Thursday, 01 October 2020 12:31

የበዕውቀቱ ዓይናፋር የፍቅር ስንኞች!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

"-ፍቅር ሲወለድ አንዳንዴ ከኋላው የሚያስከትለው ግልገል አለ፡፡ ያ ግልገል ቅናት ነው፡፡ ብዙ ከያንያን ስለ ቅናት ብዙ ያቀነቅናሉ፡፡ እኛም በየጓዳችንና በልባችን እልፍ እንቀኛለን፡፡ ሆድ እየባሰን፣ ቅናት እያመሰን! በአደባባይ የሚናገሩ ግን ብፁዐን ናቸው፡፡ መድሃኒቱን ያገኛሉና!"
                 
          ደብልዩ ኤች አውደን ግጥምን “Memorable speech” ይሉታል፡፡ ስለ ግጥም ብያኔ፤ ድንበር ማበጀት፣ ድንኳን ጥሎ ስያሜ ማሠጠት አልተቻለም፡፡ አንዳንዶቹ በሙዚቃው ሲመሰጡ፣ ሌሎቹ በቃላቱ ከፍታና ስደራ ሲደነቁ፣ ሌሎቹ ደግሞ ሃሳቡን ሲያንቆለጳጵሱ ሁለት ሺህ ዓመታት ያህል አልፈዋል፡፡ በርግማን የተባሉ የዘርፉ ሊቅ፤ “how of poetry have been searching for an accurate definition of it for atleast two thousand years” ያሉትም ለዚሁ ነው፡፡ ዘመኑ ከዚያም ይርቃል፡፡ ይሁንና ይህ ነው የሚባል ጠርዝና እስከዚህ የሚባል አድማስ አልተበጀለትም። ዋነኛው ዜማ ነው ለሚሉትም፣ ቃላቱ እንደ ምጣድ ላይ ተልባ ዘልለው ሰማይ ይረግጣሉ፣ ለሚሉት፣ ቀለም የተነከረ ዓለም ነው - ብለው ለሚዘምሩትም የየራሳቸው መግቢያ በር - የሚመዙት ጥቅስ አላቸው፡፡
እኔ ግን “memorable speech” በሚለው ሃሳብ፤ የፍቅርን እልፍኝ የዳሰሰውን የገጣሚ በዕውቀቱ ሥዩምን ግጥሞች ነቅሼ፤ ስሜቶቹን እዳስስ ዘንድ የመስከረም ስሜት፣ የአዲሱ ዓመት ሰማይ ጠቅሶኛል፡፡ በዕውቀቱ  “ለማለዳ ድባብ” ውስጥ ስለ እንቁጣጣሽ ጽፏል፤ ግን ስለ አበቦቹ አይደለም፡፡ በአበቦቹ መካከል ስለሚመላለሱት የእቴ አበባ ድምፆችም አይደለም፡፡ ሌላ ነው፤ ስለ ሌላ ሌላ፡፡ ባለፈው ዓመት በመስከረም ወር ከገጣሚ አበረ አያሌው ግጥሞች ጋር ያፈነገጡ መልኮቻቸውን አሳይቻለሁ፡፡ ግጥምና ፍልስፍና አንዳንዴም ፍንገጣ ነው። በሃሳብ ማፈንገጥና በቅርጽ ማፈንገጥም ለገጣሚ መብቱ ነው፡፡
ዛሬ ግን የበዕውቀቱ የፍቅር ዋሽንቶች ዜማ፣ ልቤን ስለኮረኮረው ነው መሰል፣ ፍቅርና ትዝታ ከንፈር ለከንፈር እንዴት ገጠሙ ብለን እንድናይ ወይም እንድንቆዝም፣ አፀዱ ላይ ያሉትን አበቦች ሽታ እዋሳለሁ፡፡
