Print this page
Monday, 05 October 2020 00:00

"ባንጃው፤ ከዕቅዱ እስከ እርምጃው”

Written by  ሻሎም ደሳለኝ
Rate this item
(0 votes)


             ለምን ሞተ ቢሉ
ንገሩ ለሁሉ
ሳትደብቁ ከቶ
“ከዘመን ተኳርፎ
ከዘመን ተጣልቶ”
(ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ፤ የብርሃን ፍቅር ቅፅ-፪)
አለም ላይ በርካታ ኩነቶች ተከናውነው አልፈዋል። በደጉም በክፉም የሚታወሱቱ፣ በታሪክም በኪነትም መዝገብ ላይ ተፅፈው፣ ተተውነው፣ ተሞዝቀው አይተናል። ለአብነት ያህል የፈረንሳይ አብዮትን ማንሳት ይቻላል። የእነ ቻርልስ ዲከንስ ብዕር መዝግቦ ይዞታልና። በኔ እይታ የሁለት ከተሞች ወግ ኪናዊ የታሪክ መዝገብ ነው። ለነገሩ ለልቦለድ ባህሪው ነው። አይነተኛ ሚናው ምን ሆነና?! የማህበረሰቡን ልማድ፣ ባህልና መሰል ኩነቶች ኪናዊነት አላብሶ ማሳየትም አይደል? በእኛም አገር ተመሳሳይ ነገር አልጠፋም።
ይሄ በተስፋላስኪ ተፅፎ ያነበብነው፣ የዋና ገፀባህሪውን ስም ይዞ የታተመው “ባንጃው” የተሰኘ ሁለተኛ የልቦለድ / ልብ ወለድ /(ይህቺ ቃል እነ ገ/ክርስቶስ ደስታንና ዳኛቸው ወርቁን ሁላ ታቧቅስ ነበር አሉ) ስራው፤ ነቅ የወረረውን የታሪካችንን ክፍል እያስቃኘ፣ ከደርግ ውድቀት ማግስት አንስቶ፣ እስከ ዛሬዋ ኢትዮጵያ የሚያደርሰን ኪናዊ አሳንስር ነው።፣
ልጅነታችን ከሚያጋራን ጉዳዮች አንዱ ሕልመኝነት ይመስለኛል። ሃኪም ወይም ሳይንቲስት ፤ ፓይለት አልያም መሐንዲስ ወዘተ . .  ለመሆን  በልጅነቱ ያልተመኘ ሰው ይኖር ይሆን? ዛሬስ የት ነን? ከመንገዱ ፈቀቅ ያለ ስንቱ ነው? ከሕልሙ የሸሸን፣ ከግቡ የፎረሸን ብንጠይቀው፣ ይናገረው ታሪክ ይሰጠው ምክንያት ያጣ ይሆን?
“ማንኛውም ነገር የሚናገርለት ሰው ቢኖረው፣ የራሱ የሆነ ታሪክ አይጠፋውም” ይሉት አባባል ሀሳባችንን አያፀናልን ይሆን? ባንጃው ህግ ማስከበር ህልሙ የነበረ ወጣት ነው። ቤተሰቡን ከድህነት ሊያወጣ የሚሻ ልጅ እግር። ጉልምስናው ላይ ሲደርስ ህልሙን ምን በላው? ይሄን እና መሰል ታሪኮችን እያወሳ፣ 217 ገፆችን ይጓዛል። የቤተሰብንና የጓደኝነትን መስተጋብር፣ ተምሳሌታዊ አድርጎ እሩቅ ያሻግረናል።
“ልጅነት” እና “ጉርምስና” የሚሉ ሁለት ክፍሎች ያሉት መፅሐፉ፤ታሪኩን ሲጀምር በወቀሳ ነው። የአባቱን ምሬት እየተናገረ። ድርሰቱ ሰቆቃን የሚተርክ፣ ሀዘንን የሚሰብቅ ሆኖ ይጀምራል። አተራረኩም ያንን እንዲያጋባ የታሰበ ይመስላል። እምብዛም ቀልብ ገዝቶ አያቁነጠንጥም፡፡  
ማንም ሰው ልጅነትን ሲያስታውስ፣ የዘነበ ወላንና የተስፋዬ አባተን የወንጌ ውሽሚት መጽሐፍ መጥቀሱ አይቀርም። አሊያም የዓለማየሁ ገላጋይ #የብርሃን ፈለጎች; እና  የአዳምን ብዙዎቹን ስራዎች። እነዚህ መጽሐፎች ልጅነትን በአብዛኛው ሲጠቅሱ አማላይነቱንና ፈንጠዝያውን ነው። ነገር ግን ከዚህ ውጭ የጨፈገገ የልጅነት ታሪክ ሳይኖር ቀርቶ አይደለም። የልጅነት ጊዜው 1997 ገደማ የሆነና እሱን ተከትሎ የተከሰተውን የሰቆቃ ታሪክ እየሰማ፣ ያደገ ልጅ ምን ይመስል ይሆን? የሱንስ ታሪክ ለአብነት እንደጠቀስነው፣ የፈረንሳዩን አብዮት ሁሉ ማን መዝግቦ ይያዝለት?
