሪያ ከመንግስት አካላት ጋር ሲመክር መሰንበቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በፕሮፌሰር መስፍን ቤተሰቦች (ልጆቻቸው) ፍላጐትና ኮሚቴው በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሠረት በሚፈፀመው የቀብር ስነስርዓት ዝርዝር መርሃ ግብር ዙሪያም በዛሬው እለት  ለመገናኛ ብዙሀን መግለጫ እንደሚሰጥ አርቲስት ደበበ እሸቱ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
በአሜሪካ የሚኖሩ የፕሮፌሰሩ ሁለት ሴት ልጆችም ዛሬ ኢትዮጵያ እንደሚገቡና ከኮሚቴው ጋር እንደሚመክሩ ታውቋል፡፡
አንጋፋው ምሁርና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም፣ ሚያዝያ 12 ቀን 1922 ዓ.ም አዲስ አበባ ስድስት ኪሎ አካባቢ ነው ተወልደው ያደጉት፡፡ በልጅነታቸው በአካባቢው በሚገኝ የቄስ ትምህርት ቤት (የኔታ ጋር) ገብተው፣ ከእኩዮቻቸው ጋር ፊደል የቆጠሩት መስፍን፤ በቤተ ክህነት ትምህርትም ገፍተውበት ድቁና ማዕረግ ክህነትን እስከመቀጠል ደርሰዋል፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በተፈሪ መኮንን ት/ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃ በጀነራል ዊንጌት የተማሩ ሲሆን በትምህርታቸውም “ሰቃይ” ከሚባሉ ተማሪዎች የሚመደቡ እንደነበሩ ታሪካቸው ያወሳል፡፡ በ1943 ዓ.ም ከ12ኛ ክፍል በቀጥታ የውጭ ሀገር የትምህርት እድል በእንግሊዝ ያገኙት መስፍን፤ ከህንድ ፑንጃብ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን፤ ሁለተኛና ሶስተኛ ድግሪያቸውን ደግሞ ከአሜሪካው ክለርክ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ ከዚያም ወደ ሀገራቸው በመመለስ በካርታና ጂኦግራፊ ኢንስቲቲዩት የበኩር ስራቸውን የጀመሩ ሲሆን በኋላም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጂኦግራፊ መምህር ሆነው በጡረታ እስከተገለሉበት 1983 ዓ.ም ድረስ በትጋት አገልግለዋል፡፡
በተማሩበት የሙያ መስክ ከማስተማርና ትውልድን ከማፍራት ባለፈ ገና የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተማሪ እያሉ፣ ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ ያደርጉ እንደነበር በተለያየ ጊዜ ባሳተሟቸው ጽሑፎች ጠቁመዋል፡፡
በውጭ ሀገር ራሳቸውን በእውቀት ካደረጁ በኋላም የአፄ ሃይለስላሴን ስርአት በመተቸት፣ ደርግም ሲመጣ ያለምንም ፍርሃትና ይሉኝታ ደርግን በመተቸትና ለማቃናት በመሞከር፣ ደርግ ወድቆ ኢህአዴግ ስልጣን ሲይዝም በተመሳሳይ ለሀገራቸው  ይበጃል ያሉትን ፊት ለፊት በድፍረት በመናገር ይታወቃሉ ፕ/ር መስፍን፡፡