ብርሃኑ ገበየሁ “የአማርኛ ስነ ግጥም” በሚለው መጽሐፉ እንዳሰፈረውና በገሃድም እንደምናየው፣ የቀድሞ የሀገራችን ገጣምያንና መካከለኞቹ ስለ ፍቅር ለመጻፍ እምብዛም ድፍረቱ አልነበራቸውም፡፡ የዚህ መነሻው ምንድነው? የሚለውን ፍለጋ ለማሰብ መባተትም አያስፈልግም፡፡ ባህላችን ፍቅርን፣ ለሴት መሸነፍን እንደ ስንፍና… እንደ ልፍስፍስነት የሚቆጥር በመሆኑ ነው። እንደኛ ዐይነቱ ቆፍጣናና ጦረኛ ሕዝብ፤ ሴት እግር ስር ወድቆ መገኘትን በእጅጉ ይኮንነዋል፡፡ “እወድሻለሁ” ብሎ መናገር እንኳ በዘመድ አዝማድ ያስወቅሳል፡፡ እንደ ዛሬ የፈረንጅ ባህል አለቅጥ እላያችን ላይ ሳይጋልብና መስመር ሳንስት፣ የማህበረሰቡን ድንበሮች እንፈራቸው ነበር፡፡ ግን ደግሞ ፍቅር ነፃነት ነው፡፡ ፍቅር ሕይወትም ነው፡፡ ፍቅር ውብ ዓለምም ነው… ለማለት አሁንም ጓዳ ጓዳውን ካልሆነ ገና ነን፡፡
በዕውቀቱ ሥዩምንም በዚህ እጠረጥረዋለሁ፡፡ ገና በለጋው አሳትሞ ለገፀ ንባብ ያበቃት “ኗሪ አልባ ጐጆዎች” የግጥም መድበሉ፤በርካታ ማህበራዊ፣ ፍልስፍናዊና ጥበባዊ ጭብጦችን ይዛ ስትመጣ ስለ ፍቅር ለመጠበብ ግን ተቆጥባ ነበር፡፡
አሁን ግን ከዕድሜ ተምሮ ይሁን ንባብ አበልጽጐት አሊያም ለውጭው ዓለም መጋለጡ፤ ፍቅርን ለመግለጥ የስሜቱን ከፍታ ለማሳየት ዐይኖቹን የገለጠ ይመስለኛል፡፡ ከበዕውቀቱ ጋር በልቤ ኩርፈኛ ነኝ፤ ነፍሴ ግን በፍቅር ጅረት ይፈስሳል፡፡ ስለዚህ ሥራዎቹን አንዴ ብቻ ሳይሆን ሁለቴ ሦስቴ አራቴ… ብዙ ጊዜ እንደ አይሁድ የወይን ቦታ ዘርዘር ማለቴ አይቀርም፡፡ ሆምጣጤ ቢያፈራም፤ ጣፋጮችን ፈልጐ መጉረስ ግድ ነው፡፡ የበሰለ መሬት፣ ጤፍ የሚዘራበት ሁዳዴ በዋዛ አይተውምና አሁንም በዕውቀቱ ናፍቆቴ ነው፡፡ መዝሙሬም ሳቄም፣ ትካዜዬና ሀዘኔም ነው፡፡ እግዜር የለኮሰው የአድማስ ጥግ ሳይሆን የምድረ ዓለሙ ችቦ ይመስለኛል፡፡ ሙቀቱም ዜማውም ያስፈልገኛል፡፡ ሲያናድደኝ ለመስደብ፣ ደስ ሲያሰኘኝ ለመመረቅ ሁሌ ወገቤ የታጠቀ፣ ልቤም የተዘጋጀ ነው፡፡ በዚህ መንፈስ መጽሐፉን ስፈትሽ፣ ሰሞኑን በመስከረም ልቤ ያየኋቸው የፍቅር ስሜቶቹ መስጠውኝ፣ ወይም ቆንጥጠውኝ ነው በሱ ብቅ ያልኩት፡፡
ምናልባት ከላይ በጠቀስኩት ሀፍረት ይሁን በራሱ ምርጫ፤ የተለያዩ ሀገራት ገጣምያንን ሥራ በራሱ ለዛ አቅርቦታል። ከነዚህ ውስጥ ደግሞ በዓለማችን እጅግ ከሚወደዱት፣ የዓለምን ቀልብ ከሳቡት ገጣምያን  አንዱ የሆነውን ዊልያም በትለር ሮትስን መርጧል፡፡ እስቲ እንይለት፡-
“ህልሜን አደራ”
ባይመረመሬ፣ ጥበብ ተሽቀርቅሮ
ከወርቃማው ብርሃን፣ ከብርማ ፀዳል
የተሰራ ሻማ፣ ማግኘት ብችል ኖሮ
ከውብ እግሮችሽ ሥር፣ እዘረጋው ነበር
ግና ምንም የለኝ፣ ከህልሞቼ በቀር፣
የኔ ውድ እንግዲህ
ህልሜን እግሮችሽ ሥር፣ ከዘረጋሁ ወዲህ
ዝግ ብለሽ እርገጪ፣ ዝግ ብለሽ ሂጂ
ህልሜ ላይ ነውና፣ የምትራመጂ፡፡
ይህንን ለመተንተን ፍላጐቴ አይደለም፡፡ ብቻ ረቂቅና ተጨባጭን ለማንፀር፣ ህልምና ሀብትን በማቆም፣ ለፍቅር ያለውን ከበሬታ፣ የምርኮኝነቱን ዳር ያሳይበታል፡፡ ህልሙ ላይ የምትራመድ የተወደደች ሴት አለች፡፡ ህልም ብቻ ያለው፣ ያንኑ ውድ ያለውን የሚሰጥ ሰው አለ፡፡ ያ ሰው ድንቅ ነው! ድንቅ ሰው፤ ድንቁን ለፍቅር ያነጥፋል!