“ ትልቅ ስሆን ፖሊስ ነው የምሆነው “ (ገፅ-8) እያለ ይመኝ የነበረ ልጅ፤የሕይወት ባህር እያላጋች ተጉርምስናው ላይ ከወህኒ ዳር ትጥለዋለች። ባንጃው ከመንትያ ወንድሙ ጋር ሚዛን ላይ ሲወጣ፣ በትምህርቱ ደካማም ቢሆን፣ ገና በልጅነቱ ያነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎች፣ ይጋፈጣቸው የነበሩ አስተምህሮቶች፣ “ብስል” ያሰኙት እንዳልነበር፣ እንደምን የእግሮቹን ፍጥነት ተማምኖ አዳሪ ሆነ?
“እታባ ልጆቼን ሰው አድርግልኝ እያለች በየአጋጣሚው ፈጣሪን ስታሳስበው እሰማለሁ። ሰው አድርጎ ፈጥሮን ሰው አድርግልኝ ብሎ ፀሎት ምን ይሉታል?…’ሰውን ሰው ያደረገው ስራ ነው’ ሲሉ ስሰማ፣ የእታባ ፀሎት ገባኝ።…’ሰውን ሰው ያደረገው ስራው ከሆነ፣ ቀኑን ሙሉ በስራ የደከመው ሰው፤ እንዴት ቢያንስ ጠግቦ ማደር ያቅተዋል?” (ገፅ-9) እያለ ማህበራዊ እሳቤዎች ላይ ትችት ይሰነዝራል።
ለማህበራዊ እሳቤ ብቻ አይደለም ትችቱ የሚወነጨፈው፤ ግብግቡ ከፈጣሪ ጋር ጭምር ነው። “ቤተ ክርስቲያን ሲያስተምሩ ፤ ‘እግዜር ያልሰራ አይብላ’ ብሏል ይላሉ። እና ያልሰራ ካልበላ፣ የሠራ መብላት የለበትም? መቼም እግዜር የባቄላ ግንፍል፣ የስንዴ ንፍር፣ የሽምብራ አሹቅ በልተን ማደራችንን፣ አብልቶ ከማሳደር አይቆጥረውም። … ወይስ ሸሆናቸው ክፍት የሆኑ እንስሳት፤ ባቄላ፣ ሽንብራና ስንዴ ናቸው?” (ገፅ-10) እያለ የምሬት ስላቅ ይሰነዝራል። ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ ድህነት ነው። “የመኖር ደለል በሚባል እንዲህ ያለ ኑሮ መኖሬ፣ ጠግቦ ማደርን የመሰለ ትንሽዬ ፍላጎትን የቅንጦት ያህል ሲያርቅብኝ … የፈጠረኝን እታዘባለሁ። የወለዱኝን እወቅሳለሁ" (ገፅ-10) ብሎ የወቀሳውን ምክንያት እየዘረዘረ፣ ለዋናው የልቦለዱ ግጭት ያንደረድረናል።
ሁለተኛው የልቦለድ ክፍል ጉርምስናውን ያስቃኘናል። የልጅነቱ ጊዜ ያጠላበትን ሽፍታ እንደ ብሉይ ስፕሪንግ ተጠቅሞ፣ ከሀዲስ ኪዳኑ ያደርሰዋል። ጠባሳው አይለቀውም። ይልቁንም እየጎላና እየሰባ ይመጣል እንጂ። “ሞኝና ወረቀት የያዙትን አይለቁም” ይባላል። እውነት ነው። ነገር ግን ሌላ ማከል ሳያሻ አይቀርም። የህፃናት አዕምሮ? እንደመጣልን የምንናገር ሰዎች፣ የሚያደምጡን የልጆች ጆሮ የሚታተሙበት፣ የልጆች አዕምሮ ስለመኖሩ መዘንጋት ምን እንደሚያስከፍል፣ ወቅታዊ የአገራችን ቁመና ጠቁሞን የሚያልፈው ነገር አይኖረው ይሆን?
