Print this page
Thursday, 01 October 2020 12:33

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)

  "አዲስ አበባ የዜጐች ሁሉ እናት ናት፡፡ ትንሿ ኢትዮጵያ!... ከተማዋ ስታምር ነዋሪዎቿ ይኮራሉ፡፡ የኢንቨስተሮችንና የጐብኝዎችን ዓይን ትስባለች፡፡ የስራ ዕድል ይሰፋል፡፡ ብራቮ አዲስ!--"
               
             የተማረች ዓይጥ ነበረች አሉ፡፡ የአዲስ አበባ ድመቶች የሚቀኑባት፡፡ አንድ ቀን በሰፈሯ ጐዳና ስትንሸራሸር ከዛፍ ስር ቁጭ ብሎ መጽሐፍ የሚያነብ፣ የመለኪያ ቂጥ የሚመስል መነጽር ያደረገ “ምሁር” ተመለከተች፡፡ አንዳንድ ነገር ለመጠየቅና ለማወቅ ስለጓጓችም ቀረበችውና፡-
“ጤና ይስጥልኝ ፕሮፌሰር” በማለት ሰላምታዋን አቅርባ ሳትጨርስ፣ አድፋጩ እንዳቀረቀረ እጁን ከካባው ስር አሾልኮ ለቀም አደረጋት፡፡ ቀና ብሎም ክንብንቡን ገላልጦ ማንነቱን እያሳያት…
“ስንት ዘመን አስቸግረሽን ዛሬ እጃችን ገባሽ፣ እንደው ምን እግር ቢጥልሽ ነው?” ይላታል፡፡  
ዓይጢትም፤ “ፕሮፌሰር መስለውኝ ለመማር ፈልጌ ነው” ትለዋለች፡፡
“ካ! ካ! ካ!...ለተማረች ዓይጥ መነጽር ያደረገ ድመት ያስፈልጋል ሲባል አልሰማሽም?” በማለት ሊቀረጥማት ወደ አፉ አስጠጋት። በዚህን ጊዜ የዓይኑ መነጽር ሚጢጢዋን ዓይጥ አጉልቶ ጃርት አሳከለበትና ተደናገጠ። እየተደናገረ መነጽሩን ለማውለቅ ሲሞክር አጅሪት አፈተለከች፡፡
ድመቱም ብሽቀቱን ዋጥ አድርጐ፡-
“ስላዘንኩልሽ ለቅቄሽ እንጂ ያመለጥሽኝ እንዳይመስልሽ” ሲላት
“ዊዊዊ--” እያለች በምሁራዊ ቀልድ ተሳልቃበት መንገዷን ቀጠለች፡፡…ምን ብላው ይሆን?
***
አዲስ አበባ ትልቅ ከተማ ናት፡፡ አንዳንዶች "ትልቅ ቆሻሻ ይሏት ነበር፡፡ በዚህ ዘመን አስከፊው ገጽታዋ እየተቀየረ ይገኛል፡፡ ውብና አስደሳች፣ ምቹና ማራኪ ከተማ እየሆነች ነው፡፡ አእምሮን የሚያዝናኑ መናፈሻዎች፣ ጥሩ ጊዜ ማሳለፊያና መንሸራሸሪያ ስፍራዎች በየቦታው እየተዘጋጁ ነው፡፡ ወንዞቿ ፀድተው፣ መጥፎ ጠረን ተወግዶ፣ በመልካም አበቦችና ፍራፍሬዎች ሽታ ልትታወድ ስትተጋ ትታያለች፡፡ እናት አገሯ፤ በችግኝ ተከላ የዓለምን ሪከርድ ማሻሻሏ ሳንባዋን አፍታቶታል፣
አዲስ አበባ የዜጐች ሁሉ እናት ናት። ትንሿ ኢትዮጵያ!... ከተማዋ ስታምር ነዋሪዎቿ ይኮራሉ፡፡ የኢንቨስተሮችንና የጐብኝዎችን ዓይን ትስባለች፡፡ የስራ ዕድል ይሰፋል፡፡ ወዳጄ፡- ራስን ማገዝ አጋር ያስከትላል፡፡ “ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለ ዕዳ አይቀበለውም” ከመሰኘትም ያድናል፡፡…ብራቮ አዲስ!
የዛሬ ሳምንት የከተማዋ የጽዳት ቀን ነበር፡፡ ሰፈርተኞች አካባቢያቸውን ሲያፀዱ ውለዋል፡፡ አዲሷ ከንቲባም ጐንበስ ቀና ሲሉ ነበር፡፡ እናመሰግናቸዋለን! …ከተማዋ በአዲሱ ዓመት አዲስ ሙሽራ ለመምሰል የቆረጠች ትመስላለች፡፡ አዲስና ዴሞክራሲያዊ ምርጫም ይጠብቃታል፡፡ …
ሃሳብሽ ይሙላ እናታችን!
ወዳጄ፡- ለዓመታት የተጫነባት የመልካም አስተዳደር እጦትና ኢ-ፍትሐዊነት አዲስ አበባን ደቁሷታል፡፡ በሰው ሰራሽ የኑሮ ውድነት ጫንቃዋ ተሰብሯል፡፡ ሃብት ንብረቷ ተዘርፏል፡፡ አዲስ አበባ ግን አላኮረፈችም። በተለያየ ምክንያት፣ ከተለያየ የአገሪቱ ክፍሎች ወደ ጉያዋ ለሚጐርፉ፣ ለተሰደዱና ለሚገፉ መጽናኛና ማረፊያም ናት፡፡ አዲስ አበባ ጠበበኝ ብላ አታውቅም፡፡ የፍቅር እጆቿ ረዥም ናቸው፡፡
