Saturday, 26 September 2020 00:00

“እቀና ብዬ ነው ቤቴ የፈረሰው”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

 "እናላችሁ…ዓመልን በጉያ ማድረጉ እየተሳነን ነው፡፡ የምር እኮ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ከዕለታት አንድ ቀን የመከባበር፣ የመተሳሰብ፣ “አንተ ትብስ፣ አንቺ” የመባባል ባህል የነበረባት ሀገር አልመስል እያለች ነው፡፡ ክንፎች ሁሉ በአንድ ጊዜ ረግፈው እንዴት ወደ ቀንድ እንደሚለወጡ ግራ ግብት ነው የሚለው፡፡--"
        
           እንኳን ለብርሀነ መስቀሉ አደረሳችሁ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
አጎንብሶ መሄድ አላውቅ ብዬ እንደ ሰው
እቀና ብዬ ነው ቤቴ የፈረሰው
የምትል ስንኝ አለች፡፡ እኔ የምለው…እዚህ ሀገር መቀናናት የሚመስሉ ነገሮች የበዙ አይመስላችሁም! ልክ ነዋ… የሌላውን ሥራ ማጣጣል፣ የሌላውን ችሎታ ማጣጣል፣ ሌላው በበጎ የሚያየውን ነገር ሁሉ ማጣጣል! አንዳንዴም እኮ ‘ያኛውን ወገን’ የፈለገውን ያህል ብናጣጥለው፣ የፈለገውን ያህል… “አይደለም ልቀርበው፣ መቃብሩ ላይ አልቆምም፣” ብንለውም በጎ ሥራ፣ መልካም ሀሳብ ስናይበት…አለ አይደል… “ይህ እንኳን መልካም ሀሳብ ነው፡፡” “እዚህ ላይ እንኳን ጥሩ ሠርቷል፣” ማለቱ እኮ ትከሻችን ላይ የተደረደሩ ከሚመስሉን ኮከቦችና፤ ደረታችንን የሞሉት ከሚመስሉን ሜዳሊያዎች አንዲቷን እንኳን አይቀንስብንም!
ስሙኝማ…የኮከብ ድርደራ ነገር ካነሳን አይቀር… ‘ስሪ ስታር ጄኔራል’ ‘ፎር ስታር ጄኔራል’ የሚባሉ ነገሮች አሉ አይደል! በስርአቱ ከበርካታ አስርት ዓመታት ልፋትና፣ አገልግሎት በኋላ የሚደረስባቸው ማለት ነው፡፡ አሁን ችግሩ ምን መሰላችሁ…ራሳችን ትከሻ ላይ ኮከቦች የደረደርን፣ ራሳችን ደረት ላይ ሜዳሊያዎች ያነጠፍን በዛንሳ!
“አመልክን በጉያ ስንቅህን በአህያ…” የሚሉት ነገር አለ፡፡ እናላችሁ…ዓመልን በጉያ ማድረጉ እየተሳነን ነው፡፡ የምር እኮ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ከዕለታት አንድ ቀን የመከባበር፣ የመተሳሰብ፣ “አንተ ትብስ፣ አንቺ” የመባባል ባህል የነበረባት ሀገር አልመስል እያለች ነው፡፡ ክንፎች ሁሉ በአንድ ጊዜ ረግፈው እንዴት ወደ ቀንድ እንደሚለወጡ ግራ ግብት ነው የሚለው። “እንዴት ያለ ሰው አክባሪ መሰላችሁ!” ሲባልልት የኖረ ሰው፤በሆነ ጊዜ ላይ ከራሱ በስተቀር ሁሉንም ሲያንቋሽሽ፣ ሊያሳንስና ሊያሳጣ ሲሞክር ታገኙታላችሁ፡፡
"እቀና ብዬ ነው ቤቴ የፈረሰው" ነገሬ ላላት አሪፍ አባባል ነች፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይሄ የመናናቅ ነገር ከምን ሀገር ተሞክሮ የወሰድነው ነው? ግርም የሚል እኮ ነው፡፡ “ቀላል እንናናቃለን እንዴ!” እንዲሉ ወጣቶቹ፡፡ እናላችሁ…ገና የለየለን ቺስታዎች ሆነን፣ ገና በእውቀቱም፣ በምኑም በምናምኑም ከአብዛኛው ዓለም ኋላ ድክ፣ ድክ እያልን፣ የየጓዳችንን ጉድ ‘እየተዋወቅን‘ ይህ ሁሉ መናናቅ፣ ይሁ ሁሉ ማጣጣል፣ ይህ ሁሉ “ከእኛ በላይ ለአሳር፣” ምን አመጣው!
