Saturday, 26 September 2020 00:00

ባልደራስ እና ኦፌኮ ስለ መጪው ምርጫ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 ባለፈው ሰኔ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሣን ግድያ ተከትሎ በተፈጠረው ሁከትና ግርግር፣ በደረሰው የህይወትና ንብረት ጥፋትና ውድመት ተጠርጥረው በእስር ላይ የቆዩ የባልደራስና ኦፌኮ አመራሮች የሽብርተኝነት ክስ እንደተመሰረተባቸው ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል፤ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ተራዝሞ የነበረው አገራዊ ምርጫ ዘንድሮ እንዲካሄድ መንግስት ወስኗል፡፡ የፓርቲ አመራሮቻችን የፖለቲካ እስረኞች ናቸው ብለው የሚያምኑት የባልደራስ አመራር አባሉ አቶ ገለታው ዘለቀና የኦፌኮ ም/ሊቀ መንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ፤ ከምርጫው በፊት ሀገራዊ መግባባት መፈጠር አለበት ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ ምን ዓይነት ብሔራዊ መግባባት? ምንስ ውጤት ለማምጣት በሚለውና በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ዙሪያ ሁለቱን አመራሮች፣ የአዲስ አድማሱ አለማየሁ አንበሴ እንዲህ አነጋግሯቸዋል፡-


              “ምርጫው የግጭት መንስኤ እንዳይሆን ስጋት አለን”
                    (አቶ ገለታው ዘለቀ፤ የባልደራስ አመራር)


             ባልደራስ ዘንድሮ እንደሚካሄድ በሚጠበቀው አገራዊ ምርጫ ላይ ይሳተፋል?
እኛ እንደ ፓርቲ፣ አሁን የሚያሳስበን ምርጫ አይደለም፤ የሀገሪቱ ህልውና ነው። ምርጫን በተመለከተ ምንም የሚያሳስበን ነገር የለም፡፡ ወደኛ የሚመጣው ሰው ብዙ ነው፡፡ እኛ ግን የበለጠ የሚያሳስበን ስልጣን የመያዝ ጉዳይ አይደለም፡፡ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ችግር የሚፈታው በብሔራዊ መግባባት ነው ብለን እናምናለን፡፡ አሁን ድምጽ አዋጥተን ብንመረጥ ለኛ የተከፋፈለች ሀገርን ተረክቦ መምራት ምን ትርጉም ይኖረዋል? የተከፋፈለ ሀገርን እንዴት በምርጫ ብቻ ማዳን ይቻላል? አይቻልም። ምርጫውም ከዚህ በፊት ከነበረው የተሻለ፣ እውነተኛ የህዝብ ውሣኔ ያለበት፣ የህዝብ ድምጽ የሚከበርበት መሆን አለበት። እንደ ቀድሞው ከሆነ ምንም ትርጉም የለውም። ከዚህ አንፃር፣ ሀገሪቱ በአጠቃላይ ለሚፈለገው ውጤታማ ምርጫ ዝግጁ አይደለችም፡፡ ከምርጫው በፊት ቢያንስ በመሠረታዊ የሀገሪቱ ጉዳይ ላይ መግባባት መፈጠር አለበት፡፡ እኛ ብሔራዊ መግባባት ያስፈልጋል የምንለው በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ነው፡፡
ዋና ዋና ጉዳዮች የምትሏቸው ምንድን ናቸው?
የቅርፀ መንግስት ጉዳይ አለ፡፡ እኛ ለምሣሌ አሁን ባለው ቅርፀ መንግስት አንስማማም። በሀገሪቱ ቅርፀ መንግስት ላይ የፖለቲካ ልሂቃኑ ተወያይቶ ህዝቡም ተስማምቶ ወደፊት መራመድ ቢቻል ምን አለበት? ከዚያ በኋላ በፖሊሲ ጉዳይ ላይ መነጋገር ይቻላል፡፡ አሁን ግን ሀገሪቱ በዚያ አይነቱ የፖሊሲ ጉዳይ ላይ  ክርክር ለማድረግ ብቁ አይደለችም፡፡ የቋንቋ፣ ባንዲራ፣ የፌደራል ቅርጽ፣ የፖለቲካ አሠላለፍ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት አልተፈጠረም፡፡ ሁሉም የየራሱን መንገድ ይዞ ነው እየተጓዘና ገመድ እየተጓተተ ያለው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ከሚካሄድ ምርጫ ሀገሪቱ ምን ትጠቀማለች? አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ የኛ መሪዎችም ታስረው ነው ያሉት፡፡ ፖለቲከኞች በታሠሩበት ሁኔታስ ምን አይነት ምርጫ ነው የሚካሄደው?!