ቻይነትና ሆደ ሰፊነት፤የእናት ወግ ለመሆኑም አዲስ አበባ ምስክር ናት!
በጨዋና ትሁት ነዋሪዎች የታጨቀችው አዲስ አበባ፤ስሟን የሚያሳድፉ ህገወጦችም ይኖሩባታል፡፡ ባሌስትራ አቅልጠው ወርቅ የሚጋግሩ፣ በመኪና ፍሬቻ ሲጋራ የሚለኩሱ “አሪፍ ሌቦች”ም ይሽለኮለኩባታል፡፡
ከሁሉም በላይ ከተማዋን ያቆሸሻት ግን በ “GIGO” ሲስተም የተፈለፈሉ፣ ጐሰኝነት ፖዘቲቭ፣ ፈጠራና ግኝት ነጋቲቭ የሆኑ አውደልዳዮች በየቀበሌዎቿ መበራከታቸው ነው፡፡ አንዳንዶችም ጐጠኝነት የሚያነቃቃ “ዘፈን” በፍላሽ አስጭነው እያመጡ፣ በየመዝናኛው ቦታ በማስጮህ፣ ;የእኔ እበልጥ፣ የእኔ እበልጥ; ፉክክር ሲያደርጉ ማየት እየተለመደ መጥቷል፡፡ ስንት የጥበብ ፀጋ በተትረፈረፈበት፣ ከአገራዊ ቋንቋዎች አልፎ በሱዳን፣ በህንድና በእንግሊዘኛ በተዘፈነበት አገር፤ አበሻ በገዛ ገንዘቡና በገዛ ጊዜው ፉከራ እየሰማ እንዲያመሽ መገደዱ ያሳፍራል፡፡
ወዳጄ፡- ከከተማ ልማት ጋር ጐን ለጐን የአእምሮ ልማት ካላደገ፣ የጥቂቶች ድካምና ልፋት ብቻ በቂ ፍሬ አያፈራም ወይም ከተገቢው በላይ ድካም፣ ጊዜና መስዋዕትነት ይፈልጋል፡፡ የጥበብ ሞት የአገር ሞት እንደሆነ፣ ልብ ማለት ብልህነት ነው፡፡
በርግጥ አዲስ አበባ የዋዛ ከተማ አይደለችም፡፡ “ታጥቦ ጭቃ” የመሆን ነገር ለሷ ተረት ነው፡፡
አዲስ አበባ አርቆ ተመልካች (Far sighted) ልጆች አሏት። የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ፣ አዲስ ቀን እንደሚወለድ ተስፋ ታደርጋለች…ነገ!! ወዳጄ፡- ነገ ለአንዳንዶች ጥላ ነው፤ የሰነፎች ቅዠት፣ የጐበዞች ህልም፡፡ አዲስ አበባ ደግሞ ጐብዛለች፡፡ ለነገው ወርካ ችግኝ፣ ለመጪው መኸር ዘር በመትከልና በመዝራት የነገን ጭራ ቆንጥጣለች፡፡ “ነገ” ለአዲስ አበባ “ላም አለኝ በሰማይ” አይደለም፡፡ የብሩህ ተስፋዋ ንጋት እንጂ!!
*   *   *
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- አስመሳዩ ድመት አታሎ የያዛትን ዓይጥ ለመዋጥ ተቻኩሎ ወደ አፉ ባስጠጋት ጊዜ ያደረገው መነጽር ዓይጧን አግዝፎ ስላሳየው በሁኔታው መደናገጡን አውርተናል። ድመቱ እየተደናበረ መነጽሩን ለማውለቅ ሲንተፋተፍ፣ አጅሪት ከእጆቹ እንዳፈተለከችበትም አውግተናል፡፡ ከዛ በኋላ ምንም ዓይነት ማስመሰል (masquerade) ቢያደርግ ተመልሳ በእጁ እንደማትገባለት በመረዳቱ ሆን ብሎ የለቀቃት እንደሆነ ለማስመሰል፡-
“በጣም ስላሳዘንሽኝ ነው የለቀቅሁሽ” ሲላት “እንደሱ ሳይሆን አንተ ‘Short sight’ ስለሆንክ ነው ያመለጥኩህ” ብላው መንገዷን ቀጠለች ይባላል፡፡ ምን ማለቷ እንደሆነ ግን ፕሮፌሰር ውሮ እስከ ዛሬም ድረስ አልገባውም፡፡
ወዳጄ፡- #The world can forgive practically anything except people who believe in themselves” በማለት የፃፈልንን ሰው ታስታውሰዋለህ?
ሌላ ጥያቄ፡- “የመጨረሻው ክርስቲያን በመስቀል ላይ የሞተው ነው” ያለውስ ማነው?
መልካም የመስቀል በዓል!
ሠላም!!   

Read 556 times