በልጅነት የልቦለዱ ክፍል የምናየው ቆምጫጫነት፣ ጉርምስናው ላይ አይታይም ባይባልም እምብዛም ነው። ለምን?
“ውበት ባለችበት ውበት ትኖራለች
 ብርሃን ባለችበት ብርሃን ትኖራለች
 ደግነት ባለበት ደግነት ይኖራል…” ያለችውን ዘፋኝ፤ “ፍቅርስ ባለበት” ብንላት ምላሿ ምን ይሆን?
ድርሰቱ በአንደኛ መደብ የተተረከ መሆኑና ተራኪው አካልም ዋና ገፀባህሪ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ “ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ” የመሆን ተጋላጭነቱ ከፍተኛ ነው። ለምሳሌ ያህል ከፖሊስነት ወደ ነጥቆ አደርነት የተሸጋገረው ተራኪው ገፀባህሪ ባንጃው፤ የሩጫ ክህሎቱን እንዲህ አድርጎ ሲያንቆለጳጵስ ይታያል. . .
(ገፅ-96) “እስኪ ማን ነው እኔ ነኝ ያለ … ሮጦ የሚደርስብኝ ካለ ይያዘኝ!” እያለ ራሱን እንደ ሚዳቆ ዘላይ፣ እንደ አቦ ሸማኔ ተፈትላኪ ማድረጉ ሳያንስ “ንፋስ ሆንኩ” ሲል ይታያል። ይሄን መሰል ራስን የማመናፈስ ችግር በአንደኛ መደብ ላይ የሚያጋጣም ቢሆንም፣ ደራሲው ግን ለዚህ ማጣፊያ የሚሆን ነገር አያጣለትም። ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ባንጃው ለቡሄ ጭፈራ ከጓደኞቹ ጋር ሲሰማራ፤ “የሰፈር ጎረምሶች የተሰጠንን ብር ሊቀሙን ቢሞክሩ’ንኳ በሩጫ የማምለጥ ብቃት አለህ“ ብለው ገንዘብ ያዥ ሲያደርጉት፣ ይታያል። በዚህም የራሱን ጉብዝና ሰዎች እንዲመሰክሩለት ከማድረግ በተጓዳኝ፣ የሩጫ ብቃቱ እንደ ደራሽ ጎርፍ ጉርምስናው ላይ ብቅ ያለ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው። ይሄም በገፀባህሪ አቀራረፅ ወቅት ዘላቂነት፣ ፍፁማዊነትና ግለ ወጥነት ከምንላቸው ውስጥ ዘላቂነትን የሚያሟላ ሆኖ እናገኘዋለን።
ሌላ ማጣቀሻም ማከል ይቻላል። “እያንዳንድሽ ከዚህ በኋላ ለምን አቦሸማኔ አልሽው እያልሽ ስትለፈልፊ እንዳልሰማሽ “ (ገፅ-118) ብላ ከስራ አጋሮቿ ጋር መላተሟ ሳያንስ፣ አቦሸማኔ ብላ የሰየመችውን መጤውን ባንጃው “አሯሯጡ ከሁልሽም ይለያል” ብላ እዛው ገፅ ላይ ስትመሰክር ይታያል። ይሄም የፍየሌ የምስክርነት ቃል፣ ከባንጃው ጋር በፍቅር መውደቋን ላየ ሰው ጥያቄ ይጭርበት ይሆናል። ለጥያቄው ምላሽ ለማግኘት ወደ ገፅ-92 የመጀመሪያ ቀን ግጥምጥሞሻቸው ይመልሰናል።