የብሔራዊ መግባባት መድረክ በፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በኩል መጀመሩ ይታወቃል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩም ከፓርቲዎች ጋር እየተወያዩ ነው፡፡ እናንተስ በመድረኩ ትሳተፋላችሁ?
እኛ በእነዚህ መድረኮች ላይ እየተጋበዝን አይደለም፡፡ በተለይ ጠ/ሚኒስትሩ በሚያዘጋጁት መድረኮች ላይ አንጋበዝም። እኛ ብቻ ሳንሆን ሌሎችም የማይሳተፉ እንዳሉ ሰምተናል፡፡ ይሄ የሚያሳየው ዛሬም እንደ ትላንቱ  የሚግባቡ ፓርቲዎች እርስ በእርስ ተጨባጭበው እየተለያዩ መሆኑን ነው፡፡ የብሔራዊ መግባባት መድረክ ዋና አላማ ደግሞ የማይግባቡትን ለማግባባት ነው፡፡ እኛ እና ብልጽግና አልተግባባንም፡፡ ባልተግባባነው መካከል ነው ውይይቱ የሚያስፈልገው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ከሚደግፏቸው ጋር ቢወያዩ ምን ይጠቅማቸዋል፡፡ እኔ እንደውም በዚህ አካሄድ ብሔራዊ መግባባት የሚለውን፣ ትርጉሙንና ስሙን እያጠፋነው እንዳንሄድ ነው የምፈራው፡፡ ይሄን የተቀደሰ ሃሳብ ዝም ብለን ባናረክሰው መልካም ነው፡፡
ለምን እንዳልተጋበዛችሁ ጠይቃችኋል?
አዎ ብዙ ጊዜ ጠይቀናል፡፡ ይሄን የምንጠይቀው መብታችንም ስለሆነ ነው። በሀገራችን ጉዳይ ላይ  መወያየት ጠ/ሚኒስትሩ የሚነሱንና የሚቸሩን መብት አይደለም፡፡ እሳቸው ይሄን መድረክ የሚያዘጋጁት እንደ ብልጽግና ሳይሆን እንደ መንግስት ነው፤ የመንግስትን አዳራሽ፣ አገልግሎት ተጠቅመው ነው የሚያዘጋጁት፡፡ ስለዚህ እኛም በዚህ መድረክ የመሳተፍ ሙሉ መብት አለን፡፡ በመድረኩ ላይ ተጋብዘን ስለ ሀገራችን መምከር መብታችን ነው፡፡ ግን ጠ/ሚኒስትሩ ይሄን በችሮታቸው እንዳደረጉት በመቁጠር፣ መርህን እየጣሱ መብታችንንም እየደፈጠጡ ነው፡፡ አንዱ ተገፍቶ አንዱ የቤት ልጅ የሚሆንበት ሳይሆን፣ ሁሉም በአንድ ላይ የሚመክርበት ነው፤ ብሔራዊ መግባባት ማለት፡፡ አሁን የሚካሄደው ግን ያንን ያሟላ አይደለም፡፡
የፓርቲያችሁ ሊቀ መንበርና አባላት ታስረው፣ በሽብር መከሰሳቸው፣ በእንቅስቃሴያችሁ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ምን ያህል ነው?
ፖለቲከኞችን በሽብር መክሰስ ተመልሶ መምጣቱ አሳሳቢ ነው፡፡ እንደውም አንዳንዱ በፊት ከነበረውም  የባሰ ሆኖ ነው ተመልሶ የመጣው፡፡ በተለይ በእነ እስክንድር ላይ የተመሰረተውን ክስ ስንመለከተው ያሳፍራል። የሀገራችንን የፍትህ ተቋማት አሳዛኝ ቁመና ነው የሚያሳየው፡፡ በፍጥነት ወደ ኋላ እየተመለስን እንደሆነ ነው ጠቋሚ ነው፡፡ በተለይ የፍ/ቤት አሠራር በፍጥነት ወደ ኋላ ሄዷል፡፡ እኔ ችሎት ስከታተል የተመለከትኩት ነገር፣ የፍ/ቤቶች ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን ነው። ፍትህ ፍትህ አይሸትም፤ ካድሬ ካድሬ ነው የሚሸተው። የፍትህ ተቋማት አካባቢ አሁንም ገና ብዙ መሠራት ያለበት ስራ እንዳለ ነው የተገነዘብኩት፡፡
ምርጫው የሚካሄድ ከሆነ፣ የእናንተ ተሳትፎ እንዴት ነው የሚሆነው?