በዕውቀቱ አሁንም ይህንኑ ገጣሚ የፍቅር አፅቆቹን ሰብስቦ፣ የሰው ልጅ ሕይወት የፍቅር ሰንሰለት መሥራት የፈለገ ይመስላል። በቀጣዩ ግጥሙ ደግሞ አፍቃሪ ሁሉ እኩል እንዳልሆነ፣ ምናልባትም ከረዥም ዓመታት በፊት ራሱ በፃፈው መጣጥፍ፣ ሲግመንድ ፎሮይድ ስለ ባለቤቱ የተናገረውን፣ የውበት ጤዛ ሲረግፍ፣ የማይለወጥ የልብ ውስጥ የፍቅር ፍም የሚያስታውስ ይመስለኛል - ምርጥ ሃሳብ! ርዕሱ ግን ብዙም አይስብም፡፡  
“ግን አንድ ሰው አለ”
እርጅና ሲጫንሽ
እድሜ ተጠራቅሞ፣ እንዳስም ሲያፍንሽ
ሽበት እንዳመዳይ
በጭንቅላትሽ ላይ
በድንገት ሲፈላ
ያይንሽ ከረጢቱ፣ በንቅልፍሽ ሲሞላ
ምድጃ ዳር ሆነሽ
መጣፍሽን ከፍተሽ
ያለፈውን ዘመን፣ ገልጠሽ ስታነቢ
የኔን ቃል አስቢ፤
ስንቶች አፈቀሩት፣ በሐቅ በይስሙላ
የገድሽን አቦል፣ የውበትሽን አፍላ
ግን አንድ ሰው አለ
ከሌሎች ወንዶች ጋር፣ ያልተመሳሰለ
በዐፀድ ድንቅ ነፍስሽ፣ ፍቅር የነደደ
የመልክሽ ፀደይ ሲያልፍ
ልክ እንደመስቀል ወፍ፣ ጥሎሽ ያልነጐደ።
በሰው ልጆች የህይወት እርከን ላይ አንዱ ቀዝቃዛ ስሜት፣ የመርገፍ አንጓ፣ የትዝታ ቋጥ፣ የተስፋ ምክነት እርጅና ነው፡፡ ውበት ፈርሶ፣ ተስፋ ተደርምሶ፣ ብርሃን ደብዝዞ፣ ፍርሃትና ጨለማ ከፊት የሚገተርበት ዕድሜ! በዚህ ጊዜ የሚገለጥ መጽሐፍ አለ፤ የሚያጓጓ ሥዕል! ትዝታ!
ገጣሚው የትስ የሚለውና በምሠላ ያሳየን ይህንኑ ነው፡፡ “የውጭ ውበትሽን ዐይቶ ሁኔታዎች ሲለወጡ ከአበባ ጋር ብቅ እንደሚል ወፍ ሳይሆን ውስጥሽን የወደደ፣ ኪዳንሽን ያልከዳ፣ የተለየ ዐይን ያለው አፍቃሪ አለሽ፤ ያንን አትርሺ1; እያለ ነው፡፡ እውነት እንዴት ስሜት ይነካል? የሰው ልጅስ ጉዞ ምንኛ ያሳዝናል? መብቀል--ማበብ---መርገፍ---መድረቅ! ይኸው ነው፡፡ ገጣሚ ይህንን ለማየት ዐይኖቹ ከዋክብት፤ ልቡ ማሾ ነው! አሁን ሆኖ የሩቁን ያያል፡፡ ፍቅርና ፍቅርን!