በደርግ ዘመነ መንግስት ተሠሚነት ከነበራቸው ምሁራን መካከል ፕ/ር መስፍን በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የማያወላውል አቋም ያላቸው ፕሮፌሰሩ፤ በተለያየ ጊዜ በፃፏቸው መፃሕፍትም ኢትዮጵያዊነትን የሚያንፁ ሃሳቦችን ደጋግመው አንፀባርቀዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ በአንድ ጽሑፋቸው፤ “ይህቺ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ስንት የመከራ ወንዞችን ተሻግራለች! ገና ስንት ትሻገራለች! ስንት የግፍ ተራራዎችን አቋርጣለች! ገና ስንት ታቋርጣለች! ስንት የበደል ሰይፎችንና ጦሮችን አምክናለች! ገና ስንት ታመክናለች! ስንት የውጭ ኃይሎችን አሳፍራለች! ገና ስንቱን ታሳፍራለች!”…ስንቱን አምባገነን እያለቀሰች ቀብራለች! ገና ስንቱን ትቀብራለች”  ሲሉ ሃሳባቸውን ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያ በክፉ የሚያስቧትን ሁሉ ጥላ እንደምትሻገርም ይገልፃሉ - በዚሁ ጽሑፋቸው፡፡
የፕሮፌሰሩ ድንገተኛ ህልፈት ተከትሎ በርካታ ታዋቂና ዝነኛ ፖለቲከኞችና ምሁራን የሀዘን መግለጫ አስተላልፈዋል፡፡ ከጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጀምሮ የክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንቶች የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፣ አንጋፋ ጋዜጠኞች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፤ ፕሮፌሰሩ በህይወት ዘመናቸው ለአገራቸው ስላደረጉት አበርክቶ  አድናቆታቸውን ቸረዋቸዋል፡፡
ታዋቂው ፖለቲከኛ አቶ አንዷለም አራጌ በሰጡት አስተያየት፤ “ፕሮፌሰር የሚያስቡትን ይናገራሉ፤ የሚናገሩትን ይኖራሉ፤ ይህም በንጉሱም በደርግም በኢህአዴግም ዘመን ለእስር ዳርጓቸዋል። ብዙዎች የሚከፈሉበት ስልጣን ገንዘብና መሰል ቁሳዊ ነገሮች እሳቸው ጐን ለመቆም አቅም የላቸውም፡፡
ዛሬ አገራችን ያጣችው አንድ ሰው አይደለም፣ የአንድ ክፍለ ዘመን የታሪክ ምዕራፍ ነው የተዘጋው፡፡ ስራቸው ግን በትውልድ ውስጥ እንደ ደማቅ አጥቢያ ኮከብ ሲያበራ ይኖራል” ብሏል፡፡
የኢዜማ አመራር አንጋፋው ፖለቲከኛ፤ አቶ ግርማ ሰይፉ በበኩላቸው፤ “ሰው ሆኖ ራስን እንዴት ማስከበር እንደሚቻል ያሳዩ፣ ራሳቸው አስበው ልክ ነው ብለው የወሰኑትን ለመተግበር ፈጽሞ ወደ ኋላ የማይሉ… የጽናት ተምሳሌት ናቸው” ሲሉ አድንቀዋቸዋል፡፡
ከፕሮፌሰሩ ጋር እየተገናኙ የማውጋትና የመጫወት እድሉ ነበረኝ የሚሉት አቶ ግርማ፤ “ቤታቸው ሁልጊዜም ለማንም ክፍት ነው፡፡ ጥሬ ስጋ በጣም ይወዱ ነበር። ጥሬ ስጋ አበላላቸው በጣም ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ከዚህ በተረፈ በኪራይ በሚኖሩባት አነስተኛ ቤታቸው በፍቅር ነው የኖሩት፤ የኢኮኖሚ ጉዳይ የእሳቸው ጉዳይ ሆኖ አያውቅም። ለምንም ነገር ደንታ የላቸውም። ውጪ አገር ሲሄዱ እንኳን ልጆቻቸው ቤት ከማረፍ ይልቅ ሆቴል ማረፍን ይመርጡ ነበር። ከሳቸው ህይወት የምንማረው፤ ሰው ሆኖ ለመሞት ከፈለግን፣ ሰው ሆነን መኖር እንደሚገባን ነው፡፡” ከፕሮፌሰሩ ህይወት የቀሰሙትን ገልፀዋል፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ምክንያቱ ባይገለጽም፤ አስከሬናቸው እንዲቃጠል የሚፈልጉ መሆኑን በፃፉት ኑዛዜ ላይ ማስፈራቸው ታውቋል፡፡ አዲስ አድማስ ጋዜጣ በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ ለቤተሰባቸው፣ ወዳጆቻቸውና አድናቂዎቻቸው መጽናናትን ይመኛል፡፡ ነፍስ ይማር!   


Read 7407 times