ሌላኛው የልቦለዱ ውበት ተምሳሌታዊነቱ አልያም Symbol አበጃጀቱ ነው። ዋርካው ከእነ ቆራጩ፣ ቡናው ከእነ መልኩ፣ አትጠገብ ከእነ ሻሿ ተምሳሌታዊ ፍቻቸው ሩቅ ነው። የሙዚቃ ምርጫዎቹና የስንኞቹ አገባብ ልክክ ያለ ነው። የቃል ክምርን፣ የገለፃ ድሪቶን የሚከላ ነው። የባንጃው ተክለ ሰውነት እንኳን የተገለፀው በዘፈን ስንኞች ውስጥ እንጂ ሀላል በሆነ መልኩ አይደለም።
አባቱ አቶ አበራ ለልጃቸው ባንጃው የፃፉለት ደብዳቤ፣ በመፅሐፉ ገፅ ላይ የሰፈረበት የአከታተብ ሁኔታ ከሌላው የተለየ ሲሆን በቃልና ቃል መሀል ሁለት ነጥብ እየዶለ፣ ግድግዳ ሆኖ እየለየ የሰፈረ ነው። ይሄም ይሁነኝ ተብሎ የሰፈረና ደራሲው ለገፀ ጽሁፋዊ ውበት የተጠቀመው እንደሆነ ይታያል። “ፀፀት በደብዳቤው ላይ እንዳሉት ሁለት ነጥቦ፣ ከፊትም ከኋላም ከበበኝ” እና “ጥፋተኝነት በደብዳቤው ላይ እንዳሉት ቃላቶች ጥርት ብሎ አፈጠጠብኝ” (ገፅ-208) የሚሉት ንግግሮች፣ ይሄንኑ የሚያመለክቱ ናቸው።
አንዳንድ ቦታዎች ላይ ሊታለፍ በማይችል መልኩ የፊደል ግድፈት ከመታየቱ በተጨማሪ ደራሲው “ጎርሰን ከጉሮሯችን የደረሰውን ምግብ አላምጬ ካልሰጠኋችሁ” ብሎ ሊያስመልሰን ሲታገል እናገኛለን፡፡ እርግጥ ልቦለድ እንደ ግጥም ስላልሆነ፣መዘርዘር ወይም ማብራራት ይችላል፡፡ እስካልተደረተ ድረስ። ነገር ግን በህቡዕ ተገልጠው ሊታለፉ የሚችሉ ታሪኮችን፣ ቀሚሳቸውን ገልቤ እርቃናቸውን ካላሳየዋችሁ ይለናል፡፡ ይሄ ደግ አይመስለኝም። እኔስ ምን ስራ አለኝ፣ ሁሉን አንተ ከሰራኸው? ለማለት እንወዳለን፡፡
ፕ/ር ብርሃኑ ዘሪሁን እንደሚሉት፤ ጭብጥ ዘላቂነት ሊኖረው ይገባል። ዘመን ተሻጋሪ ሆኖ በየጊዜው የሚወደድ ስራ እንዲሆን መትጋት፣ የደራሲው ትልቅ ፈተና ይመስለኛል። እንደኔ እንደኔ፤ ድርሰቱ የተሸመነበትና ገፀባህሪያቱ የተሰየሙበት መንገድ እንደ ጆርጅ ኦርዌሉ “አኒማል ፋርም” ቢሆን እመርጥ ነበር። ነገር ግን ታሪኩ፣ መቼቱና መሰል አላባውያን ለሁላችንም ቅርብ በሆነና በጭፍን የሚለይን ታሪክ፤ ስምና ፆታ ቀይሮ ገፀባህሪን መቅረፅ፣ አንባቢን ማጃጃል ነውና፣ ደራሲው ለህትመት የቀረበበትን መንገድ መምረጡን አሜን ብዬ እንድቀበል ተገድጃለሁ። የሀብታሙ አለባቸውን “አውሮራ”፣ ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።
በመጨረሻ አንድ ጥያቄ ሰንዝሬ የመጽሐፍ ቅኝቴን ልቋጭ፡፡ እውነት እንደሚባለው በዚህ ዘመን ተተኪ የልቦለድ ደራሲያንን አላፈራንም ማለት ይቻላል? መድረኩ ለውይይት ክፍት ነው። መልካም ሰንበት፡፡


Read 3689 times