ፍቅር ሲወለድ አንዳንዴ ከኋላው የሚያስከትለው ግልገል አለ፡፡ ያ ግልገል ቅናት ነው፡፡ ብዙ ከያንያን ስለ ቅናት ብዙ ያቀነቅናሉ፡፡ እኛም በየጓዳችንና በልባችን እልፍ እንቀኛለን፡፡ ሆድ እየባሰን፣ ቅናት እያመሰን! በአደባባይ የሚናገሩ ግን ብፁዐን ናቸው፡፡ ምክንያቱም መድሃኒቱን ያገኛሉና! በዕውቀቱ ስለ ቅናት የፃፋት ግጥም የብዙዎችን በር ታንኳኳለች፡፡ የብዙዎችን ስሜት ትኮረኩራለች፡፡ “እንጉርጉሮዬ” ከሚለው ግጥሙ አንድ አንጓ እወስዳለሁ፡፡
የትም ስከተልሽ
የትም ሆኖ እድልሽ
ሁሉ ያንች ወዳጅ
ሁሉ ባላንጣየ
መፈቀር ሆኖ ጣሽ፣ መቅናት ሆኖ ጣየ
ላንቺ ብስል ፍሬ፣ ለኔ ገለባ ግርድ
ላንቺ እቅፍ አበባ፣ ለኔ እቅፍ ሙሉ ብርድ
ማነው የበየነው፣ ይህን ግፈኛ ፍርድ!!
ቅናት፤ ሳይነድ፣ ነበልባሉ ሳይታይ፤ ውስጡን በጢስ አፍኖ የሚያሰቃይ ሕመም ነው፡፡ አንድ ከያኒ በግልጽ “ወድጄ አይደል የምቀናው፣ ጥሎብኝ ነው የኔ ፍቅር!” ብሎ በአደባባይ እንደተናዘዘው፤ ብዙ ጐጆዎችን ያዘመመው፣ ለብዙ ትዳሮች ቅመም ሆኖ ያጣፈጠው፣ ሚዛን ከጠበቀ ቤት የማያፈርሰው “ቅናት”፤ እንዲህ ተገልጧል። ላንዱ ወገን ብስል ፍሬ፣ ለሌላው ገለባና ግርድፍ እቅፍ አበባና የሚያንቀጠቅጥ ብርድ፤ እንቅልፍ የሚነሳም ሰቀቀን!
ፍቅር፤ ጣፋጭ የናፍቆትና የሙዚቃ ጊዜ፣ የሳቅና የፍሰሃ ዐለም ብቻ አይደለም… ካለፈ በኋላም የሚጣፍጥ አሊያም የሚጐፈንን ምስል፣ የማይፈርስ ሀውልት አለው፣ ትዝታ የሚሉት!!
በዕውቀቱ “መወድስ” በሚል ርዕስ የጻፋት ግጥም፤ በጣም ገላጭና በልብ ውስጥ ውብ ሆኖ የሚቀመጥ ትዝታ አላት፡፡ ግጥሙ ሙሉውን ከሚቀመጥ በመጀመሪያዋ አርኬ ብቻ ቢቀር ግዙፍነቱ፣ እምቅነቱና፣ ድድርነቱ አጀብ ያሰኛል፡፡
ካንቺ ጋራ ሆኜ፣ የኖርኳቸው ጊዜያት
ያሳለፍኩት እድሜ
ጣፋጭ እንደ ሀጢአት
አጭር እንደ ጳጉሜ፤
እንደ ጳጉሜ … ለምን እንዳጠረች ስናስብ ምናልባት የአልበርት አንስታይን የሪሌቲቪቲ ጽንሰ-ሃሳብ ይታወሰናል፡፡ በፍቅር ላይ ጊዜ በእግሩ አይሄድም፤ ሺህ ክንፎች ያወጣል፤ ቢያባርሩ አይደርሱበትም! ገጣሚው ፍቅርን እንዲህ አሳይቶናል!   



Read 3028 times