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይሄን ከህግ ውጪ፣ በፖለቲካ ፍላጐት የተፈፀመን እስራት በአግባቡ ተረድቶ፣ ከጐናችን እንዲቆም እንጠይቃለን። እኛም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ የማንፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም። በሠላማዊ ትግል እነዚህን እስረኞች እናስፈታለን፤ ታስረው እንዲቆዩ ፈጽሞ አንፈልግም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ምርጫ ውስጥ ዝም ብሎ የሚገባ ከሆነ፣ ሜዳውን ዝም ብለን አንተወውም፡፡ ሠፊ ድጋፍ ስላለን በምርጫው እንሳተፋለን። መሪዎቻችን እንዲፈቱም የማንፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም።
በቀጣዩ ምርጫ ምን ትጠብቃላችሁ?
መቼም ብልጽግና ሊያስመርጠው የሚችል ድጋፍ ያለው ድርጅት አይደለም። አዲስ አበባ፣ አማራ ክልል፣ ኦሮሚያና ትግራይ ላይ ብልጽግና ምን አይነት ቅቡልነት እንዳለው ከወዲሁ እየታየ ነው፡፡ ታዲያ የትኛው ክልል ቢሄዱ ነው ተመራጭ የሚሆኑት? ከዚህ አንጻር፣ ሃቀኛ ምርጫ ቢኖር ይሄ ፓርቲ ላይመረጥ ስለሚችል ሃይል ሊጠቀም ይችላል። በዚያ ላይ ብልጽግና አሁን ስለ ምርጫ ያለው ስሌትና እሳቤ፣ ከዚህ በፊት ህወኃት የነበረውን አይነት ነው። ህወኃት ምርጫ ሲደርስ የሚያሰጋትን ፖለቲከኞች ዒላማ አድርጋ በማሰር ነበር ምርጫ የምታደርገው። ብልጽግናም አሁን ያንን መንገድ ነው የተከተለው፡፡ ነገር ግን ይሄ የብልጽግና ስሌት በጣም ከባድ የሆነ ስህተት ነው፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት የፖለቲካ ሁኔታ ህወኃት ከነበረበት ጊዜ በጣም የተለየ ነው፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ሽግግር እያማጠች ያለችበት ጊዜ ነው፡፡ ለውጥ እያማጠች ነው። በዚህ ሰዓት ዋና ዋና ተፎካካሪ ፖለቲከኞችን አስሬ ምርጫውን አሸንፋለሁ የሚል ስሌት፣ ብልጽግናን ብቻ ሳይሆን ሀገር እንዳያፈርስ ነው ስጋታችን። የአሁኑ የብልጽግና አካሄድ፣ አለማቀፍ ስታንዳርድ ያለው፣ ሃቀኛ ምርጫ ለማካሄድ ፍቃደኝነቱ እንደሌለው የሚያሳይ ነው። ትክክለኛ ምርጫ ለማድረግ የሚፈልግ አካል፣ ምርጫ ሲቃረብ እንደውም የፖለቲካ ምህዳሩን፣ የሚዲያ አውዱን ያሠፋል እንጂ እያጠበበ አይሄድም፡፡ ብልጽግና አሁን በያዘው አኳኋን የሚቀጥል ከሆነ ምርጫው የግጭት ምክንያት እንዳይሆንም ያሠጋናል። የታጠቁ ሃይሎች ባሉበት ሁኔታ ምርጫ የግጭት አውድ እንዳይሆን ነው እኔ በግሌ የሚያሳስበኝ፡፡ ከሁሉ በላይ የሀገር ጉዳይ ሊያሳስበን ይገባል፡፡

Read 1114 times