ፖለቲከኛ ነኝ ባዩ ሌላኛውን ፖለቲከኛ ነኝ ባይ ሲንቅ፣ “እሱ ብሎ ፖለቲከኛ፣ ቼ ጉቬራ ማነው ብትለው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ነበር የሚልህ እኮ ነው፡፡”
“አንተስ፣ ቼ ጉቬራ ማነው?”
“የሩስያ አብዮት መሪ ነዋ!”
“ሳስቄ ፈረስኩት!” ያለችው ማን ነበረች!
የስነጽሁፍ ባለሙያ ነኝ ባዩ፣ ሌላኛውን የስነጽሁፍ ሰው ሲንቅ…
“ስማ እንትና እኮ የግጥም መጽሐፍ አወጣ፡፡”
“ምን! በቃ እዚህ ሀገር ስነ ጽሁፍ የማንም መጫወቻ ሆነ ማለት ነው!”
“ተው እንጂ፣ የእሱ ግጥሞች እኮ መልካም ከሚባሉት መሀል ናቸው፡፡”
“ምድረ ቲፎዞ ነዋ እንደዛ የሚለው! በቃ የተዘባረቀው ሁሉ በመጽሐፍ ይወጣ ጀመር!”
“እሱ እኮ ሦስተኛ መጽሐፉ ነው፡፡ አንተ ገና አንድስ መጽሐፍ መቼ አወጣህ…”
“ስማኝ፣ እኔ የይድረስ ይድረስ መጽሐፍ ይዤ የምወጣ ሰው አይደለሁም፡፡ ታሽቶ ተበጥሮ ነው የሚወጣው፡፡ ምን አለ በለኝ፣ የእኔ መጽሐፍ በሚወጣ ጊዜ እዚሀ ሀገር እውነተኛው የግጥም ሪቮለዩሽን ጀመረ ማለት ነው፡፡”
“ሳቅቼ ፈረስኩት!” ያለችው ማን ነበረች!
የሚዲያው ሰው፣ ሌላውን የሚዲያ ሰው ሲንቅ…
“እንትና በቀደም እንትን ጋዜጣ ላይ ያወጣውን ጽሁፍ አይተኸዋል?”
“አይቸዋለሁ፣ ደህና የሚነበብ ነገር አለው፡፡”
“አየህ… የአንተንም ጭንቅላት ጠምዝዘውታል፡፡ አሁን ያ ጸሁፍ ምን የሚነበብ ነገር አለበት! ደግሞስ እሱን ማነው ጸሀፊ ያደረገው!”
“እኔ ግን ከሌሎች ሰዎችም የሰማሁት በጽሁፉ አነጋጋሪ ነገሮችን እንዳነሳ ነው፡፡”
“ምን አነጋጋሪ ነው፣ አደናጋጋሪ በለው እንጂ! ሚዲያው እኮ እንደ ሰንበቴ ቤት የፈለገ ሰተት ብሎ የሚገባበት ሆኗል፡፡”
“እኔ እንደሚመስለኝ እሱ እያለፈ፣ እያገደመም ቢሆን ጫር፣ ጫር ያደርጋል፡፡ ቢያንስ በዚህ ክሬዲት ልትሰጠው ይገባል፡፡”
“የሆነ የኬጂ ህጻን ሊጽፈው ለሚችለው ጽሁፍ ነው ክሬዲት የምሰጠው፡፡ እንደ እኔ ቢሆን ጋዜጣ ባለበት ዝር እንዳይል የዕድሜ ልክ እገዳ ነበር የምጥልበት፡፡”  
   “ሳቅቼ ፈረስኩት!” ያለችው ማን ነበረች!
እናማ… ”እቀና ብዬ ነው ቤቴ የፈረሰው“ ነገሬ ላላት አሪፍ አባባል ነች፡፡
ስሙኝማ… ይሄ ክልከላው ለቀቅ ሲል እንዴት ነው እንዲህ ሀምሳ ዓመት ተቆልፎብን ድንገት የተለቀቅን እያሰመሰልን ያለነው! እንደምንሰማው ከሆነ ከተማዋ ማታ፣ ማታ እንደገና በጥፍሯ መቆም ጀምራለች አሉ፡፡ እንግዲህ “አሉ” ነው፡፡ (ሁሉንም ነገር…ሹክ ባይ አያሳጣንና!) ቂ…ቂ…ቂ…
“ናይት ላይፉን ለምን አታየውም!”  እያላችሁ ምልመላ ነገር የምትሞክሩ ወዳጆቻችን ለጊዜው የእኛንም እናንተ ካያችሁልን ይበቃል፡፡
“ስማ ማታ ወጣ፣ ወጣ አትልም እንዴ!”
“የት ነው ወጣ፣ ወጣ የምለው?”
