ባለፉት ስምንት ዓመታት ለእይታ የበቁትን የመጨረሻዎቹን 3ቱን የባትማን ፊልሞች ዲያሬክት ያደረገው ክሪስቶፈር ኖላን፤ ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ፤ የባትማንን ፊልም በሌላ ክፍል የመስራት ፍላጎት እንደሌለው ገልፆ ገፀባህርይው ለብዙ ክፍሎች የሚበቃ በመሆኑ ዋርነር ብሮስ ተተኪውን ቢያፈላልግ ጥሩ ነው ሲል መክሯል፡፡የመስርያ በጀቱ 250 ሚሊዮን ዶላር የሆነውን “ዘ ዳርክ ናይት ራይዝስ”፤ ባለፈው ቅዳሜ የኦስካር ድምፅ ሰጭዎች ተመልክተውት ለብዙ ሽልማት የማይበቃ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በፊልሙ የባትማንን ገፀባህርይ በመሪ ተዋናይነት የተወነው ክርስትያን ቤል ነው፡፡ ሞርጋን ፍሪማን፤ አና ሃታዌይ፤ ማይክል ኬን፤ ኬቲ ሆልምስ፤ ሊያም ኔሰንና ጋሪ ኦልድማን ደግሞ በፊልሙ የተሳተፉ ታላላቅ ተዋናዮች ናቸው፡፡