“ከተማ ነዋ! አንተ የምታውቀው ድሮ ድራፍት በጆግ የሚጠጣበትን ከተማ ነው። ልጄ አሁን ሌላ ሆናለች፡፡ ስማ… በፊልም ላይ የምታያት ላስ ቬጋስ እኮ እዚሁ ነች፡፡ ከፈለግህ አሳይሀለሁ፡፡”
“አመሰግናለሁ፡፡ ግን እኔ ማታ መውጣትም ብዙም አይመቸኝም!”
“አንተ ሰውዬ፣ ሪሊጂየስ ሆነሃል እንዴ!”
አይ ምነው! በህግ አምላክ! የምን ‘ማነካካት’ ነው፡፡ “አዎ፣ ሆኛለሁ…” ከተባለ እኮ ቀጥሎ … አለ አይደል… “ዛሬ ያየሁትን ህልም ብነግርህ…” በተባለ ቁጥር ነገር ሊጠመዘዝ ነው፡፡
“ዛሬ ያየሁትን ህልም ብነግርህ ይገርምሀል፡፡”
“ምን አየህ?”
“የሆነ በተራሮች፣ በአረንጓዴ መስኮች፣ በምንጮች፣ የተሞላ ቦታ ውስጥ ያለሁ ይመስለኛል…” ምናምን ትሉታላችሁ። ከዛ እሰከ መጨረሻ ‘ምእራፍ’ መሄድ ሳያስፈልጋችሁ ‘ቅኔው’ ይፈታል፡፡ እሱዬው ይሄድና ምን ቢል ጥሩ ነው…  
“ስሙኝ እናንተ… ይቺ ሀገር በአጭር ጊዜ የሰማይ ቤቷን ገነት ባትመስል ምን አለ በሉኝ፡፡”
“በምን አወቅህ?”
“እንትና ራዕይ ታይቶታላ!”
“ምን! ደግሞ እሱ በእውን ያለውን በደንብ ማየት የማይችል፣ ከመቼ ወዲህ ነው ራዕይ ማየት የጀመረው!”
“አልሰማችሁም እንዴ! ሪሊጂየስ ሆኗል እኮ!”
“አትለኝም! ምነው ታዲያ እስካሁን ዩቲዩብ ቻናል ያልከፈተው!”  ቂ…ቂ…ቂ…
ቆይማ… እኔ “ህልም አየሁ” አልኩ እንጂ ራዕይ የሚል ቃል ወጣኝ! ደግሞ እኮ ህልሜን ጨርሶ አልሰማኝም፡፡ ልክ ነዋ…በኋላ ላይ በሁሉም አቅጣጫ ስለከበቡኝ የጁራሲክ ፓርክ ዳይናሶሮች መች ነገርኩት! አሀ…እሱን ቢሰማ ታሪኩ ይለወጥ ነበራ…
“ስሙኝ፣ እኛ ዓለም ዘጠኝ ብለን ተቀምጠን ድራፍታችንን ስንገለብጥ ለካስ በዙሪያችን በዳይናሶሮች ተከበናል!”
“አንተ በምን አወቅህ…እንትን አስረህ መቀለብ ጀመርክ እንዴ!”
“እንትና በራዕይ ታይቶታላ!”
“የሚያየው ሲያጣ ዳይናሶር ማየት ጀመረ?”
በቃ በአረንጓዴ መስክና በምንጮች ተከቦ ደስ ብሎት እያለ ከየት መጡ ሳይባል ዳይናሶሮች አይከበብ መሰላችሁ! እኔ እኮ ስምንተኛው ሺህ ውስጥ ገብተናል ስላችሁ አልሰማ ብላችሁ ነው!”
“ስማ፣ እሱ አረቄውን፣ ጠጁንም እያንቃረረ የቃዠውን ሁሉ ራዕይ ታይቶኛል ማለት ጀመረ እንዴ?”
“እናንተ እኮ ሪሊጂየስ መሆኑን ስላልሰማችሁ ነው፡፡”
“አትለኝም!” (እኔ የምለው…ዩቲዩብ በመቶ ሺህ ‘ቪው’ ስንት ዶላር ‘ይበጥሳል!’ አሀ…ኑሮው እንዲህ አይበጥሱት፣ አይጠመዝዙት ጅማት ቢጤ ሆኖብን በተገኘው ባቡር መሳፈር ነዋ! ሌላውን ልክ፣ ልኩን ለማጠጣቱ እንደሁ ‘የታለንት’ እጥረት የለብንም! ቂ…ቂ…ቂ…)
እናማ… ”እቀና ብዬ ነው ቤቴ የፈረሰው“ ነገሬ ላላት አሪፍ አባባል ነች፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!
መልካም በዓል!


Read 1454 times